ሄኖክ የሽጥላ (ገጣሚ)

ከምን ልጀምር? እንደው ይጨንቃል፤ ደሞ ዝም ቢሉት ያንቃል። አሁን ይሄን የምጥፈው ለማስተማር ነው ለማካረር? በልጅነቴ አንድ አብሮ አደጌ በጣም የሚወዳቸው እናቱና አባቱ እየተጋጩ ቢያስቸግሩት፣ ሄኒ አሁን አንተ በኔ ቦታ ብትሆን ማንን ትጠላለህ? ብሎ የጠየቀኝ ትዝ አለኝ። ማንን ልጥላ? ለማን አግዤስ ማንን ላውግዝ? ማንንስ ልውቀስ? ማንንስ ልጥቀስ? ሲደብር።

 

በእውነትም ይደብራል። ለካ ያራዳ ልጆች ወደው አይደለም ድብርት የሚለውን ቃል የሚያዘወትሩት። እንደነሱ ፍቅር፤እንደነሱ መተሳሰብ፤ እንደነሱ ንጽህናን ማን አውቆት። ለካ ያም እንዳይጎዳ፣ ይሄም እንዳይከፋው ፈልገው ነው፤ በቃ ተወው እሱ ደባሪ ነው፤ ብለው የሚያልፉት። ምነው ያራዳ ልጅ በሆንኩ።

ያራዳ ልጅ ብሆን፤ ገገማ አልሆንም ነበር፤ ገገማ ካልሆንኩ ደሞ ስህተት እንኩዋ ቢኖር በቃ "በሸሉ" አልፈው ነበር። ግን ምን ያረጋል? ያራዳ ልጅ አይደለሁም፤ እናም ገገማ ነኝ። ግን ብዙ አይነት ገገማ አለ ደሞ። የፌደራል አይነት ገገማ አለ። የመለስ ዜናዊ አይነት ገገማ አለ። ያቦይ ስብሃት አይነት ገገማ አለ፤ የኃይሌ ገብረሥላሴ አይነት ገገማ አለ፤ ምን የሰው ብቻ ... የድልይም፣ የግድብም ገገማ አለ (ለምሳሌ አዲሱ ያባይ ግድብ)፤ የጦርነትም ገገማ አለ፤ የበላይነትም ገገማ አለ፤ የፍቅርም ገገማ አለ (ከኔ ወዲያ ወይም በላይ፤ ማንም ማንንም መውደድ የለበትም) የሚል ምስኪን ገገማ። እና የቱን አይነት ገገማ እንደሆንኩ ባላውቀውም ግን ዛሬ ገግሜ ይህንን በመጣፌ፤ ደሞ ሌላ ገገማ መልስ ሊሰጠኝ እንደሚነሳም እያሰብኩ ነው።

እና እስቲ ልገግም እና ሆድ ያባውን ግግምና ያወጣዋል ልበል። አንድ መነኩሲት ነበሩ፤ እንደ እማሆይ ቴሬዛ፤ እንደ ቅድስት አርሴማ፤ እንደ ቅድስት ኤልዛቤጥ፤ እንደ ቅድስት ካተሪና፤ እንደ እማሆይ ጽጌ፤ እጅጉን የበቁ፤ ቸር፤ ቅን፤ ለእምነታቸው የለፉ፤ የታተሩ፤ ግን ምን ያረጋል፤ አንድ ቀን እንዲሁ ከመሬት ተነስተው በማሪያም መቅናት ጀመሩ። ምን አይነት ገገማ ናቸው እንዳትሉ፤ እሳቸው ከገገማ ትንሽ ከፍ ብሎ ገጌ ብለናቸው ብናልፍስ። ይሄን ሁሉ ዘመን ስጋቸውን ሲጎዱ፤ ይሄን ሁሉ ጊዜ መቁጠሪያቸውን ሲገፉ፤ ይሄን ሁሉ ዘመን ለሀገራቸው ሲማለዱ፤ ሲጠልዩ፤ ሲተጉ፤ ቁዋርፍ በልተው ሲያድሩ - ሊያውም ከነድንግልናቸው፤ እንደው ምን ክፉ ሰይጣን ነው ማሪያምን ያሳያቸው።

ማርያም እኮ ስጋዋን ጎድታ፤ ተግታ፤ ቆብ ደፍታ፤ ጥሬ ቆርጥማ አድራም አይደለም። በቃ አምላክ መረጣት፤ ቅድስት "ወ-ብጽኢት አንቀጸ ብርሃን ማዕረገ ሕይወት" አላት፤ ማሪያም ሆይ አንቺ
የተባረክሽ ነሽ፤ የመሃጠንሽም ፍሬ የተባረከ ነው ያላት የምንኩስናዋ ትጋት ፍሬ አፍርቶ በዛም መላኩ ገብርኤል ተገርሞ አይደልም፤ ለማሪያም የወርቅ ሙዳይነት ስጦታ ነው፤ መመረጥ ነው።

ለማሪያም የክርስቶስ እናትነት "አብ ይፈትን ልበ ወ ኩልያተ" (እግዚአብሔር ልብንና ኩላሊትን ይመረምራል) የሚለው የዳዊት መዝሙር በሱዋ በድንግሊቱዋ እና በአማላጂቱ ይሁን ተብሎ የልቡዋ ብርሃን ታይቶ ዕኮ ነው፤ አይ እማሆይ ስንት የሚኮን ሞልቶ፤ ማሪያምን ካልሆንኩ አሉ፤ ማሪያምን ገገማ ኖት። ደሞ ለርሶም የሚበጅዎ እንደማሆይ ሆነው ቢኖሩ ነው። በዚህ በትጉህ ባህሪዎ፤ በዚህ በአልበገርም ማንነትዎ ስንት ሰው እንደተፈወሰ ረሱት፤ ጥንካሬዎ እና ፍቅሮን እኔ እንኩዋ እንዴት እንደምወደው፤ ምነው ታዲያ እኔን አፍቃሪዎን ባያስቀይሙኝ፤ ምነው ፈር ቀዳጅነቶ ላይ አንድ ሳካኒያ አፈር ባይደፉበት፤ በውነት ገገማ ኖት።

በልጅነቴ የማስታውሰው አንድ ገገማ ነበር፤ ደራሲው ማሞ ቂሎ ይለዋል፤ እኔ ደሞ ማሞ ገገማው እለዋለው። ማሞ ገገማ ነው፤ ከማሞ የበለጠ ግን የማሞ እናት ገጌ ናቸው። ማሞ እዚህ ሀገር ቢሆን የተወለደው ኦ'ቲስቲክ ማሞ (Mamo The Outhits) ይሉት ነበር። በነገራችን ላይ እንደ ሉሲ ኦ'ቲዝም-ም መጀመሪያ የተገኘው ኢትዮጵያ ይሆን እንዴ? ወይ ኢትዮጵያ ምን ያልተገኘብሽ ምን ያልተፈጨብሽ ምን ያልተፈጀብሽ አለና። እና ስለ ማሞ ላውራ። አሁን ማሞ የመጀመሪያው ሁለት ስሙኒዎች ባይወድቁበት፤ ወድቀውም ባይጠፉበት፤ ጠፍተውም ለናቱ ባይናገር፤ ወተቱ በኪሱ ባልጨመረ፤ ቅቤውን አናቱ ላይ ባልጫነ፤ ስጋውን በገመድ አስሮ ባልጎተተ እና ወዘተ፤ ምን ያረጋል፤ አንዴ ተሳሳተ፤ ከዚያ በቃ፤ መጽሐፍ ሙሉ ቂልነት፤ በእውነት ማሞ ገገማ ነው።

ግን እስኪ የማሞ እናትን አስቡዋቸው፤ ተው ልጄ ስጋ ሲሰጥህ እንደዚህ አርግ፤ ገንዘብ ሲሰጥህ፤ 'ንደዚህ አርግ፤ ምንትስ ሲሰጥህ እንደዚ አርግ ብለው ቢሉት (ቢያርቁት፤ ቢመክሩት)። እርግጥ ማሞ ቂል ነው፤ ለዚህ ያበቁት ግን እናቱ ናቸው። ዘወትር አጠገቡ ሁነው፤ ልጃቸውን ያልመከሩ። መንደርተኛው ነው ቂል፤ ወተት በኪሱ ሲጨምር ከመሳቅና መሳለቅ ወዲህ ዝም ብለው ያዩ፤ ሀገሩ ነው ቂል፤ ጥበብና ፍልስፍናን እርም ብሎ ማሞን መሸከሙ፤ አድባሩ ወንዙ ነው ቂል፤ ብልህ አላፈራም ማለቱ፤ ቅን ሲባል ቅንቅን ማብቀሉ፤ ዘመኑ ነው ቂል፤ የራስ ስጋን መንገድ ላይ የሚያስጎትት። ትችት አይደለም ይሄ፤ ይሄ ብስጭት ነው፤ ይሄ ቁጭት ነው።

እንዴት አራዳ መሆን ያቅታል። በእውነት ገገሞች ነን።

የሚገርመው ሀገሬ ዘንድሮም በማጀቱዋ ማሞን ማፍራት አልታከተችም፤ ዛሬም ማሞዎች እልፍ ናቸው። እላያቸው ላይ ሲጨፍሩባቸው፤ ሲደክማቸው ይተዉኛል የሚሉ፤ የገዛ ስጋቸውን በየሄዱበት የሚጎትቱ፤ ወተት በኪሳቸው፤ ቅቤ ባናታቸው የሚሸከሙ፤ ድመት ጨምቀው የሚይዙ፤ ሀገር ሙሉ ማሞዎች፤ ስንደብር፤ በእውነት ገገሞች ነን።
እውነት እውነት እላችዋለሁ ሳድግ ከቻልኩ ገገማ አልሆንም፤ ካልቻልኩ ግን አሪፍ ገገማ ነው የምሆነው። አሪፍ ገገማ በቃ፤ አርግ የሚሉትን የማያደርግ፤ የማይታሰር የማይታረዝ፤ እምቢ ምናምን የሚል፤ አለ አይደል፤ አዎ! እንጂ ያ ቅድም ያልኩዋችሁን አይነት ገገማ አልሆን፤ በጣም ይደብራላ።

ደሞ ስለ ቴዲ አፍሮ ላውራ። በነገራችን ላይ ቴዲ የኳስ ሜዳ ልጅ ነው።

እኔ ደሞ አዲስ ከተማ ነው የተማርኩት፤ ስለዚህ ብዙ የኳስ ሜዳ ልጆች አውቃለሁ። ኳስ ሜዳ ከተወለድክ በዘርህ እርግማን ከሌለብህ ወይም እንደኔ የቤት ጣጣ ምናምን ካልነካካህ፤ እኔ ልሙት እልሃለሁ ገገማ ሆነህ አትወለድም ቢያንስ ገገማ ሆነህ ብትወለድ እንኩዋ ገገማ ሆነህ አታድግም።

የኳስ ሜዳ ማህጠን ይባረክ፤ በቃ አሪፍ ልጆች ይፈጠሩባታል። ምርጫ ቢኖረኝ እኔም ከስጢፋኖስ ኳስ ሜዳ መወለድ በመረጥኩ ነበር። ደሞ ሰፈረኛ እናዳትሉኝ፤ ምነው ሰው አድዋ በተወለድኩ ይል የለ፤ ልክ እኔ ምነው ያድዋ ዕለት በነበርኩ እንደምለው።

እና ቴዲሾ የኳስ ሜዳ ልጅ ነው፤ ስለዚህ አራዳ ነው። ደባሪም ገገማም አይደለም፤ ደባሪ ነገርም አይናገርም። የኳስ ሜዳ ልጆች እኮ ኳስ ዛፍ ላይ ሲወጣባቸው ሌላ ኳስ አንቀርቅበው ጠልዘው ነው ያቺን የተሰቀለችውን ኳስ የሚያወርዱዋት።

እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙላ ነስረዲንን፤ እድሪስ ሰሃን፤ ጀላሉዲ ሩሚን ባንድነት አንድ የኳስ ሜዳ ልጅ ውስጥ ታገኟችኋላችሁ። ግን አንዳቸውም እንኩዋን ኳስ ሜዳ ተወለድኩ፤ እንኩዋን እሩቅ እሩቅ እያየሁ የምቀናባችሁ አልሆንኩ ምናምን፤ ምናምን አይሉም፤ ምክንያቱም ገገማ አይደሉማ። የትም ተወልድ ኳስ ሜዳ እደግ፤ ቢባል ውሸት አይደለም። ለምሳሌ አንድም የኳስ ሜዳ ነዋሪ ቤት ውስጥ ማሞ ቂሎን ማግኘት አይቻልም። በልጅነቴ አንድ ቅጠል ነጋዴ፤ ማለቴ ፊደል ነጋዴ፤ ፊደል ፊደል እያል ያደኩባትን መንደር ሲበጠብጠው፤ አንድ የጎረቤታችን ልጅ (መሐመድ ሁሴን አባዲጋ ይባላል አሁን ጀርመን ነው የሚኖረው እንደውም ቅጽል ስሙ ቡንዱስ ሊጋ ነው፤ ከኛ ሰፈር ለመጀመሪያ ግዜ ጀርመን የሄደው እሱ ነው) እና መሐመድ ሁሴን ምን አለ መሰላችሁ፤ አንተ እዚህ ግቢ ደደብ የለም። ማሜ ያራዳ ልጅ ነው፤ ገገማ አይደለም፤ ሂድ ውጣ ከዚህ ከማለት በሸሉ ነው ያስቀየሰው። አራዳ መሆን በጣም ደስ ይላል። እንደውም ሳድግ አራዳ መሆን ነው የምፈልገው።

ግን ቴዲ የኳስ ሜዳ ልጅም ብቻ አይደልም፤ ቴዲ አሪፍ ብቻም አይደለም፤ ቴዲ ደፋር ብቻም አይደለም፤ ቴዲ ቅንም ነው፤ አንድ ግዜ ብቻ። ሁለት ጊዜ ቅን (ቅን ቅን) መሆን አይችልም፤ አልተፈጠረበትም፤ አቦ ተባረክ፤ አምላክ ደርቦ ደራርቦ ይግለጥልህ። ምን ይባላል። የግል ማስታወሻ የተራራው ጫፍ ትዝ ይለኛል። አቡጊዳ ትዝ ይለኛል። ለምለሙ ሳር ትዝ ይለኛል። ሁሉም ትዝ ይለኛል ከምንም በላይ ግን ሃሜት መጥላትህ ትዝ ይልኛል።

መባቻ

አራዳ ካልነበርን እንሁን። መሆን ካልቻልን አራዳ አንጉዳ። አንደኛ ገጌ መባል በጣም ይደብራል፤ ሁለተኛ እኛ ራሳችን የምንጠላውን ፌደራል በባህሪ መምሰል ምን ማለት ነው፤ ሦስተኛ ሦስቱ ሥላሴዎች ይቅር ይበሉን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ