ሄኖክ የሺጥላ

"አወይ ጉዴ ወይ መላ ጉዴ
ብቸኛው ልቤ ሰው በመውደዴ"

ነው ያለው አረጋሃኝ ወራሽ አሁን እንደሱ ልፋትና ጥረት ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የት በደረሰ። ለነገሩ ይሄ ትውልድ የተሠራውን ሁሉ በመናድ፣ የተጣፈውን ሁሉ በመካድ ነው የሚታወቀው።

 

እኔ እንኳ በዘመኔ ስንት አየሁ። አሁን ማን ይሙት አደይ ትርሃስ በፍራሽ መዋጥ ለሁለት እየከፈሉ ያፀኑት ሹሩባ የሚረሳ ሆኖ ነው "ቢዮንሴ ሄር ስታይለር" ምናምን ምንምን በሚል ሰጋቱራ ሀገሩን ያጥለቀለቅነው?! እስኪ አሁን ምን ትውልድ አለ። ድሮ ቡና እንኳ እስከ ሦስተኛ ነበር የሚጠጣው፤ አሁን ግን ኢኮኖሚው በ፲፩ በመቶ አድጎ ቡና እንኳ የሚያቆመው ሰባተኛ ምናምን ላይ ነው። በውነት ፕሮፌሠር አልማርያም እንደሚሉት ይሄ ትውልድ አቦ ሸማኔ ሳይሆን አቦል ሸማኔ ነው። አያቶቻችን ለአድዋ ጦርነት ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ሲሉ፤ መለከት: ጥሩንባ ሲነፉ ነው ታሪክ የሚነግረን። ዛሬ ግን የመለከት እና የእንቢልታ ሪሚክስ በየስርጣ ስርጡ ሺሻ መንፋት ሆኗል ግብራችን። የሰሞኑ መፈክር ኪንግ አብደላ ሼም ኦን ዩ፤ ሼም ሼም ሼም፤ ነበር አይደል፤ ምነው ሺሻው ተረሳ ታዲያ፤ አጎቶቻችን ባርነትና ውርደት ብቻ ሳይሆን ሱሰኝነቱንም አወረሱን።

እንግሊዛዊው ጋዜጠኛና ጠኃፊ Grham Hancook The sign and the Seal (The Quest for The Lost Arc of the Covenant) በሚለው መጥሓፉ ላይ The Ethiopian slept a thousand years forgetting the world by whom they were forgotten by ይላል። በነገራችን ላይ የላይኛውን የአነባበብ ዘዬ (style) አንድ ነገርን አስታወሰኝ። ባንድ ወቅት በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ያስተምሩ የነበሩ መምህር ስለ ጆን ኤፍ ኬንዲ ሞት ለተማሪዎቻቸው ሲያስተምሩ (During the time and death of John Fitzgerald Kennedy everybody was shocken) አሉ። በዚህን ጊዜ አንድ የቅዱስ ዮሴፍ ተማሪ ሳቁን ለመቆጣጠር ሲታገል ያስተዋሉ እኝሁ መምህር በነገሩ በስጨት ይሉና "ምን ያስቅሃል ሾካካ!!!" አሉ አሉ። እንግዲህ ያዙልኝ ሾክን ሾካካ ከሚለው ነው የመጣው ማለት ነው።

እሺ ይሁን ሾክንስ ከሾካካ ነው እንበል፤ አድርባይነት፣ ባንዳነት፣ ሆዳምነት፣ ታሪክ ሸቃይነት፣ ... እነዚህስ? አንድ ወዳጄን በጣም በስጨት ብዬ ኧረ ባክህ እኔ አልገባኝም ይሄ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መናቅ ከየት የመጣ ባህል ነው ስለው፤ ፈገግ ብሎ በርግጠኝነት ከቻይና አይደለም፤ ከቻይና ቢሆን ይህን ሁሉ ዘመን አብሮን አይቆይም ነበር፤ ምናልባት ከጣልያን ይሆን እንዴ አለኝ። ወይ ኢትዮጵያ! ልጆችሽ "ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም" የሚለውን ዘፈን በየስብሰባው እና ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ደጋግመው በማቀንቀናቸው ዘፈኑ ራሱ ሰልችቶት "ልጆቼ ሃያ ሦስት ዓመት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ተዘፈንኩላችሁ፤ በሉ አሁን ሌላ ዘፈን ፈልጉ፤ እናንተን እንዳየሁዋችሁ ከሆነ፤ እኔን እንደ ልደት ዘፈን በሻማ ከባችሁ ከማልቀስ ውጪ ምንም የምታመጡ አይመስለኝም፤ እና ጡረታዬን ጠብቁልኝና እስኪ ደሞ ይቺ የቀረችው ጊዜዬን እፎይ ብዬ ልኑር" አለ አሉታዲያ ምን ይዋጠን? "አንቺም ዜሮ ዜሮ" እንዳንል ዘፋኙ እንጀራው ላይ የቅንድብ ጠጉር ተገኝቶበት ገበያውን ገደለው፤ ምን ይበጀን? ምን ይሻለን። ከማቀንቀን ውጪ ሌላ ነገር ለማድረግ ዛሬም በቅጡ የተዘጋጁ አይመስልም፤ በየዝግጅቱ ላይ አበው አባቶቻችንን በ፩ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ከማሰብ ውጪ ሰምሮላቸው የተሻለ ነገር ሲያደርጉ ዛሬም አናይም።

ወደ ግራሃም ሃንኩክ ልመለስ ... አዎ! "The Ethiopian Slept ... A 1000 years forgetting the world by whom they were forgotten by."

(ይህንን ፈረንጅኛ በአማርኛ ብናራምደው ወይም ወደ አማርኛ ብንቀዳው)፤ "ኢትዮጵያዊያኖች ዓለምን ረስተው ዓለምም እነሱን ረስታ ለሺ ዓመታት አንቀላፉ" ማለት ይሆናል። ታዲያ የዚህን ሰውዬ አባባል የነብይ ግብር ለመስጠት እስቲመስል ድረስ ዛሬ ሀገሪቱ አልጋ በአልጋ ሆናለች። አዎ! ለኢህአዴግ መራዡ (ይቅርታ መራሹ መንግሥት) አልጋ ባልጋ ከዚህ ካለሁበት አማሪካም ይሁን ከአውሮጳና ከሩቅ ምስራቅ ሀገራት ለሣምንታት ተንፍሰው መምጣት ለሚፈልጉት አቦ ሸማኔዎችም አልጋ በአልጋ። አንቺ ሀገር ያለው ዘፋኝ ማን ነበር። ማንስ ቢሆን ምን ዋጋ አለው።

ታላቁ የኢህአዴግ መንግሥት ከሚከበርበትና ከሚወደስበት የቀለበት መንገድ በተጨማሪ (ግድቢ አደይ ሃዳስ (የእማማ ሃዳስ ግድብ) (ለመሃል ሀገር ሰው ይስማማ ዘንድ የኅዳሴው ግድብ እየተባለ የሚነገረውን ሳይጨምር ...) ከሚታወቅበት አንዱ እንቅልፍን ያለ ገደብ መፍቀዱ ነው። በነገራችን ላይ ያባይ ቦንድ የብዙ አባወራዎችን ትዳር በማፍረሱ፤ ያባይ ቦንብ የሚል ስም ሊሰጠው እንደሆነ ጥቃት ያደረሱትም ጥቃት የደረሰባቸውም እየተናገሩ ነው። የዚህ ያባይ ቦንብ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑት ሰዋች እንደሚሉት ከሆነ አማሪካ ቢሆን disability ክሌም ሀርገን እንደ አካፋ ዝቆ በሚያነሳ አውቶብስ ፈልሰስ እያልን እንኖር ነበር፤ እኛ ግን ከጥቃታችን ሳናገግም፤ ተገድቦ የት ያደርሰናል ያልነው አባይ ጉሮሮዋችንን ገድቦ ይስረቀርቃል ብለዋል። ለነገሩ አባይ አፍ የለውም እንጂ ቢጠይቁት የደደቢት ዱርዬዎች ሃንግ አረጉኝ ብሎ ለአውሽና ቦርከና ይናገር ነበር። ምን ያረጋል ታዲያ አባይ እንኳን አፍ ማደሪያ የለውም። አባይ በስምሽ ስንት ታሪክ ተሠራ። ትገርሚያለሽ፤ በቃ ግንዱ አልበቃ ብሎሽ የዲያስቦራን ዶላር ትጠርጊ ጀመር፤ ለነገሩ አንቺ ምን ታረጊ፤ ሆዶ ነው ቁም ነገረኛ ያረገሽ። እዚህ ዛሬ ከኛ ጋ ተቃውሞ ማታ ደሞ ኢትዮጵያ ደውሎ፤ እንዴት ነው ቦንዱ፤ ግድቡ እያለቀ ነው፤ ምን ይጠበቅብኛል ጌቶች የሚለው፤ ይሄ ሁለት ቢላ ህዝብ አባይዬ በናትህ በጣና ይሁንብህ፤ ይህንንማ ውስክስክ ላፍልኝ፤ መቅኖ አስቀረው፤ አላርፍ ያለ ዲያስፖራ ያባይ ቦንድ ይገዛል አሉ።

የጎጃም ገበሬ እንኳ ዛሬ ቦንድ ካልገዛህ አባይ አጠገብ ዋሽንት መንፋት አትችልም ሊባል እንደሆነ ሰምቼአለሁ፤ ዋሽንቱስ ይሁን፤ ቢያንስ ውሃ ሽንት ይፍቀዱላቸው።

በአባይ ቦንድ መሸወዳቸው የገባቸው አንዳንድ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ሲናገሩ እንደሰማነው ከሆነ "ቦምብን በቦንድ ስም መንግሥት ሲያስታጥቀን ዝም ብሎ የተመለከተው ሰማያዊ ፓርቲ ይጠየቅልን ብለዋል።" ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው መንግሥትም ሰማያዊ ፓርቲ ከዚህ አፍራሽ ድርጊቱ ካልተቆተበ አሸባሪ ተብሎ ከነግንቦት ሰባትና መሰል ድርጅቶች ተርታ ሊፈረጅ እንደሚችል አስምሮበት አልፏል። ይልቁንም ሰማያዊ ፓርቲ በአባይ ቦንድ እና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ታቅቦ፤ ልማታዊ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር በማለት የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ እከሌ ተናግረዋል (እከሌ ያልኩበት ምክንያት ከመለስ ሞት ወዲህ ሰው አጥፊ ብቻ ሳይሆን አላፊና ጠፊ እንደህነ ስለተረዳሁ ነው)፤ አያይዘውም ሰማያዊ ስሙ ከኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ጋም የተያያዘ ስለሆነ፤ የሕገ-መንግሥት የበላይነት እና የእምነት እኩልነት በሰፈነበት ሀገር ፓርቲያቸው ኢህአዴግ እንዲህ አይነት መድሎ ስለማይቀበል፤ ሰማያዊ በሚለው ላይ ተቀጽላ ጨምሮ (ሰማያዊ አል ረካት) ብሎ እንዲያስተካክለው እናሳስባለን፤ ይህ ባይሆን ግን፤ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት፤ ሕጋዊ እርምጃ እንደምንወስድ እናሳስባለን። በነገረችን ላይ ይሄ የአሸባሪነት ሕግ ከመጠን በላይ መናፈስ በጀመረበት ዘመን የልጅ ልጃቸውን ማየት የቻሉ አያት፤ ልጃቸው እማ ልጄን ማን ልበለው ብላ ለጠየቀቻቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ ማንስ ብትይው ምን ዋጋ አለው፤ ገና ሳይወልድ እኮ ነው መንግሥት ስም ያወጣለት፤ ስለዚህ አድጎ ግራ ከሚገባው አንድ ፊቱን አሸብር በይው አሉዋት። ኧረ እቴ!

በነገራችን ላይ የጎጃም ገበሬ ነው አሉ፤ ስለ አዲሱ የአደይ ሃዳስ ግድብ ወይም ኅዳሴ ግድብ ከጋዜጠኛ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፤ እናንተ የኢትዮጵያን ባህልና ወግ ለመናድ ስትታገሉ፤ አባይ ደሞ የአማራ አፈርን ሲንድ፤ ነው የማወቀው፤ እንግዲህ ዛሬ አባይ ከዚህ ጸያፍ ድርጊቱ ታቅቦ፤ እንደ ሴተኛ አዳሪ እዚህም እዚያም ከማስካካት እናንተ ባበጃችሁለት ቦይ ለመንዶልዶል መወሰኑ ጥሩ ጅምር ነው፤ ዋናው ቁም ነገር ግን መንግሥት ከዚህ ግድብ ምን ይማራል ነው፤ ይህ የሺህ ዓመት ቦዘኔ፤ ጨርቄን ማቄን ሳይል፤ ጉዋዙን ጠቅሎ እዚሁ የተፈጠረበት ሀገር ለመስተር መሞከሩ፤ መንግሥትን ምን ያስተምረዋል፤ የገዛ ሀገራቸውን አንጡራ ሀብት ለባዕዳን የሚቸበችቡ አሻጥረኞች ከዚህ ምን ይማራሉ ነው። ብሎ አስተያየቱን ሰጥቶ አልፏል።


"ሲታረስ ሳያምር ሲታጨድ ሳያምር
ዋራን አሳመረው የድንጋይ ቤት ክምር"
ያለው ማን ነበር?


"ሲነገር ሳያምር ሲወራ ሳያምር
ደለል ሻኛ ሆነው የጭቃ ቤት ክምር"
ብለን ለአባይ መሳ ግጥም ገጥመን እንለፋ።

እና ስለእንቅልፍ ተመልሰን እናውራ ...

እናላችሁ መተኛት ለሚፈልግ ከምግብና መጠጥ ሌላ ሁሉም ይሟላለታል። እንኳን ሰዉ ዛፍ እንኳ እንቅልፍ ለምዳል። መወዛወዝ የለ፤ ቅርንጫፍ ማፏጨት የለ፤ ዘነበ አልዘነብ የለ፤ ከሰው ጉንጭ ውስጥ ገብቶ ለጥ። ማ ወንድ ነው የዘንድሮን ዛፍ የሚቀሰቅሰው። ስሙስ ቢሆን እሱም እንደ ቢዮንሴ ሄር ስታይለር ... ተቀይሮ። ድሮ አባቶቻችን ስለዛፍ ሲያወሩ፤ ዝግባ፣ ዋንዛ፣ ቀርቀሮ፣ ጥድ፣ የባህር ዛፍ፣ ወይራ፣ ኧረ ስንቱ! ... የዘንድሮ ዛፍ ለስለስ ያለ ስም ነው ያለው። ለስለስ ያለ እጅም ነው የሚይዘው። የዘንድሮ ዛፍ ምንጣፍ ተነጥፎለት ነው ቤት የሚገባው እንጂ በአህያ ጀርባ ተጭኖም አይደል። ከትግራይ ውጭ በአራቱም ማዕዘናት ይበላል፤ አወዳይ ወይም በፈረንጅኛው (I will die) ገለምሶ፣ በለጬ፣ ጉራጌ፣ ... ገለመኔ ነው ስሙ። የዚህ የእንቅልፋም ትውልድ ቀርቀሮና ዝግባ። ይሄ ትውልድ በእውነትም እንቅልፋም ነው።

ደጉ መንግሥቴ በክርስትና ስሙ (የዘመናት ብሶት የወረሰው፤ ወይም የወረረው) (በዳቦ ስሙ ባለ ራዕዩ መንግሥቴ) ... የአቡነ ጴጥሮስን ሐውልት አፍርሶ (ነቅሎ)፤ ቁልቁል ሲንደረደር በተኛበት ቤቱ የፈረሰበት ሰው ነው አሉ እንዴ ይሄ ባቡር ሳይገባ ገጭቶ የጨረሰን ሲገባ ምን ልንሆን ነው አለ አሉ። ሲገባማ ምን ችግር አለው፤ ያባልነት መታወቂያ ከያዝክ እንቅልፍህን ትራንሰፈር ታደርገው ዘንድ በርህ ላይ ቆሜ እየጠበቅኹኽ ነው የሚል አይመስልኽም።

ባለ ራዕይ ስል ... የቀድሞ የሳውዝ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኔልሰን ማንዴላን የቀብር ሥነሥርዓት በቴሌቭዥን ሲከታተል የነበረ አንድ ታጋይ (በሃደግ) ለማንዴላ እንደኛ ባለ ራዕዩ መሪ የጎዳና ተዳዳሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎች ያላለቁሱለት ለምንድን ነው አለ አሉ። ስላልወለዳቸው እናም ስላላገባቸው ልበልህ። ምን ልበል እኛ በሕግ የተመዘገበ፤ ሕገመንግሥቱ የሚያውቃት ልጃቸው ቢሊየነሩዋን ሰማኸል መለስን ነበር፤ ታዲያ ጆቢራው ሲሞት ባንዴ (ባሌ ባሌ፣ አባቴ አባቴ ባዩ መብዛቱ) ድሮም ሾፌርና የእንትን ወንድ ይሉ ነበር ዘመዶቼ።

ማን ነበር ሎዚች ጦላ ሎጦሞቆ ሴት ሙተኛት ነበር ያለው። አይ ሀገር፤ ቡና ቤት አረጉሽ፤ አይ ትውልድ ቁመን አየንሽ።


"ሲታረስ ሳያምር ሲታጨድ ሳያምር
ዋራን አሳመረው የድንጋይ ቤት ክምር"

ያለው ማን ነበር?


"ሲፈጥረው ሳያምር
ሲገለው ሳያምር
ክፋት ግብር ሆነው የደደቢት ንስር።"

ብዬ ለአባባ መልስ እኔ ወዲ ሃድጊው በጎዳ ልጆች ስም ግጥም ባበረክትስ።

ቸር ይግጠመን!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ