የማለዳ ወግ፤ የመረጃዎች እውነት - ሐሰት ፍልሚያ
የተመላሾች ጉዳይ ...
ነቢዩ ሲራክ
ከሳውዲ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ዜጎችን በሚመለከት የጀርመንና የአሜሪካ ራዲዮን ጨምሮ በርካታ የመገናኛ ብዙኀን አንድ አይነት የሚመስል መረጃ ግፉአን ተመላሾችን እማኝ እያደረጉ መረጃ አቀብለውናል።
"ራፕለር" በያዝነው ሣምንት ባቀበለን መረጃ፤ ሻንጣቸው ጠፍቷቸው በአንድ የሻንጣ ማጠራቀሚያ ግቢ ሻንጣቸውን ሲፈትሹ የሚያሳየውን ፎቶ አስደግፎ የተመላሾችን አስተያየት አካቶበታል። ዜጎች ወደ ሳውዲ ሲሰደዱ ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድና ከተለያዩ ቦታዎች የወሰዱትን የብድር ገንዘብ ስላልመለሱ ኑሯቸው የሰመረ እንዳልሆነ እየተናገሩ ነው። ሀገር ቤት ገብተው የሥራ ማጣት እና እሳት የሆነው የኑሮ ውድነት ግራ ያጋባቸው በርካቶችም አሁንም መልሰው ለስደት እንደቋመጡ እኛ የምንቀርበው መረጃ ባይስማማ የፈረንጆቹ መገናኛ ብዙኀን የሚያቀርቡት የገሃዱን እውነት አንድምታ ያሳያል።
በግል ሀገር ቤት ገብተው የማገኛቸውን በርካቶች ሀገር ቤት ተመልሰው ያጋጠማቸው የኑሮ ውድነት አማሯቸዋል። መልሶ ማቋቋሙ ደግሞ ከወሬ ባለፈ አለመጀመሩን እየሰማን ነው። ባሳለፍነው እሁድ በጀርመን ራዲዮ እንወያይ ፕሮግራም የቀረበው ተመላሽ ወንድምም ተመላሾችን በማደራጀቱና መልሶ በማቋቋሙ ረገድ የተጀመረ ነገር እንደሌለ መረጃውን አካፍሎናል። በአንጻሩ በመንግሥት ኢቲቪና የቀሩት በሥሩ የሚተዳደሩት መገናኛ ብዙኀን የሚናገሩት የሚታመን ከሆነ "ተመላሾቹ በየክልሉ ተደራጅተው እራሳቸውን የሚያቋቁሙበት ሥራ ተጀምሯል!" የሚል መልካም መረጃ እያስተላለፉ ይገኛሉ። ከዚህ ጋር ያያዝኩት አዲስ ዘመን ጋዜጣ "ከስደት ተመላሾች ሥልጠና ጀምረዋል!" በሚል ሁላችንም ሳውዲን ለቀን ወደ ሀገር እንገባ ዘንድ የሚያበረታታ መልካም የብስራት ዜና አሰራጭቷል። ... እውነት ከሆነ ማለቴ ነው! ይህንን አሻግሮ ተቀምጦ "እውነት፤ ሐሰት" ማለት አይቻልምና ሊናገሩ የሚገባቸው ባለቤቶቹ ብቻ ናቸው። ተመላሾች ሆይ ምን ትላላችሁ?
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተጠሪ IOM መስሪያ ቤት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም 13.1 ሚሊዮን ዶላር ወይም 9.5 ዩሮ እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርጓል። የስደተኞች ንብረት በተለይ የሻንጣ ጌጣጌጡን መጥፋት ጉዳይ አሳሳቢነት ግን ከፍተኛ ኃላፊዎችን ሳይቀር ያስደመመ እንደሆነ ከሚሰራጩት መረጃዎች ለመረዳት አልገደደንም።
"ወደ ሀገር ግቡ አንገባም፣ እንግባ አትገቡም ..."
ከአሰሪያቸው ጋር የማይሠሩና በሕገ ወጥነት የተፈረጁ ዜጎች ወደ ሀገር እንዲመለሱ የሚጠይቀው የሳውዲ መንግሥትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤንባሲና የቆንስል መስሪያ ቤቶች ጥሪ ነው። ጥሪው በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰነዳቸውን ያላሟሉ የሚባሉት በባህር በኡምራና ሃጅ ብቻ ሳይሆን በሥራ ኮንትራት መጥተው ከአሰሪዎቻቸው ጋር የማይሠሩ "ሕገወጥ" የተባሉ ዜጎች ግን፤ "ሳውዲን ለቃችሁ ውጡ!" የሚለውን ጥሪ ችላ በማለት ዘና ብለው የተለመደ ኑሯቸውን መኖር ጀምረዋል። ፍርሃትና ጭንቀቱ የት እንደገባ ባይታወቅም የሳውዲ መንግሥት ባሳለፍነው ሣምንት ጉዳያቸውን ጀምረው ላልጨረሱ የሰጠው የሁለት ወር ማስተካከያ ጊዜ ገደብ ነዋሪውን ያዘናጋው ይመስላል። ያን ሰሞን በስጋት እቃቸውን ሲጠራርፉ የነበሩት፤ ዛሬ እቃቸውን ወደ ነበረበት መልሰው የለመዱትን የመዘናጋት ኑሮ መግፋት ይዘዋል። አንዳንዶቹን ጠይቄያቸው "ዛሬም የሳውዲ መንግሥት አይጨክንም ሕጉን ያሻሽለዋል!" በማለት ሲመልሱልኝ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ "ሀገር ቤት የሄዱት የኑሮ ውድነት እያማረራቸው እየሰማን መሄዱ ማበድ ነው" ሲሉ መልሰውልኛል። እስርና ቅጣቱስንስ እንዴት ትቋቋሙታላችሁ? አልኳቸው፤ "የፈለገው ቢሆን እዚሁ ኹነን መቋቋም እና መቀበሉ ይቀላል!" ሲሉ ክችም ያለ መልስ ሰጥተውኛል። እኒህ ለእኔ ቀቢጸ ተስፈኞች ናቸው ...
የሳውዲን መንግሥት ወደፊት ጠንከር ብሎ ይወስደዋል ተብሎ የሚጠበቀውን እርምጃ የፈሩ ጥቂቶች አሁንም ወደ መጠለያ በመግባት እና ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው። ያም ሆኖ በጅዳ የሽሜሲ መጠለያ ሰነዳቸው ይሰራላቸው ዘንድ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ በስልክ እየደወሉ "ተቸገርን! የምግቡ ችግር ቢቻልም፣ በመጓጓዙ ላይ ዘገየን፣ መላ ወደሚገኝበት ቦታ ጩኸልን!" እያሉ ተማጽነውኛል። ሰኞ ከቀትር በኋላ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት መረጃ ያቀበሉኝ፣ ከመዲና፣ ከጅዳና ከተለያዩ ቦታዎች ከቀናትና ከሣምንታት እና ከወር በፊት ወደ ሽሜሲ ገባን ያሉኝ ወገኖች "ጉዟችንን ለማፋጠን በቆንስላችን ክትትልና ትብብር ስለማይደረግልን እየተጉላላን ነው!" ሲሉ ጭንቀታቸውን ገልጸውልኛል። በኮንትራት ሥራ የመጡትን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ችግሩ መቋጫ አግኝቷል ቢባልም፤ አሁን ድረስ ችግሩ አለመፈታቱን ነዋሪዎች ከሽሜሲ መጠለያ በምሬት ገልጸውልኛል። "ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ ወደ መጠለያ ለመግባት ፈልገን ወደ መጠለያ የሚወስደንና የሚቀበለን አጣን! ውጡ ብለውን እንውጣ ስንል የሚያስወጣን አጣን!" ያሉኝ በርካቶችም በጅዳ ሸረፍያ እንደሚገኙ አጫውተውኛል። ሕግን ተጋፍተው በሳውዲ ለመኖር ተስፋቸው የተሟጠጠ እነዚህኛዎቹ የሚደግፋቸው ይሻሉ።
የጅዛን እውነት
ጅዛን በተደጋጋሚ የሚደርሰኝን መረጃ በማቅረቤ ያን ሰሞን የወገን ለወገን ደራሽ ኮሚቴን የጠለፉት የመንግሥት ፖለቲካ ድርጅት አንዳንድ ካድሬዎች፤ እዚህ ጅዳ ከጎኔ ተቀምጠው አዲስ የማጥላላት ዘመቻ ጀምረዋል። የወገንን ሳይሆን ለመንግሥት ኃላፊዎች በማደግደግ እንደፈለጉ በሚፈነጩበት የህዘብ ግንኙነት የፊስ ቡክ ገጽ "እውነቱ ይሄ ነው" በሚል ባስነበቡን መረጃ የእኔን ሳይሆን የተበዳዮችን እውነት ጥላሸት ሊቀቡት ከጅለው ሳይ አዝኛለሁ። "በሉ!" ትዕዛዙን ይፈጽሙ ዘንድ እንደተባሉት በማስተጋባት እውነቱን "ሐሰት!" ብለውታል። ሳያፍሩ፣ ሳይፈሩ!
የተሳሳተ መረጃ ደርሶኝ ይሆን ስል አጠራጠሩኝ። ግን እንዲያ አልነበረም። መረጃውን ለማጣራት ጅዛኖችን ደጋግሜ "ሃሎ" ብያቸው ነበር ... ያገኘኋቸው አስገራሚና አሳዛኝ መረጃዎች፤ "አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል!" አስብሎኛል። ከሕግ ታሳሪዎቹ ጋር በነበረኝ ቆይታ "የጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች የእናንተን ጉዳይ እየሠሩ እንደሆነ ተነግሮኛል፣ እውነት ነውን?!" ያልኳቸው ወንድሞች፤ የተባለው መረጃ ትክክል አለመሆን ተበሳጭተው የሚጠይቅላቸው ስላጡትና በሚሠራው ሥራ ዙሪያ ብዙ አጫውተውኛል። በአሳዛኝ እና በአስገራሚው የስደት ሕይወት እጁ የተቆረጠውን ወንድም፣ ታናሽ ወንድሙን እና እሱ በረሃ ላይ ሲጓዙ ተይዘው ዛፍ ላይ ታስረው ተንጠልጥለው ሲውሉ አቅም አንሶት ከፊቱ ላይ ደክሞ ተዝለፍልፎ የሞተ ታናሽ ወንድሙን ታሪክ ወንድሙ ራሱ ይነግረናል። ይህ ወንድሙን በበረሃ ላይ ያጣ ወንድም ስድስት ወር እንዲታሰር ቢፈረድበትም ከዓመት በላይ ጠያቂ አጥቶ መንገላታቱን መስማት ያማል! ይህንንም በድምፅ ይዠዋለሁ! ትሰሙታላችሁ ... እናም በጅዛን ፍርዳቸውን የጨረሱ የሕግ ታራሚዎች ድምፅ "ወደ ሀገር እንድንገባ ድጋፍ የሚያደርግልን የመንግሥት ኃላፊዎችን አጣን!" የሚል ነው! የጅዛን እውነቱ ይህ ነው!
መንግሥት ሆይ ስማን! ... ወገን ሆይ ስማን!
ሰነድ የሌላቸው ዜጎች "ሕግን ተላልፋችኋል!" ተብለው፤ "ከሀገር ይውጡ!" ተብሏል። ዜጎች ከሀገር ውጡ ሲባሉ መንገዱን በማመቻቸቱ ረገድ ከኢትዮጵያ መንግሥት የኤንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ከመረጃ ጀምሮ ብዙ ይጠበቃል። ቢያንስ ሁሌ እንደምለው "መውጣት አልፈልግም!" የሚለውን ዜጋ ምክንያት ሊሰማና ሊደመጥ ይገባልና፣ ስሙት! "እንውጣ!" ሲል እንግልት የሚገጥመውን ዜጋ ታደጉት! በዐረብ አሰሪዎች ቤት ሆነው "ወደ ሀገራችን እንግባ ድረሱልን!" የሚሉ የኮንትራት ሠራተኞችን ያላባራ ጩኸት ይሰማል። የሰማነውን ለኃላፊዎች ብናሰማም መፍትሔ የሚሰጥ ጠፍቷል። ይኸው አሁንም ያሳስባል! "ድረሱልን!" ሲሉ ደራሽ ያጡትን የኮንትራት ሠራተኞች ፈጥናችሁ ድረሱላቸው! መውጣት ያለበት "ሕገወጥ" የተባለ ሁሉ ዜጋ ይውጣ! አስከፊውን የስደት እንግልትና መከራን ማየቱ ይብቃን!
ሰው ተጨንቆ ተጠቦ፣ የመረጃዎችን እውነትነት እና ሐሰትነት የሙግት ጅማሮ ቀልቤን ባይስበውና መነታረኩን ባልፈልገውም፤ ለሚወረወረው አሳሳች መረጃ እውነቱ ለማስጨበጥ ስድቡን ባልገባበትም ትክክለኛውን መረጃ ከምንጩ ለማቅረብ ወደ ኋላ የምል አይደለሁም! ይህም በመሆኑ ይህንና ያንን በሰፊው እስክመለስበት ሰላም!
ቸር ያሰማን!
ነቢዩ ሲራክ