አስገራሚው የሳውዲው "ኮራጅ " አባት ምክር

ነቢዩ ሲራክ
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ከ20 ዓመት በፊት ሳውዲው ወጣት ራሱን ለሁለተኛ ደረጃ ፈተና ከማዘጋጀት ይልቅ በረቀቀ መንገድ ለፈተናው መልስ የሚሆነውን ማጭበርበሪያ የመልስ ወረቀት አዘጋጅቶ ለፈተና ይቀርባል። ፈተናውን በረቀቀ መንገድ አጭበረብሮ ሰርቶታልና ፈተናውን በተገቢ ውጤት አልፎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለማለፍ በቃ!

 

ከዚያም በታዋቂው ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ተከታትሎ ይመረቃል። ይህ ሁሉ አልፎ ስራ ይዞ እና ጎጆ ቀልሶ ለወግ ለማዕረግ በቃ! ከጎጆም አልፎ የሰመረው ሕይወቱ የልጆች አባት እስከ መሆን ታደለ።

በያዝነው ሣምንት የድሮው ተማሪና የዛሬው አባወራ ጆሮውን ያልተለመደና የማያውቀው ሕመም ያሰቃየው ገባ። ወደ ሐኪም ቤት ጎራ በማለት ምርመራ ሲያደርግ ለሕምሙ ዋና ምክንያት በጆሮው ውስጥ ቁራጭ ወረቀት እንደሆነ የሚያስረዳው አስገራሚው ውጤት ተነገረው ... አረጋዊው አባት በወጣትነት ዕድሜው ተግቶ በማጥናት ለፈተና ቀርቦ ማለፍ ሲገባው አስነዋሪ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙን እያስታወሰ አልተደሰተም፤ አዘነ እንጅ ...

ዛሬ ለማጭበርበሩ የተጠቀመበትን ወረቀት በጆሮው እንዴት ሊያስገባው እንደቻለ ማመን ቢያዳግትም ከ20 ዓመታት በፊት ለኩረጃ እና ለማጭበርብር የተጠቀመበት ወረቀት በቀዶ ጥገና ከጆሮው እንዲወጣ መድረጉ አስገራሚውን ዜና እየተቀባበሉ እየዘገቡ ካሉት የዐረብ መገናኛ ብዙኀን ለመረዳት ችያለሁ። ከሁሉም የሚያስገርም የሚያስደስተው በሠራው ሥራ የሚያፍር እንጅ የማይኮራው አባት ልጆቹንና ወጣቶችን ሲመክር "ልጆቼ ሆይ! ፈተና ለማለፍ አታጭበርብሩ!" ማለቱ ተጠቅሷል። የትናንቱ ተማሪ የዛሬው አባወራ ሳውዲው አባት በሠራው ሥራ ተጸጽቶ ቀሪውን ለመምከር ወደ አደባባይ መውጣቱ ቢያስደስተኝ በዝንቅ መረጃየ ስር መረጃውን ላካፍላችሁ ፈቀድኩ።

ሳውዲውን አባት መልካም ምክር ካነሳሁ አይቀር ሰሞነኛ የማለዳ ወጌ እንግዳ ለማድረግ ስለፈቀድኩት አንድ ከ20 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ባንድ ወቅት አንቱ የተባለ ስም ስለነበረው ብርቱ ወንድም ላጫውታችሁ፤ አብደላ አህመድ ኦመር ይባላል። ቀዳሚው የኢትዮጵያን ሰርከስ መስራች ነው። በሥራው ቻይናን ጨምሮ በርካታ ሀገራትን ጎብኝቷል። ብርቱ ስፖርተኛ ከመሆን ባለፈ አንድን ሙያ ልያዝ ብሎ ከተነሳ በፍጥነት ክኽሎትን የማዳበር ልዩ ተፈጥሮ ያለው ወንድም እንደሆነ ሰምቻለሁ። ዛሬ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ነገር ቢኖር ብዙኀን ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ሰርከስ መስራች ማን እንደሆነና የት እንዳለ የሚያውቁ አይመስለኝም። ... ብርቱው የቀድሞው ስፖርተኛ እና የሰርከሱ መስራች አብደላ ግን ሳውዲ ዐረቢያ ጅዳ ትዳር መስርቶ እና ልጆች ወልዶ በስደት ሕይወትን በመግፋት ላይ ነው።

አብደላን ሳላውቀው ... ላውቀው

መልከ መልካምና ደልዳላ ተክለ ቁመና ካለው ወንድም ጋር ለዓመታት ልጆቼን በማስተምርበት በጅዳ የኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት እንተያያለን፣ ግን አንተዋወቅም። በአንድ ወቅት ከአንድ ወዳጀ ጋር የትምህርት መለቀቂያ ሰዓት ደርሶ ልጆቻችን ስንጠባበቅ አብደላ ሰላምታ አቅርቦልን አለፈ። አብደላን አንድ ወዳጀ ያውቀው ነበርና እንዲህ አለኝ ... "ለመሆኑ ይህን ሰው ማን እንደሆነ ታውቀዋለህ?" ሲል ጠየቀኝ፤ ኧረ አላውቀውም ስል መለስኩለት። "አየህ ሳውዲ ያልያዘችው፣ ያላቀፈችው ሐበሻ አይነት የለም፣ አንተ ደግሞ የሩቅ የሩቁን፣ በበርሃ የምታገኘው ዘፋኝና ግፉዕ ተዓምር ለቃሚ ግመል ጠባቂ እህቶችን እንጅ እንዲህ በቅርብ ያለውን አይታይህም" ሲል የመሰለውን አስተያየት ሲሰነዝር፤ እንደ መቀለድ እያለ በፈገግታ ተሞልቶ ነበር። እኔም እንደመሳቅ አልኩ። ወዳጀ ወጉን ቀጠለ ...

"አብደላን በትንሹ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ አውቀዋለሁ። ስፖርተኛ፣ አስማተኛ፣ የስነ ጽሁፍ ክኽሎትን የተካነ በሁሉም የሙያ መስክ የምታገኘው ሰው ነው። ዛሬ እንዲህ አንገቱን ደፍቶ፣ ሰውነቱ ገዝፎ ስታየው የዋዛ አይምሰልህ (ፈገግ ብሎ)፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት ታዋቂው የአካል እንቅስቃሴ አሠልጣኝ ግርማ ቸሩ ለዓመታት በአሠልጣኝነት ይሠራባቸው ከነበሩ በወቅቱ ታዋቂ ቱጃር በነበሩት የሸህ አልዙማን ሥራ ተሰናብቶ ሳውዲን ሲለቅ፤ የተተካው ፈርጣማው ጎልማሳ አብደላ ነበር። ከዚያም የባለፀጎቹን ቤተሰቦች በአካል እንቅስቃሴ አሠልጣኝነት እና በልዩ ጥበቃ ለዓመታት በመሥራት ያልዞረበት ሀገር የለም። በአዕምሮው በሳል፣ በአካል ፈርጣማ ስፖርተኛ ነው። አየህ ነቢዩ በሳውዲ ስደት የታቀፈው ግፉአን እህቶችና ወንድሞች ብቻ አይደሉም። እንዲህ አይነት ባለሙያም ሳውዲ ውስጥ ይኖራል። ታሪኩን ለመናገር ፈቃደኛ ከሆነ ለቀረው ትውልድ አስተማሪ ነውና አንድ ቀን አስተዋውቅህና እንዲያጫውትህ አደርጋለሁ!" አለኝ።

አብደላን ሊያገናኘኝ ከአንድ ዓመት በፊት እንዲህ ቃል የገባልኝ ቅን አሳቢ ወንድም ግን ዛሬ ከአካባቢው የለም ... ኑሮው ቢከብደው ቤተሰቦቹን ይዞ እና ጥሪቱን አጠረቃቅሞ የአቅሙን ያህል ለመሥራት ሀገር ቤት ገብቷል። ካንድም ሁለት ሦስት ጊዜ በፌስ ቡኩ መስመር ብንገናኝም ሀገር ገብቶ የሚይዝ የሚጨብጠው እንዳጣ መረጃ የሚያቀብለኝን ወንድም "አብደላን አገናኘኝ?" ብየ ማስቸገሩ ከብዶኝ መክረሙ እውነት ነው። መቸም ዘንድሮ መንገድና ፌስ ቡክ የማያገናኘው የለም፣ የኢትዮጵያውን ሰርከስ መስራች በቀጭኑ የስልክ መስመር በሌላ ጉዳይ አግኝቸው ስናወጋ ማንነቱን ሲያጫውተኝ ማመን አልቻልኩም። ፎቶዎችን፣ ሰነዶችን በመረጃ ማስረጃነት ሲያጋራኝ ግን የማይታመነውን አጋጣሚ ለማመን ተገደድኩ! ከወንድም አብደላ ጋር ልንገናኝ ቀጠሮ ይዘናል። ... በቀይ ባህር ዳርቻዎች ከቤተሰቦቻችን ጋር ተገናኝተን፣ ልጆቻችን ሲጨዋወቱ ነፋሻውን የባህር አየር እየማግን የኢትዮጵያ ሰርከስ መስራቹን የአብደላን ዠንጉርጉር ሕይወት እኔ እየጠየቅኩ እሱ በትዝታ እየነጎደ እስኪያወራኝ ቸኩያለሁ ...

መልካም ቀን!
ነቢዩ ሲራክ / የካቲት 2006 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ