ነፃነት ዘለቀ (አዲስ አበባ)

Doro. የአንድ ዶሮ ዋጋ የዐርባ አምስት በሬ ዋጋ ሆነ
ክርስቲያን አንባቢዎቼ እንኳን ለ2007 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ። ሙስሊሞችና ሌሎችም እንኳን ለኛ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ ለእናንተም በዓል(ላት) በሰላም እንዲያደርሰን የጋራ የሆነውን ፈጣሪን በጋራ እንለምነው።

ይቺ የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል ከቀደሙት ትንሽ ለዬት ሳትል አትቀርም። ይሄ ግፋፎ ብር እዬለየለት መጥቷል። የሰሞኑ ገበያ በጣሙን ተበሻቅጧል። መንግሥቶቻችን ሲያቀብጣቸው ብሩ ላይ የወፍ ስዕል አኑረውበት ብሩ በዓለማችን የመጨረሻው ፈጣን ወፍ ሆነ። ሲበር ፍጥነቱ ልዩ ነው፤ በሣይንሳዊ መሣሪያ እገዛ ካልሆነ በዐይን ብቻ አይታይም። አቶ ብሩ ጉድ አፍልቷል። በአብዛኛው ከሆዱ ባለፈ የማይጨነቅ የልምድ ነጋዴ በሞላባት አገራችን ውስጥ በአቋራጭ ለመክበር የሚስገበገበው ሰው በዛና አቅልን የሳተ የገንዘብ ግንኙነት ነግሦ ሁላችንንም አቅል እያሳጣን ከሰውነት ተራ እያስወጣን ይገኛል። የዛሬው አዋዋሌ ራሱ ከወትሮው የተለዬ ሆኖብኝ በጣም ሲገርመኝ ውሎ አመሸ። ከማን ጋር እንደማወጋው ጨንቆኝ ሳለ እናንተ ትዝ አላችሁኝ። እስኪ ተንፈስ ልበል።

ትዳር ያደረገ ልጄ (በትግርኛ አማርኛየ ቅር አትሰኙም መቼም) - ትዳር ያደረገ ልጄ ዶሮ አጋዛኝ ብሎ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ ይደውልልኛል። ወዲያውኑ እንገናኝና የካ ሚካኤል አካባቢ ወዳለው ሾላ የዶሮ ገበያ እንሄዳለን። ትርምሱ ሌላ ነው። ከቤት የቀረ ሰው ያለም አይመስልም፤ በዚያም ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እዳር ተመካክሮ ሰው ከማፍራት ውጪ ተኝተው የሚያድሩ አይመስልም፤ የሰው ፋብሪካ በየቤታችን የተከልን እንመስላለን - ብዛታችን ሲታይ። ለማንኛውም ከልጄን ጋር የተለያዩ ሸቀጦችንና ዕቃዎችን ዋጋ በእግረ መንገድ እየጠያየቅን ወደዶሮ ተራ አመራን። የሁሉም ነገር ዋጋ ሰማይ ነው፤ ከምናውቀው ሰማይ በላይ ሌላ ሰማይ ካለም ከዚያም በላይ። የሁሉም ሸቀጥና ዕቃ ዋጋ ያስደነግጣል። ሁሉም ነጋዴ ቁጥር የሚያውቅ አይመስልም። ቁጥሩ ቀላል የማይባለው ሸማችም እንዲሁ ቁጥር የሚያውቅ አይመስልም። ነጋዴው ስምንት መቶ የሚለውን የቻይና አቃጣይ ጫማ - ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ከሁለት መቶ በዘለለ የማይሸጠውን ጫማ ማለት ነው - ብዙም ሳይከራከር በሰባት መቶ ሃምሳ የሚሸምት ገዢ አለ። ተራዋ የላስቲክ ነጠላ ጫማ እንኳ ነፍስ አውቃ መቶና መቶ ሃምሳ ብር ስታወጣ ማየት ብርቅ ከመሆን አልፏል። ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው። ደሞዝ ባለበት እየረገጠ የዕቃዎች ዋጋ በየሴከንዱ ሽቅብ እየተወነጨፈ እንዲህ ያለ ተናግዶት ማየት ገንዘቡ ከየት መጣ ያስብላል፤ አንዳንዱ ሰውማ ከቤቱ ውስጥ ገንዘብ ማተሚያ ማሽን ያለው ይመስላል።

 ኑሯችን ዕንቆቅልሽ ነው። ተቆጣጣሪ ብሎ ነገር የለም። ያለውና የሌለው በምን ምክንያት እንዳለውና እንደሌለው ሊታወቅበት የሚያስችል አንድም ብልሃት የለም። በአገራችን መንግሥት አለ ማለት የሚያስችል አንድም ምልክት ደግሞ የለም። በኪነ ጥበቡ ውለን ከመግባታችን በስተቀር የመንግሥትን ቀርቶ የሕዝብን ኅልውና የሚያስረግጥ አንድም ነገር ማግኘት አልቻልኩም። ዛሬ ሃያ ብር የሚሸጥ ነገር ነገ በትንሹ መቶ ብር ሲሸጥ ማየት ምን ማለት እንደሆነ መረዳ የሚከብደው ሰው አይኖርም። የሀብት ክምችት እሽቅድምድሙ እንደመቶ ሜትር ሩጫ ፍጥነቱ ንፋሳዊና ብርሃናዊ ሆኗል። በዚህ ላይ ዳኛ የለ፤ ታዛቢ የለ፤ ሕግ የለ፤ አዳሜን እየረጋገጥህና እየረመረምክ ባዋጣህ መንገድ መሮጥና የምትፈልገው የሀብት ደረጃ ላይ ወጥተህ ፊጥ ማለት ነው። የመንግሥት አካላት ደግሞ አሯሯጮች ብቻ ሣይሆኑ ሯጮችም ናቸው። ስለዚህም በሩጫው ተረገጥኩ ብለህ የምታመለክትበት ቢሮ የለም። ተጋግጠህ ከሩጫው ሜዳ ትወጣለህ ወይም እንደምንም ብለህ እዚያው ትንከላወሳለህ። እንዳሁኑ የጠበቀ ሕግ ሳይወጣለት በዱሮ ዘመን የእግር ኳስ ጨዋታም እንዲህ ነበር አሉ - ማንም ጉልበተኛ ኳሷን በጥበብ ሣይሆን በጉልበት ነጥቆ በመውሰድ እግብ የሚከትበት። በአገራችን የአሁን ሁኔታ በገቢህ ላይ ምንም የተጨመረ ነገር ሳይኖር ዋጋዎች እንዲህ ሲንሩ ስታይ ሕይወትህ በነሲብ የሚነዳ እንጂ በሕግና በሥርዓት የሚመራ አይመስልህም። ደናቁርት ደናቁርትን እየጎተቱ ወደ ገደል እየጨመሩ ናቸው።

ዝኮነ ኮይኑ ልጄና እኔ ዶሮ ተራ ገባን። ከድስት የማይወጣ ጫጩት ዶሮ ዋጋው 250 ብር ይሉናል። እዚያም እዚህም ስንጠይቅ የተማከሩ ይመስል - ተማክረውም ሊሆን ይችላል - የሚጠሩትም ሆነ የሚሸጡበት ዋጋ አንድና አንድ ነው። እውነቴን ነው የምላችሁ - ብዙ ሰዎች ጫጩት ዶሮ በ200 ብርና ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ ሲገዙ አየን። አንዳንዱ ገዢማ ስለለመደው ይመስላል በዋጋው መናር ሲያቅማማ አይስተዋልም። እኛ ግን ደነገጥን። ሥጋ ቢኖረው ግዴለም። ግን ለወግና ባህል ሲባል ብቻ አንዲት ስትታረድ ከአየር ወርዶ መሬት የሚደርስ ደም እንኳን የሌላት ጫጩት ዶሮ በ200 ብር መግዛት ግፍ የሚሆንብን መሰለን። ልጄ ግን ሚስቱ እንደምትቆጣው አስረዳኝና እንደምንም ተከራክሮ በ190 ብር አንዲቷን ወንድ ጫጩት ገዝቶ በፌስታል ቋጠራት። ይህ እንግዲህ የድሆችን ዶሮዎች በሚመለከት የታዘብኩት ነው። የኮርማ ዶሮ ታሪክማ ሌላ ነው።

ወደ ሀብታም ሰዎች የዶሮ ግዢ ደግሞ ልውሰዳችሁ። አንዱ ሀብታም ሁለት ወፋፍራም ዶሮዎችን አነሳና ዋጋቸውን ጠየቀ። ለያንዳንዳቸው 375 ብር ተባለ። ብዙም አልተከራከረም። 700 ብር ውልቅ አድርጎ ከፈለና ሁለቱንም ወሰደ። ያለው ማማሩ አልኩ - በልቤ። ወደሌላ የዶሮ መሸጫ ቦታ አመራሁ። የኔ ቤት ድስት የማይችለውን አንድ ዶሮ አንዷ ሴት ሀብታም ብድግ አደረገችና ዋጋውን ጠየቀች። አምስት መቶ ብር ተባለች። እንደነገሩ ተከራከረችና በአራት መቶ ሃምሳ ተስማምታ ይዛው እብስ አለች። አንድ ዶሮ አራት መቶ ሃምሳ ብር! ይህን ትክክለኛ መረጃ ከሌላ ቦታ የምታገኙት አይመስለኝም። አንድ ዶሮ አራት መቶ ሃምሳ የኢትዮጵያ ብር ሲሸጥ እቦታው ነበርኩ። ጉድ ነው። ዶሮው ግን እንዳልኳችሁ ፍሪዳን ያስንቃል። ቢሆንም ግን ዶሮ ነው። በሬ ወይም በግና ፍየል አይደለም፤ እናም ዶሮ 450 ብር ሲያወጣ አየሁ። በዱሮው ዘመን አሥር ብር ፍሪዳ ይገዛ ነበር፤ እናም ዘንድሮ አንድ ዶሮ የተገዛበት ብር በዱሮው ዘመን አርባ አምስት ፍሪዳ ይገዛበት ነበር ማለት ነው። የሒሣብ ዕውቀቴ ወንዝ ባያሻግርም ከዚች የዶሮ ግዢ ነጥብ አንጻር የገንዘባችን ግሽበት 4500% ይመስለኛል።

ዱሮ በግራም ሁለትና ሦስት ብር ይሸጥ የነበረውን የ18 ካራት ወርቅ ከአሁኑ ሰባት መቶና ስምንት መቶ ብር ዋጋው ጋር ስታነጻጽሩትም ግሽበታዊ ሥሌቱ በድንጋጤ ደም ቀጥ ያደርጋል። በ“ሰው በላው ሥርዓት” በኪሎ አንድ ብር ይሸጥ የነበረው ቅቤ ዛሬ 210 ብር ሲሸጥ ዕድገታችንን ለመለካት ምን መሣሪያ መጠቀም እንዳለብን ለማወቅ ወያኔን መጠየቅ ነው። ዱሮ በ120 ብር የሚሸመተውና ማንም ተራ ዜጋ የሚለብሰው የእንግሊዝ እውነተኛ ከሱፍ የተሰፋ ሙሉ ልብስ ዛሬ ሌላ ነገር ተቀያይጦበት በአሥራዎቹ ሺዎች ሲገዛና የደረጃ መለያ ሲሆን ዕድገታችን የደረሰበትን ጫፍ ማሰብ እንችላለን። በቅርብ በደርግ ዘመን እንኳን በሦስት ሺህ ይገዛ የነበረ ያማሃ ሞተር ሣይክል ዛሬ ከመቶ ሺ ብር በላይ ሲገዛ የገንዘባችንን “ጥንካሬ” ያሳያል - ሊያውም እኮ በወረፋ ለወራት ጠብቀህ።

ዱሮ አሥር ብር መንዝረህ ለመጨረስ “የጓደኛ ያለህ” እንዳላልክ ዛሬ አሥር ብር አንዲት ቡትሌ ቢራ እንኳን የማይገዛ ከንቱ ወረቀት መሆኑን ስትረዳ አገርህ ከየት ወዴት እያመራች እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታይሃል። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ሚስቱ ልጅ ስለወለደችለት ፈረስ በሚያስጋልብ አዳራሽ ቅልጥ ያለ ድግስ ደግሶ ከአልማዝና ዕንቁ ውድ ስጦታዎች በተጨማሪ የ2.5 (ሁለት ነጥብ አምስት!) ሚሊዮን ብር መኪና ቁልፍ ለሚስቱ በስጦታ መልክ የሚያበረክት የትናንት ሙልጭ ድሃ የዛሬ ወፍዘራሽ ከበርቴ በቀየህ ስትታዘብ የት እንዳለህ ታውቅ ዘንድ ዐይንህን ብታሽ ከድቅድቅ ጨለማ ውጭ የሚታይህ ሌላ ነገር የለም። ጥሬ እውነት ነው እየነገርኩህ ያለሁት - ለሥነ ጽሑፍ ውበት ብዬ ያጋነንኩ እንዳይመስልህ። …

በዕድሜየ ቆዳ መልስ ሁለትና ሦስት ብር በግና ፍየል ሲሸጥ አይቻለሁ። በዚያን ዘመን አንድ አነስተኛ ከብት (በሬ/መሲና) አርዶ ለመብላት በትንሹ አሥር ብር ያስፈልግ እንደነበር ቀድሜ እንደጠቆምኩት እኔ ራሴ ኅያው ምሥክር ነኝ። ያኔ አሥር ብር ይሸጥ የነበረው በሬ ዛሬ እስከ ሃያ ሺህ ብርና ከዚያም ባለፈ ስልሣ ሺህ ብር ድረስ መቸብቸቡን፣ ያኔ ከ12 ዕንቁላሎች ጋር 10 ወይም 15 ሣንቲም ይሸጥ የነበረው ዶሮ ዛሬ ያለ አንዲትም ዕንቁላል 450 ብር መሸጡን ለታሪክ ፍጆታም ቢሆን መዝግቡልኝ። ዕንቁላልማ ቀድሞ በብር መቶና ከዚያ በላይ የነበረው ዛሬ አንዲት ዕንቁላል ብቻ 3 ብር ከሃምሳ ገብታለች። ተረት ተረት የላም በረት! ኑሯችን ተረት ተረት ሆነና ዐረፈው። የጥንቶቹ የኛን ኑሮ ኖሩና አለፉ፤ እኛ ደግሞ ዕዳ ከፋይ ብቻ ሆነን ቀረን። እናሳዝናለን - አዛኝ ቢኖር።

የበጉንና የፍየሉን ገበያ ያየን እንደሆነም ያው ነው - የተለዬ ነገር የለውም። ጨቅላ በግና ፍየል ይዞ በሺዎች መጥራትና መሸጥ የተለመደ ነው። ሰውም ለምዶታል። ሐበሻ ደግሞ በዓመት ሦስቴና አራቴ የሚኖር ይመስል በዓል በመጣ ቁጥር ቤቱን እያራቆተ ከሰው ላለማነስ በሚል ጅል ፈሊጥ በተጠየቀው ዋጋ ሁሉንም ነገር ይገዛል። አንዳንዱማ ሳይገዛ መተው ራሱ እንደምርጫ አይታየውም። ባይገዛ የሚሞት ይመስለዋል። ነገ ለማከክ የዛሬን በዓል በቅርጫም፣ በዶሮም፣ በበግ/በፍየልም ማሳለፍ ይወዳል። አብዛኛው ይህን የሚያደርገው ለባህሉና ለቤተሰብ ፍላጎት እንጂ አቅሙ ፈቅዶለት አይመስለኝም - ከእግር ጥፍሩ እስከራስ ፀጉሩ በብድርና በመሥሪያ ቤት ዕዳ የሚወጣጠረው ሰው ብዙ ነው - ይህ የከማን አንሼ ባህል ጠፍቶ የማይበት ዘመን ይናፍቀኛል፤ ብዙዎቻችንን ከሰው በታች ያደረገን ይሄው መጥፎ ልማድ ነው። በተረታችን “ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም” የሚል ትክክለኛ ብሂል አለን - የሚተገብረው ግን ጥቂቱ ነው። የሠርግና የልደት ወይም የክርስትና ድግሶችን ብናይ ብዙ ያናግረናል፤ ምን አለፋችሁ የባህል አብዮት ማካሄድ ከምንም በላይ ያስፈልገናል።

በዚህ ሰሞን በዓል ሲተረማመስ የሚታየው ሁሉ ወግና ልማድ ለማሟላት እንጂ ውስጡ አምኖበት እንዳልሆነ መገመት አይከብድም። አለባበሱ የተጎሳቆለ ሰው በሁለት መቶ ብር ዶሮና በሁለት መቶ አሥር ብር አንድ ኪሎ ቅቤ ገዝቶ ወደቤቱ ሊሄድ የታክሲ መሣፈሪያ እንኳን ቸግሮት በእግሩ ሲንጠራወዝ ስታዩት ምን ያህል የባህል እስረኛ እንደሆነ በማጤን ከልባችሁ ታዝኑለታላችሁ። መማር ዓይነቱና የጥራት ደረጃው ቢለያይም እንዳለመማር ያለ ክፉ ደዌ የለም። የኛን ማኅበረሰብ ከልጅነት እስከዕውቀት ስታዘበው ብዙም የተለወጠ ነገር የለውም። ቀጣዩ መንግሥታችን ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል። እግዜር ያጽናው። ለመምራት ብቻ ሣይሆን ለመመራት የተዘጋጀ ዜጋ ማግኘትም ከባድ መሆኑን ልናምን ይገባል።

ወደዶሮኣችን እንመለስ። በበኩሌ ዋጋው ውድ ስለሆነብኝ ሳልገዛ ቤቴ ገባሁ። ማንጠግቦሽ ተቆጣችኝ። ራስሽ ሂጅና ግዢ ብዬ እኔም ተቆጣሁ - ለመቆጣት ማን ከማን ያንሳል። ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ከነበርኩበት ቦታ ተጣድፌ ስመጣ አጅሪት ምንም ሳትገዛ መጥታ “ነፁ፣ በጣም ይቅርታ አድርግልኝ። ጫጩት በሁለት መቶ ሃምሳ ገዝቼ ከምመጣ ብዬ ተውኩት። ነገ ጧት ወደ … ሂደህ ሁለት ኪሎ ሥጋ ገዝተህ ትመጣና ጦማችንን እንገድፋለን። …” አለችኝ። ያኔ በሐበሻዊ ያሸናፊነት ስሜት ኮራ አልኩና ተደሰትኩ። ሁሌ ተወቃሽ ነበርኩና ዛሬ ግን ከርሷው ከባለቤቴ በመምጣቱ በቤታችን ደም ያለመፍሰሱ ክስተት የሁለታችንም ስምምነት በመሆኑ ከእስከዛሬው በበለጠ እኔን አኮፈሰኝ። ሌላ ጊዜ “ገንዘብ እንዳታወጣ ብለህ እንጂ ዶሮ መቼ ተወደደና …” እያለች ትነተርከኝ ነበርና።

ቅቤ እንዳልኳችሁ 210 ብር አካባቢ ነው። ዱሮ በገረወይና 18 ብር የነበረ ቅቤ አሁን እንዲህ ሆነና ለመድኃኒትም ብርቅ ሆነ። ሊያውም ትክክለኛ ቅቤ፣ ትክክለኛ ዘይት፣ ትክክለኛ የበርበሬ ድልህ፣ ትክክለኛ ሥጋ፣ ትክክለኛ ቆጥረህ የማትዘልቀው ሸቀጥ ሁሉ በቀላሉ አይገኝም፤ አገር ምድሩን ያጥለቀለቀው የቀጣፊ “ፌክ”ና “ፎርጅድ” ምርት ነው። አስገራሚ ነገር ልንገርህ፡- አዲስ አበባ ውስጥ በየሠፈሩ የሚሠራ ቅቤ በአይሱዙ መኪና ይጫንና ወደሸኖ ይሄድልሃል፤ ከዚያ ከአይሱዙው ጋር ተጭነው የሄዱ ሰዎች - ሊፍት ተሰጥቷቸው ወይም ገንዘብ ከፍለው የተሣፈሩ ሰዎች - “የሸኖ ቅቤ ገዛን” እያሉ ተሣፍረው በሄዱበት መኪና ወደሸኖ የተጓዘውን “ንጹሕ ቅቤ” በውድ ዋጋ ገዝተው ይመጣሉ። ሲያነጥሩት ግን ይምበከበክና ጥቂት ቅቤ ይወጣዋል አለዚያም ከናካቴው ይደፋል። በሌሎች ነገሮችም እንዲሁ ነው። በሊትርም ግዛ፣ በኪሎም ግዛ፣ በሜትርም ግዛ፣ በክንድ ልኬትም ግዛ በአብዛኛው ግን ትሸቀባለህ ወይም የማይረባ ዕቃ ይዘህ ወደቤትህ ትመለሳለህ - ስንቱ ቀልጧል መሰለህ። በዚያ ላይ ዕድሜ ለቻይና እሷም ከስግብግብ ነጋዴ ጋር እየተሻረከች ከደረጃ በታች የሆነ ውዳቂ ምርት ከከተማ እስከ ገጠር እያሰራጨች እስከመቅኒያችን ድረስ ገብታ እየመጠመጠችን ነው፤ አቤት የገባንበት ዕዳ! ከዚህ ሁሉ ሲዖላዊ ሕይወት የሚገላግለን አንድዬ ብቻ እንጂ በሰው ትግል ብቻ የሚሆንልን አይመስለኝም።

እኔ ወንደላጤ እያለሁ በኪሎ አንድ ብር የነበረ ምሥር ክክ አሁን 40 ብር አካባቢ ነው - አሁን እየጻፍኩ ሳለሁም ሊጨምር ይችላል፤ እኛ አገር ደግሞ መጨመር እንጂ መቀነስ ብሎ ነገር ሲያልፍ አይነካንም። የምግብ ዘይቱ፣ አተር ክኩ፣ አትክልቱ፣ ጤፉ፣ ሽምብራው፣ ከሰሉ፣ ላምባው፣ ስሚንቶው፣ አሸዋው፣ ጠጠሩ፣ ብረቱ፣ ኮረንቲው፣ ውኃው፣ ሥጋው፣ ወተቱ፣ ምኑም ምናምኑም የዘንድሮው ዋጋ ከዱሮው ጋር ሲነፃፀር በትንሹ 1000% አድጓል። ለምሣሌ እኔ ቤት ስሠራ 41 ብር የገዛሁት ባለ14 ቁጥር አንድ ቤርጋ የአርማታ ብረት አሁን ከአምስት መቶ ብር በላይ ነው። ይህን የዋጋ ንረት ያመጣው የኢኮኖሚ ዕድገት ነው ቢሉኝ ከመሣቅ ውጭ ሌላ አማራጭ የለኝም። እኔ ወጣት እያለሁ በብር ከስሙኒ እመገበው የነበረው ባለቅልጥም ቀይ ወጥ ዛሬ በአማካይ 60 ብር ገብቷል መባልን ስሰማ “ወይ ስምንተኛው ሺህ! እንዲህም አለ ለካ!” ከማለት ውጪ ምንም ማለት አልችልም። ዱሮ ሰባት ብር የነበረው አንድ ኩንታል ስሚንቶ ዛሬ ሊያውም በጣም ረከሰ ተብሎ 320 ብር መሸጡን የሚያውቅ ሰው አገር መውደቋን ሣይሆን ማደጓን የሚያምን ከሆነ በኑሮና በቁጥር መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ የማይችል ደደብ መሆን አለበት። ዱሮ በሃያ ሣንቲም የምንጠጣው አረንቻታ (ለስላሳ) ዛሬ በየሆቴል ቤቱ በአሥራዎቹና በሠላሣዎቹ ሲሸጥ እያዬ አገር አደገች የሚል ካለ ስለዕድገት ቅንጣት ግንዛቤ የሌለው የለዬለት ‹ጀዝባ› ነው። ዱሮ ዐርባ ሣንቲም ይሸጥ የነበረው እንደ እርጎ የሚገመጥ ቢራ ዛሬ ብሻን ጮረሬ ሆኖ በአሥራዎቹና በስልሳዎቹ ብር ሲቸበቸብ የሚያይ ሰው አገራችን አደገች ብሎ የሚፈነጥዝ ከሆነ ወያኔያዊ ወገናዊነቱ እንዳለ ሆኖ ወደሚቀርበው የዕብዶች ሆስፒታል መሄድ ይኖርበታል - የዕብድ ሆስፒታላችን ከአንድ ያነሰ ቢሆንም።

ዱሮ ከአሥር ሣንቲም ባነሰ ዋጋ ይገመጥ የነበረው ጠረንገሎ ፓፓያ ዛሬ በኪሎ ከሃያ ብር በታች በቀላሉ እንደማይገኝ እየተረዳ “ኑሯችን ተሻሻለ” የሚል ገልቱ ዜጋ ካለ በርግጥም ገልቱነቱ ሥሙር ነው። ዱሮ ሉካንዳ ቤት ተገብቶ በ”ከዚህ መልስ ቁረጥልኝ” ለኩሊዎች ሸክም የሚከብድ ሥጋ በአንድ ብርና በሁለት ብር ይገዛ እንዳልነበር ዛሬ በምሣሌ ሆቴልና በመሳሰሉት ሆቴሎች ተገብቶ ለኪሎ ቁርጥ/ጥብስ ከአምስት መቶ ብር በታች እንደማይከፈል የሚገነዘብ ሰው ይህን ዘመን የመቅሰፍት እንጂ የዕድገት እንደማይለው ጤናማ አዕምሮ ያለው ሁሉ የሚፈርደው ነው። ዱሮ ውኃ ጠማኝ ለሚል መንገደኛ ከወተትና ከጠላ ውጪ መስጠት ያሣፍር ነበር፤ ቆየት ብሎ ሥልጣኔ ሲጀምር ደግሞ በቀን አንድ ሊትር ወተት እየተወሰደ በወር ሁለትና ሦስት ብር ይከፈል ነበር - በሊትር ከ10 ሣንቲም በታች መሆኑ ነው። ዛሬ ግን አንዲት ሊትር ወተት ከ18 ብር በታች ማግኘት አይቻልም - ሻይ ባቅሟ በብዙ ተራ ቡና ቤቶች አምስት ብርን ካለፈች ቆየች። ይህ ጊዜ የዕድገት ነው ከተባለ ያኛውና በነሼኪ ሻይ ቤት በ35 ሣንቲም ፓስታ በዳቦ ምሣና ራት ግጥም አድርገን የምንበላበት ዘመን ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም።

የሃያ ብር ኩንታል ጤፍ ሁለት ሺህ ብር ሲገባ የአገር ዕድገት ከተባለ፣ የስሙኒ ስኳር ለወያኔው መንግሥት ምሥጋና ይድረሰውና ከፍተኛ ቁጥጥር ተደርጎበት 16.50 ሲገባ ዕድገት ከተባለ፣ የ500 ብር የግንባታ አሸዋ 11000 ብር ሲገባ ዕድገት ከተባለ፣ የሁለት ብር የቆርቆሮ ምሥማር ሃምሳ ብር ሲገባ ዕድገት ከተባለ፣ የ60 ሣንቲም ቤንዚን አሁን በዓለም ደረጃ ዋጋው በጣም ቀነሰ ተብሎ እንኳን 17 ብር ከ43 ሣንቲም ሲገባ ዕድገት ከተባለ፣ ከትውልድ ሀገሬ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ 9 ብር ከአምስት ሣንቲም ያወጣሁበት መንገድ ዛሬ 150 ብር ግድም በመንግሥት አውቶቡስ ስጠየቅበት ዕድገት ከተባለ፣ አንዳች ነገር ቀምሶ ማደር የሚያቅተው የሕዝብ ቁጥር የትዬለሌ መሆኑ እየታወቀ በጥቂቶች መዘባነን ዕድገት የሚለካ ከሆነ፣ ከሁለትና ሦስት ሰዎች ስደት ተነስተን ብዙ ሚሊዮን ዜጎች አገዛዙን እየጠሉ ወደ ውጪ ሲጎርፉ አሁንም ዕድገት ከተባለ፣ … “ዕድገት” የሚለው ቃል ከነባር ፍቺው ተዛንፏልና አዲስ ትርጓሜ ሊያገኝ ይገባዋል። ለማንኛውም በድጋሚ መልካም አዲስ ዘመን - ማነው - መልካም ትንሣኤ ይሁንልን!

ለገምቢና አስተማሪ አስተያየት፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ