የአንበሳ ልጅ ሳለ የጅብ ልጅ ገነነ፣ አላስበላም አለ ጸጉሩ እየበነነ
ይገረም አለሙ

ነገር በምሳሌ
ጠጅ በብርሌ፣
ይሉ የነበሩቱ
አበው እና እመው እነዛ የጥንቱ፣
እንደ አሁኖቹ ቃላት ሳይደርቱ
ዙሪያ ጥምዝ ሄደው ነገር ሳይጎትቱ፤
በምሳሌ አዋዝተው በስንኝ ቋጥረው
በሁለት መስመር ቃል - ቅኔ ተቀኝተው፤
ምክረ ነገራቸው - ከጆሮ ደጃፍ ነጥሮ ሳይመለስ
ከውስጠ ልቦና ከአዕምሮ እንዲደርስ፤
አድርገው ነበረ የሚያስተላልፉት
ሳይወርሰው ቀረ እንጂ ይሄ ትውልድ ንቆት፤
አልፎ አልፎ ለጽሁፌ የአበውን አባባል የምጠቀመው በሁለት ምክንያት ነው። ዋናውና የመጀመሪያው ምክንያቴ አባባሉ መልዕክቱ ጥልቅ ይዘቱ ምጥቅ የሆነና ዘመን ባዘመነው ይሁን ባደነዘዘው የእኛ ብዙ ደቂቃዎች የሚወስድ አገላለጽም ሆነ ቢጻፍም ገጽ የማይበቃውን ነገር መረዳት ለሚችልና ለሚፈልግ ሰው በአጭር የሚገልጽ በመሆኑ ነው። ሁለተኛው ሥልጣኔ የራስን እየተዉ፤ በተውሶ ነገር መኮፈስ ማለት ይመስል እንኳን ለልጆቻውን ሊያስተምሩ ለራሳቸውም ወግ ባህላቸውን የአነጋገር ዘያቸውን እየረሱ ላሉት ወገኖች በእግረ መንገድ ማስታወስ ከተቻለ በሚል ነው። ፕ/ር አዱኛ ወርቁ ጥርት ባለው አገርኛ አነጋገር ሲናገሩ፤ ሰለጠን ባዮቹ ቢከፍቱ ተልባዎች ብዙ እንደሚሉ ባውቅም፤ እኔ ግን እንዴት እንደምኮራባቸውና እንደምቀናባቸው እኔና እኔ ነን የምናውቀው።
ጥቅሙም ጉዳቱም መሳ ለመሳ የሆነውን ፌስ ቡክ የሚባል ዘመን አመጣሽ፣ ትውልድ አኮላሽ ነገር፤ በከማን አንሼ እኔም እንደ እቅሚቲ ስጎረጉር ከተለያየን ዓመታት ያስቆጠርን ወዳጄን መስመር ላይ መሆኑን ነረኝና ደወልኩለት። በመገናኘታችን ሁለታችንም ደስ ብሎን ስንጠያየቅ፤ የኢትዮጵያውያን ሁለተኛ አገር እየሆነች ወደ መጣችው አሜሪካ ከተጓዘ አንድ ሦስት ወራት እንደ አስቆጠረ ነገረኝ። የሄደው ታዲያ በስደት ሳይሆን በዲቪ ነው።
ከዚህ ወዳጄ ጋር ያስተዋወቀን ፖለቲካ ነው፣ ብዙ አሳልፏል፣ ይህን ይህን አድርጓል፣ እንዲህ እንዲህም ተደርጎበታል ብሎ መዘርዘሩ ከሱ ፈቃድ ውጪ አግባብ አይሆንም። ብዙዎች ገና የአሜሪካንን ምድር ሳይረግጡ ሜዲትራኒያን ሰማይ ላይ ሆነው፤ ያለ እኔ ፖለቲከኛ፣ ከእኔ በላይ የታገለ ለአሳር በሚሉበት ዘመን አሜሪካ ሦስት ወር ሲያስቆጥር፤ አይደለም መስዋዕትነቱን መናገር እዛ መሆኑንም መግለጽ አለመፈለጉ እዩኝ እዩኝ ባይ ባለመሆኑ ነውና አደነኩት። እኔም ታዲያ ላሳየው ስላፈለኩ ነው በደምሳሳው መግለጼ።
ይህን ማንሳቴ ለነገረ ትኩረቴ ማያያዣና መንደርደሪያ እንጂ፤ ስለ እሱ ለመተረክም አይደለም። ወዳጄን ከማግኘቴ ሦስት ቀን አስቀድሞ እንዲሁ አሜሪካ አንድ አራት ዓመት የሆነውንና ተገናኝተን የማናውቅ ወዳጄን ፌስ ቡክ በጽሁፍ ሳይሆን በድምጽ አገናኝቶን ስናወጋ፤ አገር ቤት እያሉ ከእኛ በላይ የአንድነት ታጋይ ሲሉ የነበሩ፣ ኢትዮጵያ ወይም ሞት እያሉ ሲፎክሩ የምናውቃቸው ሰዎችን ስም እየጠራ (እኔ ግን መግለጹን አልወደድሁትም)፤ ሁሉም በየጎሣቸው ቅርጫት ገብተው ከለማበት የተጋባበት ይሉ አይነት ሆነው ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ መሆናቸውን አጫውቶኝ ነበርና ንጽጽር ውስጥ ገባሁ።
የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ በስም የተጠቀሱትን ሰዎች አውቃቸዋለሁ፤ ስደት ለጉራ ይመቻል ሆኖ ካልሆነ በስተቀረ በተለይ ቀደም ብዬ ከገለጽኩት ድምጹን አጥፍቶ እየኖረ ቀን እየጠበቀ ካለው ወዳጄ ተግባር ጋር ሲመዘን፤ አይደለም ለፉከራ የሚያበቃ ለቡና ላይ ወሬ የሚሆን ተግባር የሌላቸው ናቸው። ይህ ደግሞ የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የብዙዎቹ በየግዜው ባህር ተሻግረው ከአገር ርቀው ለመኖር የበቁ ወንድም እህቶቻችን ተግባር ነውና፤ በድርጊታቸው አፍረንና አዝነን ማለፍ ብቻ ሳይሆን የነገሩን እንዴትነት፣ የምክንያቱን ምንነት ጠለቅ ብሎ ለማየት መሞከርና ቢቻል እነዚህንም ለመፈወስ መጣር ካልሆነም ወደ ፊት ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከአገር ወጪዎች በበሽታው እንዳይለከፉ መድኃኒት/ክትባት መፈለግ ቢቻል ይበጅ ይመስለኛል።
ነገሩ ምን ይሆን? ከመነሻው አገር ቤት ሳሉ አንድነት አንድነት እያለ የሚያዘምራቸው፣ ሰንደቅ ዓላማ የሚያስለብሳቸው ስሜት እንጂ እውቀት አልነበረም ማለት ነው? ወይንስ ኑር እንደ ዘመኑ የሚለው ስልት ገብቷአቸው፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ ይህንኑ እየተገበሩ ያሉ የራሳቸው የሆነ ነገር/ማንነትና ምንነት የሌላቸው ሆነው ነው? ወይንስ በደረሱበት ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው የተቀበሉዋቸው አለበለዚያም እንኳን ደህና መጣህ ብለው ሻይ ቡና የጋበዙዋቸው ፈጥነው የጎሣ ክትባት ከተብዋቸው ይሆን።
በየግዜው በተለያየ ምክንያትና መንገድ ከአገር ከሚወጣው ሰው መካከል ቁጥሩ ቀላል የማይባለው በየሚደርስበት አገር የቀደሙት በተለከፉበት በሽታ እየተለከፈ የፖለቲካውንም የኃይማኖቱንም የጎሣውንም ክፍፍል ባያከረው ኖሮ የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች ብቻ ልዩነቱን አሁን በሚገኝበት ደረጃ ማድረስ ባልቻሉ ነበር።
ከመነሻው እምነት ያለውና በእውነት መንገድ ላይ ያለ ሰው ጊዜያዊ ጥቅምን እያሰላ፣ እንደ እስስት ማንነቱን እየለዋወጠ መኖር አይሆንለትም። ነገር ግን ፖለቲካውንም ሆነ ኃይማኖቱን፣ ጎሣውንም ሆነ ጓደኝነት ጓዳዊነቱን የሚፈልገው ለንግድ ከሆነ እሱ የሚገኘው እውነት ባለበት ቦታ ሳይሆን ወደ ኪስ የሚገባ ነገር ይገኛል ባለበት ቦታ ነው። የህሊና ጥያቄ የሆነው ዓላማ ሳይሆን ሆድ መሙላት የሚያስችለው ቁሳዊና ዓለማዊ ነገር ነው የሚያማልለው። ለእርሱ ማን ሄደ ማን መጣ ወይም ይመጣል አያሳስበውም። ከኢትዮጵያዊነት ወደ ጎሠኝነት በነፋስ ፍጥነት መቀየር የቻለ፣ የኢትዮጵያዊነትን ቡልኮ ጥሎ የጎሣ ጥብቆ ሲለብስ ያልጠበበውም ያላስቸገረውም በመሆኑ፤ ወያኔ ከሥልጣን ተወገደ አልተወገደ የማያሳስበውን ያህል የሚመጣው ማን ሆነ ምን አያስጨንቀውም። ፈጥኖ ካባ ገልብጦ አንደበቱን ስሎ ከመጣው ጋር መስሎ ጥቅም ማግኘቱን ስለሆነ የሚያስበው፤ ስለሚችልበትም የሁሉ ዘመን ሰው ይሉት አይነት ነው።
በእጅጉ የሚያሳዝነው፣ እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ተከትለው አብረው ዳንኪራ የሚረግጡት ናቸው። ሌላው ቢቀር ይህ ሰው ትናንት እንዲህ ነኝ ሲል ነበር፤ እንዲህም እንዲያም ሲናገር ሰምተነው ነበር፤ ታዲያ ዛሬ ለምንና ምነው ብሎ ራስን ጠይቆ ትንሽ የጭንቅላት ጅምናስቲክ ሰርቶ ለመከተልም ላለመከተልም መወሰን ሲገባ፤ በስሜት ብቻ እየተነዱ፣ በሞቅታ እየጋሉ ለለውጥ ሳይሆን ኪስ ለማሳበጥ ከሚታገሉ ጋር መወገን ትርፉ ጸጸት ነው። እነርሱ እንደሆኑ የተሻለ ነገር ከታያቸው ወይንም የያዙት ንግድ አትራፊነቱ ካጠራጠራቸው ሳይነግሩም ሳያማክሩም ነው ሽል የሚሉት።
አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በምላሳቸው ተታልሎ በስህተት ሲከተላቸው ከዚህ አልፎ ሲያደንቃቸውና ነፋስ አይንካብኝ ሲል የነበረው፣ እንዴ! መቼ እንዴትና በምን ሁኔታ? እዛ ተገኙ የሚለው ነገሩ ካለፈ በኋላ ነው። ከዛ በኋላ ውግዘት ቢያዥጎደጉዱ፣ ክስ ቢደረድሩ፣ እንዲህ ነበር እንዲያ ነበር ቢሉ ወዘተ ፋይዳ የለውም። የአንበሳ ልጅ ሳለ የጅብ ልጅ ገነነ፣ አላስበላም አለ ጸጉሩ እየበነነ እንደሚሉት አበው፣ ለአገራቸውና ለወገናቸው ስንት የሰሩ፣ መስዋዕትነታቸው ያልተነገረና ያልተዘከረ አያሌ ኢትዮጵያውያን ለሁሉም ግዜ አለው ብለው አንገታቸውን ደፍተው በሚኖሩበት አገርና ዘመን፤ ከምኑም ያልነበሩና አሁንም የሌሉ በእርዳ ተራዳ እየተጯጯሁ አላስቆም አላስቀምጥ ሲሉ፣ ግርዶሹን ገልጦ ማንነታቸውን አፍርጦ የሚሉትን አለመሆናቸውን በማስረጃ አረጋግጦና አስረግጦ መንገር ያስፈልጋል።
እንዲህ አይነቶቹን ሰዎች የምንቃወምና ድርጊታቸውን የምንኮንን ሰዎችም ብንሆን፣ በመረጃና ማስረጃ መሞገት ማጋለጥ እንጂ፤ ተራ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ በመግባት ለእነርሱ አጫዋች መሆን የለብንም። ቁም ነገር የላቸውምና የታጠቁት ዓላማ አሸጋግረው የሚያዩት ግብ የላቸውምና እሽኮለሌውን የቃላት ጦርነቱን ይፈልጉታል። ይህን ካጡ ምን ይሰራሉ በምንስ ይነግዳሉ። እናም በአንድ ጽሁፌ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የነጋዴ አናጋጅ ከመሆን፤ ራሳችንን እንጠብቅ፣ እናቅብ።