La tour eiffel, Paris

ላ ቱር ኤፌል (ኤፌል ታወር)፣ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ

ከዘንድሮ የበጋ እረፍቴ ውስጥ አስሩን ቀን ፈረንሳይ ለማሳለፍ አስቤ ወደ ፓሪስ አቀናሁ

ወለላዬ ከስዊድን

ተማሪዎች ሁሉ ክፍል ተመድበው ትምህርት በጀመሩበት የጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ መርዕድ አዝማች ስብስቴ ነጋሲ ት/ቤት ተገኘሁ። ትምህርት ቤቱ እንደ ስብስቴ ረዥም ዕድሜ እንዳለው ይነገርለታል። ከዛ ት/ቤት ስም በስተቀር ለሌላ ሰው ወይም ተቋም ስም ሲወጣ ሰምቼ አላውቅም። ስሙ እንዳይረሳ ያደረገው የት/ቤቱ ስምና ሩቅ ዘመንን ለመግለጽ “ኡ ... የስብስቴ ጊዜ እኮ ነው …" የሚባለው አባባል ይመስለኛል።

ዛሬ ፓሪስ ላይ ያገኘሁት ይህን አባቴን ነው
ዛሬ ፓሪስ ላይ ያገኘሁት ይህን አባቴን ነው

አስተማሪው እየመራ የወሰደኝ ክፍል በተማሪዎች ጢም ብሎ ሞልቷል። በእያንዳንዱ ዴስክ ላይ ሦስት ሦስት ተማሪዎች ተቀምጠዋል። አስተማሪው የዳይሬክተሩ ትእዛዝ ሆኖበት እንጂ፤ ክፍሉ ሙሉ ተማሪ እንዳለው ያውቃል። ብላክ ቦርዱ ጋ ላንቲካ ይመስል አቆመኝ። የስልሳ ልጆች ዓይን እኔ ላይ አረፈ። ልጆቹ አስተማሪው እዛ ወስዶ ሲገትረኝ ስለ የተጉረጠረጡ ቀያይ ዓይኖቼና ስለ ቀጭን ሰውነቴ ሊማሩ የቀረብኩ ሳይመስላቸው አይቀርም፤ ጸጥ ብለው በመገረም ነበር የሚያዩኝ። ያቺ ጊዜ የአንድ ሙሉ ክረምት ያህል ረዥም ነበረች። ግን ብርድ አልነበረም የሚሰማኝ ሙቀት ነበር፤ ፊቴ በላብ ተጥለቅልቆ እየተቁለጨለኩ ቆየሁ።

ከትንሽ ቆይታ በኋላ አንድ ልጅ እኛጋ ና ብሎ ጠራኝ ወደ ልጁ ሄድኩ ሦስት ሆነው ተቀምጠዋል። ኮከቤ ገሰሰ፣ አማረ ማሞና አለማየሁ አበበ ይባላሉ። እንደምንም ፎቀቅ ብለውልኝ ግማሽ ቂጤ መቀመጫ ይዞ ትምህርት ቀጠልኩ። የጠራኝ ልጅ ሙሉ ጉንጮች ያሉት ፊተ ክብ፣ ጠጉሩ እስከ ግንባሩ ድፍት ያለ፣ ጥሩ ጠባይ ያለውና ለቁም ነገር የሚፈለግ ጨዋና ደግ ልጅ ነው። ከዛን ቀን ጀምሮ ለብዙ ዘመን ጓደኞች ሆነን ቆየን፤ ከኛ አልፎ ቤተሰቦቻችንም የሚጠያየቁ ዘመዳሞች ሆነው እስካሁን ይኖራሉ።

የደርግ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ይህ ጓደናዬ አገር ለቆ ወጥቶ ተለያየን። እስራኤል አገር ገባ። እኔም የሱኑ ፈለግ ተከትዬ ተሰደድኹ። ስዊድን ከገባሁ ሃያኛ ዓመቴ ተቃርቧል። ከዘንድሮ የበጋ እረፍቴ ውስጥ አስሩን ቀን ፈረንሳይ ለማሳለፍ አስቤ ወደ ፓሪስ አቀናሁ። በገባሁ በሁለተኛ ቀን ምሽት ሬስቶራንት ምኒልክ ከአንድ ሰው ጋር እራት እየበላሁ ነው። ሰውየው ሙሉ ለሙሉ ፀጉሩ ተመልጧል። አጠር ያለና የሞሉ ጉንጮች ያሉት ነው። ቡና ዐይነት የደፈረሱ ዓይኖቼና ራሴን የሞላው ሽበቴ ላይ ዓይኑን ተክሎ ቆየ። ከኔ መልክ ጀርባ ስንት ትዝታ እንደሚመጣበት እርግጠኛ ነኝ። እኔም እሱን እያየሁ ጭልጥ ብዬ ሄድኩ፣ ስንትና ስንት የልጅነት ትዝታ ውስጥ ገብቼ ሰጠምኹ።

ተመስገን የተባለ ጓደኛችን ጭር ያለ ክፍል አንዲት ልጅ ሊስም ሲታገል አስቸግራው፤ አንገቷን ያዙልኝ ያለን ትዝ አለኝ። ወደ ውጪ ሊወጣ ሲል የወጣት ማኅበሩን ጸሐፊ (ጉቦ መሆኑ ነው) እቤታቸው አራት ብርጭቆ እርጎ አጠጥቶት፤ ተቅማጥ ታሞብን ስንጨነቅ ያደረነውን አስታወስኹ፣ ከፊቴ ካለው ሰው ጋር የአምስት ሳንቲም ኦቾሎኒ ገዝተን ለሁለት ተካፍለን የበላነውን፤ መቋሚያ የሚያክል ሸንኮራ በስሙኒ ገዝተን አላልቅ ብሎን ስንታገል ት/ቤት ረፍዶብን የተገረፍነውን፤ በሃምሳ ሳንቲም ሦስት ፊልም ያየነውን፤ የስሙኒ የስሙኒ ደርሶ መልስ ቲኬት ቆርጠን በአንበሳ አውቶቡስ የተመላለስነውን፤ ከኤሊየ ስቶር የእስራኤል ጃኬት በሰባት ብር፤ ሰንደል ጫማ ከመርካቶ በአራት ብር ከአሃሳ ተገዝቶልን የዘነጥነውን ሁሉ ሳይቀር በዓይነ ሕሊናዬ ተሽከርክረው አለፉ።

እነኾ ይህ ሰው የስድስተኛ ክፍል መቀመጫ ያጋራኝ አማረ ማሞ ነው። አማረ በአካልና በዕድሜ ይለወጥ እንጂ፤ የልጅነት ባህሪው እንዳለ ነው። ሰው መውደዱ፣ ትህትናና ቅንነቱ አሁንም አለ። አማረ ካገኘኝ ጊዜ አንስቶ ለኔ እንደ አባት ነው በዘወትር ጸሎቱ እንኳን ሳይለየኝ ኖሯል። ቦታ በመሥጠት የጀመረው ደግነቱ እስካሁን አልተለየኝም፤ እውጪ አገር እንደወጣ መንገዱን ያመቻቸልኝና የረዳኝ እሱ ነው። ዛሬ ፓሪስ ላይ ያገኘሁት ይህን አባቴን ነው።

ከመስዬ ለ ሜር (ከክቡር ከንቲባ) ጋር ተዋወኩ

አቶ ሰለሞን ይትባረክ በፓሪስ
አቶ ሰለሞን ይትባረክ በፓሪስ (ፈረንሳይ) የሬስቶራት ምኒልክ ባለቤት

ከአማረ ጋር የተገናኘነው የሬስቶራት ምኒልክ ባለቤት ከሆነው ከሰለሞን ይትባረክ ምግብ ቤት ነው። ሬስቶራንቱ መካከለኛ መጠን ያለው አዳራሽ ነው፤ ገና ወደውስጥ ሲገቡ ዓይንዎት የሚያርፈው ግርግዳ ላይ በተሰቀሉት የቀድሞና ያሁን ዘመን ታሪካዊ ፎቶዎች፣ ስዕሎችና ጌጦች ላይ ነው። ፎቶዎቹ ታዋቂ የአገራችን ሰዎችን፣ የቀድሞ ንጉሦቻችንን፣ ስፖርተኖችና ሙዚቀኖችን፣ ጀግኖችና የጦር አዝማቾችን ተካተውበታል። በምግቡ ቤቱ ከዶሮ ወጥ እስከሽሮ ወጥ ዐይነት በዐይነት የሚማረጥበት ሲሆን፣ ከአማረ እንጀራ ጋር የሚቀርበው የበግና የበሬ ጥብስ ክትፎና ድሎቱ እጅ ያስቆረጥማል። በተለይ ዱለቱ በአውሮፓ ከሚገኙ አገርኛ ምግብ ቤቶች ቅድሚያ እንደያዘ ይነገርለታል። ሰለሞን ሬስቶራንቱን ከከፈተ ሃያ አራተኛ ዓመቱ ነው። በዚሁ ምግብ ቤት ሥራ ላይ ብዙ ውጣውረድ አይቷል። እንደጀመርኩ ስድስት ምግብ ብቻ የሸጥኩበት ቀን ነበር በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል። በስሕተት የከፈትኩ ይመስለኝ ነበር እስከማለት የደረሰበትም ሁኔታ እንደነበር ያወሳል።

በኋላ ግን ጥሩ ሆነልኝ ብዙም ሰው ተዋወቀልኝ። የአገሬ ሰው ብቻ ሳይሆን ለብዙ የፈረንሳይ ሰዎችም ምግቡ ተመራጭ ሆነ። በተለይ ታዋቂዋ ፈረንሳዊ ዘፋኝ ሄለን ሴጋራ ምግቡን ስለወደደችው እሷን በማለት ብዙ የፈረንሳይ ታላላቅ ሰዎች መምጣትና መመገብ ጀመሩ። ሄለን በማስተዋወቁ በኩል የራሷን ድርሻ ተወጥታለች። ለምግብ ቤቱ ገናናነትና ለዚህ መድረስ ጉልህ ሚና አላት ይላል ሰለሞን፤ ሄለንን አንስቶ አይጠግባትም። እስካሁንም እንደምትመገብ ይናገራል።

እንዲሁም በአሜሪካ የፈረንሳይ አንባሳደርና ምክትል አምባሳደሯ፣ የዩኔስኮ ዳይሬክተርና ምክትል ዳይሬክተር፣ የተለያዩ አገራት አንባሳደሮች፣ ኢትዮጵያ የሠሩ የፈረንሳይ አንባሳደሮች ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸው ታላላቅ የፈረንሳይ ዜጎችና የውጪ አገራት ሰዎች ይመገቡ እንደነበርና አሁንም የሚመጡ እንዳሉ፤ ከኢትዮጵያ ታዋቂ ሰዎች ደግሞ ቅጣው እጅጉ ቤቱን እንደጎበኙና እንደተመገቡ፣ ጌታቸው መኩሪያና አስናቀች ወርቁም በመጡ ጊዜ የሚመገቡት እሱጋ እንደነበር፣ መሐሙድና አለማየሁ እሸቴም አሁንም ድረስ ሲመጡ እንደሚጎበኙት ሲገልጽ ከቡዞዎቹም ጋር አብሮ የተነሳው ፎቶ ለመታሰቢያነት በምግብ ቤቱ ተሰቅሏል። በቅብብሎሽ በሚነገር የምግብ ቤቱ ጥሩ ዝና ቤቱ ተወዳጅ እንደሆነለት የሚናገረው ሰለሞን፤ ፈረንሳይ ነዋሪ የሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያንም የዕለት በዕለት ተመጋቢዎቹ እንደሆኑ፤ እዚህ ተወልደው ያደጉና ከኢትዮጵያ የመጡ ወጣት ልጆችም ምግቡን እንደሚወዱት፤ ለዚህም ምክንያቱ በተቻለ መጠን በጥራት ስለምንሠራ ለሥራው ቅድሚያ በመስጠት ስለምንደክም፤ እኔን ታናሽ ወንድሜ ሙሉ ኃላፊነት ወስደን ራሳችን ጭምር ስለምንሠራ ምግብ ቤቱ ተውዳጅነቱና የአቅርቦቱ ጥራት ላይጓደል እንደቻለ ይናገራል።

በዚህም ምክንያት የረጅም ጊዜ አገልግሎቴንና በባህላዊ ምግብ አሠራር ለቱሪዝም ባቀረብኩት አገልግሎት BFM የተባለ የፈረንሳይ ቴሌቭዥን በእንግድነት ያቀረበኝ ሲሆን፣ የፈረንሳይ ከንቲባም የእውቅና ደብዳቤ እንደጻፉለት አጫውቶናል። ካለው እርካታ ደግሞ ሲናገር ብዙ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች እዚህ ቤት እየሠሩ ራሳቸውን ማሻሻል በመቻላቸው ትልቅ ደስታ አለኝ ብሏል። ወደፊት ምን ዐይነት የሥራ እቅድ እንዳለው ደግሞ ሲናገር፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ከወንድሞቼና ከኅቶቼ ጋር አብሬ ሆኜ እናትና አባትችንን ስም የሚያስነሳ መታሰቢያም የሚሆን ሥራ ለማቋቋም እቅድ አለኝ ብሏል።

ሬስቶራንት ምኒልክ የሚገኘው በፓሪስ የሕዝብ ሰፈር ነው ተብሎ በሚነገርለት ቦታ ሲሆን፣ የንግድ ሰፈር በመሆኑ ሞቅና ደመቅ ብሎ የሚውልና የሚያመሽ ነው። ሰለሞን በአካባቢው የሚወደድ፣ ከሁሉ ጋር የሚግባባና እንደ አውራ የሚታይ በመሆኑ፤ ያካባቢው ነዋሪዎች መስዬ ለ ሜር (ክቡር ከንቲባ) እያሉ ይጠሩታል። ክቡር ከንቲባውን የተዋወኩትና ያገኘሁት በዚህ መልክ ነበር።

ሜሪ-ሮዝ ብላኮስ የከንቲባው ደንበኛ

ሜሪ-ሮዝ ብላኮስ
ሜሪ-ሮዝ ብላኮስ

ከንቲባው ምግብ ቤት ከሚመጡት ተመጋቢዎች መካከል አንዷ ሜሪ-ሮዝ ናት። ሜሪ የግሪክ ዝርያ ያላት ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዳ ያደገች እዛው የተማረችና የኖረች ናት። “ኢልካ” እና “ኢንተርናሽናል ላይፍ ኬር ፎር አፍሪካ” በተሰኙ መሥሪያ ቤቶች ለረዥም ዓመታት ሠርታለች። የተማረችው አዲስ አበባ በሚገኘው ሊሴ ገ/ማርያም የፈረንሳይ ት/ ቤት ነው። አባቷ ጆርጅ ብላኮስ ይባላሉ። ቢስ ካንፓኒና ጆስ ሐንሰን በጄኔራል ማናጀርነት ሠርተዋል። እናቷ ደግሞ ሮዚት ብላኮስ ይባላሉ። ኤር ፍራንስ በኋላም የፈረንሳይ ኤምባሲ ይሠሩ ነበር። ሜሪ ብቻ ሳትሆን እናቷም አባትዋም ሁለት ወንድሞቿና እኅቷም ኢትዮጵያ ተውልደው እንዳደጉ ሜሪ ትናገራለች።

አገሬ ኢትዮጵያ ናት። የምትለው ሜሪ ኢትዮጵያን ስታነሳ በስስትና በፍቅር ነው። ከሥራዋ መባረሯና አለውዴታዋ ወደ ፈረንሳይ መውጣቷ ያንገበግባታል። አማርኛዋ አንድ ኢትዮጵያዊ ከሚናገረው በላይ ጥርት ያለ ነው። መጻፍና ማንበብ ያልቻለችው ሊሴ ገብረማርያም ስለተማረች እንደሆነ ትናገራለች። ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር አብረን ነው የተማርነው፤ ሌሎችም ጓደኞች ነበሩኝ። አዜብ ተስፋና ፀዳለ አሰፋ አይረሱኝም። ሴንት ጆሴፍ (ቅዱስ ዮሴፍ) ሲከፈት የምርቃቱ ጊዜ አበባ ለጃንሆይ የሠጠሁት እኔ ነበርኩ። ጃንሆይ ስሜን ጠየቁኝ፣ አበረታቱኝም ያን ጊዜ ስምንት ዓመቴ ነበር። የምማረው ናዝሬት ስኩል ነበር።

“ሴንት ጆሴፍ (ቅዱስ ዮሴፍ) ሲከፈት የምርቃቱ ጊዜ አበባ ለጃንሆይ የሠጠሁት እኔ ነበርኩ” ሜሪ-ሮዝ
“ሴንት ጆሴፍ (ቅዱስ ዮሴፍ) ሲከፈት የምርቃቱ ጊዜ አበባ ለጃንሆይ የሠጠሁት እኔ ነበርኩ” ሜሪ-ሮዝ

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1985 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ወጣሁ። የምትለዋ ሜሪ ተወልጄ ያደጉበት አገር በመሆኑ ለኢትዮጵያ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር አለኝ በማለት ትናገራለች። እናትና አባትዋ እንዳረፉ፣ ሌሎች ዘመዶች ግን እንዳሏት፣ ብዙ ጊዜም ወደ ኢትዮጵያ እንደምትሄድ አጫውታናለች። ሜሪ ባሁን ጊዜ ነዋሪነቷ ፈረንሳይ ፓሪስ ሲሆን፤ የከንቲባው (የምኒልክ ሬስቶራንት) ቋሚ ደንበኛ ናት።

ፈረንሳይ ብዙ ሊታዩ የሚገባቸው ቦታዎች አሏት። ፓሪስ ገብቶ ሁሉንም ማዳረስ ባይቻል እንኳን ላ ሉቭር ሙዚየም (ሞናሊዛን ጨምሮ በዓለማችን ምርጥ ስዕሎች ያሉበት)፣ ላ ቱር ኤፌል (ኤፌል ታወር)፣ ሻንዜሊዜ ጎዳና፣ ሴክሪ-ከር ደ ሙንማርትር፣ ሻቶ ደ ቨርሳይ (ቤተመንግሥቱ)፣ … ቅድሚያ ሊሠጣቸው የሚገቡ ናቸው። እነዚህንና ሌሎችንም ለመጎብኘት ችያለሁ። ለዚህ ጉብኝት መሳካት አቶ ሰለሞን ይትባረክ፣ ባለቤቱ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ይትባረክንና አቶ ግርማ ትልቅ ድርሻ አላቸው። ከአማረ ጋር ምስጋናችን ይድረስልን።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!