Prof. Fikre Tolossa & PM Dr. Abiy Ahmed

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳና ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ከዶክተር ዐቢይ ጋራ በቢሮአቸው ውስጥ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮዎች ተነጋገርን

(ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ) በሐምሌ ወር መጨረሻ ይመስለኛል። ከዐምስት ወራት በፊት። በምኒልክ ቤተመንግሥት አዲስ በገነቡት ቢሮአቸው ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን አገኘኋቸው። ገና እንደአገኙኝ አቅፈው ተቀብሉኝ።

ከእዛም የእኔ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” መጽሐፍ ኢትዮጵያዊነትን ለማዳበርና የኢትጵያን አንድነት ለማጠናከር እንደሚረዳ አበሰሩኝ። መጽሐፉንም የሥራ ባልደረቦቻችው እንዲያነቡት እንዳደፋፈሩና ከውስጡም እያወጡ ይጠቅሱ እንደነበር አወጉኝ። የእዛን ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአካል ከማግኘቴ በፊት ግን ቤተመንግሥቱን እንድጎበኝ እድል ሠጥተውኝ ነበር። ስለእሱ በመጨረሻ እመለስበታለሁ።

ከዶክተር ዐቢይ ጋራ በቢሮአቸው ውስጥ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮዎች ተነጋገርን። በመጨረሻ፣ ሕዝብ ስለእሳቸው አመራር የሚለውን አንዳንድ አስተያየት ባካፍላቸው ቅር ይላቸው እንደኾነ ጠየቅኳቸው። ቅር እንደማይላቸው ገለጹልኝ። እኔም የተለያዩ ሕዝባዊ ቅሬታዎችን አቅርቤላቸው አጥጋቢ መልስ ሠጡኝ። ሁሉንም የእኔን ጥያቄዎችና የሳቸውን መልስ እዚህ ማስፈሩ፤ ነገርን የሚጠመዝዙና የሚነታረኩ ሰዎች ሲሳይ እንዳይኾን ጥቂቶቹን ብቻ እጠቅሳለሁ። ለምሳሌ በአንዱ ለመጀመር “ሕዝብ፣ ለምን ወንጀለኞችን አያስሩም” ይሉዎታል፣ አልኩአቸው። እሳቸውም “አሁን ደግሞ ወንጀለኞችን ለምን አትፈታም ይሉኛል። ወንጀላቸው ተረጋግጦ ያሰርናቸው ብዙ ሰዎች እሉ። ታዲያ እኔን ሁሉም ‘የእኔ ወገኖች ስለታሰሩ ፍታልኝ’ ይላል። የማንን ወገን ፈትቼ የማንን በእስር ላቆይ? ጥፋተኛ ጥፋተኛ ነው” አሉኝ።

በዛን ጊዜ የተወዳጅነታቸው ዝቅ ማለት ስለ አሳሰበኝ፣ ተወዳጅነታቸው እንደመጀመሪያው ጊዜ ከፍ እንዲል አንድ ሥራ ቢሠራ መልካም መኾኑን ባማክራቸው፤ “አንደኛ አሁንም የሚወዱኝ ብዙ ሰዎች አሉ። ሁለተኛ፣ እኔ ሕዝብ እንዲወደኝ ብዬ ምንም ነገር እላደርግም። ደግሞም እውነትና ትክክል ነው ያልኩትንም አቋም ለመወደድ ብዬ አልለውጥም። እርስዎን እንደምሳሌ ልውሰድዎት። እርስዎ የኦሮሞ እና የእማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ ብለው የጻፉትን መጽሐፍ ከማሳተምዎ በፊት አያሌ ግጥሞችን፣ ተውኔቶችንና የተለያዩ መጣጥፎችን ጽፈው እንደነበር አውቃለሁ። ኾኖም ይህን ወሳኝና ሐቀኛ ታሪካዊ መጽሐፍ ለሕትመት ከአበቁ በኋላ ተቃዋሚዎች ተነሱቦት። መቼም መጽሐፉን የጻፉት እውነተኛነቱን አምነውበት ነው። ታዲያ በመጽሐፉ ምክንያት ተቃዋሚዎች ስለተነሱብዎት ለመወደድ ብለው የመጽሐፉን ሐቀኝነት ይክዳሉ? የቆሙለትንስ እውነት አውግዘው ያፈገፍጋሉ?” ብለው ጥያቄን በጥያቄ መለሱልኝ። እኔም “በፍጹም!” አልኳቸው። እሳቸውም “እኔም እንደዛው ነኝ፣” ሲሉ በቆራጥነት የተሞላ ድምፃቸውን አሰሙኝ።

በመሐላችን ጥቂት ጸጥታ ከሰፈነ በኋላ ንግግራቸውን በመቀጠል እንዲህ አሉ፤ “እኔ ሰውን በግፍ አልገድልም። ሰው መግደል ፀያፍ ነው። አግዚእብሔርም አይወደውም። ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንድም ገንዝብ አልሰርቅም። ደግሞ አንድ ቃል እገባልዎታለሁ። … የመጣው ቢመጣ የእኔ መሪነት ዘመን ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያ እንድትበጣጠስ አልፈቅድም። በእዚህ ቀልድ የለም።” የኢትዮጵያን አንድነት አስመልክቶም ኾነ ስለሌሎቹም ጉዳይዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነገሩኝ በግልጽነት፣ በቀጥታና በሐቀኝነት እንደነበር ዓይኖቻቸው፣ ድምፃቸውና ቀትራቸው እማኝ ነበሩ።

ስለ ሥልጣናቸው ደግሞ ዶክተር ዐቢይ እንዲህ አሉኝ፤ “የልቤን መሻት ብናገር እኔ የምፈልገው ሥልጣን ለቅቄ፣ ፖለቲካን ትቼ የምርምርና የሳይንስ መስኮች ላይ መሠማራት ነው። መደመር የሚባል መጽሐፍ ጽፌ ልጨርስ ነው። ይሄው ይመልከቱት። እኔን ለሚተካው መሪ አቅልዬለታለሁ። ይሄን መጽሐፍ እያነበበ በቀላሉ ኢትዮጵያን ሊመራ ይችላል።”

እኔም በእዚህ ትርምስና ኹከት ውስጥ እንዴት ይህን መሰል መርኀ ፖለቲካና ኤኮኖሚ ሊጽፉ እንደቻሉ ተደነቅሁ። እራሳቸውና ትከሻቸው እጅግ ደንዳና መሆናቸውንም አስተዋልኩ።

ስለ የውጪ አገር የመንግሥት መሪዎች ወዳጆቻቸው ሲያወሱኝ ደግሞ፤ “እኔ ብዙ ወዳጆች አሉኝ” በማለት ገለጡልኝ። “እነዚህ በአጭር ጊዜ ያፈራሁአቸው ወዳጆቼ ለኢትዮጵያ እድገትና ደኅንነት በጣም ይጠቅማሉ። በማንኛውም ረገድ ኢትዮጵያን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው።" ስለ መሪዎቹ ለትብብር መዘጋጀት ሌላም እዚህ የማይጻፉ ነገሮች ገለጡልኝ። እኔም እሳቸው በአሉት አመንኩበት።

የአፄ ምኒልክን የግል መኖርያ ቤት አቀመጥና የእሳቸውን ለአገር አርቆ አሳቢነት በተመለከተ፤ "እንዳየኸው ለአፄ ምኒልክ መኝታ ቤት በጣም ቅርብ ኾኖ የተገነባው ማረፊያ ቤት የኦሮሞው አማካሪያቸው የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እንጂ የሚስታቸው የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አልነበረም። ይህን ማድረጋቸው አንደኛ፣ ምኒልክ ሰውን የሚያቀርቡት በችሎታው እንጂ በዘር ስላልኾነ፣ ሁለተኛ በቀንም ሆነ በሌሊት ስለአገር ጉዳይ ከፊታውራሪው ከአባ መላ ጋራ ተወያይተው በፍጥነት መፍትሔ ለማግኘት ነበር” ስሉ አጫውቱኝ። በእዚህ ምክንያት አፄ ምኒልክን እኔም በልቤ አደነቅኩአቸው።

በመጨረሻም ልሰናበታቸው ቆሜ ሳለሁ፤ እሳችውም በትሕትና እባክዎን ይጸልዩልኝ አሉኝ። እኔም እሺ በማለት ልጸልይላቸው ቃል ገባሁ።

እላይ እንደጠቀስኩት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ የተነጋገርነው በዛ ያለ ነው። ኾኖም የሕይወት ታሪኬን ልጽፍ ከበቃሁ፤ የተረፈውን በሱ ውስጥ አካትተዋለሁ። የቤተመንግሥት ጉብኝቴንም ዝርዝር እንዲሁ። አሁን በአጭሩ ለማለት ግን፤ በዶክተር ዐቢይ ግንባታ እጅጉን ተደምሜአለሁ። ሊፈራርሱ የነበሩትን የእፄ ምኒልክና የእፄ ኃይለሥላሴ ሕንፃዎችን ነፍስ ዘርተውባቸዋል። የደርግና የኢሕአዴግ የቅልብ ጦሮች ሰፍረውበት በቅራቅንቦ ያቆሸሹትን ስፍራ ሁሉ አጽድተው አበቦች ተክለውበታል። በቤተመንግሥቱ ውስጥ በግፍ ተገድለው ቅጥር ግቢው ውስጥ ተቀብረው የነበሩትን ኢትዮጵያውያን አፅሞች አስቆፍረው አውጥተው በመቃብራቸው ቦታ ላይ ለምለም ሳሮች አብቅለውባቸዋል። ደርግና ኢሕአዴግ ዜጎችን አስረው ይገርፉባቸው የነበሩትን ምድር ቤቶች መዘክር አድርገዋቸዋል። ብርቅዬውን ጥቁር አንበሳ ጨምሮ ለተለያዩ የዱር እንስሳት መሰማሪያ ቦታ ተመድቦላቸዋል።

ግቢው በጠቅላላ 42 ሔክታር ሲሆን፣ ከእሱ ላይ ለሕዝብ መዝናኛ በማሰብ “አንድነት መናፈሻ” የሚባል አዘጋጅተዋል። በእዚህም ስያሜ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸውን የማያወላውል አቋም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህል የሚወክሉ ጎጆዎችም በመናፈሻው ውስጥ በየዐይነቱ ቁጭ ቁጭ ብለዋል። አነዚህን የቃኙ ሰዎች ዋናዎቹን ብሔር ብሔረሰቦች ሄደው እንዲጎበኙ የሚጋብዙ ናቸው።

በሺህ የሚቆጠሩ የጎብኚ መኪኖች ማቆሚያም አለ። በፊት የዐፄ ኃይለሥላሴ ጽሕፈት ቤት የነበረውንም አስዘምነው፣ አሳድሰውና አሳምረው ከአፄ ኃይለሥላሴ እስከ እሳቸው ድረስ ኢትዮጵያን የመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ፎቶግራፎች (ኮረኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሳይቀሩ) በቅደም ተከተል ደርድረዋቸዋል። ቤቱን በዘመናዊ የመገናኛ እቃዎች (ኮምፒዩተሮችና ኢንቴርኔትን ጨምሮ) አጭቀውም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ አገር ርዕሰ ብሔሮች ማረፊያ አውለታል። ለደኅንነታቸውም ቢሆን ሆቴል ቤት እንዳይቆዩ በመትጋት። የሆስፒታል ኮሪዶር ይመስል የነበረውን ቀፋፊና ጭልምልም የደርግና ኢሕአዴግ ቢሮ ለመዘክርነት እዛው ትተው የእንግዳ መቀበያና የስብሰባ ክፍሎች የአሉት ብሩህና ለመንፈስ ደስ የሚል አዲስ ቢሮ ሠርተዋል።

ቀድሞ በጦረኞች በብርቱ እየተጠበቀ ዜጎች ዘወር ብለው በሙሉ ዓይኖቻቸው ሊቃኙት የማይደፍሩት ቤተመንግሥት ተውቦ፤ ዛሬ ለሁሉም ዜጎች ክፍት መኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያስመሰግናቸዋል። በእንደዚህ ዐይነት ውጥረት ውስጥ ኾነው ይህን ሁሉ በዐሥራ ሁለት ወራት በቤተመንግሥቱ ማከናውን ከቻሉ፤ በተረጋጋ አገርና አመጸኛ ባልኾኑ ሕዝቦች መሐል ቆይተው ቢያስተዳድሩ፤ ምን ያህል ዕፁብ፣ ድንቅ ተግባራት በፈጸሙ ያሰኛል። እኛ ያልታደልን ኾነን ነው እንጂ፤ ኢትዮጵያን ከልባቸው እጅግ የሚያፈቅሩና ብዙ ሊሠሩላት የሚሹና የሚችሉ ታላቅ መሪስ አግኝተን ነበር። የኢትዮጵያን የ4300 ዓመታት ታሪክ እኔ የአቅሜን ያህል መርምሬአለሁ። የነገሥታቱንም ታሪክ አንብቤአለሁ። ዶክተር ዐቢይ እንደ አሉበት እንደኛ ዘመን ክፉና የተወሳሰበ ዘመን ውስጥ የኖሩ መሪዎች ግን አላጋጠሙኝም። ከእሳቸው የአመራር ዘመን ሲነፃፃር መጥፎ የተባለው የድሮው ዘመን እንኳን እንደጥሩ የሚታይ ነው። ለእኛ ግን ነገሮችን የሚያገናዝብና መልካም የሚያሳስብ ቅን ልቦና እግዚአብሔር ያድለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ስለተቀበሉ፤ በእዚህ እጋጣሚ የተሰማኝን ፍሥሐ ልገልጽላቸው እወዳለሁ። ሽልማቱ የኛ የኢትዮጵያውያን፣ የኤርትራውያንና የመላው አፍሪካውያን ነው። ሽልማቱን የተቀበሉ ዕለት ያደረጉትም ንግግር እጅግ መሳጭ ነበር። ወረቀት ሳይዙ ዘለግ ላለ ጊዜ በተሳካለት እንግሊዝኛ ያን የመሰለ ቁምነገር መናገራቸው ያስደንቃቸዋል። በሳቸው ምክንያት በሽልማት ሰጪዎቹ አፍ ኢትዮጵያ እንድትወደስ ማስደረጋቸውም ያስመሰግናቸዋል። የኖቤል ሽልማቱን ሥነሥርዓት ያካሔዱት ሴትወይዘሮ ቤሪት ሬስ-አንደርሰን፤ “ኢትዮጵያ የሰው ዘር ምንጭ ስለኾነች እኛም ኢትዮጵያዊያን ነን፣ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ተገዝታ የማታውቅ አገር ነች፤” ያሉት በእሳቸው ምክንያት ነው። እሳቸው ሽልማቱን ባያገኙ ኖሮ ሴትዮዋ ይህን ባላሉ ነበርና። ይህን ጽሑፍ ከመደምደሜ በፊት ለእሳቸውና ለቤተሰባችው ረጅም ዕድሜና ጤንነት እመኝላቸዋለሁ። ኢትዮጵያም በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት ለዘላለም እንድትኖር እጸልያለሁ። (ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ