ኢትዮጵያ ከፈረንሳይና ከጣሊያን ጋር በመከላከያ ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ተላከ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ98ኛው መደበኛ ስብሰባው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች
የመለስ አካዳሚ ስያሜ እንዲቀየር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወሰነ
ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 22, 2021)፦ ኢትዮጵያ ከጣሊያን እና ከፈረንሳይ ጋር በመከላከያ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ያደረገቻቸውን የሁለትዮሽ ስምምነቶች ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው የሚያደርገውን የማጸደቂያ ረቂቅ አዋጅ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላከ።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ የቴክኒክ አቅም እና ክህሎት ለማጐልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው የተባለውን ስምምነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ የላከው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው ስብሰባ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች አንዱ የኾነው ይህ አዋጅ አገራቱ በመከላከያ ረገድ በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸው ጭምር ነው።
በአገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲጠናከር ጭምር ያስችላል የተባለው ይህ አዋጅ ቀደም ብሎ በስምምነት ላይ የተደረሰበትን የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ያደርጋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ ያሳለፈበት ሌላው ጉዳይ፤ የመለስ አካዳሚ “የአፍሪካ የልእቀት ማዕከል አካዳሚ” በሚል እንዲሰየምና በዚሁ አዲስ ስያሜ መሠረት አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ውሳኔ አሳልፏል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በእነዚህ ጉዳዮችና የብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ረቂቅ ስትራቴጂን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ የተሰጠው ሙሉ መረጃ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)




