አሜሪካ የተደበቀው ወንጀለኛ (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

የህወሃት አባል ነው ። ከትጥቅ ትግሉ ዘመን አንስቶ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ስልጣን እስከተቆናጠጠበት ጊዜ ድረስ ያለው የጀርባ ታሪክ በንጹሃን ደም የተጨማለቀ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ ።ይህ ግለሰብ ተስፋዬ መረሳ ይባላል ።ህወሃት ጫካ በነበረበት ጊዜ ተራው ታጋይ ከሴት ጋር የፍቅርም ሆነ የግብረ ስጋ ግኑኝነት ማድረግ እንደማይፈቀድለት አስገራሚው የፓርቲው ህግ ይደነግጋል ።ይህ ህግ እስከ 1981 አ.ም የቆየ ሲሆን የበላይ አመራሩ ግን የፈለገውን የማድረግ መብት ነበረው ።ፆታዊ ግንኙነት ሲያደርጉ የተገኙ ተራ ታጋዮች ይፈፀምባቸው የነበረው ቅጣት በጥይት ተደብድቦ መገደል ነበር ።በሺህ የሚቆጠሩ የፓርቲው ተራ አባላት የዚህ ቅጣት ሰለባ ሆነዋል ።እነዚህ ታጋዮች እንዲረሸኑ ሲወሰን ለመግደል ይጣደፉ ከነበሩት እና በርካታው የፓርቲ አባላት ከሚያስታዉሷቸው ገዳዮች አንዱ እና ቀንደኛው ተስፋዬ መረሳ ሲሆን ፣ከእርሱ በተጨማሪ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ ፣ወ/ስላሴ ፣ሃይሉ (ሳንቲም) ….. . .በጭካኔ የግድያ ተግባራቸው ይጠቀሳሉ ። ፊደል ያልቆጠሩት እነዚህ ወንጀለኞች የገዛ የትግል ጓዶቻቸውን ለመረሸን እጅ በማውጣት እኔ . . . እኔ እየተባባሉ ያሳዩ የነበረው ሰይጣናዊ ፉክክር እና ጥድፊያ ብዙ የፓርቲው አባላት አሁን ድረስ ያስታውሱታል።

 

አቶ መለስ እነዚህን ግለሰቦች በደህንነትና ፖሊስ ቁልፍ ቦታ ያስቀመጡአቸው የታዘዙትን እንደሚፈጽሙላቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነበር ። እነ ተስፋዬ “ግደሉ “ሲባሉ “ስንት?” ነበር የሚሉት ።በገሃድም የታየው ይሄው ነበር ።

 

የክልል 14 ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት እና በህግ ዲግሪ የነበራቸው ሻለቃ በፍቃዱ ቶሌራ በ1996 አ.ም ያለ አንዳች ጥፋት እንዲነሱ ተደርጎ ፣በምትካቸው ወደ ስልጣን እንዲመጣ የተደረገው ተስፋዬ መረሳ በምርጫ 97 የአቶ መለስን ትእዛዝን በመቀበል የበርካታ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ደም እንዲፈስ አድርጓል ።በመቶዎች የሚቆጠሩ አካላቸው እንዲጎድል  ፣በሺዎች የሚቆጠሩ እስር ቤት እንዲጋዙ  ፣በርካቶች ከስራቸው እንዲባረሩ አድርጓል።ከአዲስ አበባ ፖሊስ 400 የሚጠጉ አባላትን በቅንጅት ደጋፊነት እና አባልነት በመፈረጅ እንዲባረሩ ወስኖአል።

 

በወቅቱ ለዚህ የወንጀል ተግባሩ ከአቶ መለስ ሙገሳ እና ውዳሴ ለማግኘት በቅቶአል። አስገራሚው ነገር  ይህ ወንጀለኛ በዚህ የጭካኔ ተግባሩ የልብ ልብ ተሰምቶት ሸራተን ጎራ ማለት ይጀምራል። የተስፋዬ ሸራተን መጥቶ መለኪያ ማንሳት ያላስደሰታቸው ሽማግሌው ስብሃት ነጋ  «አቅሙን፣ደረጃውን፣ልኩን አይቶ አይጠጣም?እዚህ መጥቶ ከእኛ እኩል መጠጣት እና መዝናናት ይፈልጋል ?የምን መዳፈር ነው ?» ሲሉ ንዴት የተሞላበት ተግሳፅ እንዲደርሰው ያደርጋሉ ።የስብሃት አደገኛነት የት እንደሚደርስ እና ምን አይነት የበቀል መዘዝ እንደሚያስከትል ጠንቅቆ የሚያውቀው ተስፋዬ አሳቻ ጊዜ ሲጠብቅ ይቆያል።

 

በ2000 አ.ም ከቢጤዎቹ ጋር አንድ ፕላን ይነድፋል። ከደህንነት ሹሞች ከነኢሳያስ ጋር የመከረው ጉዳይ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተፈጻሚ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ ።የምክክሩ ምስጢር ይህ ነበር ። በአዲስ አበባ በተለይ ፒያሳ፣አራት ኪሎ ፣ከጊዮን_- ፍልዉሃ እስከ ኢትዮጵያ ሆቴል ጀርባ ፣አሜሪካ ግቢ፣ መርካቶ ፣ቦሌ፣22 ማዞሪያ፣መገናኛ  እና በመሳሰሉት አካባቢዎች ከፍተኛ የዶላር ጥቁር ገበያ ይካሄዳል ። ከጠዋቱ 4፡00 ሰአት ሲቪል የለበሡ በሺህ የሚቆጠሩ የደህንነት አባሎች በሁሉም መደብሮች በር ላይ በተመሳሳይ ሰአት እንዲገኙ ከተደረገ በኋላ በዚያው ቅጽበት ከተስፋዬ “ጀምሩ”የሚል ትእዛዝ ሲተላለፍ . . . .መሳሪያ እየደቀኑ ዶላሩን ጠራርገው ከየመደብሩ በሃይል ወሰዱ ። ከአሜሪካ ግቢ ብቻ ከስምንት መቶ ሺህ ዶላር በላይ ሲገኝ በአጠቃላይ 4.5ሚልዮን ዶላር ገደማ በጉልበት ተወረሰ ። ከዶላር በተጨማሪ ከመርካቶ እና ፒያሳ ከ2 ሚሊዮን የበለጠ ጥሬ ገንዘብ(የኢትዮጵያ ብር) ተወስዶአል። በ1984-85 አ.ም በወቅቱ የሃገሪቱ ፕረዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የዶላር ጥቁር ገበያን አስመልክተው ሲናገሩ “ምንዛሬውን ከወቅቱ ገበያ ጋር እኩል እናካሂደዋለን  እንጂ የጥቁር ገበያውን ቁጥጥር አናደርግበትም ፣አንነካውም “በማለት ተናግረው እንደነበር ብዙዎች ያስታውሱታል። ሆኖም ግን በቃሉ የማይገኘው የኢህአዴግ መንግስት በጠራራ ፀሃይ የለየለት የአደባባይ ዝርፊያ ሲያከናውን በርካቶች ኑሮአቸው ተናግቶአል፤ አንዳንዶችም ህይወታቸውን እስከማጥፋት ደርሰዋል።

 

ይህ ገንዘብ በቀጥታ ገቢ የተደረገው ወይም የተረከበው ተስፋዬ መረሳ ነበር ።በወቅቱ በመንግስት ሚዲያ ህገወጥ የዶላር አዘዋዋሪዎች እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ እና ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ መደረጉን የገለጸው ተስፋዬ፣ይህንን በተናገረ በሳምንት ልዩነት የተዘረፈውን ገንዘብ በሳምሶናይት ይዞ በቦሌ ወደ ኬንያ አመራ ።ከዚያም ወደ አሜሪካን አቀና ።ይህ በንጹሃን ደም የታጠበ ወንጀለኛ እና ዘራፊ አሜሪካን እንደመሸገ የተረጋገጠ ቢሆንም፣የት ከተማ እንዳለ እና እንደሚኖር ማወቅ አልተቻለም።

 

‹‹ማለፊያ መደሪያ አይሆንም…›› (ግሩም ተ/ሀይማኖት)

ዘንድሮ መታዘብ ከምንችለው በላይ የምንታዘበው ነገር ገጥሞናል፡፡ እንደ እባብ ቆዳቸውን ሸልቅቀው የሚቀይሩ፣ እንደ እስስት የሚለዋወጡ የቀበሮ ለምድ የለበሱ ባህታዊያንን መለየት ችለናል፡፡ ተቃዋሚ ነኝ ብሎ ሲያቅራራ የከረመ፣ ካለፈ ካገደመው ጋር ሰጋጁ ሁሉ በጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ለምዳቸው ተገፎ እርቃን ሆነው ታይተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹ቆጨኝ›› ብላ ያቀነቀነችውን ድምጻዊ የቆጫት ምኑ እንደሆነ ለማወቅ ፍንጭ አይተናል፡፡ በሀሳቧ ተጉዛ ቀበቶ ላይ ደርሳ ስለቀበቶ አውርታናለች፡፡ በየቦታው የታየው ጉድ ነው፡፡ እዚህ የመን እንኳን ተቃዋሚ ነን ብለው፣ ያለ እኛ ፖለቲካ አዋቂ ያሉበትን ቆርፋዳ ትንተና የሚግቱን፣ የስደተኛውን ኮሚቴ ካልመራን፣ ድምጽ የምንሆነው እኛ ነን የሚሉ ሁሉ እጅ ሲሰጡ አይተናል፡፡ ተቃዋሚ ነን ለእኛ ፓርቲ አባል ሁኑ ሲሉ የነበሩ ኤምባሲ ሄደው ሲያለቅሱ ካላለቀሳችሁ ብለው ሲጎተጉቱን አስተውለናል፡፡ ይህን ማድረግ መብታቸው ነው፡፡ ችግሩ አላማቸው የትኛው እንደሆነ ግራ ገብቷቸው ሰዉን ግራ ማጋባታቸው ነው፡፡  አፋኝ፣ ጨቋኝ ነው ባሉበት አንደበታቸው ያለ እሱ ለኢትዬጵያ…ሲሉ ‹‹እንክርዳድ እንክርድድ የተንከረደደ ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ…›› የሚለው የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን አስታወሱን፡፡

 

በወቅቱ ጉዳይ ላይ አንድ ደቡብ አፍሪካ ካለ ጓደኛዬ ጋር ስናወራ ተቃዋሚ ነን ብለው ለተቃውሞም ለድጋፍም ስለሚያጨበጭቡ በማጨብጨብ አላማ ተጠማጆች አወጋኝ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ስላሉ አላማቸው ማጨብጨብ ስለሆነ ፖለቲከኞች ሲያወራኝ በሁሉም የደረሰ ነውና ብዬ አሰፈርኩት፡፡ እነሆ፡-

 

ድሮ የሆነ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ‹‹ማለፊያ /መንገድ/ መኖሪያ አይደለም›› ይለኝ ነበር፡፡ እውነታው የተገለጸልኝ አሁን ነው፡፡ የሰሞኑ የሀገራችን ሁናታ ሲንቱን እንድታዘብ አደረገኝ መሰለህ፡፡ እዚህ ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ‹‹ኢሳት›› የገቢ ማሰባሰቢያ አዘጋጅቶ ነበር፡፡  ብዙዎች በቦታው በመገኘት ለኢትዮጵያ መልካም ዘመን እንዲመጣ መንግስትን በመቃወም ድምጽ አሰምተዋል፡፡ ብዙ ቅስቀሳዎች እና የኢሳትን አላማ የሚያስረዳ ትንታኔዎችን በአርቲስት ታማኝ በየነ ተደርጎ ነበር፡፡ በቦታው ባልገኝም ከብዙዎች የሰማሁት ቅስቀሳ፣ በቪዲዮ የተቀዳውን በሲዲ ሙሉ ፕሮግራም አይቼዋለሁ፡፡ በአዳራሹ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያኮራል፡፡ ይበል ያሰኛል፡፡ እዚህ ሀገር በመቆየትም ብዙዎቹን በአይን አውቃቸዋለሁ፡፡ አብዛኛዎቹም አልባሳቶቻቸው ሀገርን የሚያስታውሱ እና ወቅታዊውን መንግስት የሚቃወም በመርህ ቃል ደረጃ ‹‹በቃ!!..›› የሚል የተጻፈበት ቲ-ሸርት አድርገዋል፡፡ ሁሉም ነገር በመግባባትና በመተባበር ለኢትዮጵያ መፃዒ ነጻነትን ለማምጣት በገንዘብ፣ በእውቀት በሁሉ አስፈላጊ ነገሮች እንደሚረባረቡ ቃል ተገብቶ መንፈሱን እንደጠበቀ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ፡፡

 

አሁን ደግሞ ጆሀንስበርግ ያየሁት ነገር ባለፈው የኢሳት ገቢ ማሰቢያሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከነበረው መንፈስ ጋር ተጋጭቶብኛል፡፡ በፍጹም መንፈስ የተቃረነ ሆነብኝ፡፡ እውነት ነው በሰው ልጅ ማንነት ውስጥ መፈለግ ደግሞም የፈለከውን የማድረግ ተፈጥሮዋዊ እውነት አለ፡፡ ህያው ቃሉ ‹‹..ሰው በልቡ እንዳሰበው እንደዛው ነው፡፡..›› እንደተባለው ማናችንም ከዚህ መሪ ቃል እውነት መዝለል አንችልም፡፡ ይሄ ሆኖ ሳለ በዛን እለት ያየሁዋቸው በጠ/ሚኒስትር መለስ ሞት ሀዘናቸውን ለመግለጽ በዋና ከተማዋ ፕሪቶሪያ በሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡  ማንኛውም ሰው እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በሞት ሲለየን ሰው የሆነ ሁሉ ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ዜግነት ሳይጠይቅ ማዘኑ አይቀርም፡፡ በሰውኛ አይን ካየነው የሰው ሞት በራሱ ያሳዝናል፡፡ ምክንያቱም መልካም እና በጎ መስራት ሳያቅተን ክፋትን፣ በራስ ላይ ሊደረግብን የማንወደውን በሌሎች ላይ እያደረግን ሳናስበው እውነተኛውን የሞት ቲኬት በእጃችን ይዘን መዞራችንን አለማስተዋላችን ነው፡፡ እኔም በዛን ወቅት ያየሁት ነገር እጅግ አድርጎ አሳዘነኝ፡፡

 

በአንድ ወቅት ጠ/ሚኒስትር መለስ ‹‹..አላማው ምንም ይሁን ምን አላማ ያለው ሰው አከብራለሁ..››ያሉትን አባባል ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ታዲያ ዛሬ ጠ/ሚኒስትሩ ለአንዲት ሰከንድ ተመልሰው ማየት ቢችሉ ያሉት ነገር እንዴት እንደተጣረሰ አይተው ያዝናሉ፡፡ አላማ ያለው ሰው ቢፈልጉ አለመኖሩን ይረዳሉ፡፡  ሰዎቹ ግማሾቹ በኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ‹‹በቃ!!..››  የሚለውን ቲ-ሸርት የለበሱ ሲሆኑ ግማሾቹ ደግሞ ገዢውን ፓርቲ ሲያንቋሽሹ የነበሩ ተቃዋሚ መሳይ የውስጥ አርበኛ አይነት መሆናቸውን ሲታዘቡ አላማ ያለው እንዳልተከተላቸው ያውቁ ነበር፡፡ አሽቃባጮቹ ግን ያኔ በለበሱት ‹‹በቃ!!..›› የሚለው ቲ-ሸርት ላይ ከፊቱ ‹‹አል››…..ከኋላው ‹‹ም›› የሚለውን ጨምረውበት ‹‹አልበቃም..›› ብለው አስርተው ቢለብሱት ያምርባቸው ነበር፡፡ ገና ነገም የሚመጣ ካለ ተቀብለው ይገለበጣሉ እና ለእንሱ ገና ነው አልበቃም፡፡ ሲገለባበጡ ይኖራሉ፡፡

 

ያልገባኝ ነገር ያኔ በቃ!! የሚለውን ቲ-ሸርት የለበሱ እለት የጠ/ሚኒስትሩ ጀግንነት አልታያቸውም ይሆን? ወይስ በቃ ያሉት ጀግንነታቸውን ይሆን? ድጋፋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አላማቸው ግን ለራሳቸውም የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት ከሄድን አላማቸው ለሌሎች ግራ ካጋባ አናከብራቸውም፡፡

 

መናገር፣ መጻፍ፣ መቃወም፣ መደገፍ..ሁሉም አላማ አላቸው፡፡ አማራጭ የላቸውም፡፡ በአንድ ልብ ውስጥ ግን ሁለት የተለያዩ ሃሳቦችን መደገፍና መቃወምን ማስተናገድ ግራ ያጋባል፡፡ የሰው ልጅ አቋምም አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ እንደዚህ አይነት መረዳት ጥያቄም ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ ሁሉ መጀመሪያውኑ ዝም ማለት ወደ አንድ ጎን ያራምዳል፡፡ ‹‹..ዝምታም እንደ አንድ ተቃውሞ ነው፡፡..›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ነበሩ፡፡ እራሳቸው የተናገሩትን አንዳንዴ  መጠቀሜ ሰዎቹ የያዙት ሀሳብ በአንድ ልብ ውስጥ ሁለት አይነት ሊያቀነቅኑ መሞከራቸው ከአባባሉ ጋር ምን ያክል የተጣረዘ እንደሆነ ለማሳየት ብዬ ነው፡፡ ከእነሱ ለእነሱ እንደማለት ነው፡፡ እኔማ ራሳቸውን ከራሳቸው ሰዎች አባባል  እየተነሱ ማየትም መታዘብም ጥሩ ነው ብዬ ነው፡፡ የትግራይ ተወላጅ መሆን፣ የህወሀት አባል መሆን....የመሪው ፓርቲ አባል መሆን ማለት ብቸኛው እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ማለት አይደለም፡፡ እነዚህን ሆኖ ለመገኘት ግን የግድ አላማ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ የምናያቸው ሰዎች ደግሞ አላማቸውን ያየነው ነው፡፡ አቋም ለመያዝ በነገሮች መውጣት መውረድ የማይናወጥ በሰዎች አንደበተ ርዕቱነት የማይሸራረፍ ቶሎ የማይቀልጥ አለት ልብ ያስፈልጋል፡፡

 

እዚህ ደቡብ አፍሪካ እንዳየሁት በሶስት ወራት ድጋፍና ተቃውሞ ሲሰጡ አላማቸውን በማጣት እና በማግኘት ያልተፈተሹ ፖለቲከኛ መሳይ አስመሳዬች ኢትዮጵያችን እስከመቼ አዝላቸው እያበሰበሱዋት ይኖራሉ እላለሁ፡፡ ይህን ሳስብ እነዚህ ሰዎች ‹‹ማለፊያ መኖሪያ አይደለም..›› የሚለውን አባባል አልሰሙት ይሆን? ያሰኘኛል፡፡ ወይም ሲያምታቱ ተምታቶባቸው ማለፊያቸውን እና መኖሪያቸውን አለዩ ይሆናል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የራሳቸው የሰሩዋቸው በጎም መጥፎም ስራዎች አሉ፡፡ ታሪክ ያኖራቸዋል፣ ይፈርዳቸዋል፡፡ ለሁሉም ወቅት አለው፡፡ አሁን የተሰራውን የጨበራ ተስካርም ጊዜ ይፈታዋል፡፡ ይህን ለማለት ያስቻለኝ የታዘብኩትን ብዙዎች ይወቁት ብዬ ነው ያወራሁህ፡፡ ብዙ ሰው ሲሰማ ብዙ ሰው ይድናል የሚል መረዳት አለኝ፡፡ የዛሬ ኢትዬጵያችን ችግር የአላማ መምታታት ነው፡፡ ይሄ ክፉ ፈውስ የሚያስፈልገው በሽታ ነው፡፡ ሌላው እነዚህን ባለሁለት አላማዎች ያፈራች ሀራችን አየር መንገድ ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰራውን ዜግነት የሚያጎድፍ ድርጊትም ወዳጄ ነግሮኝ ስለነበር ላውራችሁ፡፡

 

ኢትዮጵያችን የውጭዎች ወይስ የእኛ?

ጽሁፉን የላከልኝ ወዳጄ ‹‹ኢትዮጵያችን የጥቂቶች ወይስ የብዙዎች›› በሚል ርዕስ ነበር የላከልኝ፡፡ ሳየው ግን ከሀገሩ ዜጋ ይልቅ ለሌላ ክብር የሰጠ ጉዳይ ስለሆነብኝ ቀየርኩት፡፡

 

ባለፈው ሳምንት በቀድሞው ጆሀንስበርግ ኢንተርናሽናል በአሁኑ ኦሊቨር ታምቦ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እንደሚዘገይ ለመንገደኞች ይነገራል፡፡ ለወትሮው ከምሳ በኋላ 7፡00-8፡00(እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) በረራውን የሚያደርገው የዛን እለት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ሊያዘገይ እንደሚችል ተነገራቸው፡፡ ችግሩ ግን አልታወቀም፡፡ አየር መንገዱ መንገደኞችን ስብስቦ ለእራት መመገቢያ በግሩፕ ከፍለው /መድበው/ ለየግሩፑ 250 የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ መደቡ፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ከአየር መንገዱ ደረጃ ጋር የሚቃረን እና አሳፋሪ ጭምር ነው፡፡  በኢንተርናሽና ደረጃ የምግብ ዋጋ 50 ዶላር በሆነበት ወቅት በግሩፕ ከአራት ሰው በላይ እየመደቡ ያደሉት ገንዘብ አሳፋሪ የሆነው ለኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ነው፡፡ ለሌሎች የውጭ ዜጎች የተለየ ነበር፡፡ ይህ በመድሎ የታጠረ ዜግነትን ያወረደ አሳዛኝ ድርጊት ነበር፡፡ ብሎኛል፡፡ እዛው ሀገር ውስጥስ ኢትዮጵያችን ገንዘብ ያላቸው ሆና የሚታይ ጉዳይ አይደለ? ክብር ለዜጋ ቢሰጥማ ስንቱ ገንዘብ አዝሎ በመጣ የውጭ ዜጋ ኢንቨስተር ታፔላ ከእርሻ ቦታው እና መኖሪያው ባልተፈናቀለ፡፡ ለዜጋ ክብር ቢሰጥማ ለውጭ ባለሀብት እየተባለ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ቦታዎች ውዝግብ ባላስነሱ ነበር፡፡

 

ከመለስ በኋላስ?

(ተመስገን ደሳለኝ - አዲስ አበባ)

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዕሁድ ዕለት ስርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል። ለሁለት ሳምንት ያህልም ለእልፍ አእላፍት አንገብጋቢ ጉዳዮቻችን ግርዶሽ ሆኖብን የነበረው ብሔራዊ  ዘንም አብሮ አብቅቷል። ለቤተሰቦቻቸው እና ለዘመዶቻቸው መፅናናትን ከልብ እመኛለሁ። ስለዚህም ከቀብር መልስ ባሉ  ገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር መ መር አለብን ብዬ አስባለሁ። ሙሉውን አስነብበኝ ...

በጎ ምክር ለጓዶች

ተስፋዬ ገብረአብ

የኢህአዴግ የስልጣን ሽኩቻ ተባብሶ በመቀጠሉ የአመራር አባላቱ ዝግ ስብሰባ ላይ ስለመሆናቸው እየተሰማ ነው። ይህን ሽኩቻ ከህዝብ ጆሮ ለመሰወር ሲባል ስለ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በቴሌቪዥን የተላለፈው ቀሽም ድራማ ነበር። የአመራር አባላቱ እጃቸውን እያወጡ ድምፅ ሲሰጡ በቲቪ ይታያል። በምን ጉዳይ ላይ ነው ተከራክረው በድምፅ ወሰኑት? አልተገለፀም። ከኢህአዴግ ነባር ልምድ አንፃር፣ ከስብሰባው በፊት ጋዜጠኞች ገብተው ምስል ቀርፀው እንዲወጡ እንደሚደረግ አውቃለሁ። ከዚያም በሮችና መስኮቶች ተዘግተው ስብሰባው ይቀጥላል።

ሙሉውን አስነብበኝ ...

በኢትዮጵያ ወቅቱ ወደፊት መራመጃ ነው

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም (ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ)

በኢትዮጵያ ወቅቱ መጥረቢያውን ቀብሮ ወደፊት መራጃ ነው። ኔልሰን ማንዴላ እንዳስተማሩት ”ከጠላትህ ጋር ሰላምን መመስረት ከፈለግህ፤ ከጠላትህ ጋር አብረህ መስራት አለብህ በዚህን ጊዜ ጠላትህ አጋርህ ይሆናል።” እኔ ደግሞ ትንሽ ላክልበትና፤ ጠላትህ ወዳጅህና ተባባሪህ ይሆናል። ከታሪክ እንዳየነው፤ ብሔራዊ አሜሪካኖች (አሜሪካን ኢንዲያንስ) በመሃከላቸ ሰላምን ሲፈጥሩ፤ መጥረቢያቸውን፤ መቁረጫቸውን በመሬት ውስጥ ይቀብሩታል። ይህም በመሃላቸው ተነስቶ የነበረውን አለመግባባት መቋጨቱን ማረጋገጫ ነው።

ሙሉውን አስነብበኝ ...

አስገራሚው የመለስ ዘመዶች (ኤርትራውያን) መልእክት (ትርጉም ኢየሩሳሌም አርአያ)

የሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ስጋ ዘመድ የሆኑ ኤርትራውያን የጋራ “ሃዘን መግለጫ “በአይጋ ፎረም በኩል አስተላልፈዋል።

 

“የምናፈቅረው ወንድማችን እና ልጃችን “ሲሉ የገለጿቸውን መለስ ዜናዊ “ቅዱስ” በማለትም  እነዚሁ ኤርትራውያን አሞኳሽተዋቸዋል ።እነዚህ ወገኖች መለስ ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ “ሰሩ” ያሉትን አሳፋሪ ትንተና ለመስጠት ከመከጀላቸው ባሻገር ኢትዮጵያውያን የመለስን መንገድ መከተል አለባችሁ ሲሉ ሊያሳስቡ ሞክረዋል። ይህንን መግለጫ ያወጡት የመለስ  ወላጅ እናት የሟቿ ወይዘሮ አለማሽ ገብረልኡል ቤተሰቦች ናቸው ።የሚገርመው የመለስ አያቶች በእናቱም በአባቱም ደጃዝማቾች ሲሆኑ የባለቤቱ አዜብ መስፍን አያት እንዲሁ ደጃዝማች ናቸው ።መለስ ብዙ ጊዜ ፊውዳሊዝምን ሲቃወሙ ይደመጡ እንጂ በእርግጥም የተጠናወታቸው እና እስከ ህልፈተ ሞታቸው ያራምዱት የነበረው መስመር የፊውዳል ስርአት ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው ።

 

አስገራሚው “መግለጫ “እንደሚከተለው ተተርጉሞአል።

                                                           

 “የሃዘን ማፅናኛ መግለጫ “

“ በኤርትራ ምድር እና በመላው አለም የምንገኝ የደጃዝማች ገብረልኡል ተስፋማርያም  እና የአቶ ካህሱ መላ ቤተሰቦች የሆንን፤ በሞት በተለየን በምናፈቅረው፣ልጃችን እና ወንድማችን፣የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ የተሰማን መሪር ሃዘን እየገለጽን ፤ለዘመዶቹ ለቤተሰቡ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጽናቱን ይስጠን እንላለን።

 

አቶ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ እና አፍሪካ ታሪክ ርሃብን ከሰፊው ህዝብ ለመንቀል ፣የታመመው እንዲፈወስ ፣መሃይሙ እንዲማር፣መብቱ የተገሰሰው ፍትህ እና ነጻነት እንዲከበርለት እና እንዲረጋገጥለት ፣ለአንድ ቀን እና ሰአት ሳያርፍ እና እፎይ ሳይል ፣ተወዳዳሪ የሌለው ዘላለማዊ የታሪክ ሃውልት ማኖሩ ፣ለህዝቡ እና ለቤተሰቡ የማይረሳ የድል ችቦ ፣የማይናድ ቅርስ ፣የማይጠፋ መብራት ፣ተጠብቆ የሚኖር ዘላለማዊ ክብር ፣. . . . ወዘተ ትቶ በማለፉ ፣የተሰማንን ትልቅ ኩራት እየገለጽን ፤በተለይ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝብ በተለይም ደግሞ ለመላው ቤተሰቡ የጀመረውን ስራ ሳይጨርስ ፣ገና በ57 አመት እድሜው ማለፉ ሃዘናችንን ጥልቅ መሪር እና በጣም ከባድ ሸክም አድርጎታል።

 

አቶ መለስ ዜናዊ እድሜውን ሙሉ ሲያከናውነው የቆየው ፣መልካም እና የተቀደሰ ተግባራት ባይኖር ያለምንም ማጋነን እና አድሎ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት አሁን ላለበት ደረጃ ሊበቃ እንደማይችል በማመን ፣እርሱ የጀመረው ወደር የሌለው የአገር እና ህዝብ ግንባታ አጠናክረው እንደሚገፉበት እና እንደሚያጎለብቱት ያለንን እምነት እና ተስፋ በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን ።ለአቶ መለስ ደግሞ ያንን ሁሉ የህዝብ እና ቤተሰቡ ጸሎት እና መሪር ሃዘን ፈጣሪ አምላክ ሰምቶለት በመንግስተ ሰማያት ያኑረው ።

 

             ከወይዘሮ አለማሽ ገብረሉልኡል ቤተሰቦች

የጎዳና ልጆች ለቅሶ (ሄኖክ የሽጥላ)

በዚች ግጥም ልግባባችሁ...
"እንባ እንደ ጅረት ፈሰሰ
ደረት ኢንደ አፈር ፈረሰ
ምድረ ጭርንቁስ ድሃ
ተቃቀፈና አነባ
ግና ያለፈ እናዳላረፈ አረፈ
አየ አየና አለፈ"

አለ ገጣሚው...እውነት ነው ዛሬ ሃገራችን ደረት እንዳፈር ፈርሶዋል...እነባ እንደጅረት ፈሶዋል የዘመናት በደሉን የሚገልጽበት ነጻ መድረክ ተከፈተለት..."አያ ጅቦም አመካኝቶ በልቶዋል":: ኢትዮጵያዊነት የሚያሳየን ብዙ ድራማዎችም አሉ...ይቀጥሉማል:: ለውሾቻቸው የታሸገ ምግብ መግዛት ከጀመሩት የቦሌ   የሃያት እና የገብርኤል ሰፈር  ሃብታሞች  ላስኪት ወጥረው የቆሻሻ ገንዳ ግርግዳ አድርገው ከሚኖሩት ያገሬ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሃዘናቸው እንዲገልጹ ተደርጎዋል እየገለጹም ነው:: የዛሬ ጸሁፌም የሚያተኩረው ሁለተኞቹ ላይ ነው።


አንባቢያን ኢንደምታውቁት middle class ወይም በኔ ድፍየና መሃል ሰፋሪ ስለተባሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዜ ካገኘሁ እመለስበታለሁ::  አሁን ግን "ሃሳቡ እንዲገባችሁ" እኔም እንደ አቤ ቶኪቻው በአዲስ መስመር እጀምራለሁ።



ያዲስ አበባ ጎዳና ተዳዳሪዎች በጠቅላይ ሚንስትሩ መሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ:: ሃዘናቸው ያተኮረባቸው መሰረታዊ ምክንያቶች እንደሚከተለው ይቀርባል።



እኛ ባራት ኪሎና በአካባቢዋ የምንኖር የጎዳና ተዳዳሪዎች በጠቅላይ ሚንስትራችን መሞት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን ስንገልጥ በብርድ የተሰነጠቀ በጸሃይ የጠቆረ  በቅማል ወንፊት የሆነ ፊታችንን ኢንደምታዩት በሃዘናቸው ከከፊል ደመናማነት ወደ ከል  ሰማይነት እንደተቀየረ ለማስገንዘብም እየሞከርን ነው:: ተቅላይ ሚንስትራችን በህይወት ባሉ ጊዜ...የሰው ልጅ በእውነትም ሊለምደው ይችላል የማይባለውን ነገር ያስለምዱን ታላቅ መሪ ናቸው።

ከበርሃ በቀሰሙት ልምዳቸው ያለምግብ ለሳምንታት ኢንዴት መኖር እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን ባንድ ልብስ ላይውም በበከተና በተባይ በተወረረ ብጫቂ ጨርቅ ራስን ንቆ እንዴት መኖር እንደሚቻል አስተምረውናል:: ጠቅላይ ሚንስትራችን በህየውት በነበሩ ጊዜ  "ክርስቶስ በሓጣንና በጻድቃን ላይ ለመፍረድ በድጋሚ ወደዚች ምድር ይመጣል" የሚለውን አባባል " በቀን ሶስቴ ትበላላችሁ" በሚለው ተክተን እንድናምን ያደረጉን ታላቅ ሰው ነበሩ።

ጥቅላይ ሚንስትራችንን በይበልጥም ክረምት ሲመጣ "አይዞአችሁ በሃምሌ ዝናብ ተደብደቡ ..ታዛ መጠለያ አይኑራችሁ...ፌደራል ፖሊስም ሌባ እያለ ይደብድባችሁ" ብለው የመከሩንን አንረሳውም:: ጠቅላይ ሚንስትራችን በህይወት በነበሩ ጊዜ አርቆ አሳቢነታቸውን ካሳዩበት መንገዶች ወስጥ እኛ የጎዳና ተዳዳሪዎች እየበዛን በመጣንበት ሰአት "አይዞአችሁ  አዲስ ቀለበት መንገድ እሰራላሁ  " ባሉት መሰረት  ቃላቸውን ሳያጥፉ ከሚቆረቁረውና ከገረጋንቲው ጎዳና አውጥተውን ፎቅና ምድር የቀለበት መንገድ የሰሩልንን በፍጹም ከህሊናችን የሚጠፋ አይደለም።


ከኛ ከጎዳና ታዳዳሪዎችም መሃል ተቅላይ ሚኒስትሩን በሙሉ አይኖቻችን ያየናቸው ብዙ ነን። ይሄ ደሞ አብዛኛው ኢትይኦጵያዊ በተኛበት ሰአት ለሽርሽር ወደ ውጭ በሚወጡበት ጊዜ ሲሆን...ምን ያህል ንቁና የማይተኙ ሰው መሆናቸው ደሞ ከኛ ጋ በፍጹም ያመሳስላቸዋል:: በይበልጥ አንዳንዴ...ተቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ ሰውነታችን ላይ ትልቅ ቅማል ሲያዩ "ይሄ ቅማል እኔ በርሃ እያለሁ አብሮኝ የነበረውን ይመስላል ምናልባትም የኔ ቅማል ለናንተ ቅማል ቅድመ አያቱ ሳይሆን አይቀርም" እያሉ አንድ መሆናችንን ይነግሩናል።

ባለፈ ጊዜ ለሚሊኒየም ሸራተን አዲስ ዝግጅት በነበረ ጊዜ...ከሰው የተረፈው ከሚደፋ ከሼክ ሙሃመድ አላሙዲን ጋ በመነጋገር እኛ እንድንበላው ያደረጉት በፍጹም አይረሳንም:: አልፎም ተርፎም  በሃገር ውስጥም ይሁን ወውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሉጢዎች  በየመኖሪያ ቤቶቻችን እያስገደዱ እንዲደፍሩን ...ሃገራችንን ሃገር ሳይሆን ቡና ቤት ኢንድትሆን ስላደረጉአት ሃዘናችን ጥልቅ ነው:: ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ሃዘናችንን ያበረታብን  "የጎዳና ተዳዳሪዎች እኩልነት" የሚለውን ረቂቅ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት እንድንመለከተው ሰጥተውን ማስተካከያው ቸርሰን ለመመለስ በምንዘጋጅበት ሰአት ማለፋቸው ሃዘናችንን አበርክቶብናል። ለቂቅ አዋጁ እንዲ ይል ነበር....


የጎዳና ተዳዳሪዎች የእኩልነት አዋጅ የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ህዝብ ቤት ውስጥ ከመኖር ወደ ጎዳና መውጣትን መርጦዋል...ነገሩ ይበል የሚያስብል ነው:: ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በሚቀጥሉት 10 አመታት ውስጥ 40 ከ 100 የሚሆነው የሃገራችን ህዝብ ወደ ጎዳና ይወጣል ተብሎ ይገመታል የተቀረው 60% ደግሞ በጎዳና አቁዋርጦ ወደ ሌሎች ሃገርኦች ይሄዳል...ስለዚህ "አዎ ስለዚህ ይላል አዋጁ" ...ስለዚህ ከዚህ ቀደም ያልነበረ  አሁን ግን የሚያስፈልገንን ይሄን አዋጅ ስናጸድቅ የጎዳና ተዳዳሪዎች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ከተመለከት በሁዋላ በድምጽ ብልጫ ያጸድቀዋል።


አዋጅ... ከዛሬ ከ ጥቅምት ገለመኔ ጀምሮ ሁሉም የጎዳና ተዳዳሪዎች በመረጡት ጎዳና ላይ የመኖር መብታቸው በህግ የተጠበቀ ነው:: ማንኛውም የጎዳና ተዳዳሪ በሚገባው ቁዋንቁ መነጋገር ይችላል። ከንዚህም ውስጥ የልመና ቁዋንቁዋ የጥግረራ ቁውንቁዋ ያራዳ ቁዋንቁዋ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ:: ማልቀስ ብሄራዊ ቁዋንቁዋቸው እንዲሆን ወስነናል። ምክር ቤት ቀደምት የጎዳና ተዳዳሪዎችና አድሃሪ የቆሎ ተማሪዎችን ለመቆጣተር ሲል በጎዳና ተዳዳሪዎች መሃከል ቅኔ የሚናገር...ወደ በቱ ተመልሶ የሚገባ እና ወዘተን በ 15 አመት ጽኑ እስራት የቀጣል። እስራቱም የሚፈጸመው መንገድ ፈጽሞ ካልገባባቸው አካባቢዎች ሄዶ አዲስ ኑሮ እንዲጀምሩ በማድረግ ይሆናል:: ይላል!



በመጨረሻም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሞት  በተመለከተ የተሰማንን ልባዊ  ኢየገለጥን እኛ የጎዳና ተዳዳሪዎች ብቻዎትን እንዳማይተኙ አብረንዎ ከበን እሳት እየሞቅን እንደምንተኛ ቃል ኢንገባሎታለን። በመጨረሻም በቅርቡ እኛን ለተቀላቀሉት ጠቅላይ ሚንስትራችን ቤተሰቦች መጽናናቱን እየተመኘን...የተቅላይ ሚንስትራችንን መሞት ተከትሎ በሚደረገው ሃገራዊ የድንኩዋን ሰበራ ላይ እየተሳተፉ ያሉትን በጎዳናና በቤት መሃከል የሚኖሩ ወገኖቻችንን..እንኩዋን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለ መለስ ዜናዊ በአለ ሞት አደረሳችሁ አደረሰን እያልን... እኛም በ-አምስት አመት መርሃ ግብራቸው ውስጥ ካካተቱት የዘኬ ለቀማችን እንሄዳለን:: ድል ለችግርና ረሃብ! ያዲሳባ ጎዳና ተዳዳሪዎች...ነሃሴ ምንትስ ሺ አርት መቶ አራት!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ