ኦባማ የሚባል መንፈስ (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)
መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር) ጥር 2000
አሜሪካ ጉድ ፈልቶበታል! አሜሪካ በነቡሹም ቢሆን የታወቀ የነፃነት አገር ነው፤ ይህንን እውነት ሊክዱ የሚዳዳቸው ሰዎች በተለይም አምባ-ገነኖች ሞልተዋል። ነጻነት መንታ መልኮችና ባሕርዮች አሉት፤ በአንድ በኩል በጎና ሰላማዊ፣ ሥራንና ሀብትን ፈጣሪ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እኩይና ቀጣፊ፣ የሌላውን ሀብት ዘራፊና የወንጀል ፈልፋይ ይሆናል። የነጻነት ባሕርይ ያልገባቸውና ነጻነትን የሚፈሩት እኩዩን የነጻነት ባሕርይ ለማፈን ሲሉ በጎውንም ባሕርዩን አብረው ይከረችሙታል። ምድረ አሜሪካ ሁለቱም የነጻነት ባሕርዮች በገሀድ የሚታዩበት ነው። በአሜሪካ ጉልበትና ገንዘብ ማናቸውንም ነገር የሚያነቃንቁ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ሕጉን ቢያዶለዱሙትም በትክክል ይሠራል። ጉልበትና ገንዘብ ያላቸው ሁሉ የልማት እንቅስቃሴውን ብቻ ሳይሆን የዜና ማሰራጫዎቹን ሁሉ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የፈለጉትን ፖለቲከኛ የሚያነሡትና ወይም የሚጥሉት እነሱ ናቸው።