Yederasiw Mastawesha የደራሲው ማስታወሻመድረኩ ካልተደገፈ፤ ማን ነው የሚደገፈው?

ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ሚያዝያ 16 ቀን 2002 ዓ.ም.

“… “ከቁጥጥራችን ውጭ የማይሄድ ፌደራሊዝምና የምርጫ ሂደት ከተከተልን ለረጅም ጊዜ ትግራይን ሥልጣን ላይ ማቆየት ይቻላል” ይላሉ እነ መለስ። ስየ ከመነሻውም ይህን ይቃወማል። በዚህ ዘዴ ለረጅም ጊዜ መዝለቅ አንችልም ባይ ነው። አማራው እስከዛሬ እንደተጠቀመበት ኢትዮጵያዊነት የሚለውን በሽፋን ተጠቅመን ውስጥ ውስጡን ግን የትግራይ ተወላጆችን በሀብትና በእውቀት በማጠናከር ለረጅም ጊዜ ልንገዛ እንችላለን። አፄ ዮሐንስ ያደጉትን አንደግምም፤ ሥልጣን ከእጃችን ከወጣች ተመልሶ ማግኘት ከባድ ነው“ ይላል ስየ …»

ተስፋዬ ገብረአብ - ከየደራሲው ማስታወሻ ላይ የተወሰደ

 

“… ገብሩ አስራት ከስየ የከፋ ሰው ነው እንደውም። ስየን ገልጠነዋል። ዶ/ር ነጋሶ የእግዚአብሔር በግ ነው። ሦስቱ ናቸው እኮ ወደ ታቃውሞ የገቡት። ዶ/ር ነጋሶ መለስን “አሁን መንግሥቱ ኃይለማሪያምን መሰልከኝ” ብለው የተናገሩት ስየን ተማምነው ነው። በፍጹም ደፍረው አይናገሩትም ነበር። ስለዚህ ዶ/ር ነጋሶን እንደተቃዋሚ ማሰብ አልችልም። ገብሩ አሥራት ዓረና ትግራይ ብሎ ነው የመጣው። አሁን የትግራይ አካባቢ ነው ያለው። አረጋሽ ተመሳሳይ የስየና የገብሩ አስተሳሰብ ባልደረባ ናት። እነዚህ ሦስቱ ከላይ የሚታዩት ግለሰቦች፣ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ጅብ ይብላህ ወይንስ ነብር ይብላህ? የሚል ጥያቄ ቢመጣ ምንም ምርጫ መምረጥ ያለብን አይመስለኝም። ግን ጅብ ቀስ ብዬ እበላሃለሁ ካለ፣ አይ እንግዲያው ጅብ ብለህ ልትመርጥ ትችል ይሆናል። በዚህ መለኪያ እነኝህን ሰዎች የምናወዳድራቸው ከሆነ ህወሓት ኢትዮጵያን መግዛት አለበት ብለው አክርረው ከመለስ ይልቅ የሚያምኑ አክራሪዎች ናቸው። እነርሱ ተመልሰው ወደ ሥልጣን የሚመጡ ከሆነ በዚያች በሁለቱ ዝሆኖች በሚለው ላይ እንደገለጽኩት “አማራው በአጼ ምኒልክና በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን በኢትዮጵያ አንድነት ስም የአማራውን የበላይነት በቋንቋ፣ በሥልጣን ድልድል እንዳስጠበቀው ሁሉ እኛም በዚያ ዘዴ ልናስጠብቅ እንችላለን” ብለው የሚያምኑ ቡድኖች ናቸው። በፍጹም እነዚህ ሰዎች የዲሞክራሲ አካሄድን ተከትለው የሕግ የበላይነትን አስከብረው ህዝቡ የሚመኘውን ዘመን ያመጣሉ ብዬ እኔ አላምንም። ህልም ነው በፍፁም ሊታሰብ የማይችል ነው። …”

ተስፋዬ ገብረ አብ - ከከረንት አፌርስ ፓልቶክ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተወሰደ

 

“… ከተስፋዬ ገብረአብ የስነጽሑፍ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን፣ በደራሲው ማስታወሻ ውስጥ ከሚያንጸባርቀው የፖለቲካ አመለካከት ጋር ምንም ፀብ የለኝም። እንዲያውም ብዙውን የምጋራው ነው …”

የግንቦት ሰባት ሊቀምንበር ዶር ብርሃኑ ነጋ - የደራሲው ማስታወሻን ካነበቡ በኋላ የጻፉት መቅድም

 

የዘመኑ ቴክኖሎጂ ከወለዳቸውና በሀገራችን ፖለቲካ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ካሉት ውስጥ፣ የፓልቶክ የመወያያ መድረኮች ይገኙበታል። ከነዚህም ፓልቶክ ክፍሎች መካከል ”ከረንት አፌርስ” ተብሎ የሚታወቀው ክፍል አንዱ ነው። የዚህ ክፍል አድሚኖች (አስተዳዳሪዎች) የፓልቶክ ክፍላቸውን ኢትዮጵያውያን ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት የኢትዮጵያውያን የመወያያ መድረክ ነው ይሉናል። (ኢህአዲጎች ዲሞክራት ነን እንደሚሉት ማለት ነው)

 

ነገር ግን ክፍሉ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ “ዊንግ” ሆኖ የሚያገለግል፣ በሀገር ቤት የሚደረገውን ሠላማዊ ትግል የሚያሳንስ፣ ከሻዕቢያ ጋር በመሥራት የሚደረገውን ትግል በአዎንታዊነት የሚያቀርብ፣ ፍፁም የተለየ ሃሳብን ማስተናገድ የማይችልና ፀረ-አንድነት እና ፀረ-መድረክ ፓርቲዎች ዘመቻ የከፈተ የፓልቶክ ክፍል ነው። ብዙዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ የኢትዮጵያዊነት ጨዋነት በጎደለው መልኩ ይሰደባሉ። በግንቦት ሰባት ንቅናቄና በሻዕቢያ ላይ ተቃውሞን ያዘለ አስተያየት የሚሰጡ እንዲያቆሙ ይደረጋሉ። ብዙ ኢትዮጵያውያን እዛ ክፍል ውስጥ እንዳይገቡ ከናካቴው ታግደዋል።

 

“ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” እንዲሁም “የቡርቃ ዝምታ” የሚባሉ መጻሕፍትን ከዚህ በፊት የጻፉት፣ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ የሚባሉ ሰው “የደራሲው ማስታወሻ” የሚል አዲስ መጽሐፍ በቅርቡ አውጥተዋል። በዚህ መጽሐፋቸው ዙሪያ በከረንት አፌርስ ፓልቶክ ክፍል ቀርበው ቃለ መጠይቅ እንደተደረገላቸው ሰማሁ። በከረንት አፌርስ ክፍል እንዳይሳተፉ ከታገዱት ኢትዮጵያውያን አንዱ በመሆኔ፣ ቃለ መጠይቁን ለመስማት ዕድል አላገኘሁኝም። ነገር ግን ቃለ መጠይቁ በከረንት አፌርስ ድረ ገጽ ላይ በመውጣቱ፣ እየዘለልኩ የተወሰነውን ከቀናት በኋላ ለማዳመጥ ችያለሁ።

 

ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ የሚለው መጽሐፍ የህወሓትን የጦርነት ገድል የሚተርክ ሲሆን፤ የቡርቃ ዝምታ የሚለው መጽሐፍ ደግሞ በ“ኦሮሞው” እና በ“አማራው” መካከል መተላለቅ እንዲኖር የሚጋብዝ፣ መርዛማና አደገኛ መጽሐፍ ነው።

 

አዲሱ “የደራሲው ማስታወሻ” የሚለው መጽሐፍም የከፋፋይነት ተልዕኮ ያለው መጽሐፍ ሆኖ ነው ያገኘሁት። በ“ትግሬው” እና በተቀረው ኢትዮጵያዊ መካከል ልዩነት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የታጻፈ …

 

ከዚህ በፊት ሻዕቢያ ከህወሓት/ኢህአዲግ ጋር አብሮ በሚሠራበት ወቅት፣ የ“አማራው” እና የ“ኦሮሞው” መከፋፈል ጥቅም የሚያስገኝ አድርጎ ነበር የሚያስበው። ያኔ፣ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ በ“አማራው” እና በ“ኦሮሞው” መካከል፣ መከፋፈል አለመተማመን ስር እንዲሰድ የቡርቃ ዝምታን የጻፉትም በዚሁም ምክንያት ነበር።

 

ሻዕቢያ ከህወሓት/ኢህአዲግ ጋር ፀብ በሚፈጥርበት ጊዜ፣ የጨዋታው ሕግ ተቀየረና ወደ “አማራው” እና ወደ “ኦሮሞው” መመለስ የግድ ሆነ። አሁን “አማራው” እና “ኦሮሞው” አንድ መሆናቸውን፣ “አማራው” እና “ኦሮሞው” አንድ ላይ መጥተው ኢትዮጵያዊነት እያበበ እንደሆነ፣ አቶ ተስፋዬ እየነገሩን ነው።

 

በርግጥ የቡርቃ ዝምታን በጻፉበት ብዕራቸው፣ ኦሮሞውና አማራው አብሮ የኖረ፣ የተዋለደ፣ የማይለያይ መሆኑን መገንዘባቸው መልካም ጅማሬ ልንለው በቻልን ነበር። ነገር ግን አቶ ተስፋዬ አሁንም በጥላቻና በዘር ፖለቲካ ልክፍት የተለከፉ መሆናቸውን ነው እያየን ያለነው። በትግሬውና በተቀረው ኢትዮጵያዊ መካከል መከፋፈልና አለመተማመንን ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። በአድዋ፣ በጉንደት፣ በጉራ፣ በመተማ እንዳደረጉት ሁሉ፣ የትግራይ ተወላጆች ለኢትዮጵያ አንድነት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር መሰለፋቸው እንደ ኃጢያትና እንደ ወንጀል ተቆጥሮ፣ አቶ ተስፋዬ “አማራውና ኦሮሞው ከተባበረ ይበቃል፤ ትግሬዎችን አትመኗቸው፤ መለስን አስወግደው ሌላ ትግሬ ሊያነግሱባችሁ ነው” የሚል እንድምታ ያለው፣ በሃያ አንደኛው ዘመን ከሚኖር፣ ከተማረ ሰው የማይጠበቅ አሳዛኝና አሳፋሪ መልዕክት ነው ሲያስተላልፉ የምንሰማቸው።

 

በዚሁ በከረንት አፌርስ በተደረገው ቃለ መጠይቃቸው፣ አቶ ተስፋዬ በትግራይ እየተከፈለ ያለውን መስዋዕትነት “ድራማ” ብለው አጣጥለውታል። በርሳቸው ቤት፣ የእነ አረጋዊ ገብረዮሐንስ ደም የፈሰሰው ድራማ ለመሥራት ሲባል ነው። በአክሱም፣ በመቀሌ፣ በተንቤን፣ በአድዋ፣ በሽሬ፣ በአዲግራት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለመብታቸው በመቆም፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት አንግቦ በተነሳው በመድረኩ ስብስባ መሳተፋቸው፣ ለአቶ ተስፋዬ “ድራማ” ነው።

 

በነአቶ ስየ ላይ ያወረዱት ውርጅብኝማ የሚያስገርም ነው። አቶ ስየ አብርሃ ወደ አንድነት ፓርቲ፣ ከአንድነት በፊት ወደ ቅንጅት እንዲገቡ ብዙ ግፊት ያደርጉ ከነበሩ ወገኖች መካከል አንዱ ነበርኩ። አቶ ስየ ወደ አንድነት ፓርቲ እንዲገቡ ግፊት ያደረኩትም፣ ከገቡም በኋላ የተደሰትኩት ያለ ምክንያት አልነበረም።

 

አቶ ስየ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ጠንካራ አቋም እንደነበራቸው፣ በተለይም ኢትዮጵያ የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ፣ የአልጀርሱን ስምምነት እንደማይደግፉ እስር ቤት እያሉ ነበር የማውቀው።

 

የቅንጅት መሪዎች ከታሰሩ በኋላ አቶ ስየን በደንብ የሚያውቅ አንድ የቀድሞ የህወሓት ታጋይ ተዋወኩ። በአቶ ስየና በአቶ መለስ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ገለጸልኝ። “… የህወሓት አባላት ተሰብስበን በምንወያይበት ጊዜ፣ አቶ ስየ ስብሰባውን ረግጦ ወጣ። በዚያም ብዙዎቻችን ተናደድን። እነ ስየ ሲወጡለት፣ መለስ በአዳራሹ ያለውን ሰው “ታያላቹህ፣ እኔ እናንተን አክብሬ እናንተ የምትፈርዱትን ለመስማት ስመጣ፣ እነርሱ እናንተን ንቀው ስብሰባውን ረግጠው ወጡ” በማለት በአዳራሹ የነበርነውን ተሰብሳቢዎች በብዛት ለማሳመን ቻለ። ያኔ ነው ለመለስ ድጋፍ ሰጠነው። እንጂ ስየ ከጅምሩ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ከነመለስ ጋር ብዙ ጊዜ ይጋጭ ነበር። ሻዕቢያ በጣም የሚጠላው እርሱን ነው …” ሲል ነበር ይህ የውስጥ አዋቂ የነገረኝ፤ “ማን ይንገር የነበረ፣ ምን ያርዳ የቀበረ” እንደሚባለው።

 

ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ ወያኔ/ኢህአዲግ በሥልጣን ለመቆየት ሲል የተጫወተው ጨዋታ በዘር ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ነበር። የቅንጅት መሪዎችን ዘር በማጥፋት ወንጀል ከሷቸዋል። “እኛ ከሌለን አማራውና ኦሮሞው ትግሬውን ያጠፉታል። ኢንተርሃሙዌ ነው የሚሆነው” እያሉ ትልቅ መሰረት የሌለውና አሳፋሪ የማስፈራራት ዘመቻ ሲፈጽሙ ነበር። በዚህም ምክንያት በትግሬውና በተቀረው ኢትዮጵያዊ ዘንድ አለመተማመኑና ጥላቻው ስር እየሰደደ ሄዶ ነበር።

 

አንድ ወቅት እንደውም ከዋሽንገተን ዲሲ ይተላለፍ በነበረው የንጋት ሬዲዮ አገዛዙን ከህዝቡ ሳይነጥሉ፣ በትግሬው ላይ በጠቅላላ ያነጣጠሩ፣ ጎጂ የሆኑ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ይተላለፉ ነበር። ያን ያህል በአደባባይ እስኪወጣ ድረስ ጥላቻው አድጎ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር ማለት ይቻላል።

 

የቅንጅት መሪዎች ከእስር መፈታት፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሜኔሶታ የትግራይን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ፣ የፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም የያኔው ጠቃሚ ጽሑፎች (አሁን የሚጽፉትንና የሚያደርጉትን አፍራሽ እንቅስቃሴ እንተወውና) ይህ የዘር ጥላቻ ፖለቲካ መጠኑን (ሞሜንተሙን) እንዲቀንስ አድርገውታል።

 

ያ ብቻ አይደለም የነ አቶ ስየ የአንድነትን ካምፕ መቀላቀል፣ የነ አቶ ገብሩ አሥራትና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በመድረክ ውስጥ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር መሰባሰብ፣ ትላንት ብዙዎቻችንን ሲያሰጋና ሲያሳስብ የነበረው፣ በወያኔ/ኢህአዲግ ርካሽ ፖለቲካና በነ ቡርቃ ዝምታ አይነት መርዛማ መጻሕፍት ምክንያት ተፈጠሮ የነበረው በወገንና በወገን መካከል ያለው ሥር የሰደደ ጥላቻና መከፋፈል፣ ይወገድ ዘንድ ትልቅ መሰረተ እየጣለ ነው።

 

አቶ ስየ ትግሬውን ብለው አይደለም እየታገሉ ያሉት። አቶ ስየ “እኔ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ ነኝ” ብለው የተነሱ ሰው ናቸው። ዶ/ር ነጋሶ “እንደ ጫጩት በቀፎ መታሰር የለብንም። ከብሔራችን አልፈን በሰፊው ማየት ያስፈልጋል። ለኢትዮጵያዊነታችን የበለጠ መሥራት አለብን” ነው ያሉን። አቶ ቡልቻ በበኩላቸው “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። አንድ ነን። መበጣጠሳችን የትም አያደርሰንም። ኃይላችን አንድነታችን ነው። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት” በማለት አዲስ ምዕራፍ እንደተከፈተ ገልጸውልናል።

 

ይህ የኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር መሰባሰብ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ቡድኖችን ሊያሳስብ መቻሉ አያጠራጥርም። መድረኩ በግልጽ እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት ይታገላል። አሰብ የኢትዮጵያ ልትሆን ይገባል ብሎ አጠንክሮ ያምናል።

 

ይህ የመድረኩ አቋም፣ ለሻዕቢያ ባለሥልጣናት አይዋጥላቸውም። በወደብ ዙሪያ የአቶ መለስ ዜናዊ አቋም በእጅጉ ይመቻቸዋል። በመሆኑም መድረኩ ተቀባይነት እንዳያገኝ ከወዲሁ ብዙ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ አያስገርምም። ሻዕቢያ እንደ ቀድሞው ኤኤፍዲ አይነት፣ የኤርትራን ጥቅም ያልጎዳ ስብስብን እንጂ እንደ መድረክ አይነት፣ ሊቆጣጠረው የማይችል፣ ለኢትዮጵያ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ስብስብ ማየት አይፈልግም። (ኤኤፍዲ በኦነግ፣ በኦብነግ፣ በህዝብ ባልተመረጡ በውጭ ሀገር የነበሩ የቅንጅት ድጋፍ ድርጅት መሪዎች፣ ህዝብ ሳይመክርበት፣ ኢትዮጵያዊነትን ያልተቀበለ በድብቅ የተቋቋመውና የሞተው ትብብር ነው)

 

ለዚህ ነው በተዘዋዋሪ መልኩ እንደ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ አይነት ግለሰቦችን እያሰማራ፣ ኢትዮጵያውያን ቀበቷቸውን መታጠቅ በሚኖርባቸው ወሳኝ ወቅት፣ ትኩረት ለመሳብና በመድረኩ የተጀመረው የኢትዮጵያዊነት ንቅናቄ ወደ ፊት እንዳይገሰግስ ለማድረግ እኩይ ተግባር እየሠራ ያለው።

 

ሌላው እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ እንደ ግንቦት ሰባትና ከረንት አፌርስ ያሉ በውጭ ሀገር የሚገኙ ቡድኖች ያላቸውን ሁሉ በሻዕቢያ ጠረጴዛ ላይ ዘርግፈው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሳይሆን የሻዕቢያን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንቅስቃሴ ላይ መሰማራታቸው ነው።

 

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የአቶ ተስፋዬ መጽሐፍ ላይ ጠብ እንደሌላቸው እንዲያውም በአብዛኛው ደግሞ እንደሚስማሙ ጽፈዋል። ይህን በማድረጋቸው ዶ/ር ብርሃኑ መድረኩ ሊደገፍ እንደማይገባ፣ መድረኩ ሥልጣን ከያዘ ከመለስ አገዛዝ የባሰ ግፈኛ እንደሚሆን እንደተናገሩ ሊቆጠር አይችልምን? እኝህ ሰው ይህን ያህል ከአቶ ተስፋዬ ጋር በመሆን እነ አቶ ስየን በተዘዋዋሪ መንገድ ሲተቹ፣ አገር ቤት የሚደረገው ምርጫ እንዲከሽፍ መግለጫዎች ሲያወጡ፣ እርሳቸውና ድርጅታቸው የምናወቀውን የወያኔ/ኢህአዲግ ግፍ እንደ ዳዊት ጠዋትና ማት ከመድገም ውጭ፣ ይኽው ሁለት ዓመት አስቆጠረዋል፣ ምን ያመጡልን አማራጭ አለ? እነ አቶ ስየ፣ እነ ኢንጂንየር ግዛቸው፣ እነ አቶ ቡልቻ የሚሠሩትን እያየን ነው። ዶ/ር ብርሃኑ ኢትዮጵያ ያሉትን ከውጭ ሀገር ሆነው ለማዘዝ ከመሞከር እርሳቸው የሚሠሩትን የተጨበጠ ነገር ቢገልጹልን ጥሩ ነበር።

 

ይልቅ ዶ/ር ብርሃኑ የሚሰሙን ከሆነ ቆም ብለው ያሉበትን ሁኔታ ቢመረምሩ መልካም ነው እላለሁ። ብዙ እየተሳሳቱ ያለ ይመስለኛል። ውጤት ሊያመጡበት ከሚችሉበት የሠላማዊ ትግል ሜዳ ወጥተው የማይሆን ቦታ በመገኘታቸው የሚሠሩት የጠፋባቸው ይመስላል። እርሳቸው ምሁር፣ ፀሐፊ፣ ጎበዝ ተናጋሪ ናቸው። ሰውን የማሳመንና የማግባባት ችሎታ አላቸው። ይህንንም የቅንጅት መሪ የነበሩ ጊዜ በገሃድ አስመስክረውታል።

 

ዶ/ር ብርሃኑ ጦረኛ አይደሉም። የጦርነትና የብራቫዶ ንግግር አያምርባቸውም። የቅንጅት አመራር የነበሩ ጊዜ በብዙ ሺህ የሚሆኑ ዜጎችን የማረኩበት፣ የሠላማዊውን ትግል መልቀቅ አልነበረባቸውም።

 

ውጤት ማለት እኮ ሥልጣን መጨበጥ ብቻ አይደለም። በዘጠና ሰባት ሥልጣን ስላልተያዘ የሠላማዊ ትግል ከሸፈ ማለት እኮ አይቻለም። እርሳቸው የቅንጅት አመራር በነበሩ ጊዜ በብዙ ሺህዎች የምንቆጠረውን ኢንስፓየር አድርገውናል። ያንን ብቻ እንደ ትልቅ ውጤት ሊቆጥሩትና በሠላማዊ ትግል ሊገፉበት ይገባ ነበር።

 

አሁንም ገና አልጨለመም። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የመንቀሳቀስ ዕድሉ አቶ መለስ ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ለርሳችው አዳጋች ቢሆንም፣ በውጭ ሀገር ሆነው፣ ሀገር ቤት የሚደረገውን ሠላማዊ ትግል ማገዝ ይችላሉ። በደስታ ነው የምንቀበላቸው።


ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ሚያዝያ 16 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!