ከሀገር በስተጀርባገሠሠ እንግዳ

በኢትዮጵያ በህይወቴ ዘመን ሦስቱን ሥርዓቶች ማለት የዓፄ ኃይለሥላሴ፣ የኰለኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም እና የመለስ ዜናዊ መንግሥታት መልካቸው ብቻ ሳይሆን ተግባራቸውንም ጭምር ለማስተዋል ከበቁት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ። በተለይም በሀገራችን ለውጥ ለማምጣት “ዳቦ ለተራበ”፣ ”መሬት ላራሹ” የሚል ህያው መፈክር ይዞው “አትነሳም ወይ የግፍ አገዛዝ አይበቃህም ወይ?!” እያሉ በአደባባይ ወጥተው ይጮኹ ከነበሩት ተማሪዎች አንዱ ሁኘ ብዙ ውጣ ውረድ አልፈው እዚህ ከደረሱት ትውልድ አንዱ ነኝ። የወጣቱ አስራት አብርሃምን መጽሐፍ ሳነብ የቀሰቀሰብኝ ትዝታም ያ ያሳለፍኩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የእሳትነት ዘመኔ ነበር።

 

ደርግ የህዝቡን ትግል በአቋራጭ ነጥቆ በፋሽሽታዊ የአገዛዝ ቀንበር እንዳስገባው ሁሉ የመለስ ዜናዊ አገዛዝም በተመሳሳይ የመንግስቱ ኃይለማሪያምን እግር ተክቶ ሲሠራ ስመለከት “ያ ድሮ በ66ቱ የትግል ችቦ ያቀጣጠለውን ታጋይ ትውልድ አልቋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይነሳም። የኢትዮጵያዊነት መንፈሥ ተዳክሟል። ወጣቱ በአብለጭላጭ ነገሮችና በሥርዓቱ ስንክሳር ፕሮፓጋንዳ ተለክፏል፣ ደንዝዟል። በኢትዮጵያ ትልቅ የባህል የታሪክና የትውልድ ክፍተት ተፈጠሯል። ይህችን ሀገር ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ የሚያሸጋግር ድልድይ ፈርሷል” የሚል ፍራቻና ስጋት ነበረኝ። አሁንም አለኝ።

 

ከሀገር በስተጀርባ

 

በተለይም በትግራይ በአንድ ድርጅት ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) ሞኖፓላዊ የአፈሙዝ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ገብቶ ለ35 ዓመታት ያህል “ያለ ማሌሊታዊ መንገድ ሌላው መንገድ የጥፋት መንገድ ነው። የአማራና የኦሮሞ ትምክህት ጠላቶችህ ናቸው። የኢትዮጵያ ታሪክ የግዛት መስፋፋትና የነገሥታት የእንቆቅልሽ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ የኤርትራ ቅኝ ገዢና ወራሪ ናት። ስለዚህ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ስለሆነ ፍትሓዊ ትግል ነው መደገፍ አለብህ። አንተ ጀግና ነህ ሌላው ግን በተፈጥረው ፈሪ ነው። ከተመቸን በአትዮጵያ ውስጥ አብረን እንኖራለን ካልተመቸን ግን ተገንጥለን የትግራይን ሪፓብሊክ መስርተን ለብቻችን እንኖራለን” በሚል ስታሊናዊ ርዕዮተ ዓለም ተኰትኩቶና ተጠምቆ ያደገው የትግራይ ወጣት ዛሬ ስለ ሀገሩ ጉዳይ፣ ስለሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ፣ ስለሰው ልጅ ነፃነት፣ ስለዲሞክራሲ፣ ስለሀገሩ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ምን ዓይነት አመለካከትና ራዕይ ይኖረው ይሆን? ዛሬ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ከረጢት ውስጥ ገብቶ የመለሲዝም አመለካከት እየተማረ እንዲያድግ እየተደረገ ያለው የትግራይ ወጣት ስለሌላ ነፃ አማራጭ መድረክና አማራጭ ሕይወት ማሰብ ይችል ይሆን? የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆን? ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ትውልድ እያፈራች ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ሁሉ ጊዜ በአዕምሮዬ ውስጥ ይመላለሳሉ።

 

በዚሁ ሁኔታ ተሸብቦ ነፃነትና ዲሞክራሲ እየናፈቀው በትግራይ ምድር ተወልዶ ያደገው ወጣቱ አስራት አብራሃም “መጽሐፍ ጽፎ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማሳተም ተከልክሏል” የሚል ዜና በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ስሰማ፤ በዚያው በእሳት አፋፍ ላይ ሆኖ ምን ዓይነት መጽሐፍ ጽፎ ይሆን? ምን ዓይነት ራዕይስ አምጥቶልን ይሆን? በማለት ለማየትና ለማንበብ ትልቅ ጉጉት ነበረኝ። ከህዝብ የሚደበቅ ነገር የለምና ዕድሜ ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጽሐፉ በዜጎች ትብብር በልዩ ዘዴ ታትሞ ብዙ ኬላዎች አልፎ አሁን ወደ ገበያ ቀርቦ ገዝቼ ለማንበብ በመብቃቴ በጣም ደስ ብሎኛል።

 

በመሆኑም ለጥረቱና ለመጽሐፉ ትልቅ ግምት በመስጠት አንብቤ ጨርሼዋለሁ። አንዳንድ ያልገቡኝና ያልተለመዱ አባባሎችና የአፃፃፍ ስልቶች ታክሎበት በመገረም ደጋግሜ አይቻቸዋለሁ። በአጠቃላይ ሌላውን ዝርዝር ለናንተ ትቼ መጽሐፉን በማንበብ የተገነዘብኩትን ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፦

- ሌሎች ስለህወሓት ሲጽፉ ደምረው ቀንሰው ነው። አስራት አብራሃም ግን የወጣት ነገር ነው መሰለኝ ያየውንና የሰማውን ሁሉ ሳይደምር ሳይቀንስ ታሪኩን እንዳለ ነው ያስቀመጠው።

- በአንዳንድ ምዕራፎች የጠቀሳቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ስመለከት ምስጢሩን ከየት አገኘው? የሚለውን ጥያቄ እንዳነሳ አድርጎኛል። ለምሳሌ ስለ የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴና የደህንነት ኃላፊ ስለነበረው አቶ ክንፈ ገብረ መድህን እና ስለጄነራል ኃየሎም አርኣያ አሟሟት ከኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ጋር አያይዞ ጠቅሷል። ስለሔጉ እና ስለአልጀርስ ውሳኔዎች እንዲሁም ህወሓት ከኤርትራ ጋር የነበረው ግንኙነትና በስተጀርባው ያለው ድራማ ፍርጥርጥ አድርጎ አውጥቶታል። የትግራይ ወጣት ሆኖ በዚያው እየኖሩ ያልተለመደ ድፍረት።

- ሌላው ከመጽሐፉ ለመረዳት የሞከርኩት ነገር፤ የፀሐፊው ራዕይና የወደፊት ተስፋው ምንድን ነው? የሚለው ነው። ጽሑፉን አንብቤ እንደተረዳሁት ከሆነ የብርቱኳን ዓይነት ሀገራዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና የሠለጠነ ራዕይ ያላቸው ወጣት ትውልድ በየቦታውና በየመድረኩ ብቅ ብቅ እያሉ እንደሆነ ነው።

- ከመጽሐፉ በላይ ያስገረመኝና ያስደነቀኝ ነገር ቢኖር፤ የፀሐፊው ድፍረት ነው። ለለውጥ ያለው ቁርጠኝነት፣ ለሀገሩንና ለአንድነቱ ያለው ፍቅርና እምነት ነው። በመጽሐፉ እንደተጠቀሰው በትግራይ በኰሌጅ በአስተማሪነት ተቀጥሮ ሲያገለግል በነበረበት ጊዜ የአቶ መለስ ዜናዊ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ታማኝና አባል እንዲሆን በህወሓት ሰዎች የአባልነት ፎርም እንዲሞላ ተጠይቆ አሻፈረኝ በማለቱ በተፈጠረው ውዝግብ ድራማው እንዴት እንደነበር ለወጣቱ ትውልድ በሚያስተምር መልኩ በዝርዝር አቅርቧል።

- መጽሐፉ እንደማንኛውም መጽሐፍ አንዳንድ የቃላትና የፊደል ግድፈቶች ቢኖሩትም በአጠቃላይ ከስሜታዊና ከጥላቻ የፀዳ በሳልና የሠለጠነ አቀራርብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

 

ስለሆነም “ከሀገር በስተጀርባ” የሚለው መጽሐፍ በተለይም ሀገር ተረካቢ የሆነው አዲሱ ትውልድ እንዲያውቀው ተብሎ የቀረበ ትልቅ ስጦታ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህንን መጽሐፍ ማንበብ ብዙ ወጣቶችን ያበረታታል የሚል ፅኑ እምነትም አለኝ።

ወጣት አስራት አብርሃምም ብዙ ጥረት አድርገህ ይህንን ዓይነት መጽሐፍ ማውጣትህ በዚሁ አጋጣሚ እንኳን ደስ አለህ እያልኩኝ ትልቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ለወደፊትም መልካም ዕድል እንዲሆንልህ ከልብ እመኝልሃለሁ።

 

ይህ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ትግል ነውና እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን እላለሁ።


ገሠሠ እንግዳ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ