20210302 adwa

Yewegene Tore Tizetaye, የወገን ጦር ትዝታዬ በኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ

”... ”የወገን ጦር ትዝታዬ” የተሰኘው ይሄ መጽሐፍ የደርግን የ17 ዓመት ታሪክ ለማወቅ የሚሹ በሙሉ ሊያነቡት፣ ሊመረምሩት፣ ለትውልድ ሊያሳልፉት የሚገባ መጽሐፍ ነው ብዬ አምናለሁ። ስለደርግ ብዙም መጻሕፍት አልተፃፉም፤ በተለይም በደርግ አባላትና በወቅቱ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ግለሰቦች የሚያውቁትን ታሪክ ለትውልድ አላካፈሉም። ...”

 

Yewegene Tore Tizetaye, የወገን ጦር ትዝታዬ የወገን ጦር ትዝታዬ

በኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ

ደራሲ ሻለቃ ማሞ ለማ

አሳታሚ ሻማ ቡክስ

አታሚ የተባበሩት አታሚዎች (አዲስ አበባ)

የሕትመት ዘመን 2001 ዓ.ም.

የገጽ ብዛት 497

ይዘት የኢትዮጵያ ጦር ታሪክ

የተዘጋጀበት ቋንቋ አማርኛ

 

በቅርቡ ገበያ ላይ የዋለው ”የወገን ጦር ትዝታዬ” መጽሐፍ ደራሲ፣ ሻለቃ ማሞ ለማ ለ17 ዓመታት በሰሜን ጦር ግንባር (ከሻዕቢያና ከወያኔ/ኢህአዲግ ጋር በተደረጉ ጦርነቶች) በተለያዩ ጦር ሜዳዎች በማገልገል ከዝቅተኛው የጦር ክፍል ጀምሮ በየደረጃው ባሉ የጦር ክፍሎች በተዋጊነት፣ በመሪነት፣ በአዛዥነትና በዘመቻ መኮንንነት ሠርተዋል። በመጨረሻም የጦር ኃይሉ የዘመቻ እንቅስቃሴ ማዕከል በሆነው በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መምሪያ የቀጠና መኮንን በመሆን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ያገለገሉ ናቸው።

 

ደራሲው በምድር ጦር ሠራዊት ውስጥ ያለፉበትንና የሚያውቁትን መሠረት በማድረግ በ17 ዓመቱ የኢትዮጵያ ጦር (ደርግ) እና ”ጠላት” (ሻዕቢያና ወያኔ/ኢህአዲግ) መሃከል በተደረገው ጦርነት ስለሀገራቸው አንድነት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት ሲሉ ሕይወታቸውን፣ አካላቸው፣ ደማቸውንና አጥንታቸውን የገበሩ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ወታደሮችን እውነተኛ ታሪክ በመጽሐፉ አካትተዋል። (በመጽሐፉ ላይ በወቅቱ አጠራር ”ጠላት” ተብሎ የተጠቀሰው የሻዕቢያና የወያኔ/ኢህአዲግ ሲሆኑ፣ ”ወገን” የተባለው ደግሞ በወቅቱ ደርግ ይመራው የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው። በዚህ ስለመጽሐፉ በተጻፈው ጽሑፍ ላይ የመጽሐፉን አባባልና ትርጉም መጠቀሜን ለአንባብያን መግለጽ እወዳለሁ።)

 

መጽሐፉ 14 ክፍሎች አሉት። እነርሱም የአምስት ዓመት ሰንሰለታማ ጦርነት፣ የበረሃው ንዳድ፣ አንዳንድ ውጊያዎችና ትውስታቸው፣ ከጠላት ጀርባ፣ የወገን አለህ፣ አጋጣሚ ተገጣጣሚ፣ የሰው አልባው መሣሪያ ጥቃት፣ መክት ዕዝ፣ ታላቁ ጦርነት፣ የፍፃሜው ዋዜማ፣ መፈንቅለ መንግሥትና መዘዙ፣ ፍፃሜው፣ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ውድቀት መቼ? ለምንና እንዴት?፣ እንዲሁም የጦርነትና የአዕምሮ ስነቅርስ የሚሉ ናቸው።

 

በጦርነት ላይ ምንም እንኳን ሞት እንደተራ የዕለት ገጠመኝ ቢቆጠርም የሰውን አስከሬን ቶሎ መበላሸት ደራሲው እንደሚከተለው ይገልጹታል። ”... በበረሃ የሚወድቅ የሰው ልጅ የሚያምርና ብሉኝ ብሉኝ እንደሚል የሙዝ ልጣጭ ይመስላል። የሙዙ ልጣጭ ተልጦ በተጣለ በደቂቃዎች ውስጥ የሚያምረው መልኩ በልዞና ጠቁሮ ተበላሽቶ ደብዛው እንደሚጠፋ ሁሉ፤ የሰውም ገላ ሰዓታት ሳይጠብቅ እንደሙዙ ልጣጭ ይሆናል። …” (ገጽ 28)

 

”አንዳንድ ውጊያዎችና ትውስታቸው” በሚለው በመጽሐፉ ክፍል ሦስት ውስጥ፤ በ1974 ዓ.ም. ከ100 ሺህ በላይ የሠራዊት ቁጥር ባለው ኃይል ስለተደረገው የቀይ ኮከብ ዘመቻ አጀማመርና አጨራረስ፤ እንዲሁም በወታደራዊ ስልት፣ በመረጃ አጠባበቅ ሥርዓትና አመራር ጉድለት ስለደረሰው ውድቀት፣ ከሞት የተረፈው ሠራዊት በጭዳነት ቀርቦ እንዲገደል የተደረገበትን ታሪክ ያሳያል። ከዚህም ሌላ በውጊያ ወቅት ስለሚገጥሙ አስገራሚ፣ አሳዛኝ፣ አሰቃቂና አንዳንዴም አስቂኝ ገጠመኞች ተካተውበታል።

 

በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ ደራሲው ”ከበላይ” በሚል ስለደረሰው አስደንጋጭ ትዕዛዝ ሲገልጡ፤ ”አሁን ለደረሰው ውድቀት መነሻ በሆኑት ሰዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ወስዳችሁ እንድታስታውቁን” ስለተባለ ሻለቃ አዛዦችና የፖለቲካ ሰዎች እራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ጥቃቅን ስህተት ያዩባቸውን አስተላልፈው 23 ሰዎች አለጥፋታቸው እንደተገደሉ አጋልጠዋል።

 

በጦርነት ታሪክ የወገንን ጦር ለመጉዳት የሚሰለፈው ጠላት ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን በሚፈጠር ስህተት ወገን የራሱን ወገን የሚጎዳበት ገጠመኝ ስለመኖሩ፣ የጦርነት አስከፊና መጥፎ ገጽታ የሚፈጠረውን ቁጭትና ፀፀት፤ የፀረ-ሰው፣ ፀረ-ታንክና ፀረ-ተሽከርካሪ ፈንጂዎች ስለሚያደርሱት አሰቃቂ ጥቃትና የጦርነትን አስከፊ ገጽታዎችን የሚያሳዩ እውነተኛ ታሪኮች በመጽሐፉ ተዘርዝረው ቀርበዋል።

 

”አጋጣሚ ተገጣጣሚ” በሚለው የመጽሐፉ ክፍል ውስጥ፤ ሞቶ፣ ተቀብሯል ተብሎ ተመልሶ በሕይወት የሚገኝ የጦር ሜዳ ጀግና ታሪክ ከሌላ አጋጣሚ ጋር ተመሳስሎ ስለተፈጠረው ውዥንብር ተተርኳል።

 

በአስመራና ዙሪያና በደጋው የኤርትራ ክፍል ስለተደረገ ወታደራዊ እንቅስቃሴ፤ በኤርትራ ይካሄድ የነበረው ጦርነት ከሽምቅ ውጊያ አልፎ የመደበኛ (ኮንቬንሽናል) መልክ ከያዘ በኋላ የጠላት ኃይል በመሣሪያና በሰው ኃይል አድጎ ከወገን ጦር እኩል ለመሆን በተቃረበበት ወቅት ሁለት መንግሥታት የሚያደርጉትን ውጊያ የመሰለ ታላቅ ፍልሚያ መደረጉንና ውጤቱን መጽሐፉ ይተርካል።

 

የ1981ዱን የመፈንቅለ መንግሥት በሚመለከት፤ በአዲስ አበባ፣ በአስመራና በሌሎች ቦታዎች የመፈንቅለ መንግሥቱን አጀማመርና አጨራረስ፣ የቀጠፈውን የሰው ኃይል፣ ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ የሠራዊቱ አቋም፤ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሰበብ ስለተገደሉትና ስለሞቱት ሀገሪቱ ስላፈራቻቸው 26 ጄነራሎች እና 12 ከኮሎኔል እስከ ሻምበል ማዕረግ ስላላቸው ከፍተኛ መኮንኖች ተተንትኗል።

 

በወታደራዊና በመንግሥት ሥልጣናቸው እጅግ ከፍተኛ የሚባሉ የገዘፉ፣ በወታደራዊ ዕውቀታቸውም ሆነ ልምዳቸው ከውጭ ከሚታየው አቋማቸው የማይተናነስ፣ በሳል አስተማሪነታቸውንና አዛዥነታቸውን አቻዎቻቸው ጭምር ከሚመሰክሩላቸው ታላላቅ የጦር መኮንኖችን ውስጥ ጄነራል ኃይለጊዮርጊስ ኃይለማርያም ተጠቅሰዋል። እነዚህ ታላቅ የጦር መኮንን ከፕሬዝዳንቱ (ኮሎኔል መንግሥቱ) ሳይቀር አንቱታና ከበሬታ ይለገሳቸው ስለነበር በሀገር መከላከያ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን፣ ወሳኝነትና ተደማጭነት እንደነበራቸው ለመገመት የማያዳግት ቢሆንም፤ እውነታው ግን ከሚገመተው ተቃራኒ እንደነበር በመጽሐፉ ተተርኳል።

 

በወቅቱ በራስ መተማመን መጥፋቱን፣ አድር ባይነት መስፋፋቱን፣ የሰው ዕውቀቱ ልምዱና ችሎታው መርከሱን፣ ለሀገር ፍቅርና ለህዝብ ታማኝነት ከሞኝነት መቆጠሩንና ለአንድ ፕሬዝዳንትና ሊቀመንበር መታመንና መታዘዝ የብቃት መለኪያና መመዘኛ በሆነበት ሥርዓት ዋናው እሳት ላይ ተጥደው ከነበሩት እጅግ የገዘፉ የጦር መኮንኖች ውስጥ አንዱ ጄነራል ኃይለጊዮርጊስ እንደነበሩ ደራሲው ይገልጻሉ።

 

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ህዝቡንና ሠራዊቱን ጥለው መኮብለላቸውን ተከትሎ 200 ሺህ የሚሆነው የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ከኤርትራ ተፈናቅሎ ወደ ሱዳን ያፈገፈገበት መራራ ታሪክ በመጽሐፉ ተካትቷል።

 

በመጽሐፉ ሁለት የመጨረሻ ክፍሎች ውስጥ፤ ሠራዊቱ በሚደርስበት የአመራር ስህተትና ብልሹነት እጥፍ ድርብ መስዋዕትነትን በመክፈል እንደሻማ እየቀለጠ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት አስከብሮ የኖረበት አሳዛኝ ታሪክ በማስረጃ ቀርቧል። ከዚህም ሌላ ለበርካታ ዓመታት በጦር ሜዳ መቆየት ሕይወት ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለማሳየት ተሞክሯል።

 

”የወገን ጦር ትዝታዬ” የተሰኘው ይሄ መጽሐፍ የደርግን የ17 ዓመት ታሪክ ለማወቅ የሚሹ በሙሉ ሊያነቡት፣ ሊመረምሩት፣ ለትውልድ ሊያሳልፉት የሚገባ መጽሐፍ ነው ብዬ አምናለሁ። ስለደርግ ብዙም መጻሕፍት አልተፃፉም፤ በተለይም በደርግ አባላትና በወቅቱ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ግለሰቦች የሚያውቁትን ታሪክ ለትውልድ አላካፈሉም።

 

ይህ መጽሐፍ ሌሎች በደርግ ዘመን በተለያዩ የመንግሥት፣ የመከላከያ እና በሌሎች የሚንስቴር መሥሪያ ቤቶችና አቅራቢያዎች የነበሩ ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን መረጃዎች፣ የሚያውቁትን፣ ያሳለፉትን፣ የሰሙትን፣ ... ለትውልድና ለታሪክ ጽፈው እንዲያልፉ መነሳሻ ይሆናቸዋል።

 

ስለመጽሐፉ ይሄን ያህል ካልኩ፤ ”አጋጣሚና ተገጣጣሚ” ከሚለው የመጽሐፉ 6ኛ ክፍል ትንሽ ቀንጭቤ ላስነብባችሁ። ታሪኩ በኮሎኔል ለሜሳ እና በመቶ አለቃ ወጋየሁ ደግነቱ መሃል ያጠነጥናል። ወጋየሁ ደግነቱ (ነፍሱን ይማረውና!) አርቲስት እና የሻለቃ ማዕረግ የነበረው ሲሆን፣ በዚህ በያዝነው ዓመት ሐምሌ 10 ቀን 2001 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶናል። ወጋየሁ ”አድሃሪን ጉቦኛን ቆርጦ ቆርጦ መጣል ነበር” በሚለው የአብዮት ዘፈን እና ”ቀበጥባጣ ወጣት” በሚሉት ዘፈኖቹ እንደሚታወቅ ደራሲው ጠቅሰዋል። በመጽሐፉ ከገጽ 192 - 194 የተተረከው ታሪክ እንደሚከተለው ይገኛል።

 

”... ኮሎኔል ለሜሳ በጥስ ብርጌድን በሚያዋጉበት ወቅት አንድ ሻለቃ ማዘዣ ላይ ሲደርሱ ሻለቃ አዛዡ ከሻምበል አዛዡ ጋር በመገናኛ ራድዮ ሲጨቃጨቅ ይሰሙትና ጠጋ ይላሉ። ጭቅጭቁም ሻምበል አዛዡ አንድ ተራራ አጥቅቶ እንዲይዝ ግዳጅ ተሰጥቶት ”ተራራው ላይ ያለው የጠላት መትረየስ አላስጠጋ አለኝ፤ በቀኝ በኩል 50 ካሊበር አለ፤ እሱም አላላውስ አለኝ” በማለት የመድፍና ከተቻለም የአየር ድጋፍ ይጠይቃል። በዚህም በሚደረድረው ምክንያት ማጥቃቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ በተራራው ወገብ ላይ ጦሩን ይዞ በመከላከል ”አልቻልኩም!” እያለ ”ይሄ ይመታ፤ በዚህ በኩል ሽፋን ይሰጠኝ” እያለ ያነበንባል።

ኮሎኔል ለሜሳ ሁሉን ነገር ካዳመጡ በኋላ ”ለመሆኑ ሻምበል አዛዡ ማን ነው?” በማለት ይጠይቃሉ።

”መቶ አለቃ ወጋየሁ ደግነቱ ነው” የሚል ምላሽ ያገኛሉ።

ከት ብለው ይስቁና ”እሱ ነው እንዲህ የሚያሾፈፍብህ? መነጋገሪያውን ስጠኝ” ይሉታል።

”ወጋየሁ ትሰማኛለህ?” አሉት።

እሱም በኮድ ስሙ እንጂ ትክክለኛ ስሙ በራድዮ መጠራት ስለሌለበት እንደመደንገጥ ብሎ ”ይሰማኛል፤ ቀጥል” ይላል።

”አውቀኸኛል?” ይሉታል።

”አላወቅኩህም” ሲል ይመልሳል።

”አባትህን አታውቅም እንዴ?” በማለት ሲኮረኩሩት ይነቃል።

”አውቄያለሁ፤ አውቄያለሁ፣ ...” ይላል።

”በደንብ ስማ!” ይሉትና ”ቆርጦ ቆርጦ መጣል በዘፈን ብቻ አይደለም። አሁን በተግባር ማየት እፈልጋለሁ። ይህ ካልሆነ አንገትህን ነው የምቆርጠው፤ ገባህ?” በማለት ቆሌውን ገፈፉት።

”ተቀብያለሁ፣ ተቀብያለሁ!” ይላል።

በማያወላውል ሁኔታ ትዕዛዛቸውን ካስታወቁት ገና አስር ደቂቃ ሳይሞላው ወጋየሁ ያለበትን ተራራ በጦር ሜዳ መነጽራቸው እያዩ እንደገና ”ወጋየሁን በራዲዮ አገናኙኝ” ይላሉ። መቶ አለቃ ወጋየሁ ለራድዮ ጥሪያቸው ይቀርባል።

”ይሰማሃል ወጋየሁ?”

”እሰማለሁ፣ ይሰማኛል” አለ እየተጣደፈ።

”እያየሁህና እየጠበቅኩህ ነው። ያዘዝኩህን እስክትፈጽም ዓይኔም ጆሮዬም ካንተ ላይ አይነሱም” ይሉታል።

”እሺ! ... እሺ! ... እቀጥላለሁ” ይላል።

ወዲያው መቶ አለቃ ወጋየሁ ጦሩን አስተባብሮ ወደፊት በማለት ማጥቃት ሲጀምር ተራራው በተኩስና በቦምብ ተደበላለቀ።

ኮሎኔል ለሜሳም ”ይሄ ነው የኔ ልጅ! እውነተኛው ቆርጦ መጣል ይሄ ነው! በራድዮ በመዝፈን ብቻ ጠላት ተቆርጦ አይወድቅም” በማለት ሲያዳምቁለት አካባቢያቸው ያለውን ሰው ሁሉ አሳቁት።

መቶ አለቃ ወጋየሁ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጠላትን ምሽግ ሰብሮ ተራራው አናት ላይ ቁጭ በማለት ስፍራውን መቆጣጠሩን አስታወቀ። ቀልድና ቁም ነገር በዚህ ዓይነት ዘዴ የተቀናጁበት አስገራሚ የድል ምዕራፍ ተከተበ።

መቶ አለቃ ወጋየሁ ዝነኛና የታወቀ የምሥራቅ ፖሊስ ኦኬስትራ ባልደረባ ድምፃዊ ነው። በመኮንንነት ከተመረቀ በኋላ አዲስ በተወቀቀረው ”ጅቦ” ጦር ውስጥ በመሪነት ተመድቦ አብሮ ዘመተ እንጂ፤ ሙያው እግረኛ ጦር መምራት አልነበረም።

ስሙም የተጠራለት በኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ ወቅት ”አድሀሪን ገቦናን ቆርጦ ቆርጦ መጣል ነበር” ብሎ በመዝፈኑና ቀደም ብሎም ”ቀበጥባጣ ወጣት” በሚለው ተወዳጅ ዘፈኑ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!