Abaté Yachin Seat አባቴ ያቺን ሰዓትፀሐፊ - ደረጀ ደምሴ

ቋንቋ - አማርኛ

አሣታሚና አከፋፋይ - Aesop Publishers & Distributors

ዋጋ - 25 የአሜሪካ ዶላር

“አባቴ ያቺን ሰዓት” በደረጀ ደምሴ የተጻፈና በቅርቡ በገበያ ላይ የዋለ አዲስ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ፀሐፊ ደረጀ ደምሴ ስለ አባቱ ሜ/ጄ ደምሴ ቡልቶ፣ በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ በአመራር ላይ ስለነበሩት ከፍተኛ መኮንኖች፤ እንዲሁም ስለ ግንቦት 81 መፈንቅለ መንግስት የጻፈው አዲስ መጽሐፍ ነው። ደረጀ ከአባቱ ጋር በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ያየውን እና በቦታው ከነበሩ የተለያዩ ከፍተኛ መኮንኖች ያጠናቀረውን፤ በጣፋጭ ትረካ አቅርቦታል።

 

New book; Abaté Yachin Seat አባቴ ያቺን ሰዓት በአቀራራቡ ልዩ በሆነው በዚህ መጽሐፍ ላይ ከዚህ በፊት ተደብቅው የነበሩ ምስጢሮችን የያዘ ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ የነበሩት ችግሮች ምን ነበሩ? የሌ/ኮ መንግሥቱን ሥርዓት ለመጣል የተደረገው ሙከራ ሂደት እንዴት ነበር? የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ዓላማስ ምን ነበር? መንስዔዎቹስ ምንድን ነበሩ? የኢትዮጵያ ሠራዊትና መሪዎቹ ያጋጠሙዋቸው ችግሮች፤ በተለይም የፖለቲካ ሥርዓቱ በጦሩና በመሪዎቹ ላይ የፈጠራቸው ዘርፈ ብዙ መሰናክሎች ምን ይመስሉ ነበሩ? መፈንቅለ መንግሥቱስ እንዴት ከሸፈ? የመፈንቅለ መንግሥቱስ አሳዛኝ ፍጻሜ የሀገራችንን እጣ ወዴት አመራው? … ወዘተ ብዙ ዓመታት በፈጀ ጥናት፣ በርካታ ቃለ ምልልሶችና በፀሐፊው ገጠመኞች ተመስርቶ በሰፊው ይዳስሳል።

 

የመጽሐፉ አተራረክ በአባትና ልጅ ታሪክ ላይ የተመሰረት እና አንባቢን የሚስብ፣ ከገጽ ወደ ገጽ በጉጉት የሚያስተላልፍ፣ በአይነቱ ከዚህ በፊት ከወጡት መጻሕፍት የተለየ ነው። ከመጽሐፉ በስተጀርባ የተያያዘው የሜ/ጄ ደምሴ ቡልቶ የግል የጦር ሜዳ ማስታወሻ ነው። ከሐምሌ 29 ቀን 1977 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 3 ቀን 1978 ድረስ የባሬንቱን ከተማ ለማስለቀቅና ናቅፋን ለመቆጣጠር በተደረጉት ዘመቻዎች ጄ/ል ደምሴ ቀን በቀን የያዙት ማስታወሻ በራሳቸው እጅ ጽሑፍ እንዳለ ለታሪክ ተመራማሪዎች እንዲያገለግል ደራሲው አቅርቦታል።

 

የ”አባቴ ያቺን ሰዓት” ፀሐፊ ደረጀ ደምሴ የጄ/ል ደምሴ ቡልቶ አራተኛ ልጅ ሲሆን፣ ነዋሪነቱም በሰሜን አሜሪካ ነው። ደረጀ ከጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲ በመንግሥት ፖለቲካ ትምህርት በባችለር ዲግሪ፣ ቦስተን ከሚገኘው ከሳፈክ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ ተመርቋል። በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካን ሀገር በጥብቅና ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው።

 

የመጽሐፉን ይዘት ለማመልከት ያህል ከዚህ በታች ከመጽሐፉ የተቀነጫጨቡ ትረካዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

 

  • “… በፍርሐት ተይዞ የነበረው ጦር ከየምሽጉ እየወጣ ማጥቃት ጀመረ። ሞራሉ ተገንብቶ ካላጠቃሁ ካልተዋጋሁ ማለት ጀመረ። ጄ/ል ደምሴ ወደኛ ዞር አሉና “ይሄ ተራ ሽፍታ ነበር ሠራዊቱን አስጨንቆ የነበረው። ወንበዴው አይደለም። እናንተ ናችሁ ሠራዊቱን ፈሪ ያደረጋችሁት። የመሪ እንጂ የተመሪ ፈሪ የለውም!” አሉ። ከሞሰቦ አካባቢ ማጥቃቱ ቀጥሎ በተከታታይ ያለማቋረጥ እያጠቃ የኢትዮጵያ ጦር ውቅሮን ተቆጣጠረ። እንደገና በመቀጠል የወያኔን ጦር ማጥቃት ቀጠለ። …”

 

  • “… ብ/ጄ ታሪኩ አይኔ ላይ … የተደረገው ያሳዝናል ዕድሜ ልኩን ጦር ሜዳ ኖሮ … ተይኝ እባክሽ፣ ሰሞኑን ደግሞ ሲቪል ሆነው ለዓመታት ሲሠሩ የነበሩትን እያነሱ የጦር አዛዥ ማድረግ ሆኖአል ሥራቸው። ዘለቀ በየነ በሜ/ጄኔራልነት የደቡብ ዕዝ አዛዥ ሆኗል። ይሄ ማነው ውብሸት ደሴ በሻለቃነት ወደ ሲሺል ተቀይሮ የፖለቲካ ሥራ ሲሠራ የኖረ ነው። አሁን ከ15 እስከ 20 ዓመት ልምድ የሚጠይቀውን ቦታ ያውም ሦስት ደረጃ ዘሎ በሜ/ጀኔራልነት የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ … ምን ትይዋለሽ ታዲያ ይሄንን፣ ቀልድ አይደለም?” ጄ/ል መርዕድ የሚናገረውን ማመን እንዳቃተው የፈጠጡት ዓይኖቹና ወደ ጎንና ወደ ጎን የሚዘዋወረው ጭንቅላቱ ይገልፃሉ። …”

 

  • “… አባቴ “ወርቁ ይህ ሁኔታ እስከመቼ ነው በዚህ መልክ የሚቀጥለው? መሠረታዊ ለውጥ ካልተደረገ ይህች ሀገር ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው የምትወድቀው” ብሎ ሲጀምር፣ ጀ/ል ወርቁ ወዲያው ተቀብለው፤ “ጀነራል እኛ እኮ ለህዝብ የተሻለ ሥርዓት እናመጣለን ብለን እንጂ፣ የአንድ ሰው አምባገነን መንግሥት ለመመስረት አልነበረም ለውጡን የደገፍነው” አሉ። የፖለቲካ ኃላፊ እንደዚህ ሲናገር ሰምቼ ስለማላውቅ ግራ ገባኝ። ይህ ሰው ተናግሮ ለማናገር ፈልጐ ቢሆንስ? ...”

 

  • “… በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጊዜ፣ መንግሥቱ ከወረደና ሻዕቢያ የተወሰነ ሥልጣን እስከተሰጠው ድረስ፣ የኤርትራን ነፃነት ጥያቄ ለማንሳት ዝግጁ እንደነበር ገልጸዋል። እንዳውም ሻዕቢያ አስመራ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተካሄደ ወደ ህወሓት (TPLF) መልዕክት እንደላከ እና መልዕክቱም በፍጥነት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን እንድንደግፍና ከአስመራ ከእኛ ጋር ለመገናኘት የሚላኩትን የመፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ቡድን ወኪሎችን በአዲቋላ በኩል እንድንቀበላቸው የሚጠይቅ ነበር ብለዋል። ህወሓት ግን ይህን ጥሪ እንዳልተቀበለውና ውሳኔውን በራሱ ራዲዮ ሲገልጽ፣ የሻዕቢያ አመራር በውሳኔው ማዘናቸውን ገልጸዋል። …”

 


ጥቆማ መጽሐፉን ኢንተርኔት ለመግዛትም ሆነ አከፋፋዩን ለማግኘት የሚከተለውን አድራሻ ይጠቀሙ።

Aesop Publishers & Distributors

ስልክ: 202-386-3037

www.demissiebulto.com

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!