የ“ኢ/ር ታደለ ብጡል የሕይወት ታሪክ አርኣያነት” መጽሐፍ የምረቃ በዓል

ተረፈ ወርቁ

ኢንጂነር ታደለ ብጡል እስከ ዛሬ ድረስ ፲፬ የሚያህሉ መጻሕፍት ለንባብ አብቅተዋል። እነዚህ መጻሕፍት በአብዛኛዎቹ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ሀገራችን ታሪክ፣ አኩሪ ባህል፣ ቅርስና የቀድሞ ገናና ሥልጣኔያችንን የሚያወሱ ዘመን አይሽሬ ናቸው። ”The Origin of Humankind” የሚለው የኢትዮጵያን የሺ ዘመናት ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔና የህዝቦቿን ነጻነትና ልዑላዊነት በሰፊው የሚተርከው፣ በፋሽስት ኢጣሊያ ስለተወሰደውና ወደ እናት ምድሩ እንዲመልስም ከፍተኛ የኾነ አስተዋጽኦና ጥረት ስላደረጉበት የአክሱም ሀውልት፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሠረት ጣይ ስለሆነው ስለ ዐፄ ቴዎድሮስና ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ የጻፏቸው የታሪክ መጻሕፍት ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም ኢ/ር ታደለ የሀገር ባለውለታና ቅርስ የኾኑ የከበደ ሚካኤልን የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸውን የሚዘክርና በቅርቡም ደግሞ ‹Pioneers of Change› ከሚባሉት፣ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ታላቅ ራእይ ከነበራቸው የ፳ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱትን የሐኪም አዛዥ ወርቅነህ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል። ኢ/ር ታደለ ‹ሦስትዮሽ እና ሌሎች ግጥሞች› የምትል የግጥም መድብልም አሳትመዋል።

በዘጠናኛ/፺ኛ ዕድሜያቸው ዋዜማ ላይ የሚገኙትና የእነዚህ ሁሉ ሥራዎች ባለቤት የኾኑት ኢ/ር ታደለ ብጡል በበርካታ ምዕራፎች የሚገለጸውን የራሳቸውን የሕይወት ታሪካቸውን ግን አልጻፉም ነበር። ይሁንና በርካታ ወዳጆቻቸው ለትውልድ ቅርስ ኾኖ የሚተላለፍ የሕይወት ታሪካቸውንና ትዝታዎቻቸውን ይጽፉ ዘንድ መወትወታቸው አልቀረም። ይህ የብዙ ወዳጆቻቸውን ውትወታ ወደ ተግባር ተቀይሮ ዕውን ይኾን ዘንድ ያደረገውን አጋጣሚ የፈጠረ አንድ ክስተት ነበር።

አክሊሉ አበሩ የተባለ አንድ የፊዚክስ አስተማሪ የሆነ ወጣት ‹ራስን ማብቃት› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን በሳይንሳዊ ቀመሮችንና ትንታኔዎችን መሠረት አድርጎ የጻፈውን መጽሐፉን ለማስገምገም ወደ ኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ይዞ ይሔዳል። ማኅበሩ ግን ካለበት የሥራ ጫናና የባለሙያ እጥረት ምክንያት ከአራት ወራት በኋላ እንጂ አሁን ሊያዩለት እንደማይችል ይነግሩታል። ይህ ወጣትም ይህን መጽሐፉን በተለያዩ መድረኮች ወደሚያውቃቸው ወደ ኢ/ር ታደለ ብጡል ይዞ ይመጣል። ኢ/ር ታደለም በአጭር ጊዜ ውስጥ መጽሐፉን አንብበው ከአስተያየታቸው ጋር ይመልሱለታል።

በመጽሐፉ ላይ በሰጡት አስተያየትና ባነሷቸው ሐሳቦች እጅጉን የተደነቀው ወጣት መምህር አክሊሉም የእርስዎ ታሪክ ለትውልድ አርኣያና ተምሳሌት ነውና እባክዎ መልካም ፈቃድዎ ከኾነ የሕይወት ታሪክዎን የሚዳስስ መጽሐፍ ባዘጋጅ የሚል ትሑት ግብዣ ያቀርብላቸዋል።

የእዚህን ወጣት መንፈሳዊ ቅናት፣ ጥንካሬና ብርታት ያዩት ኢ/ር ታደለም ፈቃዳቸው ኾኖ ለወጣት አክሊሉ አስፈላጊ የኾኑትን መረጃዎች ሁሉ በመስጠትና ትዝታዎቻቸውን በመንገር ‹የኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት የሕይወት ታሪክ አርኣያነት› የሚል መጽሐፍ ባሳለፍነው እሑድ- የቀድሞ የአ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዝዳንት፣ የሰላምና የአረንጓዴ ልማት አርበኛ መ/አ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ የኢንጂነር ታደለ ቤተሰቦች፣ አብሮ አደግ ጓደኞቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ የሀገር ባለውለታና ቅርስ የኾኑ- ሕዝባቸውንና ወገናቸውን በቅንነት ያገለገሉ ታላላቅ ሰዎች፣ አምባሳደሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች በክብር እንግድነት በተገኙበት በካፒታል ሆቴልና ስፓ በደመቀ ዝግጅት ይህን መጽሐፋቸውን አስመርቀዋል።

በእርግጥ በዚህ ጽሑፍ አርዕስቴ እንደገለጽኩት ይህ ደማቅ ዝግጅት የኢ/ር ታደለ መጽሐፍ ምረቃ የተካሄደበት መድረክ ብቻ ሣይሆን፣ ለአገራቸውና ለወገናቸው ታላቅ ሥራን ሠርተው ያለፉና አሁንም በሕይወት ያሉ ግን ደግሞ የዚህ ዝግጅት የመድረክ መሪና አስተባባሪ የኾነው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በቁጭትና በእልክ ደጋግሞ ለመግለጽ እንደሞከረው፣ ”ከእነርሱ ይልቅ ሥራቸው ጎልቶ የሚናገር እነርሱ ግን ዝምታን የመረጡ፣ ትውልዱ የዘነጋቸው ግን ሊያመሰግናቸው የሚገባቸው” የሀገር ባለውለታ የኾኑ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን የተዘከሩበት፣ የደመቁበትና የተመሰገኑበት ድንቅ ዝግጅት ነበር።

እስቲ ስለ መጽሐፉ ምረቃ አንዳንድ ቁምነገሮችን ከማለቴ በፊት ኢ/ር ታደለ ብጡልን በቅርብ እንዳውቃቸው ያደረገውን አጋጣሚዬን ላንሣ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የአክሱምን ሀውልት ለማስመለስ የተቋቋመው ኮሚቴ መካከል ዋና የነበሩት እኚህ ሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተገኝተው ስለ ሀውልቱ አመላለስ ያደረጉት ሌክቸር፣ ለኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ ያላቸውን መቆርቆር በሚገባ እንዳውቃቸው ልዩ አጋጣሚን የፈጠረልኝ ነበር።

ከዛም በኋላ እኚህ ሰው በተለይ ታላቁ ደራሲና የሥነ ጽሑፍ ሰው የሆኑት ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ተገቢው ክብር እንዲሰጣቸውና ሥራቸውም በወጣቱ ትወልድ ዘንድ በሚገባ እንዲታወቅ፣ እንዲሁም ምንም እንኳን የዘገየ ቢሆንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሀገርና ለህዝብ ላደረጉት ታላቅ አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ድግሪ እንዲሰጣቸው በማድረግ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር ያደረጉት በጎ ሥራ፣ እንዲሁም በተለያዩ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያላቸው የጎላ ተሳትፎና አስተዋጽኦ በይበልጥ እንዳውቃቸውና እንዳከብራቸው አደረገኝ።

እኚህን በኢትዮጵያ ታሪክ እውቀታቸውና በቅርስ ተቆርቋሪነታቸው እንዲሁም ደግሞ በበጎ ሥራ የጎላ እንቅስቃሴያቸው የማውቃቸውንና የማደንቃቸውን ኢ/ር ታደለ ብጡልን በአካል እንድንተዋወቃቸው ያደረገን አንድ አጋጣሚ ይህ ነበር። ይኸውም ከሁለት ዓመት በፊት የፀረ-አፓርታይድ ታጋይና የዓለም የሰላም ኖቤል አሸናፊ በኾኑት በኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ የትግል ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ዘጋቢ ፊልም ለመሥራት ከደቡብ አፍሪካና ከብሪቲሽ ፊልም ካምፓኒ ወደ ሀገራችን የመጡ ባለሙያዎች ነበሩ።

ይህ ”The Mandela’s Gun” ርእስ የሚሠራው ዘጋቢ ፊልም ዋና ዓፀመ ታሪኩ ደግሞ ማንዴላ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጥቶ በነበረበት ጊዜ ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ/ከአሰልጣኙ ከጄ/ል ታደሰ ብሩ የተበረከተለት ቡልጋሪያ ሰራሽ ማካሮቭ ሽጉጥን መነሻ ያደረገ ነው።

ይህች የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ/ANC የትጥቅ ትግል ማብሰሪያ ምልክት የሆነች ሽጉጥ ደግሞ ማንዴላ ወደ አገሩ በተመለሰበት ወቅት በሀገር መክዳት ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ወደ ወኅኒ ሲወርድ በፓርቲው የህቡዕ መሰብሰቢያ ግቢ ውስጥ እንዲቀበር ነበር የተደረገው። ከሃያ ሰባት ዓመት እስር በኋላ ማንዴላ ከእስር ነጻ ወጥቶ የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዝዳንት ሲሆን ይህችን በእጅጉ ከሚያከብራት ከሚወዳት ኢትዮጵያ የተበረከተለትን የANC ትጥቅ ትግል ማብሰሪያ የኾነች ሽጉጥ ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ ከተቀበረችበት ለማውጣት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ይቀራል።

እንግዲህ ደቡብ አፍሪካውያኑና እንግሊዛውያኑ የፊልም ባለሙያዎች በዚህች ደብዛዋ በጠፋው ሽጉጥ ዙርያ ኢትዮጵያን ማእክል አድርገው ለሚሠሩት ፊልም ለመወያየት በሒልተን ሆቴል ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ጊዜ የነበሩ ታሪክ አዋቂ ኢትዮጵያውያን፣ የደኅንነትና ከፍተኛ የወታደራዊ መረጃ ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አባላት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ምሁራን፣ የመገናኛና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት ስለ ዘጋቢ ፊልሙ የውይይት መድረክ ተካሂዶ ነበር።

ታዲያ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከተገኙት ታላላቅ ሰዎች መካከል ኢ/ር ታደለ ብጡል አንዱ ነበሩ። በስብሰባው ላይም እንዲህ ሲሉ ብዙዎቻችንን ያስማማ ንግግር ተናገሩ። ”ይህ ኢትዮጵያን ማእክል አድርጎ በማንዴላ የትግል ሕይወት ላይ የሚሠራው ዘጋቢ ፊልም- የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት የነጻነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክ፣ የህዝቦቿን ባህል፣ ቅርስና ማንነት የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት።” በማለት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል ውስጥ የነበራትን ጉልህ ድርሻና ደማቅ አሻራ በሰፊው አብራሩት።

በዚህ ዘጋቢ ፊልም ሥራ ውስጥ በሲነር ሪሰርችርነት በታሪክ መረጃ አሰባሳቢነት በሠራሁበት ጊዚያትም ይህ ኢ/ር ታደለ ብጡል ለአገራቸው ታሪክና ቅርስ ተቆርቋሪነት፣ ፍቅርና ክብርም እጅጉን አስደንቆኝ ነበር። ታዲያ በቅርቡ በፋሽሰት ወረራ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረባ ሆኖ ስላገለገለው ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን ስለሚባል አፍሪካ አሜሪካዊ በተጻፈው የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ ተመርኩዤ ስለዚህ አሜሪካዊ የአየር ኃይል ሰው የሚያውቁትን ታሪክ እንዲነግሩኝ ፈቃደኛ ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ በቤታቸው ተገኘሁ።

የኢ/ር ታደለ መኖሪያቸውን ቤት ከማለት ይልቅ መለስተኛ ቤተ-መዘክር/ሙዚየም ብሎ መጥራት ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም። በበርካታ መጻሕፍት ከተሞላው ከግላቸው ቤተ መጽሐፍ ጀምሮ በሳሎናቸው ውስጥ የሚታዩ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ሰዎችን የሚዘክረው ታሪካዊና ዕድሜ ጠገብ ሥዕላት፣ ምስሎችና ፎቶግራፎች፣ ቅርጻ ቅርጾች እንዲሁም የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ በተመለከተ በጽሑፍ፣ በሰነድ፣ በምስል፣ በድምፅና በቪዲዮ ያሰባሰቧቸው መረጃዎችና ቅርሶች እንደ አንድ የታሪክና የቅርስ ባለሙያ እጅጉን ያስደነቀኝና ያስገረመኝ ነገር ነው።

ኢ/ር ታደለ ብጡል በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፓና በአሜሪካ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ነጻነትና ጀግንነት ሌክቸር ሰጥተዋል፣ ኢግዚቢሽን አሳይተዋል። ለአብነትም በአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ግብዣ ተደርጎላቸው ስለ አክሱም ሀውልት አወሳሰድና በኋላም ወደ አገሩ እንዲመለስ የተደረገውን ትግል በተመለከተ በቪዲዮ መረጃ አስደግፈው የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ለማየት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር። ኢ/ር ታደለ በኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ ላይ እርፍት ያላቸው ሰው አይመስሉም።

እኚህ ብርቱ ታሪክ አፍቃሪ ኢትዮጵያዊ በኢጣሊያ፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ታላላቅ ቤተ መጻሕፍትና አርካይቮችን በመመርመር ያዘጋጁት ዘጋቢ/ዶክመንተሪ ፊልምም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ነጻነትና ጀግንነት ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ቋሚ የታሪክ ቅርስ ነው።

ኢ/ር ታደለ ብጡል ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ስላላቸው ክብርና ተቆርቋሪነትና ለሕዝባቸው ስላላቸው ፍቅርና ወገናዊነት በዚህ አጭር ገጽ ለመሸፈን የሚሞከር አይደለም። ይሁንና እንደእነ ኢ/ር ታደለ ብጡል ያሉ ለአገራቸው ታላላቅ ሥራን ሠርተው ስላለፉና አሁንም በሕይወት ያሉ ባለውለታዎቻችን ክብር፣ ፍቅርና ምስጋና ሊቸራቸው ይገባቸዋል ለማለት እወዳለሁ። በመቀጠልም ስለ ኢ/ር ታደለ መጽሐፍ ምረቃ ጥቂት ቁም ነገሮችን በማንሣት ጽሑፌን ልደምድም።

አስቀድሜ በጽሑፌ መግቢያ እንደጠቀስኩት የኢ/ር ታደለ ብጡል የመጽሐፍ ምረቃ በተለይ በአዳራሹ ለተገኘን ወጣቶች ባለውለታዎቻችንን እንድናስብና እንድንዘክራቸው ሓላፊነትና የታሪክ እዳ እንዳለብን ያስገነዘበን ነው ብል የተሳሰትኩ አይመስለኝም። በዚህ መጽሐፍ ምረቃ ላይ ከክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል እስከ አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ያሉ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ሰዎች ሥራቸው የተዘከረበት፣ በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት በተገኙ በልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው የታወሱበት ብዙዎቻችንን በደስታና በሐሤት የሞላ እጅጉን የተዋጣለት ደማቅ ዝግጅት ነበር።

የመድረኩ አስተባባሪና መሪ የሆነው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገንም እነዚህ ባለውለታዎቻችን ከዚህ የምስጋና ባለእዳ ከሆነው ከእርሱና ከትውልዱ ፍቅር፣ ክብርና ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ ያደረገበት አስተውሎቱ ሊደነቅ የሚገባው ነው። በዚህ መድረክ ላይ ስለ ኢ/ር ታደለ ከተናገሩትና በሕይወት ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ ሰፋ ያለ አስተያየት ከሰጡ ሰዎች መካከል የኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም አስተርጓሚ የነበሩት አዛውንቱ አቶ ግርማ በሻህ አንዱ ነበሩ።

እኚህ የበርካታ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆኑ ሰው ደራሲና ተርጓሚም ናቸው። ከተረጎሟቸው መጻሕፍት መካከልም በ፲፮ኛው መቶ ክ/ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ፖርቹጋላዊው ቄስ አልቫሬዝ በፖርቱጋል ቋንቋ የጻፈውን ዳጎስ ያለ የጉዞ ማስታወሻ ወደ አማርኛ የተረጎሙልን ባለውለታችን ናቸው። እኚህ ሰው ስለ ኢ/ር ታደለ ብጡል ከተናገሯቸው ቁም ነገሮች መካከል ሁለቱን ብቻ ልጥቀስ።

ኢ/ር ታደለ ታሪካዊ ሰነዶችንና መረጃዎችን በጥንቃቄ ሰብስቦ የሚያስቀምጥ ብልህ አርካይቪስት ነው። ትዝ የሚለኝ አሉ አቶ ግርማ- ከሃምሳ ዓመታት ገደማ በፊት ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ የሰጧቸውን የአርበኝነት ጊዜ ፎቶግራፋቸውን በጥንቃቄ አስቀምጠው የሕይወት ታሪካቸው መጽሐፍ ሲጻፍ አብሮ እንዲካተት መልሰው ያበረከቱላቸውን ታሪካዊ ፎቶ በአድናቆት አንስተው ነበር። አቶ ግርማ ኢ/ር ታደለ በሀገራችን የሙዚቃ ት/ቤት እንዲጠናከርና እንዲሁም ቀን መማር የማይችሉ ሰዎች ማታ ማታ እየተማሩ እውቀት እንዲገበዩና ኑሮአቸውን ማሻሻል እንዲችሉ ያደረጉትን አስተዋጽኦቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው አብሮ አደጋቸውና የረጅም ዘመን የት/ቤትና የሥራ ባልደረባቸው የነበሩት አምባሳደር አየለ ሞልቶት የልጅነትና የትምህርት ቤት የማይረሳ ትዝታቸውን የተረኩበት አጋጣሚ ብዙዎችን ያስደነቀና የዘመን ተጋሪዎቻቸውን በትዝታ በርካታ ዓመታትን ወደኋላ እንዲመለሱ ያደረገ ነበር። በግሌ እንደእነዚህ ዓይነቶቹ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ሰዎች ታሪካቸውንና ትዝታቸውን ለትውልድ የሚያስተላልፉበት ቋሚ መድረክ ምናለበት በሰፊው ቢኖር ብዬ እንድመኝ አስገድዶኛል።

ከሴት ባለውለታዎቻችንና ጀግኖቻችን መካከልም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከዛሬ ኀምሳ ዓመት በፊት ሲቋቋም የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ወ/ሮ ዕሌኒ መኩሪያ በዚህ መድረክ ላይ ተገኝተው ነበር። ወ/ሮ ዕሌኒ ”ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ኀምሳኛ ዓመቱን በደማቅ ዝግጅት ሲያከብር ባያስታውሰኝም …” በማለት የቅሬታ ስሜታቸውን የገለጹበት አጋጣሚ ብዙዎችን ግራ ያጋባና ያሰደነገጠ ነበር። ግን ደግሞ አሉ ወ/ሮ ዕሌኒ፣ ”በዚህ ታላቅና ታሪካዊ መድረክ ላይ እንድገኝ ስላስታወሳችሁኝ አመሰግናችኋለሁ!” በማለት ከኢ/ር ታደለ ብጡል ግጥሞች መካከል ለዝግጅቱ ታዳሚዎች ያነበቡት ድንቅ ግጥም ለመድረኩ ልዩ ውበትን የፈጠረ ነበር።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የረጅም ጊዜ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ መዓዛ ቅጣው ከኢ/ር ታደለ ብጡልና ከሌሎች ወገን ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ለደራሲ ለክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የተደረገውን መልካምና በጎ ሥራ ያስታወሱበት አጋጣሚም ሌላኛው የኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ መረዳዳት የቆየ አኩሪ ባህላችንና ለወገን ያለንን ፍቅርና መቆርቆር ይህ ትውልድም ጠብቆ እንዲያቆየው የአደራ መልእክት የተላለፈበት መልካም አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል።

በመጨረሻም ኢ/ር ታደለ ብጡል በዚህ የመጽሐፍ ምረቃ በዓል ዝግጅት ታሪክ የማይዘነጋቸውን ኢትዮጵያውያን ባለውለታዎቻችንና ጀግኖቻችንን ሥራቸው በሚገባ እንዲዘከርና ምስጋና እንዲቸራቸው በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። በዚህ ረገድም መንግሥት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና መስሪያ ቤቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ ለወገን ፍቅርና ክብር አለን የምንል ሁሉ የሀገርና የህዝብ ባለውለታ የሆኑ ባለውለታዎቻችንና ጀግኖቻችንን ታሪካቸውንና ሥራቸውን መዘከር ግዴታና የታሪክ እዳ እንዳለብን በመግለጽ ጽሑፌን ላጠናቅ። አበቃሁ!!

ሠላም!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!