ሸንቁጥ አየለ

"Yetefat Zemen" new book by Muluken Tesfaw

ወያኔ ”የጥፋት ዘመን” የተሰኘውን የሙሉቀን ተስፋውን አዲስ መጽሐፍ በመላ ሀገሪቱ እንዳይሰራጭ፣ እንዳይሸጥ እና እንዳይነበብ አግዳዋለች። ግን ለምን?

ህወሓቶች እንዲህ አይነት መጽሐፍ ታትሞ ቢሰራጭ እንደሚያግዱት ገና ከጅምሩ ግምት ሳይሆን ጠንካራ ድምዳሜ ላይ ደርሼ ነበር። ይሄም የሆነው በተለያየ ወቅት ከበርካታ ወጣቶች ጋር በአማራ ህዝብ ላይ የተሰራውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመጽሐፍ መልክ ስለማሳተም እየተወያዬን ስለነበረ እና ወያኔም መጽሐፉ ታትሞ ቢወጣ ሊያግደው እንደሚችል ሰፊ ትንታኔ ሰርተንበት ስለነበረ ነው።

ታሪኩን ለማሳጠር በመሃል ሙሉቀንን ሳገኘው ትክክለኘውን ሥራ የሚሠራው ይሄ እሳት የላሰ ወጣት መሆኑን በመረዳቴ ሙሉቀንን ማበረታታትን መረጥሁ። ሙሉቀንም በፍጥነት ሥራውን ማቀላጠፉን ያዘው።

በጣም በተሳካ ሁኔታም ሞረሽ የጥናቱን ወጭ ሊሸፍን ሲነሳ፣ የመረጃ ምንጮቹ ኔትወርኮች ደግሞ ተያይዘው መፍሰስ ጀመሩ። በተለይም የመላው አማራ ህዝብ ድርጀት (መአህድ) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለብዙ ዓመታት የደከሙበት የአማራን ህዝብ ፍጅት በመረጃ እየመዘገቡ ያጠራቀሙት የመረጃ ቋት እንደ ኩል ውሃ ኮለል እያለ ለመነሻነት እና ለመንደርደሪያነት ማገልገል ጀመረ። በተጨማሪም የሰበዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሰበሰቧቸው መረጃዎች በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰውን ፍጅት ፍንትው አድርገው ማሳዬት ጀመሩ።

ለሃያ አምስት ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ፍጅት ሲፈጸም እና የአማራ ህዝብ ከአባቶቹ ሀገር ከኢትዮጵያ ምድር ያለ ዕዳው ሲሳደድ፤ በርካታ ሚዲያዎች ምንነቱ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት አፋቸውን መለጎም ቢመርጡም ስለ እውነት ሲሉ ግን ሳይታክቱ መረጃ ይይዙ የነበሩ ግለሰቦች፣ የፓርቲ አባላት፣ የፓርቲ አመራሮች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተራ ዜጎች ግን ብዙ ነበሩ።

እናም እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ያጠራቀሙት መረጃ አንዴ ውሉ ሲገኝ መተርተር ጀመረ። ሙሉቀን በወጣት ጉልበቱ ሳይደክም ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ ጠልቆ ገባ። ጥናቱ አድካሚ ቢሆንም አመርቂ ሥራም በፍጥነት መሠራት ቻለ። ይሄ ጥናት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ በመጽሐፍ መልክ ለሕትመት መቅረቡ የሙሉቀንን ብርታ እና ትጋት የሚያረጋግጥ ነው።

ከብዙ ወጣቶች ጋር ካለኝ ሰፊ ግንኙነት አንጽር ስገመግመው የሙሉቀን አንድ የተለዬ ተሰጥኦ ፈጥኖ ወደ ሥራ መግባቱ እና አደጋዎችን ተጋፍጦ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑ ነው። እንዲሁም በዚህ ጥናት ጀርባ ያሉት ኃይላት እና የመረጃ ምንጮች የጥናቱ ዋና የጥንካሬ ምንጭ ናቸው። በጥናቱ ውስጥ የተጠቀሱት መረጃዎች ማንንም የሚያፈናፍኑ አይደሉም። ምክንያቱም ጥናቱ ከተጨባጭ ምንጮች፤ እንዲሁም በአካል ጉዳቱ የደረሰባቸውን በሕይወት የተረፉ ተጠቂዎችን ሁሉ በማካተት የተሠራ ስለሆነ ነው።

ከላይ እንደተቀስኩትም ወያኔዎችን እንዲህ አይነት ጥናት ሊያስደነግጣቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሊያፍኑት እንደሚችሉም ሰፊ ትንታኔ ሰርተንበት ነበር። ምክንያቱም ይሄ መጽሐፍ አንድ ሰፊ ቁጥር ያለውን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ለይተው እንዴት የዘር ማጥፋት ዒላማ እንዳደረጉት በጥልቀት ያጋልጣቸዋል እና ነው። እናም መጽሐፉ እንዳይሰራጭ ሊያግዱት ቢነሱ ምንም የሚያስገርም ነገር አይኖርም።

እኔ እንዳስተዋልኩት በርካት ኢትዮጵያዊ ስለ ወያኔ የዘር ማጥፋት ወንጀል በቂ መረጃ የለውም። ወይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት በኢትዮጵያ እየተደረገ ነው ሲባል፤ ነገሩ ቀልድ የሚመስለው እና በጀርባው የተኛ ብዙ ዜጋ አለ። የሙሉቀን መጽሐፍ እንግዲህ ይሄን ሁሉ በጀርባው ለጥ ያለ ህዝብ የሚያነቃ ነው። ወያኔዎች ደግሞ የንቃተ ህሊናን ሚስጥር በደንብ ያውቁታል። ህዝብ ንቃተ ህሊናው ከፍ ካለ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ።

በእኔ አረዳድ ይሄ መጽሐፍ የአማራ ህዝብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በእኔ አረዳድ ይሄ መጽሐፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ እና ታሪክ ነው። አማራ ህዝብ ላይ የደረሰ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መጽሐፉን ሲያነበው በጣም ልቡ እንደሚሰበር የሚያጠራጥር ነገር አይመስለኝም። ሌላው ቀርቶ ከወንጀል ህሊና ንጹህ የሆኑ የህወሓት አባላት ይሄን መጽሐፍ ቢያነቡት አንድ ጥያቄ መጠየቃቸው አይቀርም። እንዲህ የሚል፦ "ግን የአማራ ህዝብ ምን ስለበደለን ነው ይሄን ሁሉ ወንጀል የፈጸምንበት?"።

ይሄ መጽሐፍ ወደፊት በምትመሰረተዋ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት የየአንዳንዱ ዜጋ ሕይወት፤ እንዲሁም የየአንዳንዱ ማኅበረሰብ ህልውና በጥንቃቄ ሊጠበቅ እንደሚገባው ብዙ ትምህርት የሚሰጥ ስለሆነ፤ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መጽሐፉን ታነቡት ዘንድ እጋብዛችኋለሁ። በቀጣይም ሰፊ ምርምር ሊሠራበት የሚችል ዘርፍ ስለሆነ፤ ምሁራን መነሻ የመረጃ ምንጭ ልታደርጉት ትችላላችሁ።

ለማኛውም ወያኔ ከሰይጣናዊ ስህተቱ ዛሬም አይማርም። አማሮቹን ማንም ዓለም ሳይሰማ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ ከምድረ ገጽ ዘራቸውን አጠፋቸዋለሁ ብሎ እንደዳከረው ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ስለአማሮቹ ጥፋት የሚያብራራውን መጽሐፍ አፍኖ ከመሰራጨት ሊያስቀረው እየዳከረ ነው።

ያላወቀው ነገር ግን ይሄ ትውልድ በእውቀት የታጠቀ እና የነቃ ነው። ምንንም ነገር ማፈን አይቻልም። እግዚአብሔርም ወንጀለኞችን የሚያጋልጡ እንደ ሙሉቀን አይነት ብላቴናዎችን ከትውልዱ መሃከል አብዝቶ ማስነሳቱን አይተውም።

በእውነቱ ነገሮችን በደንብ ቀረብ ብሎ ለመረመረ እና ላስተዋለ በኢትዮጵያ ምድር የክፋት፣ የዘረኝነት እና የልዩነት ምንጭ ወያኔ ብቻ ነው። እናም የልዩነት መንፈስን የሚያራግበው እርኩስ መንፈስ ይቃጠል ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ይሆን ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው።

ኢትዮጵያንም እግዚአብሔር ይባርካት!
በፍቅር መንፈስም ህዝቧን ይጎብኘው!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!