Happy Ethiopian Newy Year! መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልዎ!

Adwa
አድዋ

በአገርና በሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስቴር ስር፤ ሐምሌ 1973 ዓ.ም. በታተመውና “ደህንነት” በተሰኘ መጽሔት ከገፅ 28 - 38 ከአድዋ ጦርነት በፊት፣ በጦርነቱ ጊዜና ከጦርነቱ በኋላ በጣሊያንና በኢትዮጵያ ወገን የተካሄደውን የስለላ ሥራ አስመልክቶ  “በአድዋ ጦርነት የኢንተለጀንስ ሚና” በሚል ርዕስ ስር የሚከተለውን ጽሁፍ አስፍሯል።

(መስቀሉ አየለ)

ሀ) የጠላት መረጃ

የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቱ ለማድረግ ሲነሳ የራሱን ገንዘብና የወታደሮቹን ደም በብዛት ለማፍሰስ አልፈለገም። ኢትዮጵያን በቀላሉ ለመያዝ ይቻላል የማለት እምነት ያደረበት የኢትዮጵያን የፊውዳላዊ ፖለቲካ ጠባይ በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ ከመገንዘቡ የተነሳ ነበር። የዒጣሊያ ተመራማሪዎች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት በአፄ ቴዎድሮስ ላይ የደረሰው ችግር ለኢጣሊያኖች ከፍተኛ ትምህርት ሆኗል። ኢጣሊያኖች በዝብዝ ካሳ (ዮሐንስ)፣ ዋግሹም ጎበዜና (ተክለጊዮርጊስ 2ኛ) የወሎ መኳንንት ቴዎድሮስን ባይክዱ፣ ለእንግሊዞች መንገድ ባያሳዩና ስንቅ ባይሰጡ ኖሮ የብሪታኒያ ሠራዊት መቅደላ ገብቶ ቴዎድሮስን ማሸነፍ ቀርቶ ላስታ እንኳን ለመድረስ በተሳነው ነበር ብለው አመኑ። ከቴዎድሮስ በኋላ በመሳፍንቱ መካከል ስለቀጠለው ሽኩቻና አለመግባባት በሰሜን ከ“ሳፔቶ”ና ከሌሎች ሚሲዮናዊያን የኢጣሊያ መንግሥት መረጃ ሲያገኝ በመሃልና ደቡብ አገር ደግሞ ኩማሳይና ከጭፍሮቹ እንዲሁም ከ“ነቼኪ” ብዙ ዕውቀት አግኝቷል። መጀመሪያ አሰብ ቀጥሎ ምፅዋ በኢጣሊያ እጅ ከገቡ በኋላ ደግሞ በስመ አገር ጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ኢትዮጵያን በማጥለቅለቃቸው የኢጣሊያ መንግሥት ስለ አገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታዎች ከኛ የበለጠ የሚያውቅ የለም ብሎ ተማመነ።

ለጎጃሙ መስፍን ለንጉስ ተክለሃይማኖትም ድልድይ እንዲሰራላቸው ተብሎ  ከኢጣሊያ መንግሥት የተላከላቸው መሃንዲስ ሳሊምቤኒ በቅርብ አማካሪያቸው ነበር። ሳሊምቤኒ በጎጃም ጠጅና ቆነጃጅት በመማረኩ የኢጣሊያ መንግሥት ቢናደድበትም ከዮሐንስ ከምኒሊክና ከሌሎች መሳፍንት ጋር ስለነበራቸው ጠብም ሆነ ወዳጅነት ብዙ ጠቃሚ መረጃ ሰጥቷል።

የዮሐንስ ቤተ መንግሥት በብዙ የታወቁ የኢጣሊያ መልዕክተኞች ተጎብኝቷል። ከነዚህ መካከል አንቶኖሊ አንዱ ሲሆን ከተቀሩት መካከል ደግሞ ቢያንኪ፣ ኔሪኪኒና ትራቬርሲ ይገኙባቸዋል። እነዚህን መልዕክተኞች ስለ ዮሐንስ የውስጥና የውጭ ፖለቲካ ብዙ ያስጠናቸው የነበረው የነበረው የንጉዙ መሐንዲስ ኢጣሊያዊው  ጃኮሞ ናሬቲ ነበር። ናሬቲ በዮሐንስ ከመቀጠሩ በፊት ከርታታ አናጢ ነበር። ንጉሱ ስራውን ወደው የቤታቸው ግንበኞች፣ አናጢዎችና ወርቅ አፍሳሾች ተቆጣጣሪ አደረጉት። አክብረው ሸልመው፣ ሾመው ቢያስቀምጡት የአንድ ጥቁር ንጉስ አሽከር መሆን ስላላስደሰተው የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ከያዘ በኋላ ይሾመኛል በማለት የጌታውን ምስጢር በየጊዜው ይዘከዝክባቸው ነበር። መሃይሙ ናሬቲ ከኢጣሊያ ንጉስ ኒሻንና ሽልማት በይፋ ሲላክለት ዮሐንስ ለምን ብለው አይጠይቁንም ኖሯል? ናሬቲ ነገር ማቀበሉን ለነገ እንጀራ ማውጫ አስቦ መሆኑን እያወቁ ከቤታቸው ማግለል እንዴት አቃታቸው? አሉላ በአስመራ የሚያልፉትን ኢጣሊያኖችና ከነሱ ጋር የተቀራረበውን ኢትዮጵያዊ ሲጠረጥሩና አንዳንዶቹን ከነዚህም አንዱ ሳሊምቤኒ ሲሆን ሲያሴሩ አጼ ዮሐንስ አማላጅ ሆነው ማስፈታታቸውን የሁል ጊዜ እንቆቅልሽ ነው። ከአሉላ በስተቀር የኢጣሊያ ፍላጎት ምን እንደሆነ የገባው ሌላ የኢትዮጵያ መኳንንት የለም የሚለው የጊዜው የኢጣሊያኖች እምነት ልክ ይመስላል።

አጼ ዮሐንስ በበኩላቸው ኢጣሊያ በምጽዋና በአካባቢው ስለሚያካሂደው ፖለቲካ መረጃ ለመሰብሰብ ሳይሞክሩ አልቀሩም ነገር ግን ያሰባሰባቸው ዘዴና የሰብሳቢዎቹ ስም ለናሬቲና ምጽዋ ለነበሩት የኢጣሊያ ሹማምንት በመታወቁ ብዙ ጠቃሚ መረጃ አላገኙም። ለምሳሌ በምጽዋ በኩል ለዮሐንስ ወይም ለሌላ መስፍን ኢጣሊያኖች ከፍተው ሳያነቡት አንድም ደብዳቤ አያልፍም ነበር። ዮሐንስ ወይም አሉላ እንዲያውቁት የተፈለገ ነገር በደብዳቤው ከተጠቀሰ ደብዳቤውና አድራሹ ከምጽዋ እንዲያልፍ ይደረጋል። ሌላው ደግሞ አንድ ቴዎድሮስ ጂዩርጂዩ የተባለ ኢትዮጵያዊ በምፅዋ በአስተርጓሚነት ለኢጣሊያኖች ይሰራ ነበር። ከትግራይ ብዙ ደብዳቤ ይላክልሃል ተብሎ ተከሶ ለዮሐንስ ወይም ለአሉላ መረጃ ይልካል ተብሎ በመጠርጠሩ ከስራው ተባሯል።

አጼ ዮሐንስ ለብሪታኒያ መንግሥት ደብዳቤዎች ሲልክ የምፅዋ አስተዳዳሪዎች ይሰሙታል። የብሪታኒያ መንግሥት ላለማስቀየም ሲሉ ከፍተው አያነቧቸውም ግን በለንደን የሚገኘው የኢጣሊያ አምባሳደር ወደ ብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄዶ ጉዳዩን ምንድን ነው ብሎ ይጠይቅና ቁም ነገሩ ወዲያው ይነገረዋል። ትንሽ ቆይቶም የዮሐንስ ደብዳቤና የብሪታኒያ መንግሥት መልስ ቅጂዎችን ወደ ሮማ እንዲያስተላልፍ ይሰጡታል። የብሪታኒያ መንግሥት ለኢጣሊያ በኢትዮጵያ መስፋፋት ድጋፉን ያሳየው በዚህ ብቻ አልነበረም። የንግስት ቪክቶሪያን መልስ እንዲያደርስ የተላከው ሻምበል ሐሪሰን ስሚዝ የኢጣሊያንን ዕቅድ ለዮሐንስና ለአሉላ እንዳያወጣ ስለተፈራ ይቀርቡለታል ለተባሉ ጥያቄዎች ሁሉ በምፅዋ የኢጣሊያ ሹማምንት የሚሰጠውን መልስ ተደጋግሞ ከተነገረው በኋላ ነበር መንገዱን እንዲቀጥል የተፈቀደለት። ለዮሐንስ አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች የሚገዙ ነጋዴዎች በኢጣሊያኖች በጣም በመጠራጠራቸውና በዓይነ ቁራኛ በመጠበቃቸው ምጽዋ ውስጥ ብዙ ችግር ይደርስባቸው ነበር። ከሃያ ሺ ጠገራ ብር በላይ የሚያወጡ ለዮሐንስ የተገዙ ዕቃዎች ይዞ በምፅዋ ወደ መቀሌ ማለፍ ስለፈራ በዜይላ አድርጎ አዲስ አበባ ደረሰ። ወደ ትግራይ ለማለፍ በመዘጋጀት ላይ እንዳለ አንቶኒሊ ነገሩን በመስማቱ  እስጢፋኖስን አስይዞ ለዮሐንስ የገዛቸውን እቃዎች በሙሉ ለሱ እንዲሸጥለት አስገደደው። ዮሐንስንና ምኒሊክን ይበልጥ ለማቀያየምና ለማቆራረጥ ዓላማው ነበርና አንቶኒሊ የዮሐንስን ዕቃዎች በሙሉ ከኢጣሊያ ንጉስ የተላከ ገፀ በረከት በማስመሰል ለምኒሊክና ለጣይቱ ሰጠ። የእስጥፋኖስ የግል ሻንጣዎች ሲፈተሹ አንድ በቱርክ አገር የታተመ ቦስፎ ኤጂፕሲየን የተባለ ጋዜጣ ተገኘበት በጋዜጣው ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ስለምታካሂደው፣ በተለይ ደግሞ  እየጠበቀ ስለ ሄደው የኢጣሊያ መንግሥትና የምኒሊክ ወዳጅነት ዘርዘር ያለፅሁፍ ጽሁፍ ስለነበር ጋዜጣው ተወረሰ። እስጢፋኖስ ጉዞውን አቋርጦ በመጣበት መንገድ ወደ ምጽዋ እንዲመለስ ተደረገ። ጥብቅ ክትትል  እንዲደረግበት አንቶኒሊ ወደ ምፅዋ ቴሌግራም አስተላለፈ።

ምኒሊክ በአንቶኒሊ ላይ የነበራቸው እምነት በመጨረሻ ወደ ውጫሌው ውል አደረሳቸው። የውሉ ረቂቅ ሮም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ መምጣቱን በደንብ ሳይገለፅላቸው ትርጉሙን አዘጋጅቶ ካማካሪዎቻቸው ጋር ሳይነጋገሩበት አስፈረማቸው። የአማርኛው ቅጂ ብቻ ተነቦላቸው 17 አንቀፅ የሚረባ ጉዳይ ስላላዘለ ደጋግመው ለምን ያስፈልጋል ይቅር ቢሉት ቢጨመርስ ምን ይጎዳል ስላላቸው በውሉ እንዲያሠፍረው የፈቀዱለት በነበረው የቀረበ ግንኙነት ነበር። 

ምኒሊክ አንቶኒሊ የተጠቀመባቸውን ያህል የመሳሪያ ስጦታ እንዲያስመጣላቸው አድርገው ከተጠቀሙበት በኋላ ለክብራቸውና ላገራቸው ነፃነት ሲሉ የውጫሌን ውል ለመሰረዝ ወሰኑ። እ.ኤ.አ በየካቲት 1893 ውሉ ውድቅ መሆኑን በይፋ ለዓለም አስታወቁ። የኢጣሊያ መንግሥትም የአንቶኒሊ ፖለቲካ የተባለው እቅድ የከሸፈበት ምክንያት በምንሊክ በቃል አለመርጋትና ከሐዲነት ነው ብሎ አስተባበለ። በ 17ኛው አንቀፅ ሳቢያ ያገኘው መብትና ስልጣን ግን በምንሊክ ቃል ብቻ አይቀርምና በጦር ኃይል ለማስከበር ተዘጋጀ።

የኢጣሊያ ወታደሮች መረብን ተሻግረው ትግራይን መውረራቸውን ምኒሊክ እንደሰሙ ክተት አወጁ። እ.ኤ.አ በመስከረም 1895 የምንሊክ ሠራዊት ወደ ሰሜን ጉዞ በመጀመሩ የኢጣሊያ መንግሥት ከመጠን በላይ ተደስቶ ምንሊክ ትግራይ ደርሰውለት በጦር ሜዳ አሸንፎ ኢትዮጵያን በቀጥታ ለመያዝ ቸኮለ።

በ 17ኛው አንቀጽ ምክንያት ምኒልክ የውጫሌን ውል በመሰረዛቸው አንቶኒሊ ወደ አገሩ ቢመለስም በአዲስ አበባ ብዙ የኢጣሊያ መንግሥት ወኪሎች ቀርተው ነበር። አንደኛው ኮፑቺ የተባለው ወኪል ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ የኖረና የምኒልክን ሠራዊት ጥንካሬ በየጊዜው የሚገመግምና ምኒልክ ከሌሎች መሳፍንት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመከታተል ብዙ ዘገባ ያስተላለፈ ነበር። ዮሐንስ ገና በህይወታቸው ሳሉ አንድ ጊዜ የከዳ ሁለተኛም ይከዳልና በመሳፍንቱ እርስ በእርስ አለመጣጣም ተጠቅመን አሁኑኑ ኢትዮጵያን በኃይል እንያዝ እያለ የኢጣሊያንን መንግሥት ለመገፋፋት ሞክሯል።

ለእርቅና ለስምምነት የሚሆኑ ሃሳቦችን አምጥተናል በማለት በዚሁ እ.ኤ.አ በ1893 የገቡት ኮሎኔል ፒያኖና ዶክተር ትራቪርሲ ዋና ተልዕኮአቸው የምኒልክን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ለይቶ ማወቅ ነበር። ሁለቱም መልዕክተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተቀመጡና ለምንሊክ የውስጥና የውጭ ፖለቲካ እንግዶች ባለመሆናቸው እ.ኤ.አ በህዳር 1894 ለኢጣሊያ መንግሥት ያቀረቡት ዘገባ የማሸነፍ እምነቱን አረጋግጦለታል። በነዚህና በሌሎች ወኪሎቻቸው ምንሊክ ወደ ሰሜን መጓዝ እስከ ጀመሩበት ጊዜ ድረስ የሠራዊታቸው ብዛት፣ የመሳሪያቸው ጥራትና መጠን ለኢጣሊያኖች ገልጾ ነበር።

የኢጣሊያ መንግሥት ምኒልክንና መንገሻን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹን መሳፍንትም በቅርብ ተከታትሏል። በሐረር የቢየነንፌልድ ኩባንያ የስለላ ተግባሩን ቀጠለ። በሳኮኒ ሞት ምክንያት የሐረር ቅርንጫፍ ኃላፊ ሆኖ የተተካው ፌልተር የራስ መኮንን ጥሩ ወዳጅ ሆነ። ራስ መኮንን ፌልተር የኢጣሊያ መንግሥት ወኪልና ሰላይ መሆኑን አውቀዋል። የፌልተር ተልዕኮ መኮንን ምን ፍንጭ እንደሰጡት ለጊዜው አይታወቅ እንጂ እሱ እንዳግባባቸው እስከ አድዋ ጦርነት ዋዜማ ድረስ ጨርሶ አልተጠራጠረም። የኢጣሊያ መንግሥት ከምኒሊክ ጋር ገና ከመጋጠሙ በፊት እንዳሸነፈ ያመነበት ዋናው ምክንያት ይህ ነበር።

በወሎና በአውሳ አውራጃ የኢጣሊያ ወኪልና ሰላይ ፔርሲኮ ሲሆን የርሱ ረዳትና አማካሪ ደግሞ አብዱራህማን ቤን ዮሱፍ የተባለ ኢትዮጵያዊ ነበር። አንቶኔሊ ከአውሳ ባላባቶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥሮ ነበርና ፔርሲኮ የስለላና የማስከዳት ተግባሩን ለመፈፀም የጣረው አውሳ ተቀምጦ ነበር። በአብዱራህማን አማካኝነት ፔርሲኮ ከብዙ የአፋርና የሶማሊያ ባላባቶች ጋር ተዋውቆ በሃይማኖት ሳቢያ ኢትዮጵያውያንን  የከፋፈለ መስሎት ነበር። እንዲሁም በአብዱራህማን በኩል ከወሎው ገዥ ከራስ ሚካኤል ጋር ብዙ ጊዜ ስለተገናኘ ሚካኤል ምኒሊክን ይክዳሉ ብሎ አምኗል።

ሳሊምቤኒ ከጎጃም ከወጣ በኋላ ቋሚ የሆነ የኢጣሊያ ወኪል በደብረ ማርቆስ ባይኖርም ከተክለሃይማኖት ጋር የነበረው ግንኙነት አልተቋረጠም። በደብረ ማርቆስ ባለፉት ካንዳንድ የኢጣሊያ ዜጎችና እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን መልዕክተኞች ባገኙት መረጃ ተክለሃይማኖት ምኒልክን በመፍራታቸውና በምኒልክ ትልቅነት በመቅናታቸው ከጎኑ እንደማይሰለፉ የኢጣሊያ መንግሥት ተስፋ አድርጓል። የሽሬው ገዢ ራስ ሃጎስ ለመንገሻ ታማኝ በመሆናቸው በኢጣሊያኖች ቢታወቅም ሚኒልክን ይወጉልናል ብለው ተማምነዋል።

በመኮንን የሚመራው ጦር አምባላጌ ላይ መሽገው የነበሩትን ኢጣሊያኖች እ.ኤ.አ በታህሳስ 1895 ሲደመሰስ እንኳ መኮንንና መንገሻ ወደ እኛ ይዞራሉ የሚለው የኢጣሊያ እምነት ምንም አልቀነሰም። እንዲያውም ፌልተር ከሐረር በአስቸኳይ ተጠርቶ  በምፅዋ በኩል ወደ መቀሌ ተላከና በአንድ በኩል ምኒልክ የኢጣሊያንን መንግሥት የበላይነት እንዲቀበሉ በሌላ በኩል ደግሞ መኮንን እንዲከዱ ለማድረግ ብዙ ጥረት አደረገ። መቀሌ ውስጥ የተከበቡት ኢጣሊያኖች ከሰንደቅ አላማቸውና ከመሳሪያቸው ጋር ወደ አዲግራት እንዲመለሱ ሚኒልክ ቢፈቅዱም የኢጣሊያ መንግሥት ፈርተው ያደረጉ መስሎት ወዲያውኑ በማከታተል ያቀረበላቸው የሰላም ውል የሳቸውን ክብርና የኢትዮጵያን ነፃነት ጨርሶ የሚገፍ ሆነ። ባራቲየሪ የሰላም ውል ረቂቅ እያስያዘ ተራ በተራ የጦር መኮንንኖቹን የላከው ምኒልክ ያቀብሉታል በማለት ሳይሆን የሚኒልክን ሰፈርና የሠራዊታቸውን ወኔ በየ እለቱ ለመገምገም ሳይሆን አይቀርም። እ.ኤ.አ በ1896  በየካቲት ወር መጀመሪያ ገደማ ሚኒልክ መቀሌን ከለቀቁ በኋላ ግን በየት አቅጣጫ እንደሚያመሩ ባልታወቀበት ጊዜ ወደ ሰፈራቸው የላከው ሻለቃ ሳልሳ ዓላማው ውል ለመዋዋል ሳይሆን ወደ አዲግራት ያመሩ እንደሆን ለማወቅና የሠራዊታቸውን ስንቅ ሁኔታ ለማጥናት እንደነበረ አያጠራጥርም።

በምኒልክ በኩል ደግሞ የኢጣሊያኖች ኃይል ብቻ ሳይሆን አሰፋፈራቸውና የጦር ዕቅዳቸው ሁሉ በደንብ የታወቀ ይመስላል። ሚኒልክም ሆኑ መንገሻና አሉላ መረጃውን ያገኙት ከነ እገሌና እገሌ ነበር ለማለት የሚያስችል ምንጭ እስካሁን ባይገኝም፤ ባራቲየሪ ደጋግሞ እንደፃፈው ሚኒልክ አንዳችም ነገር አላመለጣቸውም። ለዚህም ነው ኢጣሊያኖች እንደጠበቁት ሚኒልክ በዕዳጋ ሐሙስ አድርገው ወደ አዲግራት ያላመሩት። እስካሁን ድረስ የሚኒልክ ኃይልና የጦር ስልት ያላሰጋው የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒም የሚኒልክ ወደ ዓድዋ ማዝገም የኢጣሊያንን ጦር ከየምሽጉ ለማስወጣት የታቀደ ዘዴ መሆኑን መረዳት ጀመረ።

እ.ኤ.አ በ1895 ጥር ወር መጨረሻ እስከ ዓድዋ ጦርነት ዕለት ድረስ ሁለቱ ወገኖች የእያንዳንዳቸውን ጦር ሠፈር በብዙ መንገድ ሰልለዋል።  በመሰለል ብቻ ሳይወሰኑም አሳሳች መረጃዎችንም ነዝተዋል። የሚኒልክ ጦር ከመቀሌ ተነስቶ ዓድዋ እስኪገባ ድረስ የኢጣሊያ መኮንኖች መጠነኛ ርቀት በመጠበቅ ተከትለውታል። መረጃቸውንም በመስተዋት በማንፀባረቅ እስከ ባራቲየሪ ሠፈር ድረስ አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ከሚኒልክ ጦር ጋር ከሚጓዙ ሠዎች መካከል ኢጣሊያኖች የተማመኑባቸው ሰላዮቻችን ናቸው የሚሏቸው ነበሩ። የነዚህ ሠዎች ተግባር የየዕለቱን ሁናቴ ከማስተላለፋቸውም በላይ የሚኒልክ የጦር ዕቅዶች ምን እንደነበሩ ማወቅም ነበር። በስም ከታወቁት አንዱ ፊታውራሪ ገብረዝጊ ነበሩ። በገብረዝጊ ይላክ የነበረው መረጃ ምኒልክ አሉላን መረብን ተሻግረው አዲኳላ የነበረውን የኢጣሊያኖች ምሽግ እንዲወጉ ልከዋቸዋል፤ ራሳቸውም ከጦራቸው ጋር ይከተላሉ የሚል ነበር። ባራቲየሪና ጄነራሎቹ ምኒልክ አዲኳላ ዞረው ሊከቡን ነው ከአስመራ ጋር ያለንን መገናኛ ሊቆርጡብን ነው ብለው ስለሰጉ ዓድዋ ላይ ለመዋጋት ከተገደደበት ዋናው ምክንያት ይህ ነበር።

ኢጣሊያኖች የኛ ሰላዮች ናቸው ካሏቸው ሌሎች ሠዎች ብዙ ዓይነት መረጃ በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ ደርሷቸዋል። አብዛኞቹ ሚኒልክን ዓድዋ ጦርነት ላይ መገፋፋት ብቻ  ሳ ይሆን የማሸነፍ እምነታቸውን የሚያጠናክሩ ነበር። ከሚኒልክ ሠፈር ደጋግመው የደረሱ መረጃዎች የሚኒልክ ጦር ስንቁን ጨርሶ ወደ ዝርፊያ ገብቷል በዝርፊያ ምክንያት እርስበርሱ እየተጨራረሰ ነው። በሠፈሩ ወረርሺኝ ገብቶ ወታደሩ እየረገፈ ነው የሚሉ ነበር። የነዚህ መለእክቶች አብሳሪዎች እነማን እንደነበሩ እስካሁን ከተገኙት ምንጮች ለማወቅ ያስቸግራል የምኒልክ ፀኃፊ የነበሩት ግራዝማች ዮሴፍ ለፈረንሳዊው ሞንዶን ቪያዩት ወዲያው ከአድዋ ጦርነት በኋላ ሲፅፉ መረጃዎቹን ለኢጣሊያ የጦር መሪዎች የሰጠ አንድ እጁ ሽባ የነበረ ሠው ነው ብለዋል።

ክሪስፒ በኢጣሊያ ምክር ቤት በተጠየቀበት ጊዜ እኛ አላጠፋንም ያጠፋው ምኒሊክ ነው ብሏል። አንቶኔሊ በ 17ኛው አንቀፅ ላይ ያጭበረበረው እንደማጭበርበር ሳይቆጠር ሚኒልክ ራሴንም አገሬንም ለባርነት አሳልፌ አልሰጥም ማለታቸው በክሪስፒና በባራቲየሪ ዓይን ክህደት ሆነ። በክሪስፒ አስተያየት ሚኒልክ የውጫሌ ውል ያፈረሱት በአገርና በነፃነት ፍቅር ሳይሆን በኢጣሊያን ጠላቶች(ፈረንሳዮችን ማለቱ ይሆናል)ቀስቃሽነት ነው። ምኒልክ መንገሻ መኮንን፣ ስብሐት ሐጎስ ተፈሪንና ሌሎችም ሁሉም በቃላቸው የማይረጉ፣ ለኢጣሊያ መንግሥት የሰጡትን ተስፋ የረሱ ናቸው ተብለው ተወቅሰዋል፣ ተሰድበዋል። ይህ የሚያሳየው ኢጣሊያኖችና፣ እንዲሁም ሌሎች ኤሮጳውያን በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን ንቀት ምንኛ እንዳሳሳታቸው ነው። የኢጣሊያኖች ስህተት ሞኝ አገኘን ሲሉ በመሞኘታቸው ነው፡ አንድ ቀንደኛ ፋሺስት የአድዋ ጦርነት ጥናቱን “በውትድርናችንና በዘራችን በመመካታችን፣ በተለይ ደግሞ ከፊታችን ስለነበረው ጠላታችን ምንም ነገር ባለማወቃችን የነዚያን ብጭቅጭቅ ለባሽ ሕዝብ እውነተኛ ዋጋ ለመገመት አልቻልንም። ብጭቅጭቅ ልብሳቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ያለው የውትድርና ጠባያቸውን ደብቆት ነበርና” ሲል ደምድሟል።

ለ) የወገን መረጃ

ከዓድዋ ድል በኋላ ከአፄ ምኒልክ ሠራዊት ያመለጡት ጥቂት የኢጣሊያን መኮንኖችና ወታደሮች “ሱማትራ” በምትባለው መርከብ ተጭነው እ.ኤ.አ መጋቢት 24 1888 ዓ.ም ናፖሊ ሲገቡ በጦርነቱ ጊዜ የደረሰውን ሁሉ በውነተኛ መልኩ ይገልጡ ጀመር። “ያየ ይናገር፣ የቀበረ ያርዳ” እንዲሉ የጦርነቱ ወላፈን የገረፋቸው ሠዎች የሰጡት ምስክርነት በየፈርጁ ተሰብስቦ ቢሆን ኖሮ የኢጣሊያኖችና ተቆርቋቂዎቻቸው ስለ አድዋ ድል ከጊዜ በኋላ የለጣጠፉት የሐፍረት ምክንያት ከታሪክ ገፅ እየተቀረፈ እንደሚረግፍ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያ አሸነፈች ሲባል የሞራል ድል የተመቱት ኢጣሊያኖች ብቻ ሳይሆኑ በዚያን ጊዜ አውሮፓን “ማን ያህልሻል” “ምን ተስኖሽ” እያሉ የካቡ አዝማሪዎችና የጣሊያንን ወራሪ ሠራዊ “ባሻህ ውረድ” በማለት የሸኙ አጫፋሪዎች ሁሉ ነበሩ።

ዓድዋ ላይ በዱብ ዕዳው እንደተደናገጡ አውሮጳውያን እውነት እውነቱን ተናገሩ። በኋላ ግን ልባቸው መለስ ሲል የኢጣሊያ ወራሪዎች ውርደት የነሱም መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያን ድል ለማወየብና ታሪኳንም ለማድበስበስ ፀሃፊዎቻቸው ያላውጠነጠኑት ዘዴ አልነበረም። በተለይም የታሪኩን ሐቅ ለማዛባት “ኢትዮጵያ ለምን አሸነፈች?” በማለት ፈንታ “ኢጣሊያኖች ለምን ተሸነፉ?” በሚል ጥያቄ ላይ በማተኮር:-

➢ የሃበሻ ሠራዊት በብዛቱ ዋጣቸው

➢ የኢጣሊያን ሠራዊት ወደ ዓድዋ ሲያመራ መንገድ ተሳሳተ

➢ በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ አንድ መቶ ከሠላሳ ሦስት የመስኮብና ስድሳ የፈረንሳይ መኮንኖች ስለነበሩ ስትራቴጂውን የመሩት እነሱ ነበሩ።

በማለት እውነቱን ለማፋለስና ገመናቸውን ለመሸፈን ይጥሩ ነበር። ይኸሁሉ ሀበሻ ፈረንጅን በጀግንነቱና በጦር ስልቱ አሸነፈ እንዳይባል ነበር።

እኛ ግን በኢትዮጵያዊነታችን ያንን ሁሉ ወሬ ተመልክተን ተጨባብጠን ሁኔታ ከትክክለኛው ምክንያት ጋር ለማገናዘብና እውነቱን ለመሳት ስንሞክር የሚገጥመን የታሪክ ክስተት ሌላ ነው። የዓድዋ ድል በሠራዊት ንቃት በመሳሪያ ብዛትና በአመራር ጥራት ብቻ የተገኘ ሳይሆን የጀግንነትና የመስዋዕትነት ሚናም ተጫውተዋል። ከሁሉም የሚያስደንቀው ግን በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የኢትዮጵያ የመረጃ ድርጅት በኢጣሊያ ላይ መረቡን ዘርግቶ ለድሉ ያደረገው አስተዋፅዎ ነበር።

የመረጃ ስራ ህቡዕ ስለሆነ በታሪክ ጉልህ ቦታ ተሰጥቶት አይታይም ነበር። የመረጃ ሠራተኞች በሙያቸው ጠባይ ምክንያት ስማቸው ሳይጠራ ማዕረጋቸው ሳይታወቅ ሲያልፉ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ በይፋ ይታወቁ ይሆናሉ። ሌሎቹም ከጊዜ በኋላ ለመጪው ትውልድ ስም አውርሰው ይሆናል። በአጠቃላይ ህቡዕ ሠራዊት ግን መኖሩ ሳይታወቅ፤ አለመታወቅ መመሪያው በመሆኑ ሠይፍ መዝዞ ገዳይ ሳይል ያልፋል።

በዓድዋ ጊዜ ይህ ህቡዕ ሠራዊት ኢጣሊያንን ምን ያህል አስቸግሮት እንደነበረና በተልእኮ ላይ የተያዘውም ቢሆን ሕይወቱን ከምንም ሳይቆጥር እንዴት መራሩን ፅዋ በጸጋ እንደተቀበለ ያዩ ኢጣሊያኖች ከአድዋ በኋላ ከሰጡት ምስክርነት አንዳንዱን እንጠቅሳለን።

የዓድዋ መነሻ ውጊያ ሁለት ቀን ሲቀረው የጦር ኃይሉ ጀነራሎች ከፍተኛ ውይይት ለማድረግ አዲግራት ውስጥ በተሰበሰቡ ጊዜ የበላይ መሪያቸው ጀነራል ባራቲየሪ ስለጦር ግንባሩ ጠቅላላ ሁኔታ ገለጣውን በማጠቃለል “የሁለት ቀን ስንቅ ቀርቷል። ከኋላ መንገዱ ተዘግቷል። ምርጫው መዋጋት ወይም ማፈግፈግ ነው። ያለን መውጫ አዲቀይህ ብቻ ነው። ምን ትመክራላቹ?” ብሎ መድረኩን ለውይይት ከፈተ። በዕድሜ ከሁሉም ያንስ የነበረው ጀነራል ዳቦርሜዳ “ወደኋላ ማለትን አገራችን አትቀበለውም። ሁለትም ሶስትም ሺህ ሠው ቢሞትብንም ተዋግተን እንሸነፍ እንጂ አናፈገፍግም” አለ። ጀነራል አረሞንዲና ጀነራል አልቤርቶኒ ይህንኑ ሃሳብ ደገፉ።

በእድሜ የሁሉም ታላቅ የነበረው ጄነራል ኤሌና የተሰነዘሩትን አስተያየቶች በጥሞና ካዳመጠ በኋላ “የደረሱን መረጃዎች ምን ይላሉ?” ብሎ ጥያቄ አቀረበ። እዚህ ላይ ታሪኩን የተረከው ሠው የባራቲየሪን መልስ መቅደምና የራሱን አስተያየት ጣልቃ በመግባት “ባራቲየሪ የኛን ብር በልተው በማይጠግቡ መረጃ አቅራቢ ሃበሾች ተከበዋል። ሠዎቹ ውስጥ ውስጡን ለጠላት እየሰለሉ ይጫወቱብናል” በማለት እውነቱን አጋልጧል።

አሁን ባራቲየሪ ለኤሊና የሰጠውን መልስ እንስማ

“ከምኒሊክ ሠራዊት አንዱ ሲሶ ከድቶ እግረ መንገዱን አክሱምን ዘርፎ ወደ ሽሬ ዘልቋል። አንዱ ሲሶ ደግሞ ወደ ሸዋ ተመልሷል። ንጉስ ተክለሃይማኖትና ራስ ሚካኤል ነገሩ እስኪለይለት አንቀሳቀስም ብለዋል የሚል መረጃ ደርሶናል”

ሲል መልስ ይሰጠዋል። ጄኔራል ኤሊና ይህን መልስ ሲያገኝ “እንግዲያውማ የሚሻለው ያለንን ኃይል አስተባብረን ጠላትን መምታት ነው” ይልና የሌሎቹን ጄኔራሎች አስተያየት ያጠናክራል። ጀነራል ባራቲዬሪ “ሌላ የምጠብቃቸው መረጃዎች አሉ ሲደርሱኝ መጨረሻውን ውሳኔ አስታውቃችኋለው” ብሎ “ዛሬ ማታ ራታችን አድዋ ላይ ነው” በሚለው እንደ ተረት ሲጠቀስ በሚኖረው ዓረፍተ ነገር ውይይቱን ይዘጋል። ጄኔራል ኤሊና አሁንም የመረጃው ነገር ስለከነከነው ወደ  ጄኔራል ጋሊያኖ መለስ ብሎ በጆሮው “ይህ የራቱ ነገር ምን ይመስልሃል” ብሎ ሲለው “ጄኔራል እንዲህ ካሉ ጠላት አድዋን ለቆ  መሄዱን በእርግጥ ቢደርሱበት ነዋ” ብሎ መለሰለት። በዚሁ ጉባኤው ተበተነ።

በማግስቱ ሲጠበቅ የነበረው “ዓድዋ የሚገኙት ሃበሾች በየድንኳናቸው ተኝተው ያንቀላፋሉ” የሚለው መረጃ ደረሰ። መረጃው የተቀናበረው በምኒሊክ ድንኳን ውስጥ መሆኑን ሳይጠረጥር፣ የላከው ሠው ምኒልክ ጦር ሠፈር ገብቶ መውጣቱ ብቻ ሙሉ ዕምነት ስላሳደረበት ጄኔራል ባራቲዬሪ የዓድዋን ውጊያ ከፈተ።

እንደ እውነቱ ከሆነ በዚያች ሌሌሊት በኢትዮጵያ ሠፈር ማንም አልተኛም። ቃፊሩም አድፍጦ ይጠብቃል፤ ሠራዊቱም በተጠንቀቅ ላይ ነበር። በማለዳ ኢጣሊያኖች የተኮስኩት የመጀመሪያ ጥይት የራሳቸውን የጦር መርዶ የሚያበስር መሆኑን አያውቁትም ነበረ። በእውነቱ የባራቲዬሪ የመረጃ ማኅደር “ከባድ ምስጢር” የሚል ምልክት ተደርጎበት እንደሆነ ምስጢርነቱ ለኢጣሊያኖች እንጂ ለኢትዮጵያውያን አልነበረም። የባራቲዬሪ አዕምሮ በእኛ ሠዎች እጅ ወድቆ ነበር ማለት ነገሩን ማጋነን አይሆንም። ዓድዋ ላይ የመረጃው ቅድመ ውጊያ ለኢትዮጵያ ጀግኖች ሰፊውን የድል ጥርጊያ በመክፈት አስደናቂ ሚና ተጫውተዋል ማለትም ታሪካዊ ሁነት ነው። የወራሪው ተቆርቋሪዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ድል የተገኘው በሠራዊት ብዛት፣ በጠላት ስህተት፣ በውጪ ዕርዳታ ወዘተ . . .  ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎችን ቀድሞ በማወቅና ጠላትን ወጥመድ በማስገባት ኢትዮጵያውያን ባሳዩት የስልት ብልጫ ጭምር ነበር።

የኢትዮጵያ ጠላቶች በተለይም የሠራዊቱን ክንድ የቀመሱት ኢጣሊያኖች በኢትዮጵያ የመረጃ ድርጅት ላይ ያላቸው ጥላቻ መጠን የለውም። ሙያውን ሲያሳንሱ ወታደራዊ መረጃ ማለት ይቅርና በተለመደው አነጋገር “ስለላ” ለማለት እንኳ ይከብዳቸዋል። በኢጣሊያኖች አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ወታደራዊ መረጃ አባል የሚባል ነገር የለም። ይህን ተግባር ለሚፈፅሙ ሠዎች የሚሰጧቸው ቅፅል “ወንበዴ” “ከሃዲ” “ወሬ አቀባይ” ወዘተ . . . ነው። እንኳን ለኢትዮጵያ የሚሰሩትን ለራሳቸው አገልግሎት የቀጠሩአቸውንም ቢሆን “ወሬ አቀባዮች” ከማለት በተሻለ ስም አይጠሩአቸውም ነበር። ምነው ቢባል፤ ሀበሻ ጥሬ ወሬ ማቅረብ ነው እንጂ ቅንብሩማ የነባራቲዬሪ ድርሻ ነውና።

በዓድዋ ጦርነት ላይ የኢትዮጵያ መረጃ የተጫወተው ሚና የጄኔራል ባራቲዬሪን አስተሳሰብ በማናጋት ብቻ አልተወሰነም፤ በጦር ሜዳውም ላይ እስከ መጨረሻው ደቂቃ የጠላትን የውጊያ አመራር አቃውሷል። ከዚህ አንፃር፣ ከሁሉም ይልቅ የመረጃውን የመጨረሻ የበላይነት የሚያንፀባርቀው “ሊዚርቺቶ ኢታሊያና” (የኢጣሊያን ሠራዊት)የተባለው መጽሔት እ.ኤ.አ በሚያያዝያ  ቀን  1888 ዓ.ም ካሳተመው ረጂም ደብዳቤ የሚገኘው ፍሬ ነገር ነው።

አስተውል፣ ዕለቱ ሰንበት፣ ጊዜው ማለዳ፣ ቦታው አድዋ ቀኑ ታሪካዊ ነው እነሆ አልቤርቶኒ፣ ዳቦርሜዳ፣ አሪሞንዴ እነዚህ ሶስት ጀነራሎች የተሰጣቸው ዓላማ ራዕዩ  የተባለውን ኮረብታ  ተባብረው መያዝ ነው። አንዱም ብርጌድ ጊዜውን ጠብቆ የተባለው ቦታ ደርሶ  የታዘዘውን ተግባር አልፈፀመም፣ ሦስቱም ብርጌዶች ጎሕ ሲቀድ ውጊያውን እንዲጀምሩ ታዝዘው ነበር። አልቤርቶኒ ተኩስ ሊከፍት አስራ ሁለት ሠዓት ተኩል ይሆናል። አሪሞንዲ በበኩሉ ወደ ጦር ሜዳ የገባው ባልታወቀ ምክንያት በሶስት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ላይ ነው። ዳቦርሜዳ ደግሞ መዋጋት የጀመረው እስከ አምስት ሠዓት አርፍዶ ነው።

ባባራቲየሪ ማኅደር ከተሰገሰገው መረጃ አንዱ ረቢ አርአየኒ እና ኪዳነ ምህረት በተባሉት ኮረብታዎች ላይ የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ጦር ሠፍሯል የሚል ስለነበረ ፡ ዳቦርሜዳ ሲሆን በድብደባ ወይም በኃይል ረቢ አርአየኒን እንዲይዝ፣ አልቤርቶኒም ኪዳነ ምህረትን በዚሁዘዴ ውንዲመታ፣ አሪሞንዲ ደግሞ መካከሉን በስላች ገብቶ የዳቦርሜዳንና የአልቤርቶኒን ብርጌዶች በማገናኘት እንዲረዳ ነበር። ጉዞ ው ሲጀመር ዳቦርሜዳ ረቢ አርአየኒን በግራው ትቶ በማሪያም ሸዊቶ አምባ ስር ሸለቆውን እየተከተለ በመዞር ከረቢ አርአየኒ ይርቃል። “ምናልባት ይላል ደራሲው መንገድ ጠቋሚዎች አታለው ይሆናል . . .  እነሱም ልክ በዚያን ጊዜ ከመቅፅበት ተሰውረው አመለጡ . . .”

በነገራችን ላይ አልቤርቶኒም ያዝ የተባለውን የኪዳነ ምህረትን ኮረብታ ስቶ ለመያዝ ከታቀደው ከራዕዩ ተራራ በመራቅ ላይ ነው። አሪሞንዲ ደግሞ ወደ ራዕዩ ይገሰግሳል። “አውቆ ይሁን ተመርቶ አይታወቅም” ይላል ደራሲው። እንግዲህ የዓድዋ ዕለት፣ “በተባለው ቦታ በታሰበው” የኢጣሊያን ብርጌዶች በመንገድ ጠቋሚዎች ምክንያት ለታላቁ ቀጠሮ ሳይደርሱ ቀሩ። መንገድ ጠቋሚዎቹ ግን ዓላማቸው መሟላቱን ከኢጣሊያን ጀነራሎች በፊት አውቀውት ስለነበረ  መልዕክታቸውን ፈፅመው ወደ መንደራቸው ተመልሰዋል። ይህ ያልገባው ወይም ያልተዋጠለት ኢጣሊያን ገና “መንገድ መሪዎቹ ወዴት ጠፉ” የሚል ገራገር ጥያቄ በልቦናው ያንገዋልለዋል። ነገሩን ለማሳጠር የዓድዋ ዕለት የኢጣሊያን ሠራዊት “ይመሩ” የነበሩት የኢትዮጵያ የመረጃ ሠዎች ናቸው ማለት ፌዝ አይደለም። ይህንኑ በመገንዘብ ተቆርቋሪዎች ባዕዳን ፀሃፊዎች የኢትዮጵያ የመረጃ ሠዎች የኢጣሊያንን ሠራዊት በዘዴ አሳስተው ገደል በመክተት ለአገራቸው ድል አስገኙ ማለት ውርደት ስለሆነባቸው፤ ዋናውን ጀብዱ በማለባበስ እንዲያው በደፈናው የኢጣሊያ ሠራዊት መንገድ በመሳሳት ተሸነፈ እያሉ ፀፀት የተመላ፣ የእውነት ግማሽ፣ የታሪክ ቅናሽ ከመለፍለፍ ተቆጥበው አያውቁም። ወይ እጅግ መቀነስ ወይ እጅግ ማብዛት እነዚህ ሁለቱ የተሪክ ጠላቶች ሲፈራረቁባት እውነት መልኳን ብትለውጥ እንጂ ጠባይዋን አትስትም።

ከአድዋ መልስ የኢትዮጵያ መረጃ ነገር ሲነሳ ኢጣሊያኖች ያንገበገባቸውና ያራዣቸው ጀመር። በተለይም የካቲት 23 ከተመቱት ምት ሳያገግሙ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ” የመቀሌው አነሰና አሁንም በአዲግራት ሁለት ሺህ የሚሆኑ ሠዎች በእነ ራስ ስብሃት ተከበዋል። እዚያ የነበሩት ኢጣሊያኖች በነአሪሞንዲና በነ አልቤርቶኒ የደረሰውን ጉድ ሰምተው ሳሩም ቅጠሉም ሰላይ ይመስላቸው ጀመር።

ዓድዋ ላይ የኢትዮጵያ የመረጃ ድርጅት በኢጣሊያን የጦር አመራር፣ በውጊያ ግንባርና በጠላት ምሽግ ውስጥ እየገባ ከፈፀመው ተግባር በቀር ከጦርነቱም በፊት የጠላትን እንቅስቃሴ በመከተል፣ ኃይሉን በመገምገምና ፀረ ስለላ ጥንቃቄ በማድረግ ያበረከተው አገልግሎት ለመጨረሻው ድል ወሳኝ እንደነበረ ታሪክ ጸሃፊዎች ያረጋግጣሉ። ይህም በእኛ ደራሲያን ሳይሆን በውጪ ሠዎችና ሰነዶች የተረጋገጠ መሆኑ ታሪኩን ከአድሎ ነፃ በማድረግ ያጠናክረዋል።

የተነገረውንና የተፃፈውን ሁሉ መደርደር ትርፍ ቃል እንዳይሆንብን የአድዋ ድል በአውሮጳ እንደተሰማ ሰኔ 15 ቀን 1888 ዓ.ም በወጣው “ረሹ ዲ.ደ.ሞንድ” በተባለው የፈረንሳይ መፅሄት አልቤር ሐንስ የሚባል ደራሲ ከጻፈው ጥናት ውስጥ ፍሬ ነገሩን በአጭሩ ማስታወስ የኢትዮጵያ የመረጃ ድርጅት ደርሶበት የነበረውን የጥራት ደረጃ ለማስገንዘብ የሚበቃ ይመስለናል።

ሐንስ በትክክል እንዳመለከተው ከአድዋ ጦርነት በፊት የጄኔራል ባራቲየሪ ዕምነት “የሃበሻ ብሔረ ሰቦች ስለ ተቀያየሙና በውስጥ ቅራኔ ሆድና ዠርባ ሆነው ስለሚኖሩ ጦርነቱ ሲነሳ ይፍረከረካሉ” የሚል ስለነበር፤ የኢትዮጵያን ኅዝብ ከግምት በታች በማስቀመጥ በጦርነቱ ጊዜ ተጨባጩን ሁኔታ ማወቅ አስፈላጊ መስሎ  አልታየውም። በዚህ ምክንያት የኢጣሊያን ብርጌዶች ወደ አድዋ እንዲዘምቱ ትዕዛዝ ሲሰጥ በተቀነባበረ ግብረ ኃይል አንድ የተወሰነ ቦታ በቀላሉ ለማስያዝ ከመፈለጉ በስተቀር ወሳኝ ውጊያ ሊገጥመው እንደሚችል አልገመተም። ከባራቲዬሪም ጋር የተሰለፉት ጄኔራሎች ውጊያው እንዲከፈት ሲገፋፉት ስለሚጠበቅባቸው ሁኔታ ከእርሱ የተሻለ የሚያውቁት ምንም ነገር አልነበራቸውም። በዚህ ላይ የጄኔራሉ ዋና መንገድ መሪ በአጉል ጊዜ ጠፍቷል  . . . በአንፃሩ ግን የኢትዮጵያ መረጃ በሚገባ ተደራጅቶ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል። ሚኒልክና የጦር መሪዎቹ በቅድሚያ የኢጣሊያንን ዝግጅትና ዓላማ በሙሉ ደርሰውበታል። ሮማ የሚሰጠው የመንግሥት መግለጫና በኢጣሊያኖች ጋዜጦች የሚወጡት አስተያየቶች ሁሉ እየደረሷቸው ሚሲዮኖች ባሰለጠኑዋቸው ምሁራንና ቋንቋ በሚያውቁ ፈረንጆችም ይተረጉማሉ። እንዲሁም በኤርትራና በምፅዋ የሚኖሩ ታማኝ የውጭ ወዳጆችና በመረጃው ውስጥ የሚሰሩ የአገር ተወላጆች በመርከብ የሚመጡትን የኢጣሊያን ወታደሮች ብዛትና እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እየተከታተሉ ለሚኒልክ ወዲያው ያሳውቁ ነበር። በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን የአገሪቱን አቀማመጥ በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር መውጫ መግቢያውን በጥብቅ እያስጠበቁ ሠርገው ለመግባት የሚሞክሩትን ሰላዮች፣ አጠራጣሪ ተላላፊዎችና ባልታወቀ ምክንያት ወደ ሠፈራቸው የሚመጡትን ሠዎች ሁሉ እየተከታተሉ ያለ ምህረት በመደምሰስ ጥቅጥቅ ያለ መጋረጃ በኢጣሊያኖች ፊት ዘርግተውባቸው ነበር። ኢትዮጵያውያን አልፈው ተርፈው የጠላታቸውን አድራጎትና እንቅስቃሴ በዝርዝር ከመከታተላቸውም በላይ አንዳንድ ምልክቶችንና የሌሉ ሁኔታዎችን አስመስለው እያቀረቡ ኢጣሊያኖችን አሳምነው እስከ መሸንገል ደርሰው ነበር።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!