በአድዋ ጦርነት የመረጃ (Intelligence) ሚና
በአገርና በሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስቴር ስር፤ ሐምሌ 1973 ዓ.ም. በታተመውና “ደህንነት” በተሰኘ መጽሔት ከገፅ 28 - 38 ከአድዋ ጦርነት በፊት፣ በጦርነቱ ጊዜና ከጦርነቱ በኋላ በጣሊያንና በኢትዮጵያ ወገን የተካሄደውን የስለላ ሥራ አስመልክቶ “በአድዋ ጦርነት የኢንተለጀንስ ሚና” በሚል ርዕስ ስር የሚከተለውን ጽሁፍ አስፍሯል።
(መስቀሉ አየለ)
ሀ) የጠላት መረጃ
የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቱ ለማድረግ ሲነሳ የራሱን ገንዘብና የወታደሮቹን ደም በብዛት ለማፍሰስ አልፈለገም። ኢትዮጵያን በቀላሉ ለመያዝ ይቻላል የማለት እምነት ያደረበት የኢትዮጵያን የፊውዳላዊ ፖለቲካ ጠባይ በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ ከመገንዘቡ የተነሳ ነበር። የዒጣሊያ ተመራማሪዎች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት በአፄ ቴዎድሮስ ላይ የደረሰው ችግር ለኢጣሊያኖች ከፍተኛ ትምህርት ሆኗል። ኢጣሊያኖች በዝብዝ ካሳ (ዮሐንስ)፣ ዋግሹም ጎበዜና (ተክለጊዮርጊስ 2ኛ) የወሎ መኳንንት ቴዎድሮስን ባይክዱ፣ ለእንግሊዞች መንገድ ባያሳዩና ስንቅ ባይሰጡ ኖሮ የብሪታኒያ ሠራዊት መቅደላ ገብቶ ቴዎድሮስን ማሸነፍ ቀርቶ ላስታ እንኳን ለመድረስ በተሳነው ነበር ብለው አመኑ። ከቴዎድሮስ በኋላ በመሳፍንቱ መካከል ስለቀጠለው ሽኩቻና አለመግባባት በሰሜን ከ“ሳፔቶ”ና ከሌሎች ሚሲዮናዊያን የኢጣሊያ መንግሥት መረጃ ሲያገኝ በመሃልና ደቡብ አገር ደግሞ ኩማሳይና ከጭፍሮቹ እንዲሁም ከ“ነቼኪ” ብዙ ዕውቀት አግኝቷል። መጀመሪያ አሰብ ቀጥሎ ምፅዋ በኢጣሊያ እጅ ከገቡ በኋላ ደግሞ በስመ አገር ጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ኢትዮጵያን በማጥለቅለቃቸው የኢጣሊያ መንግሥት ስለ አገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታዎች ከኛ የበለጠ የሚያውቅ የለም ብሎ ተማመነ።
ሙሉውን አስነብበኝ ...