የዳንኤል እጮኛ የነፃነት እህት ስትሆን፣ ዓቃቤ ሕጉ የዳንኤል የ20 ዓመት ጓደኛው ነው
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. April 12, 2008)፦ መጋቢት 19 ቀን 2000 ዓ.ም. ከእስር የተፈቱት የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ነፃነት ደምሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለእራሳቸው፣ ስለቤተሰቦቻቸው፣ ስጓደኞቻቸው፣ ስለሥራዎቻቸው፣ ስለእስሩ፣ ስለክሱና የፍርድ ሂደቱ፣ … ሀገር ውስጥ ከሚታተመው እንቢልታ ለተሰኘው ሣምንታዊ ጋዜጣ ቃለምልልስ ሰጡ።
የአቶ ነፃነት ደምሴ እህት ወ/ት የምሥራች ደምሴ የአቶ ዳንኤል በቀለ እጮኛ እንደሆነችና በቅርቡም ተጋብተው ባለቤቱ እንደምትሆን ከቃለምልልሱ ለመረዳት ተችሏል። ከዚህም ሌላ ክሱን በዋነኛነት ይመራ የነበረውና “በሞት ፍርድ ይቀጡልኝ” እያለ ሲከራከር የነበረው ዓቃቤ ሕግ ሽመልስ ከማል ከአቶ ዳንኤል በቀለ ጋር የ20 ዓመት ጓደኛሞች እንደነበሩ በቃለምልልሱ ላይ ይፋ ሆኗል።
አቶ ሽመልስ እና አቶ ዳንኤል ከዩኒቨርስቲ ወደ ሥራ እስከተሰማሩበት ጊዜ ድረስ፣ አንድ ማዕድ አብረው ቆርሰው፣ ያላቸውን ሣንቲም ለሁለት ተካፍለው አብረው በልተውና፣ አብረው ጠጥተው ከኢትዮጵያ እስከ እንግሊዝ አገር ዘልቀው፣ በአንድ አልጋ ላይ ተኝተው፣ የሆድ የሆዳቸውን ያወሩ ጓደኛሞች ነበሩ። ቃለምልልሱን ያደረገችላቸው ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ስትሆን፤ እንቢልታ ጋዜጣ ያወጣውን ሙሉውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አቀርበነዋል።
አቶ ዳንኤል በቀለ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ዲግሪ ከዚያም የዴቨሎፕመንት ስተዲስ በሚል ፕሮግራም በማስተርስ ፕሮግራም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በመቀጠል ከእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሮ የሚሠጥ ከፍተኛ የትምህርት ዕድል አግኝተው በዓለም አቀፍ ሕግ (International Law) የማስተርስ ትምህርት ተምረዋል።
አቶ ዳንኤል ለዘጠኝ ዓመት ያህል በሕግ አማካሪነትና በጥብቅና ሥራ በ«አበበ ወርቄና ጓደኞቹ» የሕግ ቢሮ ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከዚያም ወደ ሲቪል ማኅበረሰቡ ዘርፍ ተሠማርተው በመጨረሻ አክሽን ኤይድ (Action Aid) ዓለም አቀፍ ድርጅት የፖሊሲ ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።
አቶ ነፃነት ደምሴ በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ተመርቀዋል። ከዚያም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በረዳት ዳኝነት የተወሰነ ዓመት ከሠሩ በኋላ ለትምህርት ወደ ኦስትሪያ በመሄድ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። እንደተመለሱም ከመሥራቾቹ አንዱ በሆኑበት (Organization Social Justice in Ethiopia) በተባለው ሲቪል ማኅበር ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አቶ ዳንኤልና አቶ ነፃነት በምርጫ 97 እና ከዚያ በኋላ በተከሰተው አገራዊ የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ እንደማይነጣጠሉ ሆነው የሁለቱም ስም በአንድ ላይ ሲነሳ ቆይቷል። ጓደኝነታቸው የጀመረው ግን ከምርጫ 97 በፊት ሁለቱም የሕግ ባለሞያ በመሆናቸው ነው። በዚህ ሞያ ዘርፍ በሲቪል ማኅበረሰብ ውስጥ በማኅበራዊ፣ የሕግን እውቀት በማስፋት፣ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትን በማሳደግና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ቢያደርጉ ለአገሪቱ አንዳንድ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው በመሆኑ ጓደኝነታቸው ይበልጥ ተጠናከረ። ዳንኤልና ነፃነት ከጓደኝነት አልፈው ቤተሰብ ሆነዋል።
ቤተሰባዊ ግንኙነታቸው የተመሰረተው ደግሞ የአቶ ነፃነት ደምሴ እህት የሆነችው ወ/ት የምሥራች ደምሴ የአቶ ዳንኤል በቀለ እጮኛ በመሆኗ ነው። የምስራች ደምሴ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በእንግሊዘኛው ፕሮግራም ክፍል ጋዜጠኛ የነበረች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሰራለች። የምሥራች ደምሴ መልከ መልካምና ርጋታን የተሞላች ወጣት ስትሆን፣ ሁለቱ ተከሳሾች በእስር ላይ በነበሩበት የቃሊቲው ማረሚያ ቤትና ተከሳሾቹ ይቀርቡበት በነበረው ፍርድ ቤቱ ያለማቋረጥ ተገኝታ ጉዳዩን ትከታተል ነበር። በወቅቱም ሁኔታውን የሚያውቅ ችሎት ተከታታይም ሆነ እስረኛ ጠያቂ ለየምሥራች ያለውን ኀዘኔታ ከንፈር መጥጦ ከመግለፅ ውጭ ጉዳዩን የሚያነሳ አልነበረም።
የሁለቱን ጓደኛሞች ትስስር ካጠናከረውና ወንድሟም፣ እጮኛዋም ታስረውባት ከነበረው የየምሥራች አጋጣሚ ደግሞ የአቶ ዳንኤልን እስር እና የክስ ሂደት አሳዛኝ አድርገውበት የነበረው ሌላ የጓደኝነትና የከሳሽነት ትስስር አጋጣሚ ክሱን በዋነኛነት ይመራው የነበረው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ሽመልስ ከማል የልብ ጓደኛው የነበረ መሆኑ ነበር። አቶ ሽመልስ ከማል እና አቶ ዳንኤል በቀለ የማይነጣጠሉ የ20 ዓመት ጓደኛማቾች እንደነበሩ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። ከዩኒቨርስቲ ወደ ሥራ እስከተሰማሩበት ጊዜ ድረስ፣ አንድ ማዕድ አብረው ቆርሰው፣ ያላቸውን ሣንቲም ለሁለት ተካፍለው አብረው በልተውና፣ አብረው ጠጥተው ከኢትዮጵያ እስከ እንግሊዝ አገር ዘልቀው፣ በአንድ አልጋ ላይ ተኝተው፣ የሆድ የሆዳቸውን ያወሩ ጓደኛሞች ነበሩ።
ከምርጫ 97 በኋላ ግን ሽመልስ ከማል መንግሥትን ወክሎ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በመሆን “አቶ ዳንኤል በቀለ ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ሞክረዋልና በመጨረሻም በሞት ሊቀጡልኝ ይገባል” ሲል፤ አቶ ዳንኤል በበኩላቸው ከሌላኛው ጓደኛቸው ጋር በመሆን “ሕጋዊና ሠላማዊ ሰዎች ነንና በነፃ ልንለቀቅ ይገባል” ሲሉ ሁለቱም ወገኖች ችሎት ላይ ተፋጥጠው ሁለት ዓመታትን አስቆጠሩ። 20 ዓመታት በጓደኝነት፣ ሁለት ዓመታትን ደግሞ “በሞት ልትቀጣ ይገባል”፤ “የለም ነፃ ልወጣ ይገባል” በሚል የክርክር ትንቅንቅ ዘልቀው እዚህ ደርሰዋል።
አቶ ዳንኤልና አቶ ነፃነት ከቀድሞ የቅንጅት አመራሮች ጋር ተከሰውና ክሱን ሲከራከሩ ቆይተው፣ በብይን ወቅት ችሎቱን ሲመሩ በነበሩበት የመሃል ዳኛ አዲል አህመድ የልዩነት ድምፅ በ”ነፃ ሊለቀቁ ይገባል” በሚል ነፃነታቸው ተረጋግጦ የነበረ ቢሆንም፣ አብላጫው ድምፅ ክሱን ሊከላከሉ ይገባል በሚል ብይን ሰጥቷል። ከብይኑ በኋላ በክርክር ሂደት ውስጥ ያልተሳተፉትና ዝምታን የመረጡት የቅንጅት አመራሮች በምህረት ሲለቀቁ አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ነፃነት ደምሴ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን በማቅረብ ክርክራቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም የቀኝ ዳኛ መኮንን ገ/ሕይወት እና የግራ ዳኛ መሐመድ ኦሚን ሳኒ በሰጡት አብላጫ ድምፅ ጥፋተኛ ተባሉ። በመሃል ዳኛው ልዩነት ድምፅ ደግሞ በነፃ ሊለቀቁ ይገባል ቢባሉም በአብላጫው ድምፅ ውሳኔ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ተፈርዶባቸዋል። በአመክሮ የመፈታት ዕድል ባለማግኘታቸው የእስር ጊዜያቸውን መጨረስ ግድ ነበር። ነገር ግን ለመፈታት 33 ቀናት ሲቀራቸው እነሱም ዓቃቤ ሕግም ያቀረበው ይግባኝ ተቋርጦ በእነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስኃቅ አማካኝነት በምህረት ከተለቀቁ ዛሬ 15 ቀናቸው ነው። ሁለቱ ጓደኛሞች እና ቤተሰባሞች በእስር ስለነበሩበት ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዩችን በሚመለከት ከጽዮን ግርማ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ስለጓደኝነታችሁ ስጠይቅ አቶ ዳንኤል “ጓደኞች ብቻ ሳንሆን ቤተሰቦችም ነን” ብለኸኝ ነበር ቤተሰብነታችሁ በምንድነው?
አቶ ዳንኤል፡- የነፃነት እህት የእኔ እጮኛ ነች። በቅርቡም ደግሞ ሚስቴ ትሆናለች።
ወንድሟም እጮኛዋም የታሰሩባት ሴት እንደመሆኗ አይከብዳትም ነበር ወይ? እስር ቤት ስትመጣስ በምን መልኩ ታጽናናት ነበር?
አቶ ዳንኤል፡- በጣም ከባድ ነበር። ምናልባትም በጣም በችግር የተጎዳችና ከባድ ችግር ያሳለፈች ናት። እኔ እንደሚገባኝም ደግሞ ከኛ ባላነሰ እንደውም በበለጠ ሁኔታ በዚህ እስር በጣም የተጎዳች ብትኖር እሷ ነች፤ ወንድምና ጓደኛ እስር ቤት ታስሮ መመላለስ ማለት በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ነበር። ነገር ግን በጣም ጎበዝና ጠንካራ ልጅ በመሆኗ በጥንካሬ ተቋቁማው አሳልፋዋለች።
ከሳሽ የነበረው ዓቃቤ ሕግ ሽመልስ ግርማ የአቶ ዳንኤል የቅርብ ጓደኛህ ነበር? የሞት ፍርድ እንዲወሰንብህ ክስ ይዞ ሲመጣ ምን ተሠማህ?
አቶ ዳንኤል፡- እርግጥ ነው ሽመልስ ጓደኛዬ ነው። ጓደኛዬ ብቻ ሳይሆን ምናልባት እንደ ወንድሜ የምመለከተው በጣም የቅርብ ጓደኛዬ ነበር። ምክንያቱም ከት/ቤት ጀምሮ ከ20 ዓመት በላይ የቆየ ጓደኝነት አለን፣ የረጅም ጊዜ ጓደኛሞች ነን፣ ከመጀመሪያ ጀምሮ መሪ ዓቃቤ ሕግ ሆኖ ክሱን እስከመጨረሻ ከተከታተለው ሰዎች ውስጥ ሽመልስ አንዱ ቢሆንም እሱ ብቻ ሣይሆን ሌሎች ቅርብ ጓደኞቼንም በዚሁ በዓቃቤ ሕግ ቡድኖች ውስጥ ተመልክቻለሁ። እኔ የተሠማኝን ስሜት በቃላት ለመግለጽ የምችለው አይደለም። ምክንያቱም እኔ ሽመልስም ሆነ ሌሎች ጓደኞቼን ችሎት ላይ ተመለከትኳቸው እንጂ ይህንን የቀረበብኝን ክስ ለመከላከል ምስክር መጥራት ቢያስፈልገኝ ከምጠራቸው ሰዎች አንዱ ሽመልስ ከማል ይሆናል ብዬ የማስበው ሰው ነው። ምክንያቱም በጣም እንተዋወቃለን ሥራዎቼን ብቻ ሳይሆን እምነቴንም፣ አስተሳሰቤንም በቅርብ ከሚያውቁኝ ሰዎች ውስጥ ስለነበረ በእኔ በኩል በመከላከያ ምስክርነት የማስበው ሰው ነው እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ እኔን የሚከስ ሰው ይሆናል ብዬ አላስብም ነበር። ሽመልስ እኔን ብቻ ሳይሆን ከኛ ጋር ከተከሰሱት መካከል ሌሎችንም በቅርብ የሚያውቃቸው ጓደኞች እንደነበሩት አውቃለሁ። ምናልባት ሽመልስ ስለዚህ ጉዳይ ቢጠየቅ፤ “የለም እኔ ጓደኞቼም ቢሆኑ፣ የእናቴም፣ የአባቴም ልጅ ቢሆን ጥፋት ከሠራ፣ ወንጀል ከሠራ፣ በሙያ ኃላፊነቴ መክሰስና መጠየቅ አለብኝ። ስለዚህ በሙያ ኃላፊነቴ ጓደኞቼ ስለሆኑ ወደኋላ አልልም” ብሎ ሊል ይችል ይሆናል። ነገር ግን እውነቱን ትክክለኛውን ነገር እሱንም እኔንም ሁለታችንም በቅርብ የሚያውቁ ጓደኞቻችንም ሁላችንም ስለምናውቀው የማልቀበለው ይሆናል። ይከብደኛል። ሽመልስ ሞያዊ ሥራዬን እየሠራሁ ነው ብሎ ሊያምን ይችላል፣ እኔ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፣ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቅ ተመልካች የራሱን ግምት ሊወስድበት፣ የራሱን የኅሊና ፍርድ ሊሰጥበት ይችላል። እኔ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ስሜቴን ለመግለፅ በጣም ቃላቶች ያጥሩኛል በጣም፣ በጣም የሚጎዳ ነገር ነው።
ሃያ ዓመት በጓደኝነት ባህሪይ ለባህሪ ትተዋወቃላችሁ፤ ክስ ሲመሰረትብህ “ጓደኝነት” በሚለው ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ አላሳደረብህም?
አቶ ዳንኤል፦ ተፅዕኖ አላሣደረብኝም ለማለት ይከብዳል። በክሱ ሂደት የተሰማኝ ትልቅ ኀዘን የሽመልስ ከማል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በዚህ ነገር የተነሳ በጣም የቅርብ ጓደኞቼን ጭምር ማጣቴ ነው። በጣም የጎዳኝና ልቤን ከሰበሩት ነገሮች ውስጥ አንዱ የምወዳቸው የቅርቦቼ የነበሩ ወይም ቢያንስ እንደ እኔ እምነት፣ እንደዚያ ናቸው ብዬ የማምናቸው በጣም ለልቤ ቅርብ አድርጌ ይዣቸው የነበሩ ጓደኞቼን ማጣቴ ነው አንዱ ትልቁ ጉዳቴ አድርጌ የማስበው። ‘ሊድን የሚችል ጉዳት ነው ወይስ አይደለም?’ የሚለው ጊዜ የሚዳኘው፣ ጊዜ የሚፈታው ይመስለኛል እንጂ ቀላል አይደለም። ክብደቱንም በደንብ የሚገልፅልኝ ቃል ገና አላገኘሁኝም።
በፍርድ ቤት የተጣለባችሁን የእስር ጊዜያችሁን ልትጨርሱ ስትሉ ነው በምህረት የተለቀቃችሁት፤ የክርክሩን ሂደት ብትቀጥሉ ኖሮ በፍርድ ቤት አትለቀቁም ነበር?
አቶ ዳንኤል፡- እኛ በተከሰስንበት ጉዳይ ላይ ለመከሰስ ምክንያት የሆኑን ጉዳዮች ሕጋዊ እና ሠላማዊ ሥራዎች እንደነበሩ በማስረዳት ነበር ክሱን የተከላከልነው። የክርክራችን መሠረቱም የቀረበብን ክስ ያለአግባብ ነው እንደውም እንኳን በአመፅ ሥራ ላይ ተሠማርተዋል ልንባል ይቅርና ይልቁንም በወቅቱ ለነበረው የፖለቲካ ችግር በሠላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንዲፈታ አስተዋጽኦ ስናደርግ የነበረ መሆኑን በማስረዳት፤ ሌሎቹም ደግሞ በሲቪል ማኅበረሰብ አባልነታቸው የተሳተፍንባቸው ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ሕጋዊና ሠላማዊ መንገዶች የነበሩ መሆናቸውን በማስረዳት የቀረበብንን ክስ ስንከላከል ነበር። በዚህ መሠረትም በመጨረሻ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ሰምቶ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል። በአነስተኛው ድምፅ አስተያየት ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ በማስረጃ ያልተደገፈ ስለሆነ በነፃ ሊሰናበቱ ይገባል በማለት ሲወስኑ፣ በአብላጫ ድምፅ የወሰኑት ዳኞች ደግሞ ተከሳሾቹ በርግጥም በሲቪል ማኅበረሰባት አባልነት የተሳተፉባቸው ሥራዎች ሕጋዊና ሠላማዊ ናቸው፣ ተከሳሾቹም በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ቀውስ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሩ ጠቃሚ አስተዋፅኦ አድርገዋል፣ የዜግነት የሙያ ግዴታቸውንም ተወጥተዋል፣ በጣም ጠቃሚ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፣ ለሕግ የበላይነት መከበር አስተዋጽኦ አድርገዋል። ነገር ግን በሕገ ወጥ ቅስቀሳ ተጠያቂዎችና ጥፋተኞች ናቸው በማለት እስራት የፈረደብን መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ ውሣኔ ላይ ቅሬታ ስለነበረን ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበን ነበር። በሌላ በኩልም ዓቃቤ ሕግም ይግባኝ አቅርቦ ነበር። የዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ነጥቡ ደግሞ ተከሣሾቹ ክስ እንደቀረበባቸው ዓይነት መንግሥትን በኃይል ለመለወጥ በመሞከር ወንጀል ጥፋተኞች ተብለው የሞት ፍርድ ሊፈረድባቸው የማይገባበት ምክንያት የለም የሚል ይገባኝ ነበር ያቀረበው። ይህን እንግዲህ ለመረዳት እንደሚቻለው የዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ከፍተኛ ቅጣት የተጠየቀበት ይግባኝ ነው። እኛ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ባቀረብነው ክርክር፣ በኛ በኩል ያለውን እውነት ለማስረዳት ጥረት አድርገናል። ፍርዱ በተፈረደ ጊዜም ረጅም የእስር ጊዜ አሳልፈን ስለነበር ከእስር እንደምንለቀቅ ጠብቀን ነበር፣ ነገር ግን በዚያ መሠረትም ሳንወጣ ቆይተን በእስር ላይ እያለን ነው የዓቃቤ ሕግ የይግባኝ መጥሪያ የደረሰን። ጉዳዩ በዚህ ደረጃ እያለ ነው እንግዲህ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ መፍትሄ ሲፈልጉ በነበሩ ሰዎች አማካኝነትና በመንግሥት ውሳኔ የክርክሩ ሂደት ተቋርጦ ከእስር እንድንለቀቅ የተደረገው። ስለዚህ በአጭሩ ከእስር የተለቀቅንበት ጠቅላላ ሁኔታው ይኼን የመሰለ ነው።
በእናንተ በኩልስ በይግባኙ ወይም በሕግ ሂደት ውስጥ ልንለቀቅ እንችላለን የሚል እምነት ነበራችሁ?
አቶ ዳንኤል፡- እኛ በሕጋዊ አሠራርና በሕጋዊ መፍትሄ ሁልጊዜም እምነት አለን። በእስር ሆነን በፍርድ ቤት ያን ያህል ራሣችንን የመከላከል ሂደት ውስጥ የገባነው ንፅህናችንን እና በሥራችን በመተማመን፣ ንፅህናችንን አስረድተን ነፃ እንወጣለን በሚል እምነትና የዳኝነት ሥራ አካሄዱ ላይ ባለን ተስፋና እምነት መሠረት ነበር። በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ከተሰጠብን በኋላ ይግባኝም ያቀረብነው በሕጋዊ አሠራር እምነት ስለነበረን ነው፣ አለበለዚያ ይግባኙን ማቅረብ አያስፈልገንም ነበር። ይግባኙንም ያቀረብነው በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ያልታዩ ነጥቦች ታይተውልን ነፃነታችን ይረጋገጥልናል በሚል ተስፋ ነው። ነገር ግን ጉዳዩ በተለየ ዓይነት መንገድ እልባት እንዲያገኝ የሚያስፈልገው ሆኖ በመገኘቱ በመንግሥት ውሳኔ ሌላ ዓይነት እልባት እንዲያገኝ አድርጓአል። በዚህ ጉዳይ ላይ በዝርዝር ይኼንን ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ያደረጉ ሰዎች ለእነሱ አመቺና ተገቢ በሆነ ጊዜ ዝርዝሩን ይገልጹታል፤ ምናልባት እያንዳንዱ ዝርዝር ለታሪክ የሚተው ነው።
አንዳንድ ጥያቄዎች የሚዳኙትና የሚወሰኑት በፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የታሪክ ጉዳይ ስለሚሆን በታሪክም ጭምር ነው። በመሆኑም ዝርዝሩን ለታሪክ ፍርድ የሚተው ይመስለናል። አሁን ግን ከዚህ የበለጠ ዝርዝር አስተያየት ለመስጠት አንችልም።
ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ስታዩት የፍርድ ቤቱ ሂደት እንዴት ነበር?
አቶ ነፃነት፡- ረጅም ጊዜ የፈጀ የፍርድ ቤት ክርክር ነበር። እንደሚታወሰው በዓቃቤ ሕግ የቀረበብን ክስ እንደው ባጭሩ እኔና ዳንኤልን የምንወክላቸው ማኅበራትን ሕገ-ወጥ ለሆነ ተግባር በመጠቀም ሕገ-መንግሥታዊውን ሥርዓቱን ለመናድ ሞክረዋል፣ ይህን አቅደው ተንቀሳቅሰዋል የሚል ነበር። በክሱም ሆነ የቀረበው ማስረጃ ይዘትና ምንነት ካየን በኋላ እኛም በንፅህናችን የምናምን ሰዎች ስለነበርን ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህ ትክክል አይደለም፣ እኛ ጥፋተኞች አይደለንም፣ ንጽህናችንን ማስረዳት እንፈልጋለን በሚል ክርክር ውስጥ ቆይተናል። ረጅም ጊዜ የፈጀ ክርክር ነበር። ፍርድ ቤቱ የቀረበብንን ክስ እንድንከላከል በሰጠው ትዕዛዝ መሠረትም መከላከያችንን አቅርበን ነበር። በመከላከል ሂደት ውስጥ ስንቀሳቀስባቸው የነበሩ ሂደቶች በሙሉ ለማስረዳት የሰነድ ማስረጃዎችን እና ብዛት ያላቸው ምስክሮችን አቅርበናል። በአጠቃላይ የቀረበብን ክስ አግባብ እንዳልሆነ፣ ማስረጃዎችም አግባብ እንዳልሆኑ በሌላ መልኩ ደግሞ ያደረግናቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሕጋዊ፣ ሠላማዊና እንዲሁም ለሕገ-መንሥግታዊ ሥርዓቱ መጎልበት ጠቃሚ የነበሩ ሥራዎች ናቸው በማለት ለማስረዳት ሞክረናል። በዚሁ መሠረት ነበር ክርክሩ የተጠናቀቀው። ፍርድ ቤቱ ከረጅም ጊዜ ቀጠሮ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ የተከሰስንበት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ወንጀል ሳይሆን፣ ሕገ-ወጥ ቅስቀሳ በማድረግ ወንጀል በአብላጫ ድምፅ ጥፋተኛ ተብለናል። በሃሳብ የተለዩት ዳኛ በነፃ ሊለቀቁ ይገባል ሲሉ አቅርበዋል። የአብላጫው ድምፅ ግን ሕገ-ወጥ ቅስቀሳ አድርገዋል በዚያ ተጠያቂ ናቸው በማለት ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ፈርዶብናል ማለት ነው በአጭሩ የክርክሩ ሂደት ይኼን ይመስል ነበር።
የቀረቡባቸሁ ምስክሮች ነበሩ። እናንተም ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ምስክሮች ሐሰተኛ ናቸው ብላችሁ ተከራክራችኋል የምስክሮቹ አቀራረብ እንዴት ነበር?
አቶ ነፃነት፡- ብዙም ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም። ጉዳዩ በተጠናቀቀበት ሁኔታ ሲታይ አላስፈላጊ ቢሆንም ዓቃቤ ሕግ አለኝ የሚላቸውን የሰነድም ሆነ የሰው ምስክሮች አቅርቦአል። ምስክሮቹ በተለይ ያስረዱት እና በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት የሆነው ሕገ-ወጥ ቅስቀሳ አድርገዋል የሚል ነበር። እኛ ይህ ትክክል አይደለም በማለት አስረድተን ነበር፣ እንግዲህ ፍርድ ቤቱ ነው ምስክሮች ውስጥ የሚቀበለውን የማይቀበለውንና መዝኖ በዚያው መሠረት የመሰለውን ውሣኔ የሠጠው። ከዚህ ውጪ ዝርዝር ውስጥ መግባት ብዙም አያስፈልግም። የክርክር ሂደት (Public Record) ስለሆነ በኛ እምነት ማንኛውም ፍላጎቱ ያለው ሰው ይህን ፐብሊክ ሪከርድ በማገናዘብ ሊረዳው ይችላል።
አቶ ዳንአል፡- በአጭሩ ነፃነት እንዳለው እኛን ጥፋተኞች ናቸው ብሎ በከፍተኛው ፍርድ ቤት በአብላጫ ድምፅ የተሰጠው ውሣኔ በግልፅ እንዳስቀመጠው “ተከሳሾቹ በዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ሁሉንም ማስረጃዎች ከሦስት ምስክሮች ቃል በስተቀር ሙሉ በሙሉ አስተባብለዋል” የሚል ነበር። ጥፋተኛ ናቸው የተባልነውና ውሣኔ የተሠጠበት እነዚህ ሦስት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል ነው። እኛ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበነው የነበረው ይግባኝም የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን በሙሉ ትክክል አለመሆኑን አስረድተናል አስተባብለናል። ስለዚህ በዚህ መሠረት ጉዳዩ ሊወሰን ይገባል የሚል ነበር። ሆኖም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ መሠረት የሆነው በዓቃቤ ሕግ ሦስት ምስክሮች የተሰጠ ቃል ነው።
በአመክሮ ትፈታላችሁ የሚባል ነገር ነበር። ከሕጉ አንፃር ሊያስፈታችሁ የሚችል ነበር? ለምንድን ነው በአመክሮ ያልተፈታችሁት? የተገለፀላችሁ ምክንያት ነበረ?
አቶ ዳንኤል፡- እኛም በአመክሮ እንፈታለን ብለን አምነን እና ተስፋ አድርገን ስለነበር በአመክሮ ለመለቀቅ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች እንደምናሟላ ስለምናምን በአመክሮ መብታችን እንድንፈታ ለሚመለከተው አካል አቤቱታችንን አቅርበን ነበር። ነገር ግን ምላሽ አላገኘንም። በዚህም የወሰድነው ግምት እንዳልተፈቀደልን ነበር፤ ምክንያቱም ውሣኔው በተወሠነ ጊዜ በአመክሮ ለመለቀቅ የሚያስፈልገውን ሁኔታ ከሚፈለገው በላይ አሟልተን እንገኝ ስለነበረ በተለመደው አሠራር በሁለትና በሦስት ቀን ውስጥ ጉዳዩ ተጠናቆ እንፈታለን ብለን ጠብቀን ነበር። ግን ያው ከሦስት ወር በላይ ቆይቶም ምላሽ ባለማግኘታችን እንግዲህ እንዳልተፈቀደ ነው መገንዘብ የቻልነው።
የእስር ቤት ቆይታችሁ እንዴት ነበር?
አቶ ነፃነት፡- ከዚህ በፊት ታስሬ አላውቅም ነበር። የመጀመሪያ የእስር ልምዴ ነው። እንደሚታወቀው መጀመሪያ እንደታሰርን የቆየነው በማዕከላዊ ምርመራ ማቆያ ቦታ ነበር። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ቃሊቲ የተዘዋወርነው። መጀመሪያ ላይ እንደገባን ለመላመድ አስቸጋሪ ነበር። እንደሚገመተው እስር በተለይ የአገራችን እስር ቤቶች ካሉባቸው የእስረኛ ብዛት ሁኔታ አኳያ ብዙም የተመቻቸ ስላልነበረ መጀመሪያ አዳጋች ነበር። እኛም በወቅቱ ጉዳዩ ያበሳጨን ነበር። ክርክሩም ገና መጀመሩ ነው። የተከሰስንበት ጉዳይ ገና ግልፅ አልነበረምና ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። ቃሊቲ ከወረድን እና ትንሽ ጊዜ ካሳለፍን በኋላ ግን በተለይ ዋስትና ከተከለከልን በኋላ ጉዳዩ ረዘም ያለ ጊዜ ሊፈጅ የሚችል ግምት በመውሰድ በዋናነት ራሳችንን ማረጋጋት ጀምረን ነበር። ከዚያም በላይ ቤተሰቦቻችን እንዳይጨነቁ፣ ኑሮዋቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግም የሚደረግ ትግል ነበር። ከዚያ እኛም ተላመድነው። በኋላም ሠፋ ያለ ጊዜያችንን የፈጀው ያው የክርክሩ አካል ነው። ክርክራችንን ስናዘጋጅ የነበረው እኛው ራሣችን ስለነበርን ሰፋ ያለ ጊዜውን ጉዳያችን ላይ በመመካከር፣ ሃሣባችንን በመለዋወጥና በመዘገጃጀት ነበር። ከዚህ ውጪ ባሉት ትርፍ ጊዜያቶች ምናልባትም በሥራ ላይ እያለን ያላገኘነውንም ዕድልም ጊዜ ስለፈጠረልን ሰፋ ያለ ጊዜ በመጠቀም መጻሕፍትን በማንበብ፣ ስፓርት በመሥራት፣ ቁጭ ብሎ በመጫወት አሳልፈናል።
አብራችሁ የመሆን ዕድሉ ነበራችሁን?
አቶ ነፃነት፡- ሰፋ ባለ ጊዜ አብረን የመሆን ዕድል አግኝተናል። በርግጥ በመጀመሪያው እና አሁን ደግሞ ወደ መጨረሻው አካባቢ ላይ የተለያየ ቦታ ታስረን ነው የቆየነው። ቢሆንም ሰፋ ባለው ጊዜ ግን አብረን ለመኖርና የእስር ጊዜያችንን የማሣለፍ ዕድል አግኝተን በዚህም ሂደት ውስጥ እንግዲህ ከራሳችን ጋር ተነጋግረናል። ሕይወታችንን ወደ ኋላም፣ ወደፊትም ምን እንደሚመስል ለማየት፣ እንዲሁም ለማንበብ ደግሞ ጊዜ ሰጥቶናል። ከዚህ ውጪ ግን እስር ምንም ጥያቄ የለውም ከባድና አስቸጋሪ ሂደት ነው። በራስና በቤተሰብ ላይ የሚደርሰው አስፈሪ ነገር ነው። የስሜት ጉዳትና የተለየዩ ጉዳቶች ስለአሉት እስር በጣም አስቸጋሪ ሂደት ነው።
አቶ ዳንኤል፡- የምጨምረው ብዙ ነገር ያለ አይመስለኝም። እኔም የምለው በመሠረቱ እስር ከባድ ነው። አስቸጋሪና አስጨናቂነቱ ለታሣሪውም ብቻ ሳይሆን ለታሣሪውም ቤተሰብም ጭምር ነው። ለተታሣሪው ደግሞ የሚከብደው የእስር ከባድነት፣ አስጨናቂነት፣ ቤተሰቡን ከማሰብና ቤተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለ ጉዳት የሚያስጨንቀው ይጨመርበታል። ነገር ግን አንድ ሰው በተወሰነ መልኩ ሊለውጠው የማይችለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ራሱን ካገኘ በዚያ አስቸጋሪ ወይም ከባድ በሆነ ሁኔታ እያዘኑ፣ እየተከዙ፣ እያለቀሱ መቀመጥ ትርጉም የለውም። ስለዚህ ያንን አስቸጋሪና ከባድ ሁኔታም እንዴት ወደ ጥሩ ሥራ መለወጥ ይቻል ይሆናል እያልን በማሰብና ጥረት በማድረግ፣ በዚህ የተነሳ የእስር ቆይታችን በተቻለ መጠን ትንሽ ጠቃሚ ሊሆን የሚቻልበትን መንገድ መጠነኛ ጥረት ለማድረግ ሞክረናል። በዚህ መንገድ ቢያንስ ሳንታሰር በፊት በሥራ ብዛት ለማድረግ ያልቻልናቸው ነገሮች መጽሐፍት የማንበብ፣ ከራስም ጋር ለመነጋገር፣ ሕይወታችንን ለመመርመር፣ … ወዘተ ተጠቅመንበታል። በሌላ በኩል ደግሞ የአገራችን እስር ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ በዚያ ያሉ ታሳሪዎችን ሁኔታና፣ ዓይነት ለመገንዘብ ትንሽ ዕድል አግኝተናል። ይህን ለማወቅ የግድ እስር ቤት መግባት ላያስፈልግ ይችላል፤ ነገር ግን እስረኛ ሆኖ ሲመለከቱት ደግሞ የበለጠ በደንብ ማስተዋል insight ይሰጣል። እስር ቤቶቻችን በሚፈለገው መጠን አይደለም ያሉት። ይህ እንዴት ሊሻሻል ይችላል የሚለውን ለመመልከት የሚረዳ ይመስለኛል። ይህ ማለት እንግዲህ በሁሉም እስር ቤቶች ማለት ነው። እኔ ከመጀመሪያ ፓሊስ ጣቢያ ጀምሮ ነው እስር ቤቶችን እያየሁ የመጣሁት። ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ደግሞ የታሰርኩት።
በአጠቃላይ በአገራችን የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ጉዳይ ያሉ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችንም ለመመልከት፣ ዕድልም የሚሰጥ ነበር፤ ምክንያቱም ከታሣሪ ወገን ሆኖ ማየት ራሱን የቻለ ዕይታ የሚሰጥ ስለሆነ ግንዛቤ ለመውሰድ የረዳን ይመስለኛል። የእስር ቆይታችን ከባድ ቢሆንም ከቤተሰባችን፣ ከጓደኞቻችን፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ በአጠቃላይ ዓለም ዓቀፍ የሲቪክ ማኅበረሰብ አባሎች፣ የብዙ አገር የውጭ ዜጎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ያገኘነው ድጋፍና ማበረታቻ ደግሞ እንድንፅናና የእስር ጊዜያችንን ደግሞ በመጠኑ ቀለል እንዲል አድርጎልናል። የእስር ቆይታችን ይኼንንም ያንንም ዓይነት መልክ የነበረው ነው ማለት ይቻላል።
በተለይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንድትፈቱ ትልቅ ትኩረት ነው የሰጠው፣ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ከቤተሰቦቻችሁና ከቅርብ ጓደኞቻችሁ በስተቀር በተለይ የሲቪክ ማኅበራት ያደረጉት እንቅስቃሴ አልነበረም ይባላል፤ እናንተ በእዚህ ምን ተሰማችሁ?
አቶ ዳንኤል፡- ምናልባት ሙሉ በሙሉ ዝምታ መርጦአል ወይ ለማለት እርግጠኛ አይደለሁም። አገራችን ውስጥ የነበሩ የሲቪክ ማኅበረሰቦችም ቢሆኑ አቅማቸውና ሁኔታው በፈቀደ መጠን ስለ እኛና ስለተከሰስንበት ጉዳይ እንዲሁም በጋራ አብረን ስንሠራቸው ስለነበሩ ጉዳዮች የሚያውቁትን እና የሚያምኑትን ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል። ይህ በተለያየ ዓይነት መልክ ተገልፆአል። ለምሣሌ በሥራዎቻችን ላይ አብረው ተሳታፊ የነበሩ የሥራ ጓደኞቻችን በተከሰስንበት ጉዳይ በመከላከያ ምስክርነት ቀርበው የሚያውቁትን አስረድተዋል። ሁኔታው እስከፈቀደ ጊዜ ድረስ የሚያውቁትን ለማስረዳት የሚቻላቸውን ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን እነሱ ይሰሩበት የነበረው ሁኔታ ጉዳዩ በፍርድ ቤት፣ በዳኝነት እየታየበት በነበረበት ወቅት በመሆኑ ይህ የሚፈጥርባቸው ሕጋዊ ገደብ በመኖሩ የሚፈልጉትን ያህል ብዙ ለማለት አልቻሉ ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ ዝምታን መርጠው ይሆናል። በርግጥ የተወሰኑ አብረናቸው የሠራን በነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተሳተፍን ይህን ጉዳይ በቅርብ የሚያውቁ የነበሩ የሲቪክ ማኅበራት አባሎችና የሥራ ጓደኞቻችንና ባልደረቦች ግን ሸርተት ሲሉ፣ ሲሸሹም ተመልክተን ኀዘኔታ ፈጥሮብናል። ይህ በእርግጥ የሚያሳዝን ነበር። ነገር ግን ሌሎች አብረውን የነበሩ ሰዎች በሚያበረታታ መልክ፣ የሚያውቁን አብረን ስንሳተፍበት የነበረውን ሠላማዊና ሕጋዊ ሥራ ለፍርድ ቤት ጭምር ቀርበው አረጋግጠዋል። አቅማቸው የፈቀደውን ደግሞ አድርገዋል።
ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት የእናንተን ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፣ የሲቪል ማኅበራት አባላቶች ናቸው እያሉ መግለጫ ያወጡ ነበር። በአገር ውስጥ ያሉት ግን አንድም ጊዜ አውጥተው አያውቁም ተብለው ይተቻሉ። እናንተ ይሄንን አልጠበቃችሁም ነበር?
አቶ ነፃነት፡- በርግጥ እንደተባለው ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበራት ያደረጉት ጥረትና በአገር ውስጥ ያሉት ያደረጉት ጥረት ተቀራራቢ ላይሆን ይችላል። ይኼ ማለት ግን አገር ውስጥ ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ አባላትና አብረውን የሠሩ ወዳጆቻችን፣ ጓደኞቻችን እና የሥራ ባልደረቦቻችን ግን ስናከናውን የነበረውን ሕጋዊና ሠላማዊ ሥራ ለማስረዳት፣ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ጥረት አላደረጉም ለማለት የሚያስችል አይደለም። በርግጥ ዳንኤል እንዳለው እኛ እጅግ ስንጠብቃቸው የነበሩ፣ አብረውን የሠሩ፣ ጥቂት ጓደኞቻችን ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ኃላፊነት በመተው ሸሽተውናል። ያ ደግሞ እንደ እውነቱ ከሆነ ያሳዝናል፤ በዚህም አዝነናል። ሆኖም ግን በአንፃሩ ሌሎች አብረውን የሠሩ ብዙዎቹ በምስክርነትም ፍርድ ቤት በመቅረብ የሚያውቁትን በማስረዳት፣ አብረን ስንሠራቸው የነበሩ ሥራዎች ሕጋዊነትን ንፁህ ዜጎች መሆናችንን ለማስረዳት ጥረት አድርገዋል፣ ተንቀሳቅሰዋል ብለን እናምናለን። የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ምናልባትም አገር ውስጥ ያለው ሕገ ደንቡ በቀጥታ የማይመለከተው ስለሆነ በአንድ መልኩ በሌላ መልኩ ደግሞ የልምድም የጥንካሬም የተለያዩ መሥፈርቶችን ከግንዛቤ ውስጥ ልናስገባ እንችላለን። የውጪዎቹ ከአገር ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ጥያቄ ሲያሰሙ ቆይተዋል ማለት ግን እዚህ አገር ውስጥ ያሉ ከእኛ ጋር አብረው የሠሩ በሙሉ እኛን ወደጎን ገፍተው ትተውን ሄደዋል ማለት አይደለም። እኛን ያበረታታን እና ተስፋም የሰጠን ይኼው ጉዳይ ነው፤ ቢያንስ እኛ እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ በጋራ የሠራናቸው ሥራዎች በሙሉ ሕጋዊና ሠላማዊ ናቸው። ይህንን የሚመሰክሩ ወገኖች አሉ ብለን በማመን ተከራክረናል፣ ፍርድ ቤት በአብላጫነት ከሰጠው ውሳኔ ዋናው በሲቪል ማኅበረሰብ ስንንቀሳቀስ የነበረውን ሥራዎች በሙሉ ሕጋዊና ሠላማዊ መሆናቸው ተረጋግጧል ማለት ነው።
እዚህ ደረጃ የተደረሰው እነዚሁ ወገኖቻችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቁርጠኝነት በማስረዳት ለመመስከር በመቻላቸው ነው። በዚህ ምክንያት ነው ብርታት የሚሰጠን። በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበራት ከኛ ጎን በመቆም ላደረጉት ትብብር ደግሞ ደስታ ይሰማናል።
እስር ቤት በነበራችሁበት ጊዜ ከጠባቂዎቻችሁ ጋር የነበራችሁ ሁኔታ እንዴት ነበር?
አቶ ነፃነት፡- በእውነት ከፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስከነበርንበት ጊዜ ድረስ በደንብ ለማወቅና ለማስተዋል ዕድል ካገኘንባቸው መካከል በታሳሪና በጥበቃ ጓዶች መካከል ያለው ግንኙነት ነው። በእውነቱ ከሆነ አብዛኛው የማረሚያ ቤቱ ሠራተኞችና የጥበቃ አባሎች እጅግ ሠላማዊ ናቸው። ከኛ ጋር በነበረው ሁኔታ የጎላ ችግር አልነበረም። ይህ ማለት ግን አልፎ አልፎ አላግባብ የሆነ ምግባር ያሳዩን የጥበቃ አባሎች የሉም ማለት አይደለም። በአብዛኛው እንደ አጠቃላይ ስናየው ግን ምናልባትም ከላይ ጀምሮ እስከታች ያሉ የጥበቃ አባላቶች ከኛ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሠላማዊ ነበር። በኛም በኩል ደግሞ ሙያችንም፣ ምግባራችንም፣ ባህሪያችንም ከጥበቃ አባላቶች ጋር ቀርቶ ከማንም ጋር ለግጭት የሚያደርስ አይደለም።
የታሰራችሁት ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ነው፣ ዳንኤል በምርጫ 97 ድርሻህ ምን ነበረ?
አቶ ዳንኤል፡- ከምርጫው በፊት ስናደርገው የነበረው ዋነኛው ተሳትፎ በሲቪል ማኅበር ምርጫውን የመታዘብ ሥራ ነበር። ሌላው ለመራጮች ትምህርት የመስጠት ሁኔታ ነው። ሌላው የፖለቲካ ፖርቲዎች የፉክክር መድረክ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ይህንን የመሳሰሉ ከምርጫው በፊት የነበሩ የሲቪል ማኅበረሰቡ አስተዋፅኦ ሊያደርግባቸው የሚችሉና የሚገቡ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ተሳትፎ ነበረን። በዋነኛነት ግን የኛ ትኩረት የነበረው ከዚህ በፊት ትርጉም ባለው ደረጃ የአገር ውስጥ ሲቪል ማኅበራትና መሠል ድርጅቶች በተቀናጀ መንገድ የምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ ተሰማርተው የማያውቁ ስለነበር፣ ይህንን የምርጫ መታዘብ ሥራ በተሻለ መልክ ለመሥራት ይቻላል በሚል እምነትና በተስፋ፣ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሰባስበው የምርጫ መታዘብ ሥራን ተግባራዊ ለማድረግ ስንሠራ፣ ጥረት ስናደርግ፣ ስንቀሳቀስ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ ሴክሪታሪያት ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ነፃነት ይመራው የነበረው “ማኅበራዊ ፍትህ በኢትዮጵያ ድርጅት” ነው። ይህንን ሥራ ከእነ ነፃነት ጋር እና ከሌሎች የሥራ ጓደኞቻችን ጋር ስንሳተፍበት የነበረ ሥራ ነው።
ሌላው ከምርጫ በኋላ የነበረን ተሣትፎ እንደሚታወቀው እስከ ምርጫው ቀን ድረስ የነበረው አስደሳችና ሠላማዊ ሁኔታ ተለውጦ ከዚያ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት ይታወሳል። ያንን የፖለቲካ አለመግባባት መመልከት እንደጀመርን አሁንም የሲቪል ማኅበረሰቡ በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ያለመረጋጋት ሁኔታ ላይ ጉዳዩ በሠላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንዲፈታ ተገቢ ጥረት ማድረግ ይገባል የሚል እምነት የነበራቸው የሲቪል ማኅበረሰብ አመራሮችና አባሎች ተሰባስበው፣ ምን ጥረት እናድርግ ብለው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ እኔና ነፃነት በዚህ ውስጥም ተሳትፎ ነበረን። የሲቪል ማኅበራት አባላት ተሰባስበው የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በሕጋዊ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ተመካክረው ያቀረቡት የሠላም ጥሪ ነበር። እዚያ ውስጥ ተሳትፎ ነበረን። በሲቪል ማኅበረሰብ አባልነት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሀገሪቱ ሁኔታ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው ጥረት ሲያደርጉ ነበር። አንድ የሠላም ድምፅ “Voice for Peace” በሚል ስያሜ የተሰባሰበ ቡድን ነበር። በርካታ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን የነበሩበት ስብስብ ነው። የዚያ ስብስብ ዓላማ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ቶሎ መረጋጋት የሚያገኝበትና ሠላም የሚሰፍንበትና ሕጋዊ ሁኔታ ተመልሶ የሚረጋገጥበትን ጥረት ማድረግ አለብን በሚል የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ነበሩና እዚያም ውስጥ እንድንሳተፍ ግብዣ በማግኘታችን የበኩላችንን አስተዋፅኦ አድርገናል። በአጭሩ ከምርጫው በፊት የምርጫ መታዘብ ሥራን የሚመለከት ሲሆን ከምርጫው በኋላ ደግሞ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ ማረጋጋትና ወደ ሠላማዊና ሕጋዊ ሁኔታ ወደመመለስ ያተኮረ ነበረና የኛም ተሳትፎ ትኩረት ያደረገው በዚህ ላይ ነበር።
በምርጫው ወቅት ከቅንጅት ጋር በተያያዘ “ፓርላማ ግቡ አትግቡ” በሚባልበት ወቅት ሃሣብ በመስጠት ተሣታፊ ነበራችሁ። በዚያን ወቅት ገለልተኛ የሲቪል ማኅበራት አባላት በሚያሰኛችሁ ሁኔታ ነበር እንቅስቃሴያችሁ?
አቶ ዳንኤል፡- እኛ ተሳታፊ የነበርንበት የሲቪል ማኅበረሰቡ የውይይት መድረኮች ሠላማዊ፣ ሕጋዊና ነፃ ውይይት መድረኮች ናቸው። በወቅቱ አንዱ የፖለቲካ ጥያቄ የነበረው ነገር እንደሚታወሰው ቅንጅት ወደ ፓርላማ እገባለሁ አልገባም የሚል ጥያቄ በማስነሳቱና ከዚህ ክርክር ጋር በተያያዘ የተፈጠረ የፖለቲካ ግለት የነበረ መሆኑ ይታወሳል። የተለያየ አስተያየት የነበራቸው ሰዎች እንደነበሩም ይታወቃል። እኛ የነበርንበት የሲቪል ማኅበረሰብ የውይይት መድረክ ላይ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑም የየራሳቸው አስተያየት የነበራቸው ሰዎች ናቸው። የየበኩላቸውን አስተያየት አንፀባርቀዋል። “ፓርላማ መግባት ትክክል አይደለም” የሚል አስተያየት ያለው ሰው ነበር። “የለም ይህ ነገር ፓርላማ የመግባትና ያለመግባት ጉዳይ ሳይሆን ሌላ መፍትሄ የሚሻ ስለሆነ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት” የሚል አስተያየት የነበረውም ነበረ። እንዲህ ዓይነት አስተያየት ያለው ሰው አሁንም ሊኖር ይችላል ማንም ሰው የራሱን አስተያየትና ሃሳብ የመያዝ መብት አለውና።
አቶ ነፃነት፡- የመሰላቸውን ሃሣብ የገለጹ የተለያዩ ሰዎች ነበሩ። በሌላ በኩል ደግሞ “ይኼ የፖለቲካ አጣብቂኝ ሊፈታ የሚችለው ተቃዋሚው ፓርቲ በምርጫ ቦርድ የተረጋገጠለትን የፓርላማ ወንበሮች ተረክቦ ወደ ፓርላማ በመግባትና በሕጋዊ መንገድ ትግሉን በመቀጠል ነው የፖለቲካ ችግሩ የሚፈታው” የሚል አስተያየት የነበረን ሰዎች ነበርን። ስለዚህ እኛም ይኼንን በግላችን የምናምንበትን ትክክለኛ ነው ብለን ያሰብንበትን አስተሳሰብ ሌሎች የሥራ ጓደኞቻችን እንዲቀበሉት በማግባባት ጥረት አድርገናል። እኛ ትክክል ነው ብለን ያሰብንበት አካሄድ ነበር። በሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት መካከል ሁለት ቀን የፈጀ ስብሰባ ነው የተደረገው። ከብዙ ውይይት በኋላም ጠቅላላው የውይይቱ ተሳታፊዎች ወደ አንድ ዓይነት ሃሣብ በመሰባሰብ ይኼንኑ መሠረት ያደረገ የሠላም ጥሪ ያሰሙ መሆናቸው ይታወቃል። ተቃዋሚዎች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሸናፊነታቸው የተረጋገጠላቸውን የፓርላማ ወንበሮች ተረክበው ወደ ፓርላማ እንዲገቡ፣ ውዝግብ ያስነሱ የምርጫ ክልሎች በሚመለከት የተፈጠረው ውዝግብና ክርክር በሕጋዊ መንገድ በፍርድ ቤት እንዲፈታ፣ በወቅቱ ለክርክር ምክንያት የሆኑ አንዳንድ ጉዳዮች ለምሳሌ ስለ አዲሱ የፓርላማ ሕግ፣ ስለሚዲያ አጠቃቀም፣ በወቅቱ ተከስቶ ስለነበረው አደጋ ጉዳይ ደግሞ ምን ዓይነት የመፍትሄ አቅጣጫ ሊያዝ እንደሚገባ ሃሣቦች የተሰጡበት ነበር። አንዳንድ ሃሣቦች በዚያው መሠረትም ርምጃ ተወስዶባቸዋል ማለት ይቻላል። ስለዚህ ይህን የመሰለ አስተያየት ነው የሰጠነው። ይህ ደግሞ በጣም ነፃና ገለልተኛ የሆነ፣ ከሲቪል ማኅበረሰቡ የመነጨ በጣም ጠቃሚ አስተያየት ይመስለኛል። ምናልባትም አሁን ቁጭ ብለን ወደ ኋላ ሄደን ስናስበውና ስናስተውለው ከሲቪል ማኅበረሰቡ የቀረበው ጥሪ ተቀባይነት አግኝቶ በዚያ መንገድ ተሂዶ የነበረ ቢሆን ኖሮ ሁኔታው የተለየ ሊሆን ይችል ነበር ብለን እንገምታለን። ስለዚህ እኛ ተሣታፊ የነበርንበት የቀረቡት ሃሣቦችና አስተያየቶች ሙሉ በሙሉ ነፃ፣ ገለልተኛና ከእውነተኛ ስሜት የመነጨ እንጂ የትኛውንም የፖለቲካ ቡድን አስተሳሰብ ከመወገን ጋር የተያያዘ አልነበረም።
የሲቪል ማኅበረሰቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት ሳያገኙ በመቅረታቸው የትኛው ወገን ነው ተወቃሽ የሚደረገው?
አቶ ነፃነት፡- እንግዲህ ጉዳዩን በተወቃሽና ተጠያቂ ማነው በሚለው አቅጣጫ ማየቱ አግባብ አይደለም። ቀደም ሲል ዳንኤል እንደጠቀሰው ከሲቪል ማኅበረሰቡ በኩል የቀረበው የሠላም ጥሪ ሃሣብ የነበሩትን መቀበልና ተግባራዊ ማድረግ የነበረባቸው ወገኖች በሙሉ በወቅቱና መደረግ በነበረበት ጊዜ ውስጥ ሁሉም የበኩላቸውን አድርገው ቢሆን ኖሮ ምናልባት ያኔ በወቅቱ የተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ እንዳይፈጠርና የተጀመረው የዲሞክራሲና የሠላም ሂደቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር ብለን እናምናለን። በወቅቱ ማድረግ የሚገባቸው ወገኖች ሁሉ ምናልባት ይሄ ሃሣብ አልታያቸው ብሎ ይሆናል ወይ ሁኔታው አልፈቀደላቸው ይሆናል።
አቶ ዳንኤል፡- ጉዳዩ በዚህ መልኩ እልባት አግኝቶ ይቀጥል ይችል ዘንድ ማድረግ የነበረባቸው ወገኖች በሙሉ አላደረጉም ብዬ አምናለሁ። ቢደረግ ምናልባት ብዙ ነገር ሳይፈጠር ሊቀር ይችላል ብዬ እገምታለሁ። እንዲህ ያደረገው ይሄኛው ወገን ነው ያኛው ወገን ነው ማለት ግን በጣም ያስቸግራል። ምናልባት በአጠቃላይ ማለት የሚቻለው በብዙ ወገኖች በኩል የተሳሳተ ውሣኔ እና አካሄድ ተከትለው ሊሆን ይችላል። አሁን በተለይ ወደኋላ በሂደቱ ላይ የተፈጠረው ነገር ሲታይ ብዙ ወገኖች ራሳቸው ይሄን ሁኔታ እንዳይፈጠር እንቅስቃሴ ብናደርግ ይሻል ነበር ብለው እንደሚገመግሙ ግምት ወስጃለሁ። ይህ እንግዲህ ሃሣቡ የሚመለከታቸው ወገኖችን ሁሉ ማለት ነው። ምናልባትም ያ ጊዜ እንደ ሀገር፣ እንደ ህዝብ፣ እንደ ማኅበረሰብ በተወሰነ መልኩ ለውድቀት የተዳረግንበት ወቅት ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ።
እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ አባልነታችሁ ያለፈው ሂደት በተለይ የሰብዓዊ መብት አያያዙና የዲሞክራሲ ሂደቱን በሚመለከት ኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል ትላላችሁ?
አቶ ነፃነት፡- እኛ ከእስር ቤት ከተፈታን አጭር ጊዜ ስለሆነን አሁን ያለው የፓለቲካ መጫወቻው ሜዳ (Space) የመንቀሳቀስና የመደራጀት ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን ለመገምገም ዕድሉን አላገኘንም። ነገሮችን እየተገነዘብን ነው። ወደፊት አሁን ያለውን ሁኔታ ማነፃፀርና አስተያየት ለመስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ሊኖር ይችል ይሆናል። ማለትም ምርጫ 97 አካባቢ የነበረው መነሳሳት፣ መቻቻል፣ የህዝብ ተሳትፎና የመሳሰለው በወቅቱ በተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ የተነሳ በተወሰነ መልኩ ተጎድቷል የሚል ግምት አለኝ። አገሪቱ በዲሞክራሲያዊ ሂደት ምን ያህል ወደፊት መግፋት ትችል እንደነበርና ምን ያህል ደግሞ ወደኋላ መልሷታል የሚለውን አሁኑኑ መልስ ለመስጠት አስቸጋሪ ሊሆንብኝ ይችላል። ነገር ግን በብዙ መልኩ በዲሞክራሲያዊ ሂደቱ፣ በህዝቡ መነሳሳትና በነበረው የመተማመን (tolerance) ሂደት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሶባታል እላለሁ።
አቶ ዳንኤል፡- ከእስር ከወጣን አጭር ጊዜ በመሆኑ አሁን በአገራችን ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ሜዳ፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ ሥራውን የሚያከናውንበትን ከባቢያዊ ሁኔታ ምን ያህል አመቺ ነው? ምን ያህል የፖለቲካ ሜዳ አለ? የሚለውን ለመገምገምና አስተያየት ለመስጠት የሚያስችለን አይመስለኝም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ 97 የተከሰተው ሁኔታ አሉታዊ ተፅዕኖ አላሳደረም ማለት አይቻልም። አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮአል። ይህ እንግዲህ የተፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀስ እያለ የመንቀሳቀሻ ሜዳው፣ የሥራ ማከናወኛ አካባቢያዊ ሁኔታው እየተሻሻለ የሚሄድ ከሆነ የበለጠ መልሶ ወደነበረበት ሁኔታ ላይ የመመለስ ዕድል ሊኖረው እንደሚችል እገምታለሁ። አሁን ግን የሚገኝበት ሁኔታ እንደዚህ ይመስላል ብሎ አስተያየት ለመስጠት ከእስር ከወጣን በጣም አጭር ጊዜ ስለሆነ አስተያየት መስጠት ያስቸግር ይሆናል።
ከአሁን በኋላ ተመሳሳይ በሆነ የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ውስጥ ዳግመኛ አንመለስበትም የሚል አቋም አላችሁ?
አቶ ዳንኤል፡- አሁን ያለነው ዕረፍት ላይ ነው። ከዕረፍት በኋላ በምን ሥራ እንደ ምንሠማራ ገና እንወስናለን። አሁን ሥራችን ወይም የሕይወት መስመራችን ምን ይሆናል የሚለውን ገና አልወሰንም። ነገር ግን በዚህ አጋጣሚና ሁኔታ የተነሳ በሲቪል ማኅበረሰብ ሥራ ዘርፍ ላይ ሁለተኛ ፊታችንን ወደዚያ አናዞርም የሚል የመረረ ስሜት አልፈጠረብንም። ምክንያቱም እኛ ያካሄድነው ሥራ በሚገባ ለፍርድ ቤት አስረድተን የተሰማራንባቸው ሥራዎች ሕጋዊና ሠላማዊ ብቻ ሳይሆኑ በጣም ጠቃሚና ሊመሠገኑ የሚገቡ መሆናቸውን ያረጋገጠ ስለነበረ እኛ በዚህ ነገር የተነሳ ችግር የደረሰብን ቢሆንም ከእንግዲህ ፊታችንን ሲቪል ማኅበሩ ላይ ሥራ አናዞርም የሚል ስሜት ላይ ግን አልጣለንም።