አብሮነት

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (#አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (#አብሮነት) ከግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን የተከሰተው “የለውጥ ሒደት” መሰረታዊ የአገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል አግባብ ያልተካሄደና የከሸፈ መሆኑን በመገንዘብ አገሪቱን ወደ አንድ አዲስና ጤናማ የሽግግር ሒደት የሚያስገባ አማራጭ ሐሳብ በረቂቅ ደረጃ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ውይይት ማቅረቡ ይታወቃል።

ከኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን መግባት ጋር በተያያዘ በረቂቅ ሰነዱ ላይ በአሰብነው መጠን ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሔድ ባንችልም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ቀላል የማይባል የሕብረተሰብ ክፍል በረቂቅ ሰነዱ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ማድረግ ተችሏል። በአብሮነት አባል ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ መዋቅሮች በረቂቁ ላይ በስፋት እንዲወያዩበት የተደረገ ሲሆን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ከተገኙ ግብአቶች በተጨማሪ ከ700 በላይ የሆኑ አስተያየቶች በኢሜል አማካኝነት መሰብሰብ ተችሏል። የተለያዩ ምሁራንና የፖለቲካ መሪዎችም ሰነዱ እንዲደርሳቸውና ሐሳብ እንዲሰጡበት ማድረግ ተችሏል።

እነዚህን ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ አስተያየቶች ባገናዘበ ሁኔታ የአብሮነት አባል የሆኑት ሦስቱ ፓርቲዎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ካካሄዱበት በኋላ ገንቢ የሆኑ ማሻሻያዎችን በረቂቅ ሰነዱ ላይ በማድረግ ይህንን የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ሰነድ የጋራ ሰነዳቸው እንዲሆን ተቀብለውታል። በይዘት ደረጃ ማሻሻያ የተደረገባቸው ጉዳዮችም ሁለት ናቸው።

አንደኛ- አገር አቀፍ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ጉዳይ አወዛጋቢ የፖለቲካ አጀንዳ እየሆነ በመምጣቱ የሽግግር መንግሥቱ አንዱ ኃላፊነት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ማካሔድ እንዲሆን፤ ሁለተኛ- የሽግግር መንግሥቱ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ረቂቅ የማቅረብ ብቻ ሳይሆን በሕዝበ-ውሳኔ ሕገ መንግሥት የማሻሻል ኃላፊነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። እነዚህንና ሌሎች መለስተኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሰነዱ ከዛሬ ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሦስቱ አባል ድርጅቶችና የአብሮነት ኦፊሴላዊ ሰነድ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፤ የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡ ጥያቄውን እስከሚቀበሉት ድረስ ሰነዱ አንድ ቁልፍ የፖለቲካ የመታገያ አጀንዳችን ሆኖ እንዲቀጥል ተወስኗል።

አብሮነት በወቅታዊው የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የረጅም ጊዜ ግምገማ አካሂዶ የደረሰበት አቋም “አገራችን ኢትዮጵያ ከእንግዲህ መዋቅራዊ ችግሮቿን በአስተማማኝ ሁኔታ ሊፈታ በሚችል ውጤታማ የሽግግር ሒደት ውስጥ ማለፍ እስካልቻለች ድረስ እንደተለመደው በየአምስት ዓመቱ የይስሙላ ምርጫ በማካሔድ ወደ መዋቅራዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር አትችልም” የሚል ነው።

በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ የሚገኘውና ከሁለት አመት በፊት ሥልጣን ለመያዝ የበቃው ብልጽግና ፓርቲ በአገሪቱ ውጤታማ ሽግግር ለማካሔድና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ቃሉን ጠብቆ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ማሸጋገር አልቻለም። ፓርቲው ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል እውቀትና ልምድ ብቻ ሳይሆን ቅንነትና ፍላጎት የሌለው ኃይል በመሆኑ ምክንያት አገሪቱን ወደ በጎ አቅጣጫ ከመምራት ይልቅ የራሱን የፖለቲካ ሥልጣን በማጠናከር ወደ ለየለት አምባገነናዊ ኃይልነት መቀየርን የመረጠ ይመስላል።

ይህ ኃይል እራሱንም ሆነ አገሪቱን ወደ ከፍተኛና ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከማስገባቱ በፊት፣ በአገሪቱ የምንገኝ የፖለቲካ ኃይሎችና የአገሪቱ ዋና ባለቤት የሆነው ሕዝብ ተባብረን በህጋዊና ሰላማዊ ትግል ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገባ ካላስገደድነው በስተቀር በአጭር ጊዜ ውስጥ በታሪካችን አይተነው ወደማናውቅ አምባገነናዊ ኃይል እራሱን ሊቀይርና አገሪቱንም ከባድና ውስብስብ ወደ ሆነ አደጋ ሊያስገባት ይችላል።

አብሮነት አገራችንን ከእንዲህ አይነት አስፈሪ ጥፋት መታደግ የሚቻለው በቂ የስነ-ልቦናና የመዋቅር ዝግጅት ያልተደረገበት አገራዊ ምርጫ በማካሔድ ሳይሆን፣ ለሁለት አመት የሚቆይ ሁሉን አቀፍ የሆነ የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ነው ብሎ በፅኑ ያምናል።

መዋቅራዊ የሆኑ የፖለቲካ ችግሮቻችንን በአግባቡ ለመፍታት በሚያስችል የሽግግር ሒደት ውስጥ እስካላለፍን ድረስ ግን ላለፉት 29 ዓመታት በሥልጣን ላይ በቆየው ገዢ ፓርቲ፣ በስራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት እየተመራንና ከአለፉት አምስት ምርጫዎች ያልተለየ ስድስተኛ ዙር ምርጫ በማካሔድ የአገራችንን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት አንችልም። እንዲያውም ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች የተለየና የተሻለ ማድረግ እስካልቻልን ድረስ አገራችን ህልውናዋን ወደሚፈታተን የእርስ በእርስ ጦርነት ወይም መንግሥት የለሽ ሁኔታ ልትገባ ትችላለች የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለን። ይህንን የሽግግር መንግሥት ሰነድ ብዙ ተጨንቀንና ተጠበን እንድናዘጋጅ ያስገደደንም ይኸው ስለ አገራችን ህልውና መቀጠል የሚሰማን ሥጋት ነው።

ይህ ለአገራችን ህልውና መቀጠል መድህን የሚሆን የሽግግር መንግሥት መቼና እንዴት ሊቋቋም ይችላል? በማንና ለምን ሊቋቋም ይገባዋል? ሂደቱና የመጨረሻ ግቡስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር ለመመለስ በሚያስችል መጠን ተዘጋጅቶ ቀርቧል። ስለሆነም-

ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች “አገራችን ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዳ በዘላቂነት ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር በምን አይነት የሽግግር ሒደት ውስጥ ማለፍ ይገባታል?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የየራሳቸውን ዝርዝር አማራጭ ለውይይት እንዲያቀርቡ፤

የኮሮና ቫይረስን ስርጭት በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማያስተጓጉል ሁኔታ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ዙሪያ ውይይትና ድርድር አካሒደው የጋራ መፍትሔ የሚያመነጩበት አገራዊ የምክክር ሒደት /National Dialogue/ በፍጥነት እንዲያመቻች፤

የኢትየጵያ ሕዝብም በአንድ ውጤታማ የሽግግር ሒደት ማለፍ ለአገሪቱ ችግሮች በዘላቂነት መፈታት አስፈላጊና የማይተካ ሚና ያለው ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን በመገንዘብ አገራዊ የምክክር ሒደት እንዲጠራ የራሱን ግፊትና ትግል እንዲያደርግ አብሮነት በአፅንኦት ይጠይቃል።

ከዚህ ውጭ ገዢው ፓርቲ ላለፉት 29 ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም “የአገሪቱን እጣ-ፈንታ መወሰን የሚገባኝ እኔ ብቻ ነኝ” በሚል መታበይ ወይም “እኔ አሻግራችኋለው” በሚል ያልተገባ ፍልስፍና በሥልጣን ላይ የሚቀጥል ከሆነ ግን አገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አደገኛ የብጥብጥ አዙሪት ልትገባ የምትችልበት እድል ሰፊ ነው። አገራችን ከዚህ አይነቱ አሳሳቢ ሥጋት ወጥታ ወደ ዘላቂ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በየበኩሉ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል።

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (#አብሮነት)
ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!