Amhara Region Prosperity Party

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

ለትግራይ ሕዝብ ሲባል ሕወሓትን ያቀፈ የትግል ስልት መከተል ሆደ-ሰፊነት እንጂ ድንቁርና አይደለም። እስከአሁን በነበረው የትግል ጉዞ ሕወሓትን ከልክ በላይ መታገስ መስተዋሉ ተገቢና ትክክለኛ አቅጣጫ ነው። አሁንም ቢሆን ለትግራይ ሕዝብ ያልተመቸ ምንም አይነት ሁኔታ መከተል አያስፈልግም። የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት በፍጹም አንድ አይደሉም፤ አንድ ሆነውም አያውቁም።

የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት ተጽዕኖ ሊላቀቅ የሚችለው በራሱና በራሱ ትግል ብቻ ነው። በእርግጥ በአለም ታሪክ የትግራይ ሕዝብ ለሕወሓት የሰጠውን ተደጋጋሚ እድል የትኛውም አገርና ሕዝብ አላደረገውም። እንደአለመታደል ሆኖ ሕወሓት ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ራሱን በራሱ የሚያርምበት አንዳችም የልቡና ውቅር (psychological set up) የለውም። ለዚህም ነው ደጋግሞ መሳሳትን እንደአንድ የትግል ስልት የሚጠቀምበት።

ሕወሓትን የምንታገለው ከትላንትናው የተለየ ጥፋት ዛሬ ላይ ስለፈጸመ አይደለም። ደጋግሞ ስሕተት መስራት ለሕወሓት ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው። የአማራን ሕዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕወሓት የተሳሳተ አመራርና የትግል ስልት ተጎድቷል። ዛሬም ድረስ በቀቢጸ ተስፋ የትግል ስልት የሚሰቃይ ሕዝብ ነው። በተለይም የአማራ ክልል ሕዝብ የግፉ ሁሉ ገፈት ቀማሽ ነው። መሬቱንና ሕዝቡን በግፍ ተነጥቋል። ቅርሱን፣ ታሪኩን፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱን በሚያሳቅቅ ሁኔታ ተዘርፏል። ክብሩና ማንነቱ በጠራራ ጸሀይ ተደፍሯል። ከወንድሞቹና ከወገኖቹ ጋር ተከባብሮና ተፋቅሮ እንዳይኖር የቂምና የጥላቻ ቀለም ተበጥብጦ በሀሰት ብራና ላይ የቁርሾና የበቀል ስንኝ ተቋጥሮበታል። ይህ ሁሉ ሲሆን ”ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” በሚል ብልሀት ሁሉንም ታግሶ ለማለፍ ተሞክሯል።

በዚህ ሁሉ ስሕተት ጥርሱን ነቅሎ ያደገው ሕወሓት ግን ከስሕተቱ መማር አልቻለም። ይልቁንም ራሱን የቻለ አንዳች የተለየ የጀግንነት ዘረመል (exceptional heroic gene) ያለ ይመስል የአማራን ክልል ሕዝብ ዝቅ የሚያደርግ የጦር አምጣ ቅዠቱን ሲያነበንብ መዋሉ በእጅጉ ያሳፍራል። የአማራ ክልል ሕዝብ በየትኛውም የትግል መድረክም ሆነ የጦር ውሎ የተሸናፊነት ታሪክ የለውም። ወደፊትም ሊኖረው አይችልም። የተሸናፊነት ስነልቦናን በመጠጋገን ወደአሸናፊ ስነልቦና መለወጥ ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። ሕወሓት በተሸናፊ ስነልቦና የሚሰቃይ እግሩ ወደመሬት የገባ ሙት ድርጅት ነው። ነገር ግን የተሸነፈ ስነልቦናውን በጦር አምጣ ምኞት ለማከምና በንጹሀን ደም ምሱን ለማርካት የትግራይን ወጣት ወደተሳሳተ መንገድ በመምራት አጀንዳ የማስቀየር ስልት እስከመከተል የሚደርስ ኃላፊነት የማይሰማው እኩይ ድርጅት ነው።

እስከአሁን ድረስ የተፈጠረው ስሕተት በድርድር ወይም በዴሞክራሲያዊ ውይይት ይፈታል በሚል ጊዜ የተሰጠው ሕወሓት ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል አጉራ ዘለል ድርጅታዊ ትምክህት የተለያዩ የጥፋት ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም የአማራ ክልልን፣ አዲስ አበባንና ከክልሉ ውጭ የሚኖረውን የአማራ ሕዝብ እረፍት በሚነሳ ሁኔታ ለጥቃት የሚያጋልጥ ተጨማሪ ሴራ መጎንጎን ጀምሯል። የሕወሓት ሴራ ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ድንበር የለሽ ባንዳዎች ስለሆኑ የውስጥም የውጭም ተላላኪዎችን ያቀፈ የገዳይ ስኳድ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከራሱ ከሕወሓት መካከል የሚመለመሉ ጥቂት የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ፍቅረንዋይ ያሰከራቸው ሆድአደር ምርኮኞች መኖራቸው በአንድ በኩል የተረጋገጠ ሲሆን በሌላ በኩል ኦነግ ሸኔን የመሳሰሉ ጽንፈኛና አክራሪ ቡድኖች ዋነኛ የጥፋት መሳርያዎች ናቸው።

እነዚህ አካላት በዋናነት እንደሀጫሉ ያሉ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ከፍተኛ ምሁራንን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን፣ ዝነኛ አርቲስቶችንና የጥበብ ሰዎችን፣ ስመጥር ባለሀብቶችን፣ በሕብረተሰቡ መካከል ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውን ግለሰቦችና የመሳሰሉትን በግፍ ለመግደል አቅደው ገዳይ ቡድን ያሰማሩ ሲሆን ለግድያው የተቀነባበረና በምስል የታገዘ ቪዲዮ በመልቀቅ ክልሉን አኬል ዳማ ለማድረግ አልመው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

በተለይም ግድያውን ምክንያታዊና ሰበብ ተኮር ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ለመጠቀም ማቀዳቸው ይታወቃል። ሀጫሉ ከመሞቱ በፊት በኦሮምያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ቃለመጠይቅ የተደረገለት መሆኑና እሱን ተከትሎ በማህበራዊ ድረ-ገጽ ትስስር ይደረግ የነበረውን ሰጣ-ገባ አይነት ስረ-ምክንያት ከማዋቀር ወደኋላ አይሉም። ለዚህ እንዲቀናቸው የብሔረሰብ ዞኖችን፣ የኢንቨስትመንት ቀጠናዎችን፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከልና ከመንግሥት ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እንደ ግጭት መነሻ በመጠቀም እርስ በእርስ ለማጣላትና አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን እርስ በእርስ ለማናከስ የሞት ሽረት ትግል ያደርጋሉ። በተመሳሳይ ከፍ ያለ ስም ያላቸውን የሃይማኖት ተቋማት፣ የተፈጥሮ መስህቦችን፣ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችንና በአጠቃላይ የልማት ተቋማትን እስከማቃጠል የሚደርስ ዘመቻ ያደርጋሉ።

የሕወሓት ቡድን ዋነኛ አላማ እንደአገር የብሔር ግጭት ማስነሳትና የተረጋጋ አገር እዳይኖር በማድረግ የተጀመረውን ለውጥ መቀልበስና በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በሂደት የሕወሓትን አመራር ቅቡል እንዲሆን ማስቻል ነው። ይህ ካልተሳካ ለሁለተኛው ግብ ማለትም በዘረፋና በቅሚያ የበለጸገው የሕወሓት ቡድን ያለምንም ተጠያቂነት ልዕልናው ተጠብቆለት በትግራይ የሥልጣን ክልል ምስለ መንግሥት (defacto state) ሆኖ መቆየት ነው።

ሕወሓት እንደወትሮው ሁሉ ለጦርነት ቀርቶ ለአቅመ ኩርፍያ የሚያበቃ ነባራዊ ሁኔታ በሌለበት ስነ-ምህዳር ጸብ የሚጠማው ድርጅት ነው። በአሁኑ ሰአትም ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው ሁሉም አካባቢዎች የትንኮሳ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። ምሽግ በስፋት መቆፈር፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የታጠቀ ኃይል ማሰማራት፣ በክልል ደረጃ መያዝ የሌለባቸው የተለያዩ የቡድን መሳርያዎች የታጠቁ ኃይሎችን በማፈራረቅ የአካባቢውን ሰላም ማወክ፣ የሕወሓት ነባር አመራሮችና በወንጀል የሚፈለጉ የደህንነት ሰዎች በአካባቢው አሰማርቶ የቅኝት ስራ መስራት፤ በአጠቃላይ ለጦርነት የመዘጋጀት ዝንባሌ በተካረረ መንገድ ይስተዋላል።

የዚህ ሁሉ ዝግጅት ምክንያቱ ተስፋ መቁረጥና ከወደቁበት አዘቅጥ ለመውጣት የሚያደርጉት የሞት ጣር ትንቅንቅ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!