National Election Board of Ethiopia (NEBE)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16 እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ይከናወናል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን አውጥቶ ተግባራትን እያከናወነ እንደኾነ ይታወቃል። ከዚህም መካከል በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው የእጩዎች ምዝገባ አንዱ ሲሆን፤ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ተከታዩ ዋና ተግባር የመራጮች ምዝገባን ማከናወን ነው።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ተግባራትን ማከናወን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል የምርጫ ክልል ቢሮዎች ዝግጅት መዘግየት እና አስፈጻሚዎች ሠልጥነው ከተሰማሩም በኋላ ቢሆን ቢሮዎች ዝግጁ ኾነው ባለመገኘታቸው የቢሮ መከፈት መዘግየቱ፣ በተወሰኑ ክልሎች አስፈላጊው ቢሮዎች ተዘጋጅተው ባለማለቃቸው የእጩዎች ምዝገባ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት መጀመር አለመቻሉ እና ለሁለት ዙር መከፈሉ፣ ለምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት የትራንስፖርት እጥረት እና የገለልተኛ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሒደት ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጊዜ የሚወስድ ተግባር መኾኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በዚህም መሠረት ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልገው በመረዳት በመጀመሪያ ዙር የእጩዎች ምዝገባ በተጀመረባቸው ክልሎች ለ4 ቀናት ያራዘመ ሲሆን፣ በሁለተኛ ዙር የእጩዎች ምዝገባ የተጀመረባቸው ክልሎችም ላይ የቢሮዎች ዝግጅት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ችግር ኾኖ እንደነበር ተረድቷል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ተግባርንም እያከናወነ እንደኾነ ይታወሳል፤ 140 ሺህ በላይ እጩ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚነት የሚሠሩ ግለሰቦችን አዘጋጅቶ ገለልተኝነት ማጣራትን እያከናወነ ሲሆን፣ ይህም ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ሊወስድ ችሏል።

በመኾኑም ከክልሎች የሚገኘው የቢሮዎች ትብብር በመዘግየቱ፣ የእጩዎች ምዝገባ ቀናት ከተጀመሩም በኋላ ዝግጁ ያልኾኑ የተወሰኑ ቢሮዎች የነበሩ በመኾኑ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ተጨማሪ ቀናት በመጠየቃቸው እና የእጩዎች ምዝገባ በመራዘሙ፣ እንዲሁም በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠመው የቁሳቁስ ማጓጓዝ ተግዳሮቶች በመገምገም እና የእጩ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት የማጣራት ሥራን በተሻለ ጥራት ለማከናወን የመራጮች ምዝገባን ከተያዘለት ቀን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ መጋቢት 16 ቀን 2013 እንዲዘዋወር ወስኗል።

በመኾኑም የ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16 እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚከናወን ሲሆን፤ ቦርዱ ለወደፊትም ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃዎችን የሚያቀርብ ይኾናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ