መች ገባና ወጣሁ ይላል? አቶ ሙሴ ተገኝን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር የተሰጠ መግለጫ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትዮ ሚዲያ በተባለውና የትግራዩ ተወላጅ አቶ አብርሃ በላይ በሚያስተዳድረው ድረ ገጽ አማካይነት አቶ ሙሴ ተገኝ በድርጅታችን ላይ የከፈተውን ዘመቻ በተመለከተ ምላሽ ላለመስጠት ያደረግነውን ጥረት ወገን ሁሉ ይረዳዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ነገር ግን አቶ ሙሴ ተገኝ በጥቂት የአካባቢው ሰዎችና ጸረ ኤርትራ ህዝብ ጭፍን አመለካከት ባለቸው ግለሰቦች እየታገዘ በየዕቁብ ቤቱ ሳይቀር የከፈተው ጥቃት እየጨመረ በመምጣቱና የግለሰቡ ጉዞ ያበሳጫቸው ወገኖችም ለምን ምላሽ አይሰጠውም በሚል ባቀረቡልን ተደጋጋሚ ጥያቄ መሰረት ይህን መግለጫ እንድናወጣ ተገደናል።
አቶ ሙሴ ተገኝ ወይንም በተለምዶ አጠራር ፕሮፌሰር ሙሴ ሰሞኑን ከኤርትራ ለቀን ወጥተናል በማለት ራሱን እንደ ኢህአግ አባልና መሪ በመቁጠር የህይወት መስዋዕትነትን ዛሬም እየከፈለ ባለፈው አርበኛ ሰራዊት ደም መቀለዱን ስንሰማ የተሰማን ስሜት አስቆጪ እንደሆነ መግለጽ የተገባን ይሆናል።
በሰላማዊ ትግል ስም እየማሉና ከአምባገነኖች ጋር እየተሻሹ መቆየት ቀላል ሲሆን ጠመንጃ አንስቶ ለፍልሚያ መዘጋጀት አይደለም ጠመንጃ ካነሱ አርበኖች ጋር እንኳ ቆሞ ማውራት ብቻውን ምን ያህል ላብ ላብ እንደሚልና መች ከዚህ ቦታ ጠፍቼ እንደሚያሰኝ ያሳለፍናቸው ተሞክሮዎች አያሌ ናቸው።
ጠመንጃ አንስቶ ስርዓት ለመለወጥ የሚታገል ድርጅት ፋራ ነው እያሉ ሲሳለቁብን ከነበሩ የሰላማዊ ትግሉ ፋኖዎች አንስቶ ከአርበኞቻችን ጋር ፎቶ ግራፍ እየተነሱ አርበኛ አርበኛ ለመሽተት ብሎም “የመሃይምናኑ” አርበኞች መሪ ለመሆን በስተጀርባ ሲሯሯጡብን የነበሩትን በትግስት ያስተናገድንበትም ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ታግለው ባታገሉንና በትረ ስልጣኑን በጨበጡ እሰየው በነበረ ። ቅር የሚያሰኘውና እንባ እንባ የሚለው ግን በርቀት በሪሞት ኮንትሮል ካልተቆጣጠርናችሁ ማለታቸውን ጠልተን ፊታችንን ስናዞርባቸው በጠላትነት የሚፈርጁን ዝና በግዱ ግለሰቦች ለወያኔ ገመናችንን ማደላቸውና መረጃችንን ማሰራጨታቸው ይብሱን ጎዳን እንጅ።
በአዲስ መንፈስ ራሱን ያዘጋጀውና ወደ ወያኔ ጉያ ለመግባት ሰውነቱንን እያሟሟቀ የሚገኘው የዛሬውም አቶ ሙሴ ተገኝ ከነኝህ ከላይ ከጠቀስናቸው አንዱ ሲሆን በርዕሳችን ላይ እንዳመለከትነው ግለሰቡ ሲጀመርም የአርበኞች ግንባር እንኳን መሪ፤ ሙሉ አባል ያልነበረ የጤናው ሁኔታ እንኳ አጠራጣሪ በመሆኑ አርበኛው በሙከራ አባልነት በአስመራ ከተማ ነዋሪ በመሆን እንዲቆይ የወሰነበት ግለሰብ መሆኑን በቅድሚያ መግለጽ እንወዳለን።
ለዕለታዊ ኑሮ ቅመም መጨመርንና ለአንዲት ቀን አዳር ብትሆን ውበት መስጠትን የተካነበት ሙሴ ተገኝ የገንዘብ ምንጭንም ማፈላለግ እንዲሁ አብሮ አድጎበታልና ከአለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የመጀመሪያው የአስመራ ከተማ ኢንቨስተርና አካለ ስንኩላንን በስፖርት ማሰልጠን በሚል የረዴት ድርጅት አስተዳዳሪ ሆኖ የቆየ ሰው ነበረ።
የዛሬን አያርገውና በአስመራ ሲሶ መንግስት አለው እየተባለ በወቅቱ ይቀለድበት የነበረው አቶ ሙሴ ተገኝ ፕሮፌሰር በሚለው ስሙ ማልለን በአስመራ ከተማ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ወደኛ ድርጅት ያመጣልናል በሚል የአስመራና አካባቢው የአባላት ማደራጃ ጽ/ቤት ሃላፊ በማድረግና ማህተም በመስጠት ያሰማራነው ሰው ነበረ።
ከኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ አይደለም ከኤርትራውያንም ጭምር ገንዘብ በመቀበልና ማህበራዊ ሙስና ውስጥ በመዳከር ከሃገር ማስኮብለልን እንደተጨማሪ መተዳደሪያ በማድረግ እንዲህ እንደዛሬ ሳይታወቅና በኤርትራ መንግስት የወንጀለኛነት ማህደር ውስጥ ስሙ ሳይካተት የ1990ዎቹ መጀመሪያ ወቅት ነበረ ከግንባራችን አርበኖች ጋር ትውውቅ የፈጠረው።
ኢትዮጵያውያን ማለት የአባይ ተፋሰስ ሃገሮች ማለትም ጎጃም ጎንደርና ከፊል ወሎ ናቸው በማለትና በአባይ ጉዳይ ፈቃድ ልንጠየቅ የሚገባን እና ጎጃሜዎቹ ወይንም እንደሱ አጠራር ፈለገ ግዮኖቹ ብቻ ነን በማለት ጎሰኛ ድርጅት አቋቁሞ የነ መለስ ዜናዊን ዘረኛ ፖሊሲ ያቀነቅን የነበረው አቶ ሙሴ ተገኝ የአስመራ ከተማ ነዋሪ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ጥቂት አዱኛ ሰራሽ ደጋፊዎቹን በዙሪያው በማሰባሰብና የሌላውን አካባቢ ተወላጆች እርስ በርስ በማባላት የያዘው አባዜ ለኛም አርበኖች እንደተረፈ ለሚያዳምጠን ወገን ማካፈሉ ምን ያህል የመከራ ዘመን እንዳሳለፍን ያስረዳልናል የሚል እምነት ይኖረናል።
የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ ካሪዝማ ወይንም የደስደስ ቀድሞውንም ያልተፈጠረበት፤ ከትንሽ እስከትልቅ አክብሮት ተችሮት የማያውቀው፤ዛሬ አንድና ብቸኛ ባህርዩ ዜጎችን በገንዘብ የማማለል ክህሎቱ እንኳ ከላዩ ላይ ወልቃ የሾለከችበት አቶ ሙሴ ተገኝ ከውጭ የረድኤት ድርጅቶች በሚጎርፍለት ገንዘብ ሴት አካለ ስንኩላንን ጭምር ከማባለግ የዘለቀ አንድ ቀን ወንዶች ከዋሉበት ሊያውለው የሚችል ተግባር ላይ ሳይሳተፍ ራሱን አዋርዶ ኢትዮጵያውያንና ህዝቧን ያዋረደ ግለሰብ መሆኑን በድፍረት ለመናገር ግዴታችን ይሆናል።
የረድኤት ድርጅት ሃላፊ በመሆኑና በአስመራ ከተማ የኢሕአግን ደጋፊዎች ያስተባብርልናል በሚል ያስቀመጥነው ሙሴ ተገኝ በተለያዩ ጊዜያት አርበኞቻችንን ለመጎብኘት ወደ ግንባር ሲመጡ ከነበሩት ለምሳሌም ያህል ከሳይንቲስት ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ እንዲሁም አብርሃም ያየህ ጋር በመሆን ከአስመራ ይመጣ በነበረበት ጊዜ ነበረ ከሰራዊታችንና ከመሪዎቻቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የመሰረተው።
ለአርበኞች ግንባር ተዋጊዎች፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ማለት መሃከላቸው የሚተኛ አርበኛ ማለት ነው። ሳይገባ ወጣሁ፤ አባል ሳይሆን መሪ ነበርኩ በማለት ዛሬ ለያዢ እያስቸገረ ያለው ሙሴ ተገኝ ይዞ በሚንቀሳቀሰው የረድኤት መኪና አንዲት ቀን እንኳ አንድ አርበኛ ሳይሳፈርባት፣ ለአንዲት ምሽት እንኳ ከአርበኛው ጋር ጨረቃን ሳያይ፤ የአርበኛውን የሌሊት ህይወት ሳይካፈል ወደሞቀበት የከበርቻቻ መንደር ይመለስ የነበረ ሰው እንደነበረ ለወገኖቻችን መግለጽ የተገባ ነው።
በ1993ቱ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ምስረታ፤ በኋላ የግንባሩ መሪ ከሆነው መስከረም አታላይ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበረው በዕለቱ የክብር እንግዳ እንደነበሩት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት አይነት በክብር እንግድነት ተጋብዞ ተገኘ እንጂ እንደ ተራ የድርጅት አባል እንኳ አንዳችም ስፍራ እልዳልነበረው ለወገን ይፋ ማግድረግ ግዴታችን ነው።
ኤርትራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በሚያካሂዳቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ነውሮች በኢህአግ አባላት ዘንድ የተጠላው ሙሴ ተገኝ ከስራ አስፈጻሚ አባላት ጋር ወደ አርበኞቹ ማሰልጠኛ ይምጣ እንጂ ዛሬ ለጥፋት ተልዕኮ የሚጠቀምበትን ቪዲዮ ካሜራ ያጥፋ ያብራ እንጂ ፤ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ቃላት ብተና ላይ ሲንቀሳቀስ ይስተዋል እንጂ ለአንዲት ቀን እንኳ በላዩ ላይ የለጠፈውን ፕሮፌሰር የተሰኘ አንዳች የሚያክል ትልቅ ስም በአግባቡ ሲጠቀምበት ያልታየ ሰው እንደሆነ ማስረዳት አስፈላጊ ነው።
ዛሬም በጽ/ቤታችን ውስጥ ለላንቲካነት ተጎልታ የምትገኛውን ሰርታ የማታውቅ ዴስክቶፕ ኮምፒውተር ይዞ የተጠጋው ሙሴ ተገኝ ለግል ዝናው ይመቸው ዘንድ በወራት አንድ ጊዜ በማሰልጠኛው እየተገኘ የኢህአግንና የትህዴድ አባላትን በቪዲዮ ይቀርጽ የነበረ ሲሆን ጎጃም ፈለገ ግዮን የሚለው ጠባ ብሄረተኛ ፍልስፍናው ተቀባይ በማጣቱም ኢትዮጵያዊነት የሚል አዲስ መሰል ፍልስፍና በመስበክ ስሙን ለማረቅ የጀመረው በዚህ ወቅት ነበረ።
በ2004 አመተምህረት ከረን ከተማ ከምትገኝ ቡና ቤት ውስጥ ከወያኔ ከድተው ከመጡ የሰራዊት አባላት መሃከል በመንቀስ 6 የጎጃም ተወላጅ ወታደሮች ሰብስቦ ስለ ጎጃም ህዝብ የመገንጠል መብት መከበር ተገቢነትና አባይ የጎጃም ህዝብ ብቸኛ ሃብት ነው በሚል ያቀረበው ትምህርት ተቀባይነትን ሊያገኝ አልቻለም። የሚበትነው በሩ ሁሉ መልሶ እየለበለው እንደሆን የተሰማው ሙሴ ተገኝ ኢትዮጵያዊነትን ለመውደዱ ማረጋገጫ ይሆነው ዘንድ ኢትዮጵያኒዝም የሚባል ገመና መሸፈኛ ትምህርት ለጥቂት ቀናት በአርበኛው የመሰብሰቢያ ታዛ ስር ራሱን ከቪዲዮ እየከተተ ለመስጠት የሞከረውም የዛኑ ሰሞን ነበረ።
በ1996 አመተምህረት ኢህአግ ወደ ህብረት ሲመጣ ከቅርብ ጓደኛው መስከረም አታላይ ጋር በመቀራረቡ ብቻ አሁንም የኢህአግ የአስመራ ከተማ የድጋፍ ጽ/ቤት ሰራተኛና ከአባሎቻችን ላይ ገንዘብ ተቀባይ ሆኖ የሰራ ፤እንዲሁም ያለውን ትርፍ ጊዜ አጋጣሚ ይጠቀምበት ዘንድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎቻችንን ሲገናኝ የቆየ ሲሆን የመሃል ሃገር፤ የጎንደር፤ የአርማጭሆ፤ የወልቃይትና የጎጃም ተወላጆች በሚል የመከፋፈል አባዜ የተጠናወተው ሙሴ ተገኝ ተዋጊዎችን ከፖለቲካ ካድሬዎች፤ እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በማናቆር መሰሪ የመከፋፈል ተግባራትን በተፈጠረለት ትንሽ ቀዳዳ በመጠቀም ሲያከናውን የሰነበተ ፤ የድርጅቱን የአመራር አካላት በመከፋፈልም ገሚሱን ወደ ሱዳን ቀሪዉንም ወደ ሌላ ሃገር እንዲሄዱ አፍራሽ ተግባር ሲፈጽም የከረመ ነው።
በሺህ የሚቆጠሩ አርበኞቻችን የተሰዉለት ድርጅታችን ያለፈባቸው የመከራ አመታት የበዙ እንዲሆኑና በድርጅታችንም ውስጥ ለተፈጠሩት አሳዛኝ ክስተቶችም ዋነኛውንና ከፍተኛውን ሚና ሲጫወቱ ከነበሩት አንዱ ሙሴ ተገኝ መሆኑን ሳንወድ ዛሬ እንድንናገር ስንገደድ በድርጅታችን ውስጥ ለተሰሩ ወንጀሎች አቶ ሙሴ ተገኝና የቅርብ ጓደኞቹ ወደፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ሊፋረዳቸው የሚያስችል መረጃዎች ዛሬም በጽህፈት ቤታችን እንደሚገኙም በተጨማሪ መግለጽ አስፈላጊ ነው።
በጥቂት ተባባሪዎቹ አማካይነት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2000 ዓ/ም ወይንም እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር 2008 ላይ በተጠራው የድርጅቱ 1ኛ ጉባኤ ላይ ወደ ሙሉ አባልነት እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲሸጋገር ከቅርብ ጓደኞቹ በተደረገው ጥቆማ ሙሴ ተገኝ የአንድም አባል ድምጽ ሳያገኝ ጭራሹኑም ቁጣና ሁከት ተቀስቅሶ የነበረ ከመሆኑም በላይ ችግሮቹን ላንዴና ለመጨረሻ ለመቅረፍ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይም በጠቅላላ ድምጽ ከድርጅቱ እንዲወገድ የተወሰነበት ነው።
የፖለቲካ ቆሌ የራቀው ሙሴ ተገኝ ላለፉት አራት አመታት ባዘጋጀው ድረገጽ ላይ የአርበኞቻችንን ምስል በመለጠፍ ምስጢሮቻችንን ከአደባባይ በማኖርና የማሰልጠኛ ጣቢያዎቻችንን ሳይቀር ለጠላት በማስተዋወቅ የእጅ መንሻ እያደረገን የቆየ መሆኑን ወገን ልብ እንዲል እንወዳለን።
አዎ ኢሕአግ ዛሬም ወያኔን እያሳደዱ የሚቀጡ፤ የሚሰዉ፤ እንደወታደር የሚማረኩና የሰቆቃ ሰለባ የሆኑ አርበኞች ያሉት ድርጅት ሲሆን ሙሴ ተገኝ የወያኔን ቴሌቪዥን ገልብጦ ለህዝብ እንዳቀረበውም አምና በወያኔ ተማርከው አምልጠው በመውጣት ዘንድሮም አብረውት የሚፋለሙ አርበኞች ያሉት ድርጅት ነው።
እነ ሙሴ ተገኝ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኖች ግንባር ተዋጊ ኤርትራ ውስጥ የለም ማለታቸው እኛን ሁነው ማውራታቸው ከሆነ ትክክል ናቸው ለማለት እንደፍራለን። ምክንያቱም አዎ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ኤርትራ ውስጥ ምን ይፈይዳልና። የኢሕአግ ሰራዊት አባላት እየታገልን እየደማንና እየሞትን ያለነው በበቀልንበት ምድራችን፤ እትብታችን በተቀበረባትና አባቶቻችን ለዳር ድንበራቸው በወደቁባት መሬታችን ላይ ነው።
እኛ የኢሕአግ ሰራዊት አባላት እንደ አቶ ሙሴ ተገኝ አይነቱን የበሉበትን ወጭት ሰባሪና የክህደት አውራ ዋልጌ ግለሰቦች በጥብቅ እንጠላለን። በገዳዩ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ምክንያት ሃገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ዜጎች ከጅቡቲ ከሱዳንና ከመሳሰሉት አጎራባች ሃገሮች እየታነቁ ወደ ወያኔ እስር ቤት ሲጣሉ፣የኤርትራ ህዝብና መንግስት ግን ዛሬም ድረስ አቅፈው ደግፈው፣ያላቸውንም አቃምሰውንና አልብሰውን ፣ለነጻነታችንም እንበቃ ዘንድ አይዟችሁ በማለት እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ከጎናችን መሆናቸውን በድፍረት እንናገራለን።
የኢሕአግ ተራ አባል እንኳ ሳይሆኑ ከኤርትራ ለቀን ወጥተናል በማለት በየድረገጹና የመነጋገሪያ መድረኩ ያዙን ልቀቁን የሚሉት ግለሰቦች ቁጥራቸው የበዛ በመሆኑ ወገን ሁሉ እኒህን በድርጅታችን ስም የሚነግዱ፣ የድርጅታችንን ማህተም በመጠቀምም ከስደተኛ ወገኖቻችን ጭምር ሳይቀር ገንዘብ በመሰብሰብ መተዳደሪያቸው እያደረጉ ያሉትን ግለሰቦች ወጊዱ ይላቸው ዘንድ በዚህ አጋጣሚ ማስገንዘብ እንወዳለን።
ራስ ሳይጠና ጉተና እንዲሉ ስምንት ሁነው በተሰበሰቡ በሳምንቱ ንፋስ የጣለውን የኤሌክትሪክ ቋሚ ፎቶ እያነሱ ሰራዊታችን ድልን እየተጎናጸፈ ነው ከሚሉ ሃሳዌ መሲሆች ኢትዮጵያዊ ሁሉ ራሱን እንዲያርቅ ስንመክር፤ በውን መሳሪያ አንስተው ገዳዩን ስርዓት በመፋለም ላይ ያሉ ወገኖች ካሉ ግን ዜጋ ሁሉ እገዛ ያደርግላቸው ዘንድ ጥሪያችን እናቀርባለን ። ምክንያቱም በመሳሪያ ሃይል ብቻ ነውና ዘረኛው አገዛዝ ከህዝባችን ጫንቃ ላይ ተሽቀንጥሮ የሚወድቀው፤ ብሎም እውነተኛ ሰላምና ዴሞክራሲ በሃገራችን ላይ ሊሰፍን የሚችለው።
አንድነት ሃይል ነው!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር
መጋቢት 27 ቀን 2004
በስደት ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ
Coordinating Committee of Exiled members of Ethiopian Teachers Association
የተሰጠ መግለጫ
መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም.
ስንት ዘንድሮ ያልፍብናል!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የግፍ አግዛዙን ከጫንቃው ላይ አውርዶ በሕዝቡ ይሁንታ የሚመሠረት ሥርዓት ለመገንባት ብዙ መልካም አጋጣሚዎች ተከስተው እንደዋዛ አልፈዋል። አንደኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ አደጋ ደርሶ ጩኸት ሲያሰማ ሌላው እንዳላየ፤ እንዳልሰማ እየሆነ ነግ በኔን ዘንግቷል ማለት ያስደፍራል። በእርግጥ ሕዝባዊ ትግሎች በየአቅጣጫው ተጀምረው ሲፋፋሙ ጠላቶቻችን በመረባረባቸው የሚፈለገው ድል ርቆብናል። ለድሉ መጨናገፍ ግን የጠላቶቻችን ጥንካሬ አልነበረም ወሳኙ። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጠላቶቻችን አቅም ያጎለበትን ራሳችን መሆናችንን መካድ ከገሀዱ ዕውነት መሸሽ ይሆናል።
ወያኔ ኢትዮጵያን እንዲያፈርስ ውክልና ሰጥተው ባሰማሩት የውጭ ኃይሎች የሞራልና የማቴሪያል እገዛ እየተደረገለት ሲገሰግሥ ለንደን ላይ የተጀመረውን የይስሙላ ድርድር ስናስታውስና የወያኔ አገዛዝ የ 97 ትን ምርጫ በነማን እገዛ መና እንዳስቀረው ስናስብ የምናመሳክረው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ዘረኛው የወያኔ ፓርቲ ዘረኝነትን በአዋጅ ከአረጋገጠ በኋላ የሥልጣን ማሟሻ ያደረገው ለግማሽ ምዕተ ዓመት የዳበረውን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በማፍረስ ነበር። ከዚያም ከ80ሺህ በላይ የሕንጻ ኮንስትራክሽን ሠራተኞች፣የገጠር መንገድ ሰራተኞች…እያለ ማፍረስ ቀጠለ፡፡ከሁሉም በላይ ታሪካዊ የነበረዉ የባሕር ትራንዚት ሰራተኞች በአብዮት (በመስቀል) አደባባይ ከሶስት ወራት በላይ የሌሊት ቁር የቀን ሐሩር እየተፈራረቀባቸው የመብት ጥያቄ እያነሱ ቆይተው በታጣቂ ኃይል በቆመጥ እየተደበደቡ፤ በጫማ እየተረገጡ ሲባረሩ ለምን ብሎ የጮኸላቸው ወገን አልታየም፤ ትብብርም አላገኙም ነበር። ወያኔም የልብ ልብ ስለተሰማው ወኔአችንን በዘንግ እየለካ እንደአስፈላጊነቱ ቅጣት ማውረዱን ቀጥሎ እስካሁን ደርሷል። እንደባህር ትራንስፖርት ሠረተኞች ሁሉ የባንክ ሠራተኞች ባሳዩት ብልህና ቆራጥ ርምጃ መታገዝ ሲገባቸው በምትካቸው ሠራተኛ ለመቅጠር ወያኔ ማስታወቂያ ሲያወጣ ራስ ወዳዶችና ኅሊና ቢሶች ለመቀጠር የባንኩን ቅጥር ግቢና አካባቢውን የድጋፍ ሰልፍ አስመሰሉት ። አሳፋሪ ድርጊትም ነበር። በሂደቱም የባንኩ ሠረተኞች አድማ ከሸፈ።
አንድ ሕዝብ፣ አንድ አገር፣ ፍትህና ነፃነት፣ የሕግ የበላይነት፣ እኩል የትምህርትና የሥራ ዕድል፣ ከዚሁ ጋር ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ የምንል ከሆነ በአንድ የህብረተሰብ አካል ላይ የሚቃጣው ጥቃት የሌላውም ሆኖ ሊሰማን ይገባል። ያንዱ የሙያ /የሥራ መስክ ለሌላው መስተጋብራዊ ጥቅም ያለውን ያህል ችግሩም በዚያው አንጻር ተወራራሽ መሆኑ አያጠያይቅም። በእኛ ዘመን ላይ ጀምሮ እያደገ የመጣ አጉል ባህል ወይም አስተሳሰብ በሌላው መሰዋእትነት መልካም ሥርዓት ግንባታ ፣ ዕደገት ብልጽግና ፍትህ ወዘተርፈ… እንዲፈጠሩ የመፈለግ አዝማሚያ ነው። የበኩሌን ምን ላበርክት ለሚለው ጥያቄ መልስ
ለእያንዳንዱ ዜጋ የሚተው ቢሆንም ተጨባጩ ሐቅ ግን እኔን አይመለከተኝም የሚል ይመስላል። ይኸ አመለካከት መቆም አለበት።
ኢትዮጵያውያን ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ቁም ነገር ወደተግባር ለመለወጥ ባንድነት ቆመን ርምጃ ለመውሰድ ዳተኞች እየሆንን ተቸግረናል። ብዙውን ጊዜ የወያኔ ማወናበጃ ፕሮፓጋንዳ አደንዝዞ ወርቃማ አጋጣሚዎች እንዲያልፉን አድርገናል። የጋራችን የሆኑና ልንቆምላቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ አደጋ ሲያንዣብብ በየግላችን ላይ የማይደርሱ አየመሰለን የጥቃቱ ሰደድ አሳት አገሪቱን በመላ አዳርሶ ዘር፣ሃይማኖት፣ፆታ፣ወጣት፣አረጋዉያን፣አርሶ አደር፣ ሠራተኛ፣ ተማሪ፣ መምህር ወዘተ… ሳይለይ እየለበለበ ይገኛል። ባጠቃላይ የአገሪቱ ሕልዉና አደጋ ላይ ነዉ።
የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ የወያኔን የዘረኛነት ፖሊሲና አምባገነናዊ አካሄድ ከመነሻው የተረዱት ኢመማና መምህራን መራራ ትግል አካሂደው ዙሪያ ገብ መስዋእትነት ከፍለዋል። ወያኔ በማህበራቸው የውስጥ ጉዳይ እየገባ የማተራመስ ተግባሩን እንዲያቆም በኃይማኖት አባቶች፤ ያገር ሽማግሌዎች ሳይቀሩ አበክረው መጠያቃቸውን እናስታውሳለን። በዕውን የታየው ግን አገር በቀል ከሆኑት ድርጅቶችና ግለሰቦች የበለጠ የሞራልና የማቴሪያል ድጋፍ ይገኝ የነበረው ከአገር ውጪ ካሉ ግለሰቦች፣ ከዓለም አቀፍ የትምህርት ድርጅት (Education International- EI) ከአለም አቀፍ ሰራተኖች ማህበር (International labor organization – ILO) ከዓለም አቀፍ የሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን (International Confederation of Trade Union- ICFTU) ከሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) ነበር። መምህራን የሙያ ክብራቸውን፤ የትምህርቱን ጥራት፤ የመደራጀት ነፃነታቸውን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ግብግብ በተወሰነ ደረጃ ዜጎች ከጎናቸው መቆማቸው ባይካድም የትምህርት ጥራትና የተተኪው ትውልድ ዕጣ ፋንታ ያለ ሕዝብ ሁለገብ እገዛ ግቡን ይመታል ብሎ መጠበቅ ስህተት ነው። መምህራን የወያኔ የትምህርት ፖሊሲ “ትውልድ ገዳይ “ ነው ብለው ሲሟገቱ ሕዝቡ ጩኸታቸውን አዳምጦ፤ ወደትግሉ መቀላቀል በትምህርቱ ላይ የተደቀነውን ደባ አቅጣጪያውን ማስቀየር የሚጠበቅ ነበር። ነገር ግን ይህ አልሆነም።
በመምህራንና በሙያ ማህበራቸው በኢመማ ላይ የሚድርሰው ወከባና እንግልት ሳያቋርጥ እስካሁን መዝለቁን ከፍ ብሎ ጠቅሰነዋል። ለዚህም ነው ከቅርብ ወራት ጀምሮ መምህራን በኑሮ ውድነት እጅግ በመደቆሳቸው እርዛቱ፤ ረሃቡና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑት የጤንነት፤ የሞራል፤ የመብት ጥያቄ ሊያነሱ የተገደዱት። የኢትዮጵያ መምህራን እንደቀድሞው መከበርና ያለስጋት መኖር የቅንጦት ጥያቄ ያህል እየተረሳ መጥቷል። የትምህርቱ ጉዳይ ዋጋ ማጣት የመምህሩ ሙያና ክብር መርከስና መዋረድ ነፀብራቅ ሊሆን ችሏል። ቢያንስ እንደሌላው የመንግሥት ሠራተኛ ተመጣጣኝ ደመወዝ እየተከፈለን መኖር እንችል ብለው ላነሱት ጥያቄ የካድሬና የወያኔ ባለሥልጣናት መሣለቂያ እየተደረጉ ነው። በጣም የሚያሳዝነው ያለ መምህራን ምርጫ በማህበሩ አመራር ላይ የተቀመጡ ተለጣፊዎች በድሬደዋ ከተማ በተደረገ ጉባዔ ተብዬ ለመምህሩ የቆሙ መስለው ስለደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ለመለስ ዜናዊ አቅርበው ነበር። ምላሹ በመዘግየቱና የመምህራንም የኑሮ ውድነት ከሚችሉት በላይ አሻቅቦ ስለአንገፈገፋቸው ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ የሆነውን መብታቸውን በመጠቀም የሥራ ማቆም አድማ መምታት ተገደዱ። ወያኔም እንደ ልማዱ የሽንገላና የማጭበርበር ሥራውን ጀመረ። ተለጣፊዎችም በበሉበት መጮሀቸውን ቀጠሉ። ለመምህራን የተፈቀደው የደሞዝ ጭማሪ ተገቢ ነው ሲሉም የአይጥ ምስክር ድንቢጥ ሆኑ። ይህ ደግሞ ይበልጥ የመምህራኑን ሆድ አስከፋው። የተቃውሞውንና የሥራ ማቆም አድማሱን እያሰፋው መጣ።ባለፈው
በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ሰለተለጣፊው ማህበር አፈጣጠርና ባህርይ ጥቂት ተብሎ ነበር።መምህራንን አስተባብሮና የነርሱን ፍላጎት አንግቦ ለመራመድ እንደማይችል፤ ይልቁንስ መምህራን በራሳቸው ተነሳሽነት እየተሰበሰቡ ትግሉን እንዲያጠናክሩ አሳስቦ ነበር። ችግሩ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ያለ ስለሆነ በክልል፤ በከተማና በገጠር በሚል የሚታጠር ሳይሆን ከዚያም በላይ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲጎለብት ተደርጎ የትግሉ ወላፈን ቦግ እልም የሚል ሳይሆን እስከድል ድረስ የሚጫጫስ፤ የሚንቀለቀል እንዲሆን ጠቁሞ ነበር። አሁንም መደረግ ያለበት ነው።
አዎ አሁን ውቅቱ የሕልውና ጥያቄ ጉዳይ ሆኗል፤ ትውልድ የማዳን ጉዳይ ሆኗል፤ አገር የማዳን ጉዳይ ሆኗል። መምህራን ደግሞ ለዚህ ግምባር ቀደም ሆነው መሰለፍ ይጠበቅባቸዋል። በእርግጥም ምልክቶቹ የቀድሞ ታሪኩን የሚያድሱ ይመስላሉ። የኮከብ ጽባሕ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ስብሰባ ተቀምጠው ያወጡት ያቋም መግለጫ የትም ቦታ ያለውን መምህር ሁኔታ የሚያሳይና የሚያኮራ ነው። ለተግባራዊነቱ ከሁሉም መምህራንና የህብረተሰብ ክፍል መተባበርና መታገል ደግሞ ራሱን የቻለ አዎንታዊ ክንዋኔ ይሆናል።
በሰሜን ጎንደር በተለያዩ ት/ቤቶች የታየው የመምህራን እንቅስቃሴ በፈር ቀዳጅነት የትግሉን አዲስ ምዕራፍ የከፈተና የሚደነቅ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ በመላ ሊሸጋገር የሚገባ እንቅስቃሴ ነው።
ከላይ አልፎ አልፎ እንደተጠቆመው ያሁኑ የመምህራን ትግል የችግሩ መንስኤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። በቅርቡ በቴሌኮሙኒኬሽን ሠረተኞች ላይ ወያኔ የወሰደውን የጭካኔ ርምጃ ማስታወስ በራሱ በቂ ነው። የኑሮ ውድነት ያልነካው ቢኖር ወያኔና ግብረ አበሮቹ ብቻ ናቸው። ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከተለያዩ አገሮች ገንዘብ ተበድሮ ሕዝብን ዕዳ ተሸካሚ ከሚያደርግበት ለመላቀቅ ፤ ገበሬዎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ እየተወገዱና እየተሰደዱ ይዞታቸው የነበረ መሬት ለውጭ ባለሀብቶች ወያኔ ከሚቸበችብበት ተግባሩ ለመከላከል፤ በቁማችን በኑሮ ውድነት እንድናልቅ ወያኔ ከሚያደርግበት ሁኔታ ለመከላከልና ባጠቃላይ የአገሪቱን ሕልውና አዳክሞ የዜጎችን መብት ከሚረገጥበት ለመከላከል በጋራ እንነሳ። ስንት ይለያል ዘንድሮ ያልፍብናል? አናፈግፍግ።
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መምህራን እያደረጉ ካሉት የሥራ ማቆም አድማ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሠራተኛው፤ ገበሬው፤ ታክሲ ነጂው፤ ምሁሩ፤ ተማሪው፤ ነጋዴው፤ ወላጅ ከመምህራን ጎን ቆመው በመተባበርና በመሳተፍ ሕዝባዊ ትግሉን እንዲያቀጣጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!
የመምህራን ትግል ግቡን ይመታል!
ሁሉም ለመብቱ ዘብ ይቁም !
በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ
መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም.
ለበለጠ መረጃ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በመጻፍ ሊገናኙን ይችላሉ
ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የተሠጠ መግለጫ
ገዢው ፓርቲ አገሪቱን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ባለው ሁኔታ የዜጎች የመብት ጥሰት ከእለት ወደ እለት ከመሻሻል ይልቅ እየባሰ የመቀጠሉን ሁኔታ መድረክ በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለው ነው፡፡ ከነዚህ መረጃዎች በመነሳትም በሀገሪቱ ውስጥ የህግ የበላይነት አለ ለማለት ይቸግራል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመብት ጥሰት ሳይጋለጡ በሠላም ለመኖር የገዢው ፓርቲ አባላት መሆን የግድ እየሆነ የመጣ መሆኑንም ሲገነዘብ ታላቅ ቁጭት ያሳድርበታል፡፡ ምክንያቱም በኢህአዴግ ካድሬዎች ከሕግ አግባብ ውጭ ዜጎች ይታሰራሉ፡፡ ከሥራ ይፈናቀላሉ፡፡ ንብረታቸውን ይነጠቃሉ፤ ባጠ ቃላይ አለአግባብ ግፍና በደል ይደርስባቸዋል፡፡ ይህንን በገዢው ፓርቲ አካላት በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን በደል መድረክ ሲመለከተው፣ ህግ የታለ? በወረቀት ላይ የመኖሩ ፋይዳው ምንድነው? እንዲል ያስገድደዋል፡፡ ለዚህ የመድረክ ድምዳሜ ለናሙና ያህል ጥቂት ማስረጃዎችን እንጠቅሳለን፡፡
1. የመድረክ ከአባል ድርጅቶቹ አንዱ የሆነው የአረና ትግራይ አባላት የደረሰባቸውን ግፍና በደል በመዘርዘር ባወጣው መግለጫ እንደተገለፀው በአረና ትግራይ አባላት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና በደል፣ በሀገሪቱ ህገ-መንግሥት የተደነገጉትን የዜጎች መብቶች በእጅጉ የሚፃረር እንደመሆኑ ዜጎች የፈለጉትን የፖለቲካ መስመር ደግፈው ያልፈለጉትን ተቃውመው በሠላም መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ላይ መድረሱን ያሳያል የኢህአዴግን የፖለቲካ መስመር የሚቃወም ድርጅት አባል መሆን ለሕገ-ወጥ እስራት፣ ድብደባና ሕይወት ማጣት ድረስ ላለመጉዳት የሚዳርግ ከመሆን በተጨማሪ እንደሙያው ዜጎች ተቀጥረው መስራትና ይህ ለሚያስገኘው ጥቅማ ጥቅም ባለመብት አንዳይሆኑ አድልዎና መገለል የሰፈነበት ሥርዓት በሀገሪቱ መንገሱን ያሳያል፡፡
2. ከመድረክ አባል ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) በስፋት በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ካገኘው መረጃ መድረክ እንደተረዳው በዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡ ድርጅቱ በሚንቀሳቀስበት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላንና በሀዋ ወለል ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ዜጎች ሌቦች ናቸው፣ በማለት በፖሊሲና በሚሊሺያ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ከያዙዋቸው በሁዋላ፣ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ከባድ ድብደባ እንደፈፀሙባቸው ተረድተናል፡፡ ለምሳሌ በሀዋ ወለል ወረዳ አውሳ ሰመራ በተባለ ቀበሌ 1ኛ ሰንበቶ ወዬሳ፣ 2ኛ ይልቅ እስራኤል፣ 3ኛ ደገፉ ሲራጋ፣ 4ኛ ወሰኑ ዲሳሳ የተባሉ ሠላማዊ ዜጎች በፖሊስ ጣቢያ ከተፈፀመባቸው ድብደባ በተጨማሪ ሰብአዊ ከብራቸውን በማዋረድ፣ በድንጋይ ዳቦ ዘመኑ በኋላ ቀር የቅጣት መፈፀሚያ ዘይቤ ገበያ ውስጥ እያዞሩ በሕዝብ ፊት የመግረፋቸው ሁኔታ ኢሕአዴግ በ21ኛ ምእተ ዓመት ይችን ሀገር ወደኋላ ቀሩ ጥንታዊ (Primitive) ሥርዓት እየወሰዳት ነው ወይ? እንድንል ያስገድደናል፡፡ እንደዚሁም፣ በዚሁ በሀዋ ወለል ወረዳ ጉራቴ ወለል በተባለ ቀበሌ ነዋሪ የሆነ ረጋሳ ቲቾ የተባለ ሰው በየካቲት ወር በቶጆ ወረዳ ፖሊስ ተይዞ ተደብድቦ ህይወቱ ማለፉን ተረድተናል፡፡ ከዚያም ሬሳውም ወደ ተገቢው ህክምና ተቋም ተልኮ መመርመር ሲገባው፣ የወንጀል ድርጊቱን ለመሸፈን ሲባል ያለምርመራ እንዲቀበር መደረጉ ድርጊቱን ለመሸፈን የተወሰደ እርምጃ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ የሆነ የህግ ጥሰት ዜጎች በኢህአዴግ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓት ላይ እምነት ያሳጣ ስለመሆኑ የሟቹ ረጋሳ ቶቹ ባለቤት ወ/ሮ ተመስጌ ለሙ በድርጊቱ ተበሳጭታ ባሏ በሞተ እለት በመኖሪያ ቤቷ እራስዋን በመስቀል ህይወቷ በአሳዛኝ ሁኔታ ማለፉ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የዜጎች የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በእጅጉ የተንሰራፋ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ ከሟች ረጋሳ ቱቾ ጋር በወቅቱ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የነበሩት 1ኛ ሰንበቶ ወዬሳ፣ 2ኛ ገመቹ ፈጠነ፣ 3ኛ አማና ጨዋቃ የተባሉ ንፁሃን ዘጎች ከባድ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ሀኪም ቤት ተኝተው እየታከሙ መገኘታቸው ነው፡፡
1. የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ሠራተኞች በቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላን ወረዳ፣ በየካቲት ወር 2ዐዐ4 ዓም በጎዳና ጨዋቃ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ ሰዎች ላይ ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፍያ መፈፀማቸውና ተመሳሳይ ድርጊቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በኢህአዴግ የቀበሌ ባለስልጣን ካድሬዎች በሠላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈፀሙ መሆናቸው፣
2. በደቡብ ክልላዊ መንግሥት በሀላባ ልዩ ወረዳ ቀበሌ፣ የቀበሌ ባለስልጣናት የስልጣን መቀራመት ሹክቻ ባስከተለው ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፈና ከፍተኛ ንብረት መውደሙ፡፡
3. በሀዲያ ዞን፣ በምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ በቀበሌዎች አከላለል ጉዳይ ላይ በሕዝቡ መሀከል ስምምነት በመጥፋቱ መንስኤነት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ መድረሱ፣
4. በሱረማና የደዚ፣ ብሔረሰቦች መሀከል ሳይፈታ የቆየው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በኢህአዴግ ሥርዓት መልካም አስተዳደር ድቀት የተነሳ ወቅታዊና ፍትሓዊ ውሳኔ መስጠት ባለመቻሉ ቅራኔው ተባብሶ ወደ ግጭት በመሸጋገሩ የዘጎች ሕይወትና ንብረት በከፍተኛ ደረጃ መጥፋቱና በተለይም የሱርማውን አርብቶ አደር ሕዝብ ከመኖሪያ ቀየው እንዲሰደድ ምክንያት መሆኑ፣
5. ለጋምቤላ ክልል ጎደሬ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የደረሰው አሳዛኝ የጥቃት እርምጃ ይዚህ አይነቱ እንቅስቃሴዎች እየሰፋ እንዳይሄዱ መድረክን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ይኸውም በተለያዩ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ምክንያቶች መብቶቻቸው ያልተከበሩላቸው ወገኖች በሥርዓቱ ላይ ያላቸውን ጥላቻና ተቃውሞ ለማስተላለፍ ሲሉ ንፁሃንና ዜጎችን ጭምር ወደ ሚጎዳ አፍራሽ እርምጃዎች ውስጥ እንዳይገቡ መድረክ ይሰጋል፡፡
6. በቅርቡ በቤንች ማጂ ዞን የተከሰተው ምስኪን አርሶ አደሮችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው በማፈናቀል በገፍና በግፍ የማባረሩ እርምጃም በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ከሥም ሥርዓት አልበኝነት የበላይነቱን በመያዘ ሀገሪቱን ቀውሰ ውስጥ እንዳይከታት መድረክ አጥብቆ ይሰጋል፡፡
ስለሆነም፣ የተቃውሞ ፖለቲካን ለማጥፋት ሲባል የዜጎችን ግለሰብና ቡድን መብቶችን እየ ረገጠ ያለው በሀገሪቱ መልካም አስተዳደር በመጥፋት ሕግና ሕጋዉነት የማይከበርበት ደረጃ ላይ የተደረሰበትን ሁኔታ በሠላማዊ ደሞክራሲያዊ አግባብ ለመቀየር መድረክ የሚያደርገውን ትግል በመደገፍ መጠነ ሠፊ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ለመላው ሕዝባችን ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)
መጋቢት 23 ቀን 2ዐዐ4 ዓም
አዲስ አበባ
ሀገራችንን የገጠማት ችግር ዘርፈ ብዙ የመሆኑን ያህል የሚጠይቀው መስዋዕትነትም ከፍተኛ ነው። የውጭ መንግስታት የመለስን መጥፎነት ጠንቅቀው እያወቁ ድጋፋቸውን ያለማቋረጥ ሲሰጡት ስንመለከት ደግሞ ምን ያህል ትግላችን አዳጋችና ውስብስብ እንደሆነ እንረዳለን። በዚህም ምክንያት “ድሮስ ከባዕድ መንግስት ምን እንጠብቃለን” የሚል ቁጭትም በውስጣችን እንዲያጭር ያደርጋል። ነገር ግን የብዙ ጥያቄዎች የመልስ ጽንሰ ሃሳቡም በራሱ በጥያቄው ውስጥ ሊኖር መቻሉን ካጤንን ለዚህ ችግር መፍትሄውንም ማግኘት እንችላለን። (ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ)