“የሴቶችን መብት በማስከበር ለሥልጣን ማጎናጸፍ” አቶ ኦባንግ ሜቶ

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ከየካቲት ሠላሳ እስከ መጋቢት ሦስት ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የኢትዮጵያ ሴቶች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ “የሴቶችን መብት በማስከበር ለሥልጣን ማጎናጸፍ” በሚል ርዕስ ንግግር አድርገዋል። የአቶ ኦባንግን ሙሉውን ንግግር አስነብበኝ!

የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር!! (መድረክ)

ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የተሰጠ መግለጫ

 

በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የባለአገርነት ስሜት እንዲኖራቸው የሚወጡ አዋጆች መመሪያዎችና ድንጋጌዎች ሁሉ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ስምምነት ያገኘ መሆን ይኖርበታል። መንግሥት ሕዝቡ የሚተዳደርበትን የትኛውንም አይነት ሕግ ሲያወጣ ማዕከል ማድረግ ያለበት የዜግነት መብትን ለማስጠበቅ ለማጎናጸፍ እንጂ አንገት የሚያስደፋ የሚያሸማቅቅ የሚያስፈራራ አፋኝና ባጠቃላይ በመብት ገፈፋ ላይ የተመረኮዙ መሆን አይኖርበትም። የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 . በማን አለብኝነት የዜጎችን ንብረት የማፍራት የመሸጥ የመለወጥ እና የመጠቀም መሠረታዊ መብቱን በሕግ ሽፋን የገፈፈ አዋጅ ነው። በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በሥልጣን በቆየባቸው 20 ዓመታት ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የሚወጡ ህጎች ከፖለቲካና የሥልጣን ዕድሜ ከማራዘም አንፃር ብቻ ታይተው በሕዝብ ላይ የሚጫኑ ናቸው።

 

የሊዝ አዋጅ አወጣጥ እና የአፀዳደቁን ሂደት ብንመለከት ፈፅሞ የተለመደውን አሰራር የተከተለ አይደለም። የዚህ አዋጅ አፀዳደቅ እና አቀራረብ ሁለት መሠረታዊ ግድፈቶች ይታይበታል፡-

 

1. በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀፅ 3 “የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ሉአላዊነታቸው የሚገለፀው በዚህ ሕገ-መንግሥት መሠረት በሚመርጣቸው ተወካዮቻቸው እና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይሆናል።ይላል ይሁን እንጂ በአዲሱ የሊዝ አዋጅ መሬትን በመሰለ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆነውና በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተው ሕዝብ ጉዳዩ ቀርቦለት በነፃነት እና በግልፅነት እንዲወያይበት አልተደረገም

 

2. ኢህአዴግ በፓርላማው የወጣው የሕዝብ ተወካዮች /ቤት ስነ-ምግባር ደምብና አሰራር እንኳን እንደሚገልፀው ከስብሰባው 48 ሰዓት በፊት የአንድ አዋጅ ረቂቅ ለም/ቤቱ አባል መድረስ እንዳለበት ይደነግጋል። የፓርላማ አባሉ በዚህ 48 ሰዓት ውስጥ ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ባለሞያዎችን አማክሮ ይቀርባል። ረቂቅ አዋጁም ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል። ኮሚቴውም ባለሞያ ጋብዞና አማክሮ ለሕዝብና ለሚዲያው ክፍት አድርጎ ያወያያል ሃሳቡን አዳብሮ በድጋሚ ለፓርላማ ያቀርባል። ፓርላማው ሲፈልግ ያፀድቃል። ሳይፈልግ ውድቅ ደርገዋል። ግልፅ የሆነው አሰራር ይህ ሆኖ ሳለ ለራሱ ከመሰለውና ለፖለቲካ ፍጃታ ይጠቅመኛል ካለ እንኳን የሥነ ምግባር ደምብና አሰራር ቀርቶ ሕገ-መንግሥት የሚጥሰው የኢህአዴግ መንግሥት ትልቁን የዜጎች መብት ለፓርላማ አባላት ማታ 1200 ታድሎ ጧት 3 ሰዓት አዋጅ ሆኖ እንዲፀድቅ አድርጓል

 

እዚህ ላይ አንዳንድ ጉዳዮችን ወደ ኋላ መለስ ብሎ መዳሰስ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ በብዙ ጉዳዮች በኢህአዴግ መንግሥት በወንጀለኝነት የሚጠቀሰው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እንኳን የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ንብረት ለማድረግ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 47/67 መዕራፍ ሁለት አንቀፅ 1 “አንድ ቤተሰብ ወይም ግለሰብ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ የሚያውለው እስከ 500 ካሬ ሜትር የሚደርስ የከተማ ቦታ ሚኒስትሩ በሚወጣው መመሪያ መሠረት በይዞታ ሊሰጠው ይችላል። ባለይዞታ የሟች ሚስት ወይም ባል ወይም ልጆች በቦታው ተተክተው የመጠቀም መብት ይኖራቸዋል፡፡ይላል። ለም/ቤት ወይም ድርጅት በሚቀርበው አቤቱታ መሠረት ሚኒስቴር /ቤት እንደሚሰጥ በዚሁ መዕራፍ አንቀፅ 2 እና 3 ይገልፃል። በዚሁ አዋጅ ምዕራፍ 3 እና 12 የከተማ ቤት ስለማስተላለፍ በሚለው ሥርአንድ ቤተሰብ ግለሰብ ወይም ድርጅት በከተማ ቤቱ የመጠቀም ወይም ይህንኑ ቤት የማውረስ የመሸጥ ወይም የመለወጥ መብት አለው።ይላል።

 

ይህንን አዋጅ ስንመለከት የአገሪቱን የከተማ ነዋሪዎች ከግለሰብ ጭሰኝነት ነፃ ያወጣ የከተማ ቦታን የመሸጭ የመለወጥ እና የባለቤትነት ክብር እንዲጎናፀፉ ያስቻለ ነው ማለት ይቻላል። አንድ አዋጅ ትክክለኛ አዋጅ ነው። ሕዝባዊ ነው። ሊባል የሚችለው ብዙሃን ሕዝብ ሲያስደስት ነው። ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያወጣቸው አዋጆች ግን ገዢዎችን የሚጠቅም ሕዝብና ሀገርን የሚጎዳ ዜጎችን አንገት የሚያስደፋ መብትና ጥቅምን የሚጋፋ ሆኖ እናገኘዋለን።

 

ሰሞኑን የወጣው አዋጅ 721/2004 . የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅን ብንመለከት የሚያሳየን ይህንኑ ነው። የዚሁ አዋጅ ክፍል ሁለት አንፅ 6 ነባር ይዞታዎች ወደ ሊዝ ስሪት ስለሚቀየሩበት ሁኔታ ከተራ ቁጥር 1-7 ተዘርዝሮ ተቀምጧል። የኢህአዴግ ሹመኞች የነባር ይዞታዎችን አይመለከትም። ዝርዝር መመሪያ አልወጣም። ተረጋጉ እያሉ በሕዝብ ላይ ውዥንብር ይፈጥራሉ። ነባር ይዞታዎችን አይመለከትም ቢሉም ሲሸጥ ሲለወጥ ሊዝ እንደሚገባ በግልፅ ደንግጓል። አንድ ነባር ይዞታን ሲገዛ ከባለንብረቱ ከሚከፍለው ክፍያ በተጨማሪ ለመንግሥት ያንኑ ቦታ የሊዝ ዋጋ ይከፍልበታል። ይህ አሰራር ብዙ ምርምር ማይጠይቅ ንብረት በማስተላለፍ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ለማንም ግልፅ ነው። የነባር ይዞታው ባለቤት ቦታውን ሸጦ ሌላ አነስተኛ ቦታ ገዝቼ በተረፈችኝ ገንዘብ ሕይወቴን ልምራ ቢል የሚገዛው በሊዝ ነው። ነባር ይዞታዎች ከሊዝ የሚያመልጡት እንዴት ነው ይዞታው ሳይሸጥ ሳይለወጥ የንብረት ዋጋ ሳኖረው እንደ ጉልቻ በመቀመጡ ብቻ ከሊዝ አመለጠ ማለት ነውን?

 

አዋጁ ሕዝብ የአገሩን ባለቤትነት የሚነካ ነው። የሊዙ ጥሩነት ነባር ይዞታዎችን ይነካል አይነካም በሚለው አይለካም። የዜጋን ሁሉ ተስፋ ያጨለመ ነው። አዋጁ የአገሪቱን ሕዝብ ከይዞታ ባለቤትነት አሽቀንጥሮ ጥሎ መንግሥትን የመሬት ባለቤት የሚያደርግ ነው። አዋጁ አምባገነኖች በማን አለብኝነት የሚያወጡት አዋጅ ነው። ሕገ-መንግሥቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ቢልም ኢህአደግ ግን በራሱ ጠቅልሎ ሕዝብን ጭሰኛ አድርጐታል። ንብረት የማፍራት ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን ነጠቆታል። በዚህም ሕዝብ አቋሙን በግልፅ አሳውቋል። ሕዝብ ከአዋጁ መውጣት በኃላ ለይስሙላ በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ በአዋጁ መውጣት ቁጣውን ገልጿል። ሕዝብ ትክክለኛ አቋም ወስዷል። ሕዝብ ሊደመጥ ይገባል። ሕዝብ መከበር አለበት የሕዝብን እምነትና ፍላጎት በጡንቻ እየጨፈለቁ የሕዝብን ጮኸት እንደ ቁራ ጮኸት እየቆጠሩ መጓዝ ለማንም አይጠቅምም። ሕዝብ የማስጠንቀቂያ ደውሉን አሰምቷል። ሕዝብ የመደመጥ መብት አለው፡፡ በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በተቆጣጠራቸው የሚዲያ ተቋማት የመሰለውን የሚያስፈልገውን በሕዝብ ስም እያስተላለፈ የሚያካሂደው ፕሮፖጋንዳ ለራሱም ለሕዝቡም ለአገርም እንደማይጠቅም አውቆ ሊያስብበት ይገባል።

 

በአዋጁ ዙሪያ በመንግሥት ባለሥልጣናትና ካድሬዎች የሚሰጠው መግለጫና ከሕዝብ ለሚቀርበው ጥያቄ የሚሰጡት መልሶች የፌዝ መሆናቸው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክን (መድረክ) ያስገረመው ጉዳይ ነው። ይህም ነባር ይዞታህ እስክትሸጠውና እስክትለውጠው ድረስ ሊዝ አይገባም ማለትዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏትአይነት መሆኑ ነው። እነዚህ አካላት አንዳብራሩትነባር የዞታዎች ወደ ሊዝ ስርዓት የሚቀየሩበት ሁኔታ ዝርዝር ጥናት ተደርጎ 4 ዓመት ጊዜ ውስጥ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ነው።” (አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2004 .) ከባለሥልጣናነቱ ማብራሪያዎች ለመረዳት እንደተቻለው አዋጁ ከጥናት በፊት ቀድሞ የመጣ እንደመሆኑ የኢህአዴግ ሥርዓት የሕዝብን መብት ቤተ ሙከራ ማድረጉ የአገዛዙን ሥርዓት የዜጎችን ጥቅምና ክብር ማዕከል ያላደረገ መሆኑን ሕዝባችን ይገነዘበዋል። በመድረክ ዕምነት ደግሞ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ተገቢው ጥናት መካሄድ ነበረበት እንላለን።

 

ስለሆነም በገጠር ነዋሪው አርሶ አደር የይዞታው ባለቤት መሆን እንዳለበትና የከተማ ነዋሪውም የመኖሪያ ቤት የሰራበት መሬት ባለቤትነት እንዲያረጋግጥ መድረክ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ያሰፈረውን አውን ለማድረግ በተያያዘው ትግሉ እንደሚቀጥል እየገለፅን መላው ሕዝባችንም መብቱን የሚጋፉ አዋጆችንና ድርጊቶችን ለመቃወም በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ከጎናችን እንዲቆም ሀገራዊ ጥሪችንን እናቀርባለን።

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)

 

ጥር 17 ቀን 2004 .

 

አዲስ አበባ

የኢትዮ - ካናዳውያን የዲሞክራሲ ፎረም በኦታዋ - ካናዳ

የኢትዮ - ካናዳውያን የዲሞክራሲ ፎረም በኦታዋ - ካናዳ

የድጋፍ መግለጫ

 

በጄነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ለበርካታ የትግል ዓመታት ያራምድ የነበረውን ከኢትዮጵያ የመገንጠል አ ንዳን በመተው ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጐች መብት ፤ እኩልነትና ነፃነት መከበር እታገላለሁ በማለት ታህሳስ 22 ቀን 2004 ዓም ያወጣውን መግለጫ የኢትዮ ካናዳውያን የዲሞክራሲ ፎረም በኦታዋ - ካናዳ በደሥታ የተቀበለው መሆኑን ይገልፃል።


ፎረማችን በአገራችንና በህዝባችን ላይ የወደቀውን የግፍ አገዛዝ በማስወገድ በምትኩ አገራዊ አንድነቷ የተጠበቀ፤ የህዝቧ እኩልነትና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት በሚደረገው ትግል ውስጥ የትግሉ አካል በመሆን የሚጠበቅበትን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።


በመሆኑም ፎረማችን የአገርና የህዝብ ጠላት የሆነውን ህውሃት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያችን ውስጥ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ግፍና በደል በተለያዩ መድረኰች አጋልጠናል ፤ ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት ጥላ ሥር በመሰባሰብ ላይ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ፤ ሲቪክ ማህበራትና ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ አንድ ጠንካራ ህብረት እንዲመሰረት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለመስጠት ይህ ፎረም ቃል ይገባል።


በማከልም ይህንን በጄነራል ከማል የቀረበውን የኢትዮጵያዊነትን ጥሪ ባለመቀበል በተፃራሪነት የቆሙ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያውያን ህብረት ላይ የሚያካሄዱትን አሉታዊ ቅስቀሳ በመተው አቋማቸውን አስተካክለው ህዝባዊውን እንቅስቃሴ እንዲቀላቀሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።


ፎረማችን አሁንም እነ  ነራል ከማል የወሰዱትን አቋም ከልብ እየደገፈ ጊዜው የግድ የሚለውን የጋራ ትግል እንዲ ምሩልን አደራ እንላለን።


ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

በሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌደሬሽን ላይ የወያኔ ዘመቻ ሲጋለጥ

ኢትዮጵያውያኖችና አሜሪካኖች ለፍትህና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ

ሎስ አንጅለስ

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌደሬሽን ውስጥ የተሰገሰጉ የወያኔ ካድሬዎች ሲጋለጡ

ታህሳስ 30፤ 2004

 

የኢትዮጵያን የእግር ኳስ ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ ከተመሠረተ እነሆ 28 ዓመቱን በሚመጣው ጁላይ መጀመሪያ፣ 2012 ዓም በዳላስ በሚያከብረው ዓመታዊ በዓሉ በደማቅ ሁኔታ ለማስታወስ በዝግጅት ላይ ነው። ይህ ፌደሬሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በስደት ለምንገኘው ኢትዮጵያውያን በዓመት አንዴ በአንድ ከተማ ከያለንበት በመምጣት ተሰባስበን እግር ኳሱን ብቻ ሳይሆን፤ ባህላችንን ለልጆቻችንና ለምንኖርበት ዓለም የምናስታዋውቅበት ወቅት ነው። ስደተኛው ባመዛኙ በደርግና በተለይም በትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ግፈኛና ዘረኛ አገዛዝ ምክንያት ተመሮ ገሚሱም ህይወቱን ለማትረፍ ሲል ከውድ ሀገሩ ሳይወድ ተገዶ ከፍተኛ መስዋዕትነትን በመክፈል የተሰደድ ነው። የዚህን ዓመታዊና ኢትዮጵያዊ ባህል በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያዊነት መሠረቱን የሚያስታውሰውና ከውድ ወገኖቹ ጋር በይበልጥ የሚያቀራርበው ለመሆኑም የሚያጠያይቅ አይደለም።

 

በሌላ በኩል ዘረኛው የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የሀገራችንን መንግሥት በትረ ሥልጣን በሀይል ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የማያደርገውና የማይፈጽመው ተግባር እንደሌለ በሀያ ዓመታት አገዛዝ ዘመኑ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጦልናል። የኢትዮጵያ ታሪክ ከአንድ መቶ ዓመት ባላይ አያልፍም፤ ለዘመናት ተባብሮና ተቻችሎ የሚኖረውን ሕዝባችንን በዘር አጥር ውስጥ እንዲሰባሰብና አንዱ ባንዱ ላይ በጠላትነት እንዲነሳሳ፤ የሀገሪቱን ሀብት ለውጭ ባለሀብቶች አሳልፎ የሚሰጥ፤ ሀገሪቱን ያለባሕር ወደብ ያስቀረና አሁንም ህዝቡ የለፋበትን ሀብት በሚያሳፍርና በሚያስገርም ሁኔታ ከሀገር ውጭ በማሸሽ ላይ የሚገኝ የዘራፊና ‘የባዕድ መንግሥት’ ለመሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው። የጭቆና ጊዜውን ለማራዘምም ሕዝቡን በከፋፍለህ ግዛው ፓሊሲ በሀገር ቤት እያመሰው ሲሆን፤ ይኅንኑም ፓሊሲውን በወጭው ዓለም ለማስፈጸም በቂ ዝግጅት ካደረገ ቆይቶአል። ለዚህም እንቅስቃሴው እንዲያመቸው በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መ/ቤቱ አማካኝነት የአፈጻጻም ሥራ መመሪያ አውጥቶ በውጭው ዓለም ለሚኖሩ ሆድ አደር ካድሬዎቹ እንዲተገበሩት ያለሀፍረት አሰራጭቶአል። የወያኔ ከፍተኛ ካድሬዎችና ባለሥልጣናት የነበሩ ታማኝ አገልጋዮቹን በዋና አስፈጻሚነት በመላው ዓለም በሚገኙ ኤምባሲዎቹ ሁሉ መድቦአል።

 

ዛሬ በየምንኖርበት አካባቢዎች ሁሉ በሀይማኖት ተቋሞች፤ በንግድ ድርጅቶችና ማህበሮች፤ ኢትዮጵያውያኖች በሚሰባሰቡበት አካባቢ   ሁሉ ወያኔ የስለላና የብተና ካድሬዎቹን በማሰማራት ቢቻል የወያኔ ተቀጥላ ድርጅት ማቋቋም ካልሆነም እንዲበተንና አባላቱ እንዲበጣበጡ እያደረጉ ነው። በየቤተ ዕምነት ቦታዎች ሁሉ ስለሀገር መቆርቆር፤ የሕዝባችንን ብሶት ማሳወቅና ማውራት ሁሉ የፓለቲካ ጉዳይ ስለሆነ አይቻልም በሚሉ የተሳሳቱ ካህናቶች አማካኝነት የሀገር ወዳዱን ጎራ ለማኮላሽት እየጣሩ ለመሆኑ የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የሆንን ሁሉ በሚገባ የምናውቀው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሀገር ግቡና ወይንም በሀገር ቤት የንግድ ሥራ ላይ ብትሰማሩ ድጋፍ እንሰጣለን ቢሉም በፕሮፓጋንዳቸው ተታለው የገቡ ወገኖች ንብረታቸው ተዘርፎ ልፋታቸውን ለወያኔ ባለሟሎች አስረክበው የተመለሱ ወገኖች ብዛት ቀላል አይደለም። በቅርቡም ከኢትዮጵያ ካዝና ከ2009 ጀምሮ እስከአሁን ወደ ውጭ ሀገር የወጣው 11.5 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ወዴት እንደገባ ምንም ማስረጃ እንዳልተገኘለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቆአል። ስለዚህ የዚህ ዓይነቱ በንግድ ሥራ ስም የሚደረግ ጥሪ ለዘረፋ እንጂ ለልማት እንዳልሆነ ወገኖቻችን ሁሉ እንዲያውቁት ያስፈልጋል።

ከፍ ብሎ በተዘረዘረው መንገድ ነው ወያኔና ግብረ አበሮቹ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌደሬሽን ውስጥ ስዎቻቸውን ሰርገው በማስገባት በተለያዩ ጊዜያቶች ድርጅቱን ወያኔ በኢትዮጵያንና ኢትዮጵያኖች ላይ ለሚያካሂደው የጥፋት ዘመቻ ማስፈጸሚያ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ የኖሩት። አንደኛው ፤ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እንግድነት በአለቆቻቸው ትዕዛዝ መሠርት ላለመቀበል ሲሉ የብዙሃኑን አባላት ድምጽ በማፈን የወያኔ ተገዥነታቸው የተረጋገጠበት ወቅት ነበር። ለዚህም የድርጅቱ አባላት ዓመታዊ ስብሰባቸውን በማካሄድ አባላትንና ሕዝቡን ለመካፋፈልና ድርጅቱን ለመበተን ሙከራ ያደረጉትን ከሀዲዎች በሀገርና ወገን ወዳድ አባላት እንዲተኩ አድርጓል። ድርጁቱም የነዚህን ሆድ አደሮች ሴራ በሚገባ ተገንዝቦ ለወሰደው እርምጃ እኛም ሆንን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወቅቱን ጠብቆ ውለታውን እንደሚከፍል አንጠራጠርም።

እነዚህ ግለሰቦች አሁንም ሴራቸውን ያላቆሙ ሲሆን፤ እንዳውም ከወያኔና አጫፋሪው መሀመድ አላሙዲ በሚያገኙት ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ በመደገፍ ሌላና አሰገራሚ የጥፋት ፕሮጀክት ይዘው ብቅ ብለዋል። እ ኤ አ  ዲሰምበር 28፤ 2011 በተጻፈ ደብዳቤ ግለስቦቹ በተመሳሳይ ስም የሚጠራ አዲስ የስፖርት ፌደሬሽን እንዳቋቋሙ ገልጸው የቀድሞውንና ህጋዊውን ድርጅት ትታችሁ እኛ በምንመራው ማህበር ውስጥ ኑና ተሰባሰቡ በማለት ለእያንዳንዱ አባል ማህበር ጥሪ አስተላልፈዋል። በያዝነው ዓመት ለሚደረገው ዝግጅትም ሙሉ ክፍያ ፈጽመው በዋሸንግተን ዲሲ አንድ ስታዲዮምና አንደኛ ደረጃ የሆነ ሆቴል በቅድሚያ መከራየታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ለእያንዳንዱ ፈቃደኛ ሆኖ ለሚመጣ አባል የአውሮፕላን መጓጓዧ ወጭ ጨምሮ እንደሚሸፍኑ ያለማፈር አስታውቀዋል። ይኅ ሁሉ ወጭም በማን እንደሚሸፈን የአደባባይ ምስጢር ነው። በቅርቡም ለቅድመ ዝግጅታቸው እንዲረዳ በማለት እነዚሁ ግለስቦች በሎስ አንጀለስ ከተማ ለሶስት ቀኖች የሚቆይ ስብሰባ ወጭውን ሙሉ በሙሉ በመሽፈን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሎአል። ጥሪአቸውን ለሚቀበል እያዳንዱ የስፖርት ቡድን አሥር ሺ ዶላር እንደሚለግሱም ቃል ገብተዋል።

 

በአንጻሩ የማህበሩ አባላት፤ ቡድኖችና ተባባሪዎች በአንድ ድምጽ እያወገዙአቸው ይገኛሉ። እኩይ ሤራቸውም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በይፋ ተጋልጦ፤ የሴራው አቀንቃኞች ታውቀው በዋናው ማህበር ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ አንጠራጠርም። ድርጁቱን ነቅተው በመጠበቅ፤ ክነዚህ ከሀዲዎች ተከላክለው ያቆዩንና አሁንም ተንኮለኞቹ የፈለፈሉትን ሴራ ያከሸፉትን ወገኖች ከልብ ልናመሰግናቸው ይገባንል፤ ህዝብም በጎ ድርጊታችውን እንዲያውቅ የማድረግ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን። በዚህ አኳያ በሎስ አንጀለስ የሚገኙት የዳሎል፤ የኤል ኤ ስታርስና የአበበ ቢቂላ የእግር ኳስ ማህበሮች እነኝህን ሆድ አደሮች አሳፍረው በመመለሳቸው መመስገንና አይዞአችሁ ሊባሉ ይገባል። እኛም በሎስ አንጀለስ የዲሞክራሲና ፍትህ በኢትዮጵያ ስብስብ አባላት እነዚህን ሴረኞች ለመቋቋምና የጥፋት ዓላማቸውን ለማክሸፍ በከተማችን ከሚገኙ የፌደረሽኑ አባላት ጎን የምንቆም መሆናችንን እንገልጻለን።

 

ኢትዮጵያውያንና አሜሪካኖች ለፍትህና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ

 

ሎስ አንጅለስ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ