ከ፲፯ (17) ቀን በኋላ አዲስ ሥልጣን ተሰጣቸው

Ato Tsegaye Berhe, Ato Redwan Hussen, W/o Zenebu Tadesse, and Ato Tolossa Shagie

ኢትዮጵያ ዛሬ (ቅዳሜ ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 19, 2016)፦ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባለፈው ሹም ሽር ሥልጣናቸውን ላጡ ስምንት የኢህአዴግ የቀድሞ ባለሥልጣናት የሙሉ አምባሳደርነት ሹመት ሰጡ። እነኝህ የኢህአዴግ ጎምቱ ባለሥልጣናት የሙሉ አምባሳደርነት ሹመት እንደተሰጣቸው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ቢገልጽም፤ በየትኞቹ አገሮች ላይ ሹመት እንደተሰጣቸው አልገለጸም፤ ተሰናባቾቹ አምባሳደሮችም አልታወቁም።

በትናንትናው ዕለት የባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸው ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትርነት ለተነሱት ለአቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ከሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትርነት ለተነሱት ለወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ፣ ከማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትርነት ለተነሱት ለአቶ ቶሎሳ ሻጊ፣ የአቦይ ስብሃት ነጋ እኅት (ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ) ባለቤት ከሆኑትና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪነት ለተነሱት የህወሓት የጥንት ታጋይ ለአቶ ፀጋዬ በርሄ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴታነት ለተነሱት ለአቶ ረጋሳ ከፍአለ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታነት ለተነሱት ለአምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፣ ቀደም ሲል በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳር ለነበሩት ለአምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ እና ለአቶ ግርማ ተመስገን መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

ከእነዚህ ተሿሚዎች ውስጥ ስድስቱ ተሿሚዎች ባለፈው ጥቅምት ፳፪ ቀን ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ “በጥልቅ ተሃድሶ” ሂሳብ ባደረጉት ሹም ሽር ሥልጣናቸውን ያጡት መሆናቸው ይታወሳል። በአስራ ሰባት ቀን ልዩነት ውስጥ ተሻሪዎቹ አሁንም ተመልሰው ከፍተኛ ሥልጣን ማግኘታቸው የኢህአዴግን “በጥልቅ መታደስ” የሚያሳይ አለመሆኑን እና የቦታ መቀያየር ብቻ ነው የሚል ትችት በተለያዩ ወገኖች እየተሰነዘረ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ዘገባ ያስረዳል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ