(Left to right) Dr. Abiy Ahmed, Prof. Merera Gudina, Dawud Ibsa, Lencho Leta

ስምምነቱን ከተፈራረሙት የኦሮሞ ፓርቲ መሪዎች ውስጥ፣ (ከግራ ወደቀኝ)፤ የኢሕአዴግና የኦዴፓ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የኦፌኮው ፕ/ር መረራ ጉዲና፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባሩ (ኦነግ) አቶ ዳውድ ኢብሳና የኦሮሞ ዴሞከራቲክ ፓርቲው አቶ ሌንጮ ለታ።

ኢዛ (ማክሰኞ መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 1, 2019):- በኦሮሞያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን አዲስ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ነው የተባለውን ይህንን ስምምነት ከተፈራረሙት ፓርቲዎች ውስጥ በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባርና (ኦዴግ) ሌሎችም ይገኙበታል።

ዛሬ ምሽት ላይ ይፋ በኾነው በዚህ መረጃ መሠረት፣ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁለት ቀናት ምክክር ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ተጠቃሚነት ላይ በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።

የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችልና የኦሮሞ አመራሮችን በአንድ ጥላ ሥር የሚያሰባስብ (ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ) እንዲመሠረት ስለመስማማታቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

በስምምነቱ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተጀመረው በጋራ የመሥራት፣ የምክክር መድረክ እንደአገር በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ማደግ እንዳለበትና ፖለቲካ ፓርቲዎች በምን መልኩ አብረን ብንሠራ አገሪቱን ማሸጋገር እንችላለን የሚለው ጉዳይ ላይ ቁጭ ብለው መምከር እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በእለቱ ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ካኖሩትት የኦሮሞ ፓርቲዎች አመራሮች መካከል፤ የኦሮሞ ዴሞከራቲክ ፓርቲው አቶ ሌንጮ ለታ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባሩ (ኦነግ) አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረሱ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይገኙበታል።

በዚህ ስምምነት ላይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች የተገኙበት ሲሆን፣ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ዶ/ር አብይ አህመድ በተጨማሪ የመከላከያ ሚንስተሩና የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር የኾኑት አቶ ለማ መገርሳ፣ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ እንዲሁም የኦዴፓ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ