እነብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ዛሬ በ10 ሺህ ብር ዋስ ተለቀቁ
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና ኮሎኔል አለበል አማረ
ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 14, 2019):- ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በአማራ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያና “መፈንቅለ መንግሥት” ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው በእስር ላይ የነበሩት እነብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በ10 ሺህ ብር ዋስትና ተለቀቁ።
ከአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በኩል የተገኘው መረጃ እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ የተፈቀደላቸው ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ (የክልሉ የልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩ)፣ ኮሎኔል አለበል አማረ (የክልሉ የፀጥታና ሰላም ግንባታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የነበሩ) እና ኮሎኔል ባምላኩ አባይ ናቸው።
ከሦስት ወራት በላይ በእስር ከቆዩ በኋላ፤ ዛሬ በዋስትና የተለቀቁት እነዚህ ሦስት በክልሉ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ የነበሩት ገለሰቦች፤ ጉዳያቸውን በውጭ ኾነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ የተወሰነ መኾኑም ታውቋል።
እነብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በታሰሩበት ወቅት በሰኔ 15ቱ “መፈንቅለ መንግሥት” ሙከራና የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ ወደ 218 ሰዎች ታስረው እንደነበር ይታወሳል። ከእነዚህ ታሳሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ የተለቀቁ ሲሆን፣ እነጄኔራል ተፈራ ጉዳያቸውን በባህር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት ሲከታተሉ መቆየታቸው አይዘነጋም።
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር የተገደሉት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትን አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እና ሁለት ከፍተኛ የክልሉ አመራሮችን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸው ብርጋድየር ጄኔራል ገዛኢ አበራ እንደነበሩ ይታወሳል። (ኢዛ)



