Young men joined the protest at Jawar's house in the capital Addis Ababa

ቦሌ፣ አዲስ አበባ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው የጃዋር መኖሪያ ቤት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ወጣቶች

በአዳማና በሐረር የሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ፣ ንብረትም ወደመ

ኢዛ (ረቡዕ ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 23, 2019)፦ በአዲስ አበባ፣ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችና በሐረር ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የተረጋጋ እንቅስቃሴዎችን የሚፈታተን ድባብ ያጠላበት ከመኾኑንም በላይ የሰው ሕይወት የቀጠፈና በንብረት ላይ ውድመት የፈጠረ ነበር።

ወደ አዲስ አበባ የሚያስወጡና የሚያስገቡ መንገዶች ተዘግተው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል። በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ በአንዳንድ ከተሞች የተቃውሞ ድምፆችን የያዝ ግርግርም ተፈጥሯል።

ማለዳ ላይ እዚህም እዚያም የታየው ግርግር ግን የሰዎችን የሕይወት የቀጠፈ፣ ያቆሰለና ለንብረት ውድመት ጭምር ምክንያት ኾኗል።

መንሥኤ

ይህ ሁሉ የኾነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ “አክቲቪስት” በሚል ከሚታወቁ ግለሰቦች መካከል አንዱ የኾነው ጃዋር መሐመድ ዛሬ ማለዳ ላይ በፌስቡክ ገጹ ላይ የለቀቀውን አንድ መልእክት ተከትሎ ነበር።

 

ጉዳዩ ለሚመለከተው ሁሉ፡-

 

በመኖሪያዬ አካባቢ በቁጥር በርካታ ታጣቂ እየተሰማራ እንደኾነ እያስተዋልን ነው፡፡ ይኸ የታጠቀ ኋይል ከሕግ አግባብ ውጪ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቆጥቦ ወደኋላ እንዲመለስ በአጽንኦት እንጠይቀለን። ማንኛውም ታጥቆ በዚህ ጭለማ ወደ መኖሪያ ግቢያችን ለጥቃት የሚንቀሳቀስ ግለሰብም ኾነ ቡድን ላይ የጥበቃ አካሉ ሕጋዊ መብቱን ተጠቅሞ የመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ ሊታወቅ ይገባል። ይኸን ከሕግ አግባብ ውጪ የሚደረግን እንቅስቃሴ ለመከላከል በሚደርሰው ግጭት እና ጉዳት ሙሉ ኋላፊነቱን የሚወስደው ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት እና ማሳሰቢያ ኋይል ያሰማራው አካል መሆኑን ሕዝቡ እንዲያውቅልን እንጠይቃለን።

 

የሚል ነበር መልእክቱ።

ሦስት ጊዜ የታረመው የጃዋር የፌስቡክ መልእክት

የአርትዖት ታሪኩ ደግሞ ይህንን ይመስላል፤ መልእክቱ ሦስት ጊዜ የታረመ ሲኾን፣ በምስሉ ላይ ከላይ ያለው መጀመሪያ የወጣው ነው፤ መጨረሻ ላይ ያለው ደግሞ የመጀመሪያው ልጥፍ ከወጣበት ከ18 ደቂቃዎች በኋላ ታርሞ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በፌስቡክ ላይ የሚነበበው ነው። ይህ መልእክት የተለጠፈው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከንጋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ነው።

ይህ የጃዋር መልእክት ከመተላለፉ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት (ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም.) በፓርላማ በነበራቸው ቆይታ፤ ከሚዲያ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰጥተውት የነበረውን ምላሽ ተከትሎ ፖስት ያደረገው ነገር ነበር።

በትናንቱ የጠቅላይ ሚንስትሩ ምላሽ ውስጥ “በተለይ የውጭ አገር ዜጋ የኾናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፣ ስትፈልጉና ሰላም ሲሆን፣ እዚህ ተጫውታችሁ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሔዱበት አገር ያላችሁ ሰዎች፤ ትእግሥት እያደረገን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው …” በሚል ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ጃዋርም ይህንን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር እኔን የሚመለከት ነው ብሎ ትናንት ማምሻውን የገለጠው ነበር።

መልእክቱ “"እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል" አለች አይጥ ከንግዲህ ኑⶂዓችንም፤ ሞታችንም፤ ቀብራችንም ኦሮሚያ ላይ ብለን ጠቅልለን ገብተናል ፡)” የሚል ነው።

ከዚህ መልእክት በኋላ የጃዋር ደጋፊዎች በተለያዩ ማኅበራዎ ገጾች ጠቅላይ ሚንስትሩን የሚቃወሙ መልእክቶች እንዲተላለፉ ተደርጓል። ምሽት ላይ ደግሞ ጃዋር እንደገዛው በሚነገርለት ኤል ቲቪ ላይ በሰጠው ቃለምልልስ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩን የመደመር መጽሐፍና ሐሳብ፣ በኢሕአዴግ የመዋሐድ ዙሪያ፣ በቤተመንግሥቱ በአዲስ መልክ መገንባት ዙሪያ፤ … በአጠቃላይ በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አካሔድ፣ ሥራ፣ ሐሳብና አመለካከት ላይ እጅጉን ተችቷል። ከዚህም ሌላ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሌላቸው በሰጠው ቃለምልልስ ላይ ተናግሯል።

ትናንት በዚህ መልኩ ካለፈ በኋላ ግን፤ ማለዳ ላይ ቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ ከሚገኘው የጃዋር መኖሪያ ቤት “ተከብቤአለሁ” የሚለው የፌስቡክ መልእክቱ ተሰራጨ። የጃዋር ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ ወጣቶች ከተለያዩ አካባቢዎች ወጥተው በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ እንዲሰበሰቡ ምክንያት ኾኗል። ከመኖሪያ ቤቱ ወጥቶም ደጋፊዎቹን አመስግኗል።

ይህ ውጥረት ግን ለአዲስ አበቤዎች አልተመቸም። አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን በጊዜ ከሥራ እንዲወጡ ያደረጉበትም ነበር። ይሁንና ጃዋር የጠቅላይ ሚንስትሩን ከአገር መውጣት ተከትሎ ያስተላለፋቸው መልእክቶች በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ውጭ ተንፀባርቀዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የሰጠው መግለጫ

የፌዴራል ፖሊስ ረፋድ ላይ የሰጠው መግለጫ ግን የጃዋርን መልእክት ትክክል ያለመኾኑን የሚያመላክት ነበር።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው በሰጡት መግለጫ፤ አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ለደጋፊዎቻቸውና ለተከታዮቻቸው ልታሰር ነው፣ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው በማለት ያስተላለፉት መልእክት ላይ እንደተገለጠው፤ በመንግሥትም ኾነ በፖሊስ በኩል የተወሰደ እርምጃ ያለመኖሩን ነው።

ግለሰቡ እንደተለመደው የዕለት ሥራቸውን እየሠሩ መኾኑንም ኮምሽነሩ ገልጠዋል። አያይዘው ግን፤ መንግሥት ከውጭ ለገቡ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች በሚኖሩበት አካባቢ ችግር እንዳይገጥማቸው የጥበቃ ከለላ ሲያደርግላቸው መቆየቱን በማስታወስ፤ “አሁን ግን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋና ሰላም እየተረጋገጠ በመምጣቱ እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል በሰላም መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ከግንዛቤ በማስገባት፤ የግል ጠባቂዎችን ስናነሳ ቆይተና” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

አክለውም፤ ባሉት አሠራሮች መሠረት አስፈላጊ በኾነበትና ባልኾነበት ስፍራን በመለየት ይህ ሥራ በፖሊስ ውስጥ ሲከናወን የነበረ ተግባር ነው፤ ወደፊትም ይኽ ይኾናል በማለት ገልጠዋል።

ይኹን እንጂ በየትኛውም ፖሊስም ኾነ ሌላ አካል የተወሰደ እርምጃ እንደሌለና ሕብረተሰቡም ይህንን በአግባቡ እንዲያውቅ እንፈልጋለን በማለት በጃዋር ጉዳይ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

የኦሮምያ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሠጡት መግለጫ

ወደ ማምሻው ላይ የኦሮምያ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሠጡት መግለጫ ግን፤ ለጃዋር ሲደረግለት የነበረው ጥበቃ መነሳቱ አግባብ ያለመኾኑን የሚገልጥ ነው።

የጥበቃው መነሳት የመንግሥት አቋም ያለመኾኑን የሚያመለክተው የአቶ ሽመልስ መግለጫ፤ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው አካል ማን እንደኾነ ተጣርቶ እርምጃ ይወሰድበታል ስለማለታቸው መግለጫውን ካስተላለፉት መንግሥታዊ ሚዲያዎች ለማወቅ ተችሏል።

ጃዋር በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ መኾኑን ጭምር የገለጡት አቶ ሽመልስ፤ ጃዋር በመንግሥት ጥበቃ ሲደረግለት የነበረው በመንግሥት ታምኖበት ጭምር ነው ብለዋል። አሁንም ጥበቃው በነበረበት እንደሚቀጥልና የተቀየረ ውሳኔ ስለሌለ፤ በነበረው ይቀጥላል ማለታቸው ተገልጧል።

በተለያዩ ከተሞች በተደረገ ሰልፍ፤ ሕብረተሰቡ ትክክለኛ ስሜቱንና ጥያቄውን አቀርቧል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ አንዳንድ ልዩ ተልእኮ ያላቸው ወገኖች ግን ተቀላቅለው በንብረት ላይ ውድመትና ዘረፋ ለመፈፀም ተንቀሳቅሰዋልም ብለዋል። ጉዳዩ ሃይማኖትና የብሔር መልክ እንዲይዝ መንቀሳቀሳቸውንም ገልጠዋል።

አቶ ሽመልስ ለኦቢኤን በሰጡት መግለጫ፤ በተለያዩ ከተሞች ለተፈጠረው ዋናው ችግር የጃዋርን ጥበቃ ለማንሳት የተወሰደው እርምጃ መኾኑ ገልጠዋል ተብሏል።

አዳማ (ናዝሬት)

ከዚህ መግለጫ ቀድም ብሎ ግን በተለይ በአዳማ (ናዝሬት) በተደረገው ተቃውሞን የተቀላቀል ሰልፍ እስካሁን በተረጋገጠ መረጃ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። 16 ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ስለመሔዳቸው ከአዳማ ተደምጧል።

የአዳማው በተለየ የሚታይበት ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውና አንድ የዱቄት ፋብሪካ መቃጠሉ ነው። ማምሻውን እንደተደመጠው ደግሞ፤ የመከላከያና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎችና ፖሊስ በቅንጅት ከተማዋን ስለማረጋጋታቸው ተገልጧል።

ጀሞ፣ አዲስ አበባ

በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጀሞ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ፣ በተመሳሳይ በተፈጠረ ኹክት፤ በሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የተነገረ ሲኾን፣ እስካሁን ጉዳቱን የተመለከተ የተረጋገጠ መረጃ ይፋ አልተደረገም። ነገር ግን የአካባቢው መንገዶች በወጣቶች ተዘግተው የነበሩ ሲኾን፣ በአስፋልቶቹ ላይ ጎማዎችንም ሲያቃጥሉ እንደነበር ታውቋል። በአካባቢው የሚገኙ ባንኮችና አንዳንድ የንግድ ተቋማት ዝግ ኾነው ውለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ከቤታቸው ሳይወጡ መዋላቸውን ለመረዳት የቻልን ሲኾን፤ በስተመጨረሻ ማምሻውን የአካባቢው ነዋሪዎች ወጣቶቹን ከአውራጎዳናዎቹ እንዳባረሩዋቸው ታውቋል።

ቦሌ፣ አዲስ አበባ

በቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ ባለው የመኖሪያ ቤቱ የተገኙት የጃዋር ደጋፊዎች የተቃውሞ ድምፅ ከማሰማት ባለፈ የአካባቢውን መንገድ ዘግተው ፍተሻ እስከማድረግ ደርሰው እንደነበር ተግልጧል።

በአካባቢው ፖሊሶች ቢኖሩም፤ ምንም ዐይነት እርምጃ ሲወስዱ አልታዩም። ኾኖም በጃዋር መኖሪያ ቤት አካባቢ የተፈጠረው ግርግር በአካባቢው ያሉ ንግድ ተቋማት እንዲዘጉ አድርጓል። ትምህርት ቤቶች መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሠሩ ምክንያት ኾኗል።

ከዚህም በተጨማሪ የባንክ ቅርንጫፎች ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ ያልቻሉ ሲኾን፤ የንግድ ተቋማትና የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች መደበኛ ሥራቸውን ለማከናወን በመሥጋት ቢሮዎቻቸውን ዘግተዋል።

ሐረርና አካባቢው

በሐረር ከተማ የአንድ ወጣት ሕይወት መጥፋቱ የተነገረ ሲኾን፣ በዛሬው ዕለት ከተማዋ የፀጥታ ችግር እንደነበረባትና በርካታ የንግድ ተቋማት ተዘግተው መዋላቻቸው ታውቋል።

በሐረር ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ወረዳዎችም በርካታ ወጣቶች በጎዳናዎች ላይ ተሰብስበው ጃዋር መሐመድን የሚደግፉና ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን የሚቃወሙ መፈክሮችን ሲያሰሙ መዋላቸው ታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!