ዉሃን ከተባለች የቻይና ግዛት የተነሳው ኮሮና ቫይረስ

ዉሃን ከተባለች የቻይና ግዛት የተነሳው ኮሮና የተሰኘ ቫይረስ እስካሁን የ18 ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል

ኢትዮጵያም ያሰጋታል ተባለ

ኢዛ (ዓርብ ጥር ፲፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 24, 2020)፦ ዓለማችን ተዛማችና በፍጥነት የሚተላለፍ የሰው ልጆች ገዳይ የኾነ በሽታ በተደጋጋሚ ገጥሟታል። ከነዚህ በሽታዎች ውስጥ ኤድስ፣ ኢቦላና ሳርስ የሚጠቀሱ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥ ኤድስ የአጥቂነቱ ዕድሜ እየተራዘመ ሲሔድ ሌሎቹ ግን በቁጥር ስር ሊውሉ ወይም ሊጠፉ ችለዋል። በቅርቡ ደግሞ መነሻው ቻይና የኾነው ኮሮና ቫይረስ ዓለምን በሥጋት ወጥሯት ይገኛል።

ዉሃን ከምትባል የቻይና ግዛት የተነሳው የኮሮና ቫይረስ በትንፋሽ እንደሚተላለፍ የተነገረለት ሲሆን፤ በቀላሉ የሚዛመት በመኾኑ ለብዙ አገራት ሥጋት ሆኗል። በሽታው በተገኘባት በቻይና አሥራ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ፤ ቻይናን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች ስድስት መቶ በበሽታው መያዛቸው እየተነገረ ነው። ከቻይን ውጭ በደቡብ ኮርያ፣ በጃፓን፣ በታይዋን፣ በታይላንድ፣ በሆንግ ኮንግና በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በሽታው እንደገባ ታውቋል።

ይህ ከቻይና የተነሳው በሽታ ወደ አሜሪካም ሊሻገር መቻሉ ተረጋግጧል። በዚህም መሠረት አሜሪካ በተወሰኑ ግዛቶቿ የሚገቡትን እንግዶች ከበሽታው ነፃ መኾናቸውን መመርመር እንደጀመረች ታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በቀን ከ4 በረራዎች በላይ የሚያደርግ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ብቻ አየር መንገዱ ከ1400 በላይ በረራዎችን ወደ ቻይና አድርጓል። በርካታ መንገደኞች ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ በየዕለቱ የሚጓጓዙ በመኾኑ ምክንያት፤ ኢትዮጵያ ለበሽታው መተላለፍ ቅርብ እንደኾነች ይገመታል።

በዚሁ በሽታ አሳሳቢነት ምክንያት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የኾኑት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚኖሩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሰዎች ጋር ለመመካከር ስብሰባ ጠርተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ