15 ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

Ethiopia Zare (እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2000 ዓ.ም. July 6, 2008)፦ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጓጓዙ መንገደኞች ከየሻንጣቸው ውስጥ ንብረቶቻቸው እንደሚጠፋባቸው ማማረር ከጀመሩ ቆየት ብሏል። ዝርፊያው ለስድስት ወር ያህል የዘለቀ ነበር። ብዙውን ጊዜ ንብረት ከጠፋባቸው መንገዶኞች መካከል ጠንከር ብሎ ጥያቄውን ያቀረበ ንብረቱ በገንዘብ እየተቀየረ ይከፈለዋል፤ የፈራና የጣልኩት ሌላ ቦታ ነው ብሎ የጠረጠረ ደግሞ እንደጠፋበት ይቀራል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዕቃ እየጠፋ መሆኑ በተደጋጋሚ ሪፖርት ከደረሰው የቆየ ቢሆንም፤ ወደ ሕግ ከመሄድ ይልቅ የተለያዩ አማራጮችን ሲወስድ መቆየቱን ምንጮች ይናገራሉ። ከዚህ በፊት ተጠርጥረው የነበሩ፣ በዕቃ ማውረድና መጫን አካባቢ የሚሠሩ ሠራተኞች የሞባይል ስልኮችና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ይዘው እንዳይገቡ ተከልክለዋል። ምክንያቱም ሲወጡ የግላቸው በማስመሰል የሰው ዕቃ ይዘው ይወጣሉ በሚል ነበር።

 

የመንገዶኞችን ንብረት ከዝርፊያ ለማዳን የተዘጋጀው መፍትሔ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድን መንገደኞች ከዝርፊያ ሊያድን አልቻለም። በመጨረሻ አየሩ መንገዱ በወሰደው ማጣሪት በዝርፊያው ተጠርጣሪ ናቸው ያሏቸውን ሠራተኞቹን ስም ዝርዝር ለፖሊስ አስተላልፏል። ፖሊስ ደግሞ ክሱን ለዓቃቤ ሕግ በመምራቱ፣ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪ አድርጎ ክስ መስርቶባቸዋል።

 

በቁጥጥር ስር የዋሉት ሠራተኞች በብዛት ከሲቪል ሰርቪስና በዘመድ አዝማድ አየር መንገዱን የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ስም ዝርዝራቸው ይፋ ሆኗል። ሻሮን አበራ በአየር መንገዱ የትረስት ጊዜያዊ ሠራተኛ፣ ዘላለም መንግስቱ በአየር መንገዱ የኮምፒዩተር ጥገና የሥራ ባልደረባ፣ ይርጋ የሺጥላ በአየር መንገዱ የንብረት ቁጥጥርና ስርጭት፣ ጥላሁን መኩሪያ በብሔራዊ ደህንነት ባለሥልጣን የኤርፖርት ደህንነት የሥራ ባልደረባ፣ ማይክል ብርሃኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃ አውራጅና ጫኝ፣ ያሬድ ታደሰ በአትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃ ግምጃ ቤት፣ ፋንታሁን ገ/መስቀል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሴኩሪቲ ሠራተኛ፣ ዮናስ ነጋሽ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሴኩሪቲ ሠራተኛ፣ ውብሸት ቦጋለ መረጃ ደህንነት ባለሥልጣን የኤርፖርት ደህንነት ጥበቃ የሥራ ባልደረባ፣ ሲሳይ ስዩም በአየር መንገዱ የመንገደኞች ዕቃ መጋዘን የፎርክሊፍት ኦፕሬተር፣ ሁሴን መሐመድ በአየር መንገዱ የመንገደኞች ዕቃ መጋዘን የፎርክሊፍት ኦፕሬተር፣ አብርሃም ካሱ በአየር መንገዱ የመንገደኞች ዕቃ መጋዘን የፎርክሊፍት ኦፕሬተር፣ ወርቁ ታደሰ በአየር መንገዱ የፎርክሊፍት ኦፕሬተር፣ እውቀት ብርሃኑ በአየር መንገዱ የፎርክሊፍት ኦፕሬተር፣ ረ/ኢ/ር አዲስ መሉጌታ በፊ/ፖ መከላከል ዋና መምሪያ የአየር መንገዱ ጥበቃ፣ እንዳልካቸው ጌትነት የአየር መንገዱ ተሽከርካሪ ሹፌር፣ ዳንኤል ጥላሁን በአየር መንገዱ አውራጅና ጫኝ፣ ግርማቸውን ገ/ንጉሥ በአየር መንገዱ የካርጎ የመንገድ ዕቃ መጋዘን የፎርክሊፍት ኦፕሬተር በአጠቃላይ 22 ተከሳሾች በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል። ከዚህ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉት 15 ሲሆኑ፣ ሰባቱ ተይዘው እንዲቀርቡ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 

በተከሳሾቹ ላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሁሉም ግብርአበር በመሆን የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከኅዳር 2000 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 2000 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚመጡ በአትዮጵያ አየር መንገድ በሚያልፉ፣ በትራንዚት አውሮፕላኖች የሚጓጓዙ መንገደኞችን ንብረት ወስደዋል የሚል ነው።

 

ተከሳሾቹ የመንገደኞቹን የሞባይል ስልክ፣ የሞባይል ስልክ መለዋወጫ ዕቃዎች፣ ቻርጀሮች፣ መድኃኒቶችና ኮምፒዩተሮች፣ የኮምፒውተር ዕቃዎች፣ የሕክምና መገልገያ ዕቃዎች፣ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎችን በቡድን ተደራጅተው የሥራቸውን አጋጣሚ ምክንያት በማድረግ በእጃቸው ሊገቡ የቻሉትን የመንገደኞች ንብረት በመውሰድ፣ ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸውና አየር መንገዱም ዕቃቸው ለጠፉባቸው ግለሰቦች ከ65 ሺ 672. 02 ዶላር በላይ መክፈሉ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

 

ስለዚህም ተከሳሾቹ በጋራ በመሆን ለፈፀሙት የሰው ንብረት ወስደው በመሰወር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው እንዲቀጡለት ጠይቋል።

 

ፍ/ቤቱም ከተከሳሾቹ መካከል 15 ሲቀርቡ ሰባቱ ያልቀረቡ መሆናቸውን አረጋግጦ፣ ፖሊስ በሚቀጥለው ቀጠሮ ተከሳሾቹን ፈልጎ እንዲያቀርብ አዝዟል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!