ቦሌ ላይ ኮሮና ቫይረስ ይዟቸዋል ተብለው የተጠረጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን ክትትል እየተደረገላቸው ነው

የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ መግለጫው በተሠጠበት ወቅት
ለተጨማሪ ምርመራ የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳል
ኢዛ (ማክሰኞ ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 28, 2020)፦ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከቻይና ዉሃን ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበሩ አራት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው በኳራንቲን ተለይተው ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙና በደም ምርመራ ከአምስት ዐይነት የኮሮና ቫይረስ ነፃ መኾናቸው ቢረጋገጥም፤ የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩ ዛሬ ተገለጸ።
በዉሃን (Wuhan) ግዛት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ወደ አገራቸው የተመለሱት አራት ተማሪዎች የሰውነታቸው ሙቀት መጠን ከፍ በማለቱ፤ እንዲሁም በተለይም አንዱ የጉንፋን ምልክቶች ታይተውበት ስለነበር፤ አራቱንም ተማሪዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል እንደተወሰዱና ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑን ዛሬ መግለጫ የሠጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቀዋል።
ምንም እንኳን የተወሰደው የደም ናሙናቸው ከጉንፋን መሰልና ከአምስት የኮሮና ቫይረስ ዐይነቶች ነፃ ኾኖ የተገኘ ቢኾንም፤ ለከፍተኛ ምርመራ የደም ናሙናዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ መላካቸው ተገልጿል። ጉንፋ መሰል ምልክቶች የታዩበት ግለሰብን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት የአራቱም ተጠርጣሪዎች ጤና በመልካም ሁኔታ ላይ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በቻይና ኤምባሲ ጠቋሚነት ከቻይና ጓንዡ ግዛት ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሁለት ቻይናውያን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለሁለት ሰዓታት ሲመረመሩ እንደነበር ተገልጿል። ሁለቱ ግለሰቦች በሙቀት መለያ መሳሪያው ታይተው ምንም ዐይነት ምልክት ባለመገኘቱና ቫይረሱ ካለበት አካባቢ ጋር ግንኙነት እንዳልነበራቸው ተጣርቶ ወደ አገራቸውን እንዲበሩ መደረጉ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
በበሽታው ለተጠረጠሩ መንገደኞች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጊዜያዊ ማቆያና የለይቶ መከታተያ ክፍልና የሰው ኃይል መዘጋጀቱ ተጠቁሟል። (ኢዛ)