የቡራዩ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በታጣቂዎች ተገደሉ
በታጣቂዎች የተገደሉት የቡራዩ ከተማ የጸጥታ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሰለሞን ታደሰ
አብረዋቸው የነበሩ ቆስለዋል
ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 21, 2020)፦ ዛሬ ምሳ ሰዓት ላይ የቡራዩ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በታጠቁ ኃይሎች ተተኮሰባቸው ሲገደሉ፤ አብረዋቸው የነበሩ የፖሊስ አዛዥም በጥይት መመታታቸው ተገለጸ። ይህ አሳዛኝ ድርጊት የተፈጸመው የቡራዩ ከተማ የጸጥታ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ታደሰና ሌሎች ሰዎች ምሳ በመብላት ላይ እያሉ ነው።
በዚሁ ጥቃት የአቶ ሰለሞን ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ፤ የአዲስ አበባ ዙሪያ ፖሊስ አባል (አዛዥ መኾናቸው ይነገራል)፤ በጥቃቱ ቆስለው ሆስፒታል እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
ይህንን አደጋ የጣለውን አካል እስካሁን ማንነቱ ያልታወቀ ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል ጥቃት ስለመድረሱ አረጋግጦ፤ ጥቃቱን የሰነዘሩትን አካላት የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል። ባሁኑ ወቅት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በቡራዩ ፍተሻ እያደረገ ነው።
በቡራዩ አካባቢ ከዚህ ቀደም በአንድ የፖሊስ ካምፕ ላይ በተደረገ ጥቃት ስምንት የጸጥታ ኃይሎች ቆስለው እንደነበር ይታወሳል።
ቆስለው በሕክምና ላይ ያሉት የፊንፊኔ ዙሪያ ዞን የልዩ ፖሊስ አዛዥ አቶ ተስፋዬ ድንቁ ናቸው። (ኢዛ)



