የኮሮና ቫይረስ የዋጋ ጭማሪዎችን እያስከተለ ነው
ከፍተኛ የዋጋ ንረት በአገሪቱ እየተስተዋለ ነው
መንግሥት ግብረኃይል አቋቁሟል
ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 14, 2020)፦ በኢትዮጵያ አንድ ጃፓናዊ በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው መገኘቱ ከተገለጸ በኋላ ገበያውን እያወኩ ያሉ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው። ከፍተኛ ዋጋ ንረት በአገሪቱ እየተስተዋለ ነው።
በተለይ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ የአፍ ማስክ፣ የእጅ መጽጃ አልኮልና ተመሳሳይ አገልግሎት ይሠጣሉ የተባሉ ዕቃዎች ከመደበኛው ዋጋ በላይ እየተሸጡ ነው። እንደምሳሌ የሚጠቀሰው ከ50 - 55 ብር ይሸጥ የነበረ የእጅ ማበሻ አልኮል ከ120 - 200 ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ የአፍ ማስክ ደግሞ ከአንድ መቶ ብር በላይ ሲሸጥ ታይቷል። የአፍ ማስክ የኮረና ቫይረስ ጉዳይ እንዲህ ባልግነነበት ወቅት ከ10 ብር ያነሰ ዋጋ የነበረው ነው።
ከትናንት ጀምሮ ግን አንዳንዶች ዋጋውን እጅግ በማናር ሲሸጡ የታየበት ሁኔታ ገበያውን እየረበሸ ነው። ፋርማሲ የለም የተባለ የአፍ ማስክ፤ ዛሬ መንገድ ላይ እስከ 150 ብር እየተሸጠ መኾኑ በአሳዛኝነቱ የሚታይ ድርጊት ኾኗል። ሕብረተሰቡ ከትናንት በኋላ አግባብ የሌለው ግብይት እየፈጸሙ ያሉት እነዚህን ምርቶች ብቻ ሳይኾን ምግብ ነክ ምርቶችንም በብዛት መሸመታቸው የአንዳንድ ሹፐር ማርኬቶችን ሼልፍ ባዶ አድርጓል።
ትናንት ከሰዓት በኋላ የታየው የሰዎች የመግዛት ፍላጎት የአንዳንድ ነጋዴዎች ተፈላጊ ናቸው ባሉዋቸው ዕቃዎች ላይ ያደረጉት የዋጋ ጭማሪን ተከትሎ፤ መንግሥት ትናንት ማምሻውን መግለጫዎች አውጥቷል። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ዋጋ የሚጨምሩትን ለመቅጣት አንድ ግብረኃይል ያቋቋመ ሲሆን፤ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቷል። ይሁንና ዛሬም አንዳንድ ቦታ የሚታየው ነገር አሳዛኝ ነው። ተጠቃሚዎች ጥቆማ እንዲያደርጉ የተጠየቀ ሲሆን፤ በድርጊቱ የተሳተፉ ያሉ ሰዎች ምን እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደኾነ አልተገለጸም።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተጋነነ ዋጋ የሚጠይቁ ድርጅቶችን ለመቆጣጠርና አቅርቦትን ለማሻሻል የተደራጀው ግብረኃይል ዛሬ እንደሚጀምር ገልጾም ነበር። (ኢዛ)



