Prof. Hirut Woldemariam

ፕሮፌሠር ሒሩት ወልደማሪያም፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር

ለ45 ዩኒቨርሲቲዎች መመሪያው ተላልፏል

ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 16, 2020)፦ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ሁሉም የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ተቋማት ሊተግብሯቸው ይገባል ያሉትን መመሪያ አስተላለፉ። ይህ መመሪያ እንዲደርሳቸው የተደረጉት 45 ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።

ሚኒስትሯ ፕሮፌሠር ሒሩት ወልደማሪያም ዛሬ ማምሻውን ያስተላለፉት መመሪያ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች እና ጥንቃቄዎችን ይመለከታል

የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ሥጋት መኾኑ ይታወቃል። በአገራችንም እስከ አሁን አምስት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደኾነና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል። በአሁኑ ጊዜ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከልና ለመግታት መንግሥት መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። የዓለም የጤና ድርጅትም በሽታው ወረርሽኝ መኾኑን ካወጀበት ጊዜ አንስቶ ለጥንቃቄ ይጠቅማሉ ብሎ ካስቀመጣቸው መፍትሔዎች መካከል የሰዎች መሰባሰብን የሚሹ ጉዳዮችን ማስቀረት ይገኝበታል።

የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የመጡ በመኾናቸው ተቋማቱን ዘግቶ ተማሪዎቹን ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ እየተወሰዱ ካሉ ጥንቃቄዎች አኳያ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳሚያመዝን ታምኖበታል። ምክንያቱም ተማሪዎቹ ወደየመጡበት አካባቢ በሚሔዱበት ጊዜ በጉዟቸው ለቫይረሱ የመጋለጣቸው እድል ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ስለኾነም ባሉበት ኾነው ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሠጡ መመሪያዎችን ተከትለው ጥንቃቄ በማድረግ በመምህራኖቻቸው የሚሠጡ ንባቦችን እያካሔዱ ለሁለት ሳምንታት የሚቆዩ ይኾናል።

ይህም ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ

1. ለተማሪዎች አስፈላጊው ክትትል ይደረግ፤
2. ፊት ለፊትና በክፍል የሚሠጡ ትምህርቶችን በማስቀረት ለተማሪዎች handout, reference books, online, soft copy materials ወ.ዘ.ተ በበቂ ደረጃ በማቅረብ እና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም በግላቸው/ በመኝታ ክፍላቸው ኾነው እንዲያነቡ ይደረግ፣ መምህራን በኢሜይልና በተለያዩ ስልቶች የመማር ማስተማሩን ሥራ እንዲያስቀጥሉ ይደረግ፣ ይህ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን በየደረጃውና በተዋረድ ክትትል ይደረግ፤
3. ተማሪዎች እጃቸውን አዘውትረውና በተደጋጋሚ በሳሙና በመታጠብ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ተቋማት በአስቸኳይ የሳሙና፣ ሳኒታይዘር እና አልኮል አቅርቦቶችን በመግዛት ተደራሽ እንዲያደርጉና እንዲያሰራጩ ይደረግ፤
4. በቤተ መጻሕፍትና በመመገቢያ አዳራሾች መተፋፈግን ለማስቀረት የመቀመጫዎች ጥግግት እንዳይኖር ይደረግ፣ መጨናነቅ እንዳይኖርም የአገልግሎት መስጫ ሰዓት ይራዘም፤
5. ኮንፍረንሶች፣ ወርክሾፖች እና ስብሰባዎች እንዳይኖሩ ይደረግ፤ ቀድም ብለው የታቀዱም ካሉ ይሰረዙ፣ ግድ የሚሉ ስብሰባዎች ሲያጋጥሙ ቅርርብና ጥግግት ሳይኖር ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ይከናወን፣ እንዲሁም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ይካሔድ፤
6. ስለቫይረሱ ግንዛቤ የሚፈጥሩ መልእክቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ግቢዎች ውስጥ ተደራሽ ይደረጉ፤
7. በየተቋማችሁ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የሚከታተል አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትል ይደረግ፣ የቫይረሱ ምልክት የታየባቸውን ለመጠቆም የሚያስችሉ ስልክ ቁጥሮች በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ተዘጋጅተው ጥቆማዎችን የሚቀበሉና ለበላይ አመራሩ ሪፖርት የሚያደርጉ ይሁን።

በመኾኑም በሁሉም የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመጋቢት 8/2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለ2 ሳምንታት ቀጣይ አቅጣጫ እስከሚሠጥ ድረስ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 7 ያሉትን በየተቋሞቻችሁ ተግባራዊ እንድታደርጉ በጥብቅ አሳስባለሁ።

ፕሮፌሠር ሒሩት ወ/ማርያም
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ