በኢትዮጵያ ስድስተኛው የቫይረሱ ተጠቂ ተገኘ
ኮሮና ቫይረስን በምስል ለማሳየት በበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የተሠራጨ
በጥቆማ በተደረገ ምርመራ በቫይረሱ የተያዘችው እንግሊዛዊት ነች
ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 17, 2020)፦ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጣው መግለጫ አዲስ አበባ ውስጥ ኮሮና ቫይረስ ያለበት ሰው ተገኝቷል። ቫይረሱ የተገኘባት ስድስተኛዋ ሰው የ59 ዓመት ዕድሜ ያላት እንግሊዛዊት ዲፕሎማት ነች።
ግለሰብዋ በዛሬው ዕለት (መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከዱባይ አዲስ አበባ የገባች ሲሆን፤ ካረፈችበት ሆቴል በተደረገ ጥቆማ፤ ግለሰቧ በምትገኝበት ራስዋን አግልላ እንድትቆይ ተደርጎ፤ በተደረገላት ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዝዋ ተረጋግጧል።
እስካሁን በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል አራቱ የውጭ ዜግነት ያላቸው ሲሆን፤ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የውጭ ዜግነት ካላቸው ውስጥ ሦስቱ ጃፓናውያን ሲሆኑ፤ አንዷ (የዛሬዋ) እንግሊዛዊት ናቸው። (ኢዛ)



