PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ለግል ባንኮች 15 ቢሊዮን ብር እንዲፈቀድ ተወሰነ
በአበባ የወጪ ንግድ ላይ የተጣለው ዋጋ ጣራ ተነስቷል
ለወረርሽኙ መከላከያ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ ይገባሉ

ኢዛ (ዓርብ መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 27, 2020)፦ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በኢኮኖሚው ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ተጽእኖዎችን ለመከላከልና ኢኮኖሚውን ደኅንነት ሊጠብቁ ይችላሉ የተባሉ ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ጋር ዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ምክክር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከተደረገባቸው ውስጥ አንዱ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎችና ግብአቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉ ነው።

ከዚህም ሌላ የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት ለመጠበቅና የፋይናንስ ተቋማት በኮሮና ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞች ጊዜያዊ የብድር እፎይታና ተጨማሪ ብድር ለማቅረብ እንዲያስችላቸው ለግል ባንኮች ተጨማሪ 15 ቢሊዮን ብር እንዲቅርብላቸው መወሰኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 15 ቢሊዮን ብሩ ለግል ባንኮች የሚቀርበው ከብሔራዊ ባንክ ነው።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ባንኮች እንዲፈጽሙት የተላለፈው ሌላው ውሳኔ፤ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብአቶችን ለማስገባት ለሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ባንኮች ቅድሚያ እንዲሠጡ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ የወጪ ንግዱ የቀነሰው የአበባ ዘርፉን ከአደጋ ለመጠበቅ፤ ብሔራዊ ባንክ ለአበባ የወጪ ንግድ ላይ የጣለውን ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳላቸው ተወስኗል።

አበባ ላኪዎች ወደ 30 በመቶ የሚኾነውን አበባ ሲልኩ በአንድ ኪሎ አበባ መሸጥ ያለባቸው ተብሎ የተቀመጠውን ዝቅተኛ ዋጋ ሳይተገብሩ ባገኙት ዋጋ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል።

በብሔራዊ ባንክ ተጥሎ የነበረው አንድ አበባ ላኪ አንዱን ኪሎ አበባ ከ3.87 ዶላር በታች እንዳይሸጡ ነው። አሁን ባለው ገበያ በዚህ ያህል ዋጋ መሸጥ ስለማይችሉ፤ በጊዜያዊነት ባገኙት ዋጋ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል። ሌሎች ኢኮኖሚ ነክ ውሳኔዎችም ተላልፈዋል። ውሳኔው በአጭሩ ከዚህ በታች ቀርቧል። (ኢዛ)

በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የተወሰነው ውሳኔ
በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የተወሰነው ውሳኔ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!