የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ጤና ሚኒስቴር

በኢትዮጵያ በኮሮና የተያዙት ቁጥር 21 ደረሰ

ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 29, 2020)፦ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባደረገው ምርመራ ዛሬ መጋቢት 20 ቀን ሁለት ተጨማሪ ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ማረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። በድምሩ 21 ግለሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ መያዛቸው ታውቋል።

በዛሬው ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ግለሰቦች ከዚህ በፊት ዱባይ ደርሰው የመጡ ሲሆን፣ የ35 ዓመት ሴትና የ38 ዓመት ወንድ መኾናቸውን ከጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ያመላክታል።

በዚሁ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ላይ በአገሪቱ ውስጥ 17 ታማሚዎች በለይቶ ማቆያ የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ አንዲት ሴት ታማሚ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገላት እንደኾነ ያስረዳል። እስካሁን ሁለት ታማሚዎች ሙሉ ለሙሉ ያገገሙ ቢኾንም፤ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው እንደኾነ ታውቋል።

በትናንትናው ዕለት 87 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው፤ ሦስቱ ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን መረጃ መሠረት በማድረግ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ከእነዚህ ሦስቱ ታማሚዎች ውስጥ አንዷ የ26 ዓመት ዕድሜ ያላት ኢትዮጵያዊትና የአዲስ አበባ ነዋሪ ስትኾን፤ መጋቢት ውስጥ ብራስልስና (ቤልጅየም) ካሜሮን የጉዞ ታሪክ የነበራት መኾኑን ከጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ፣ የ14 እና የ48 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ነዋሪነታቸው ናዝሬት ውስጥ የኾኑ ኢትዮጵያውያን መኾናቸው ታውቋል። እነዚህ ግለሰቦች ከዚህ ቀደም ቫይረሱ ካለበት ግለሰብ ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ከታወቀ በኋላ፤ በለይቶ ማቆያ ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ፤ በትናንትናው ዕለት መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ቫይረሱ እንዳለባቸው በላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቱ ተመስክሯል። በናዝሬት እስካሁን 3 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ