የዘጠኝ ወር ሕፃን በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተጠቃ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
በቫይረሱ የተያዙ 52 ደርሰዋል
ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 7, 2020)፦ በኢትዮጵያ የዘጠኝ ወር ዕድሜ ያለው ሕፃንን ጨምሮ ስምንት አዳዲስ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች መገኘታቸውንና በኢትዮጵያ አጠቃላይ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 52 መድረሱ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በ24 ሰዓት ውስጥ ለ264 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ፤ ስምንት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ተገኝተዋል። ከስምንቱ ሰባቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ አንዷ ኤርትራዊት ነች።
ዛሬ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ሪፖርት በአሳዛኝ ሁኔታ አንድ የዘጠኝ ወር ሕፃንና እናቱ ባቫይረሱ መያዛቸውን አመልክቷል። የዘጠኝ ወሩ ሕፃን ከዱባይ የመጣና በለይቶ ማቆያ የነበረ ነው።
ከስምንቱ አንዱ የ19 ዓመት ወጣትም በቫይረሱ መጠቃቱ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፤ የውጭ ጉዞ የሌለው ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ስምንቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው። አምስቱ ከዱባይ የመጡ ሲሆኑ፣ አንዷ ከታይላንድ እንዲሁም ኤርትራዊቷ ከሎንዶን ዩናይትድ ኪንግደም የመጡ መኾናቸው ታውቋል። (ኢዛ)



