እኅተ ማርያም

እኅተ ማርያም (ወ/ሮ ትዕግሥት ፍትሕአወቅ /ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ)

“ወ/ሮ ትዕግሥት ፍትሕአወቅ እንግሊዛዊት ነች፤ የኢትዮጵያ ዜግነት የላትም” ፖሊስ

ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 1, 2020)፦ ራስዋን ንግሥተ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ በሚል በመጥራት ስትንቀሳቀስ የነበረችውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ያዋለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራዬን ቀጥያለሁ አለ። ስሟ ወ/ሮ ትዕግሥት ፍትሕአወቅ እንደኾነ፣ እንግሊዛዊት እንደኾነችና የኢትዮጵያ ዜግነት እንደሌላት ፖሊስ ገልጿል።

በዛሬው የፖሊስ መረጃ እኅተ ማርያም በሚል ስም የምትታወቀው ግለሰብ ትክክለኛ ስሟ ወ/ሮ ትዕግሥት ፍትሕአወቅ እንደኾነ በመጥቀስ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ በቁጥጥር ሥር መዋሏንም አስታውሷል። በዚህ አዋጅ መሠረት ማንኛውንም ተግባር ለመፈጸም፣ ለመነጋገር፣ ለመወያየት ወይም መሰል ተግባራትን ለማከናወን የአንድ ቤተሰብ አባላት ከኾኑ ውጪ አራት እና ከዚያ በላይ ኾኖ በአንድ ቦታ በአካል መገኘትን የሚከለክለውን ድንጋጌ ጥሳለችም ብሏል።

ይህም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ሉባር ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ፤ በርካታ ሰዎችን በመሰብሰቧ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራው እየተጣራ መኾኑን ገልጾ፤ በተጨማሪም “ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታ የለም፣ ተቃቀፉ፣ ተሳሳሙ” በሚልና ሌሎች መልእክቶች በማኅበራዊ ትስስር ገጽ በመልቀቅ፤ በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው የወረርሽኙን ሥርጭት ለመከላከል ከሚወስዱት የጥንቃቄ እርምጃ እንዲዘናጉ የማድረግ ተግባር መፈጸሟንም ጠቅሷል።

ወይዘሮ ትዕግሥት ፍትሕአወቅ እንግሊዛዊት እንደኾነችና የኢትዮጵያ ዜግነት እንደሌላት፤ በ1986 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ እንደወጣችና በ2007 ዓ.ም. ከ21 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰችም የዛሬው የፖሊስ መረጃ አመልክቷል። አያይዘውም ወይዘሮዋ በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚገኘውን ዓርማ በመቅደድና በማቃጠል፤ እንዲሁም በ2009 ዓ.ም. ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመሔድ “ታራሚዎችን ላስፈታ እመቤቴ ማርያም ልካኝ ነው የመጣሁት” በማለት ታራሚዎችን በማነሳሳት በፈጸመችው ሕገ-ወጥ ተግባር በቁጥጥር ስር ውላ እንደነበር የዛሬው መረጃ አመልክቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!