አስደንጋጩ የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ረቡዕ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
በ24 ሰዓት በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ 17 ኢትዮጵያውያን ተገኙ
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 6, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ በ24 ሰዓት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸው ይፋ ኾነ። ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቀን በቫይረሱ የተጠቁ 17 ሰዎች ተገኙ።
የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ በ24 ሰዓት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 1,382 ሰዎች ውስጥ 17ቱ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ የቫይረሱ ተጠቂ የኾኑ ሰዎች ቁጥር ወደ 162 ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በዛሬው ሪፖርት ቫይረሱ ከተገኘባቸው 17 ሰዎች ውስጥ፤ 13ቱ ከጅቡቲና ከሶማሊያ ተመልሰው በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው። አራቱ ደግሞ ከአዲስ አበባ ሲሆን፤ ከአራቱ አንዱ ግን ነዋሪነቱ አፋር እንደኾነ ተጥቅሷል።
ከጅቡቲ ተመልሰው በአፋር አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩት 7ቱም ወንዶች ሲሆኑ፣ ከ14 እስከ 65 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው። ከሶማሊያ የተመለሱትና በሶማሌ ክልል አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩት ደግሞ 6 ወንዶች ሲሆኑ፤ ከ20 እስከ 41 ዓመት የዕድሜ ክልል ክልልው ውስጥ የሚገኙ መኾናቸው ታውቋል።
ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው ከ17 ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ብቻ ሴቶች ሲሆኑ፣ እነሱም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና የ28 እና የ53 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው። በአዲስ አበባ የተገኙት አራቱም ሰዎች የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መኾኑ ተገልጿል።
ከእስከዛሬዎቹ ሪፖርቶች በአስደንጋጭነቱ የሚታየው የዛሬው የጤና ሚኒስቴር መረጃ፤ ከአዲስ አበባ ውጭ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አስገዳጅ ማቆያ ውስጥ እየተገኙ ያሉ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።
ከአዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መረጃ ባሻገር፤ ሁለት አዳዲስ ሰዎች ከቫይረሱ በማገገማቸው፤ ያገገሙትን ሰዎች ቁጥር 93 አድርሶታል። ትናንት ወደ 48 ዝቅ ብሎ የነበረው በቫይረሱ ተጠቅተው ሕክምና የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር ዛሬ 63 ደርሷል።
ዛሬ የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸውን ጨምሮ እስከ አሁን ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች 26,517 ነው። (ኢዛ)



