ኢዜማ

ኢዜማ (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ)

ፓርቲው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ የሚል አማራጭ ሐሳብ ላይ ተስማምቷል

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 6, 2020)፦ ኢዜማ (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ) ከወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የፓርቲውን አቋምና መኾን ይገባዋል ብሎ የሚያምንባቸውን እርምጃዎች የሚያመለክት መግለጫ ዛሬ አውጥቷል።

ፓርቲው “የምንሰጣቸው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ ሕገ መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል” በሚል ርዕስ ያወጣው መግለጫ ያለውን ችግር ለመሻገር ያስፈልጋሉ ያላቸውን የተለያዩ ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ አንቀጾችን በመጥቀስ አቋሙና ያንጸባረቀበት ነው።

በተለይ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫውን ለማራዘም እየተሔደበት ባለው መንገድና መኾን አለበት ያለውንምብ በዚሁ መግለጫ ላይ አሳውቋል። ፓርቲው ሁለት የመፍትሔ አማራጮች ላይ መወያየቱን ገልጾ፤ የመጀመሪያው አማራጭ “ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሔ” እንደኾነና ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ “በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች” እንደነበር አስታውቋል።

ኾኖም የመጀመሪያውን አማራጭ ፓርቲው ያልተቀበለው ሲሆን፤ በሁለተኛው አማራጭ ስር ከቀረቡት አራት አማራጮ ውስጥ ሦስቱን አለመቀበሉን ገልጿል። አራተኛውንና “በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ” የሚለውን አማራጭ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ኾኖ ማግኘቱን ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።

መግለጫው ይህንንም፤ “አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የኾነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልጽ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።” በማለት አብራርቷል። የመግለጫውን ሙሉ ቃል አስነብበኝ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ