PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ክልሎች በሙሉ የማዳበሪያ እዳቸውን ሲከፍሉ፤ ያልከፈለው የትግራይ ክልል ብቻ ነው

ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 8, 2020)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ሲባል፤ ከትግራይ ክልልና ከሕወሓት ወቅታዊ አቋም አንፃር አንድ ነገር ይነሳል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መካከል ይኸው ጉዳይ ተነስቷል። በሌላ አመለካከትም በክልሉ ላይ ጫና ያደርጋል ከሚል መንደርደሪያ ተነስቶ፤ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ተከታትለው የቀረቡበት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል እና ሕወሓትን በተመለከተ የሰጡትን ሰፋ ያለ ምላሽ ያዋዙት፤ “የትግራይ ሕዝብ ጀግናና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ጥሮ ግሮ የሚበላ ሕዝብ ነው” በማለት ነበር። ይሔ የሚካድ ሐቅ ያለመኾኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ችግር የኾነው የትግራይ ሕዝብና ፓርቲን እየቀላቀሉ መመልከቱ ነው” ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብን የሚያክል ትልቅ ሕዝብ፤ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ብቻ አድርጎ ማሰብ ትክክል ያለመኾኑንም በመጥቀስ፤ ምክንያቱም በክልሉ ውስጥ እንደ ዓረና፣ ባይቶና መሰል ሌሎች ፓርቲዎችም ስላሉ፤ እንዲሁም በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ኾነው የሚታገሉ የትግራይ ተወላጆች ስላሉ፤ የትግራይ ሕዝብ በአንድ ፓርቲ ብቻ የሚወከል አለመኾኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል መንግሥትን በሙሉ ሌባ፣ አጥፊ፣ የማይሠራ አድርጎ ማሰብ ስሕተት ስለመኾኑ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ክልሉን ለመለወጥ የሚጥሩ ብዙ ሰዎች በመሐሉ መኖራቸውንም አስረድተዋል።

ሕወሓትን ከሊቀመንበሩ ጀምሮ ሁሉም ጥፋተኛ ናቸው የሚል እምነት እንደሌላቸው፤ በፓርቲው ውስጥ ለዚህ አገር ሕዝብ መሥዋዕትነት የከፈሉ ባለውለታዎች ስለመኖራቸውና ይሔ ማለት፤ ጥፋተኛ፣ የሚሳደቡ፣ ወንጀለኛ በመሐላቸው የለም ማለት አለመኾኑንም በመጥቀስ፤ የእርሳቸውንና የመንግሥታቸውን ምልከታ ያንፀባረቁበትን ምላሽ ሰጥተዋል።

“አንድ ሰው ሲወቀስ፣ ሁለት ሰው ሲወቀስ፤ የትግራይ ሕዝብ የተወቀሰ አድርገን አንውሰድ። አማራ ነህ፣ ትግሬ ነህ፣ ኦሮሞ ነህ፣ … በሚል መባላቱን ኖርንበት፤ ከድህነት አላወጣንም” በማለትም ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ላይ የተለያዩ ጫናዎች ያደርጋሉ የሚለውንና ከበጀት ጋር ተያይዞ አሉ ለተባሉ ተፅእኖዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአኀዝ የተደገፈ ምላሽ የሰጡበት ነበር። እንዲህ ካለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከሰጡት መልስ ውስጥ፤ ትግራይ እስከ ለውጡ ድረስ በጀቱ ማደግ የቻለው 7 ቢሊዮን ብር ድረስ እንደነበር በማስታወስ ነው። ከለውጡ በኋላ የተመደበለት በጀት ግን 42 በመቶ ስለማደጉም አመልክተዋል። ይሔ እድገት ለፕሮጀክት የሚመደብን ገንዘብ የማይጨምር መኾኑን አክለው አስረድተዋል። እንደሚባለው የትግራይን ሕዝብ የመጉዳት ምንም ዐይነት የሚደረግ ጥረት የሌለ መኾኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን አባባላቸውን፤ “የትግራይን ሕዝብ የመጉዳት ዜሮ በመቶ ፍላጎት የለንም” በማለት ቁርጥ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። አያይዘውም የምንወደውን የትግራይ ሕዝብ አትወዱትም ጎዳችሁት የሚለን ካለ አቧራ ነው ያልፋል፤ አሻራው ይገለጣል፤ ያኔ ሕዝቡ እውነታውን ይረዳል በማለት አክለዋል።

በተደጋጋሚ ከሚነዙ ወሬዎች መካከል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ለክልሉ የተደረገው ድጋፍ አነስተኛ ነው የሚል አንደምታ ያለው ነበር። ይህ ትክክል ያለመኾኑን የተናገሩት ዶ/ር ዐቢይ፤ “ለትግራይ ክልል ኮሮናን የመከላከል ሥራ 46 ሚሊዮን ብር ገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል” በማለት፤ ሲናፈስ የነበረው ወሬ ሐሰት መኾኑን የሚያመለክት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ክልል ባለፈው ዓመት ተበድሮ የገዛውን የማዳበሪያ ክፍያ መክፈል ሲገባው፤ ባለመክፈሉና ዘንድሮ የማዳበሪያ ገንዘብ መግዣ የለኝም ስላለ ሥራው መቆም ስለሌለበት፤ አርሶ አደሩ እንዳይጎዳ መንግሥት 445 ሚሊዮን ብር የበጀት ድጋፍ አድርጓል በማለት፤ አለ ያሉትን እውነታ አሳይተዋል። በተቃራኒው ግን ሌሎች ክልሎች በሙሉ ለማዳበሪያ የተበደሩትን ገንዘብ መክፈላቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም።

በትግራይ ሕዝብ ላይ ጫና ደርሷል፤ ተጠቃሚ አልኾነም ከሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች አንፃር፤ “ፌዴራል መንግሥት ከለውጡ በኋላ ለክልሉ ካደረጋቸው እገዛዎች መካከል እንደ ምሳሌ ያነሱት የመቀሌ የውኃ ፕሮጀክትን ነው። የመቀሌን ውኃ ፕሮጀክት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከፍለን ያስጀመርነው እኛ ነን፤ ይሔ የሚያስመሰግነን ቢኾንም ለሕዝቡ ግን በግልጽ አይነገረውም” በማለት ገልጸዋል። የመቀሌ የባቡር ፕሮጀክት ጥናቱ በኪሎ ሜትር የቀረበው ዋጋ በጣም ውድ በመኾኑ፤ ማንም ባንክና አገር ሊያበድረን አልፈለገም፤ ነገር ግን ፕሮጀክቱ መቅረት የለበትም ብለን ስለምናምን፤ መንግሥት በዚህ ዓመት ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጎ ሥራውን ማስቀጠል መቻሉንና አሁን ሥራው ወደ 55 በመቶ አካባቢ መድረሱን ጠቁመዋል። “የእኛ ፍላጎት የመቀሌ ሐራ ፕሮጀክት እንዲቋር ሳይሆን፤ አልፎም አስመራ እንዲሔድ ነው፤ እኛ ብልጽግናዎች ትንሽ ነገር አይመቸንም፤ ሐሳባችን ትልቅ ነው” በማለትም ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ ብቻ በትግራይ ክልል ውስጥ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ስለመኾኑ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እየተሠሩ ያሉ መንገዶችንና ወደፊትም እንዲገነቡ በጨረታ ሒደት ላይ ያሉ መንገዶችን በስም በመጥቀስ ጭምር፤ የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አብራርተዋል። በመጪው ዓመትም በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በእቅድ መያዛቸውን በመግለጽ፤ ይሔንንም በቅርቡ ለምክር ቤቱ ከሚቀርብ ሰነድ ማረጋገጥ እንደሚቻልም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለአንዳንድ የትግራይ ሚዲያዎች ያሉትም ነገር ነበር። ይህንንም የትግራይ አካባቢ ያሉ ሚዲያዎች አስበውበት፣ ተዘጋጅተው እኔን ሲሳደቡ ይውላሉ በማለት ገልጸዋል። “እኔ መልስ አልሰጥም፤ ምክንያቱም ስድብ ረብ የለሽ ነው፤ የሚጠቅመን በእጃችን አፈር መንካትና አርሶ አደሩን ማገዝ ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!