የአብን ዓርማ (ግራ)፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (መኻል)፣ አቶ መላኩ አለበል (ቀኝ)

የአብን ዓርማ (ግራ)፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (መኻል)፣ አቶ መላኩ አለበል (ቀኝ)

“በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈጸመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል” አብን
“የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት በመንሳት የራስን ሰላም ማግኘት አይቻልም!” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት

ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 2, 2020)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ትናንት በኦነግ ሸኔ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ሕይወታቸው ያለፉ ዜጎች ስብሰባ በተጠሩበት ስፍራ ቦምብ ተወርውሮባቸው የተገደሉ ስለመኾኑ ተገለጸ። በዚህ ማንነትን መሠረት ባደረገ ግድያ ከ200 በላይ አማሮች እንደተገደሉ ተነግሯል።

በዚህ አሰቃቂ በኾነ ድርጊት ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በኦነግ ሸኔ ስም የሚንቀሳቀሰው ቡድን በሐሰተኛ መንገድ ነዋሪዎች ስብሰባ ከተጠሩ በኋላ ቦምብ በመወርወር ጥቃቱን እንዳደረሰ የሚያመለክት መረጃ እንዳላቸው ነው የጠቆሙት። በዚህ ጥቃት በርካት ሰዎች ስለመጎዳታቸው ያመለከቱት ቃል አቀባዩ፤ የተጎጅዎችን ቁጥር አልገለጹም።

በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጣው አብን (የአማራ ብሔራዊ ንግቅናቄ)፤ በዚህ ጥቃት ከ200 በላይ አማሮች እንደሞቱ የገለጸ ሲሆን፤ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር እስከ 250 ያደርሱታል።

ጥቃቱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትና ተቋማት መግለጫ እያወጡ ነው።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው፤ የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት አካባቢ መሰማራታቸውንና እርማጃ እየወሰዱ ነው ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ባወጣው መግለጫም፤ ንጹኀን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊኾን እንደማይችል ገልጾ፤ “እነዚህን ነብሰ ገዳዮች ከያሉበት አድኖ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ስለመኾኑ አረጋግጣለሁ” ብሏል።

በአሰቃቂነቱ በሚጠቀሰው በዚህ ጥቃት እስካሁን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ሌሎች ባለሥልጣናት ድርጊቱን የሚያወግዝና መወሰድ አለበት ስላሉት እርምጃ የገለጹ ሲሆን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ እያወጡ ነው።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አብን ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈጸመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ብሏል።

ትናንት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ የተገደሉት ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው መኾኑን ገልጿል። በዚህም የተሰማው ጥልቅ ኀዘን የገለጸው አብን፤ ሕዝቡ በየቦታው እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እንዲመክት ጥሪ አስተላልፏል።

በምዕራብ ወለጋ በተፈጸመው ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ እንዲሁም ባለሥልጣናት በየፊናቸው ያወጡትንና ያስተላለፉት መልእክት የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

“በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈጸመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል” አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በትላንትናው ዕለት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈጸመባቸው የዘር ማጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል።

በአገሪቱ ውስጥ ለበርካታ አሥርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል፤ እየተፈጸመም ይገኛል። ጥቃቶቹ ሊደርስ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ያሳወቅን ቢኾንም ተጨባጭ መፍትሔ ሊገኝ አልቻለም።

የጥቃቱ ምንጭ ውስብስብ እንደኾነ እንረዳለን። የአረመኔዎች ቅንጅት ሕዝባችን በደም ጎርፍ እንዲታጠብ አድርጓል። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል።

መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራትና ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን እርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደኅንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ተባባሪ ኾኖ ይገኛል።

በተለይም የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ፤ በየቦታው ካሉ አማራ-ጠል ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በቅንጅት አማራውን ማኅበራዊ እረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግሥቱ ነው።

በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ለማውገዝ የተጠራውን ሰልፍ፤ አማራ ማዘን እንኳን አይችልም በሚል እርቃን በወጣ አምባገነንነት የከለከለ መንግሥት፤ ሕዝባችን ላይ የሚደርስን ቀጣይነት ያለው ጥቃት ለማስቆም ፍላጎት ማጣቱ ጥቃቱን እንደሚፈልገው ዐቢይ ማሳያ ነው።

ሕዝባችን የዘር ማጥፋት ታውጆበትና መንግሥትም የጥቃቱ ተባባሪ ኾኖ ከገዳዮቹ ጋር በአንድ አገር ለመቀጠል የሚቸገር በመኾኑ፤ ሁሉም የአገሪቱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርግ አብን ጥሪ ያስተላልፋል።

ሕዝባችንም በየቦታው የሚፈጸምበትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እንዲመክት አብን ጥሪውን ያቀርባል።

ውድ አማራውያን አሁን ኀዘናችንንና ቁጭታችንን በቅጡ ለመግለጽ እንኳ አቅም ማጣታችን ግልጽ ነው። ከሒደቶች የምንገነዘበው ተጨማሪ ጥቃቶች ሊከፈቱ እንደሚችሉ ነው። ፈጣን ምክክር በማድረግ የሕልውና አደጋውን በዘላቂ ሁኔታ ለመቀልበስ በቂ ዝግጅት ማድረግ አለብን።

ይህ ጉዳይ በመደበኛ እንቅስቃሴ ሊመከት አልቻለም። የአማራ ሕዝብ የአገራዊ ፖለቲካው ሽኩቻ ሁሉ ብቸኛና ቋሚ ማስያዥያ ኾኖ ቀጥሏል። አሁን የሕግ የበላይነት ቦታ አጥቷል። መንግሥት ሕግ የማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት አለመፈለጉና አለመቻሉ ተረጋግጧል። ቀሪው ነገር የአማራ ሕዝብ ተደራጅቶ ራሱን ይከላከል የሚለው ነው።

አብን ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መኾኑን ያረጋግጣል። አብን የተደራጁ የትግል ስልቶችን ነድፎ ለሕዝባችን ይፋ እንደሚያደርግም ለመጠቆም ይወዳል።

በድጋሜ ነፍስ ይማር!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መልእክት

የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ "ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ አገር አትኖርም" ብለው ተነስተዋል። ለዚህም የጥፋት አቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።

ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የሚያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ፤ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ እርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።

መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ እርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።

የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።

ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፤ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሳ ያደርገናል እንጂ።

መንግሥት ሁሉንም ዐይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሰማርተዋል። እርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።

ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን እርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

“አማራዊ ማንነታችን የጥቃት ምንጭ መኾኑ ሊቆም ይገባል" የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል

የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በወለጋ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ በትዊተር ገጻቸው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል።

“ከወንድም ሕዝቦች ጋር በአንድነት ሥጋና ደም ገብረን ባቆምናት ኢትዮጵያ፤ አማራዊ ማንነታችን የጥቃት ምንጭ መኾኑ ሊቆም ይገባል። መከራ ያጠነክረናል እንጂ አያጠፋንም፤ ኢትዮጵያም ትቀጥላለች።

“ሁሉም ትውልድ የራሱ የቤት ሥራ አለበት። በመሥዋዕትነታችን ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በነፃነት፣ በእኩልነት እና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት የምንስተናግድባት ኢትዮጵያን እናጸናለን ”

አቶ መላኩ አለበል (የንግድ ሚኒስትር)

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በንጹኀን ዜጐች ላይ በደረሰው ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ በንጹኀን ዜጐች ላይ በደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን የገለጸው በፌስቡክ ገጹ ላይ ነው።

ምክር ቤቱ ይህን መሰል ወንጀል በተደጋጋሚ እየተፈጸመ የዜጐች ሕይወት እየተቀጠፈ ይገኛል ብሏል። በመኾኑም በእነዚህ ስለአገርና ስለሰው ልጆች ክብርና ሰብዕና በሌላቸው ወንጀለኞች ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ እናሳስባለን ሲል ምክር ቤቱ ገልጿል።

በእነዚህ የጥፋት ኃይሎችና አሸባሪዎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ምክር ቤቱ ጥሪ አስተላልፏል። ምክር ቤቱ የሕዝቡን ደኅንነትና ሰላም እንዲጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስታውቋል።

“የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት በመንሳት የራስን ሰላም ማግኘት አይቻልም!” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት

ላለፉት 40 ዓመታት በተለይም ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ፤ በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሲሰነዘሩበት ቆይተዋል። በዚህ ችግር ዋነኛው ተጠቂ ከክልሉ ውጭ ነዋሪ የኾነው ወገናችን ነው። ለዚህ ጥቃት ያበቃው መሰረታዊ መንሥኤው ደግሞ የትህነግና መሰል ኃይላት የአማራን ሕዝብ በተመለከተ የዘሩት አማራ ጠል ትርክት ሲሆን፤ የዚህ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች አማራን ለማጥቃት በትር ኾነው አገልግለዋል። በኢትዮጵያ የመንግሥት ምስረታ ሒደት ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመኾን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው አማራ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ሁሉ አገሬ ብሎ ለረዥም ዘመናት የኖረ በመኾኑ የሕዝባችን አሰፋፈር እና የአኗኗር ዘይቤው ለጠላቶቹ የበለጠ ተጋላጭ አድርጎታል።

የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ጽኑ እምነት ያለው ሕዝብ በመኾኑ፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል መኖርና ተዘዋውሮ የመሥራትና ሀብት ማፍራት 'ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ነው' ብሎ ያምናል። በዚህ እምነቱ የተነሳም፤ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ይኖራል፤ ተዘዋውሮ ለመሥራትና ሀብት ለማፍራት የሕይወት ትግል ያደርጋል። ይሁን እንጅ ትህነግና መሰሎቹ በዘሩት የተዛባ ትርክት የአማራ ሕዝብ እረፍት አጥቷል፤ በየወቅቱና በየአካባቢው ይሰደዳል፤ ንብረቱ ይዘረፋል፤ አለፍ ሲልም የቡድን ጥቃት ይፈጸምበታል። ይህ ችግር በድርጅት የውስጥ መተጋገልና በኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ መሥዋዕትነት ትህነግ ከማዕከላዊ ሥልጣኑ ከተነቀለ በኋላ የአማራው መጠቃት በከፋ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከሥልጣን ለመነቀሌ የተቃውሞ ኃይል ምንጭ ነው ብሎ የሚያምነውን የአማራ ሕዝብ፣ ከትላንት በቀጠለ ጥላቻው ዛሬም አማራን ማጥቃት የበቀልና የሥልጣን መመለሻ የቀውስ ሐዲድ አድርጎ ይቆጥረዋል።

ይህ የሚያሳየው፣ ትህነግ እንደ ድርጅት ሕልውናው እስከቀጠለ ድረስ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው መፈናቀል፣ ግድያና ጭፍጨፋ መቀጠሉ አይቀሬ መኾኑን ነው። ይኼን የምንለው የአማራ ሕዝብ በኦሮሚያም ኾነ በሌሎቹ የአገራችን አካባቢዎች፤ ዋጋ እየከፈለ ያለው በትህነግ የእጅ አዙር ጥቃት መኾኑን ከክትትልና መረጃዎች፤ እንዲሁም ከሁኔታ ትንተናዎቻችን ተነስተን ነው። ኦነግ ሸኔም ይሁን ሌሎች ፀረ-ሕዝብ የኾኑ ኃይሎች ያለ ትህነግ የፕሮፓጋንዳ፣ የትጥቅና የፋይናንስ ድጋፍ ያን ያክል ለፌደራሉም ኾነ ለክልላዊ መንግሥታቱ አስቸጋሪ ኾነው አማራን ባላፈናቀሉ፣ ባለሳደዱና ባልጨፈጨፉ ነበር። እንደ አገርም ኾነ እንደ አማራ ለገባንበት የጥቃት አዙሪት ምንጩ የመቀሌው ግዞተኛ ቡድን ነው።

በትላንትናው ምሽት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዘርን መሠረት ያደረገ በአማራ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠናል። የጥቃቱን መጠንና ዝርዝር ሁኔታዎች ከፌዴራሉና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር እያጣራን ሲሆን፤ በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት የአማራ ሕዝብና ድርጅታችን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ክፉኛ አዝኗል፤ ተቆጥቷል። በመኾኑም ይህ ድርጊት የሚወገዝ ከመኾኑም በላይ አጥፊዎቹ እንደየሥራቸው በሕግ አግባብ ሊዳኙ ይገባል ብለን እናምናለን። ስለኾነም ከዚህ በታች የሚከተሉት አካለት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን፦

1) የፌደራሉ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ በየአካባቢው እየደረሰ ያለውን ተደጋጋሚ ዘር ለይቶ የማጥቃት ወንጀል ዋነኛ የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ አድርጎ ሊወስደው ይገባል። ስለኾነም የኢፌዴሪ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የአደጋውን መጠንና ቀጠናዊ መዘዝ በማጤን፤ ዘርን መሠረት ያደረገው የአማራ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤ ስለ ጥቃቱም ዝርዝር መረጃ ለመላ ኢትዮጵያዊያን እንዲሰጥ፤ በአማራው ጥቃት ላይ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ የጥፋት ኃይሎች ላይ ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እንጠይቃለን፤

2) የአማራ ሕዝብ የሚኖርባችው ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የምትገኙ የፖለቲካ አመራሮችና የጸጥታ አካላት፤ እናንተንና የአካባቢውን ወንድም ሕዝብ አምነው፣ አገር አለን ብለው፤ ሕግና ሥርዓት አለ በሚል ኢትዮጵያዊ መተማመን ከናንተው ጋር ለዘመናት የኖሩትን የአማራ ተወላጆች ከመቸውም ጊዜ በላይ ጥበቃ እንድታደርጉላቸውና ሕዝባዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤

3) በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ተከታታይ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ፤ የችግሩ ዋነኛ መንሥኤ አማራን በየአቅጣጫው በመውጋት በንጹኀን ደም የፖለቲካ ቁማር የሚሠራው የመቀሌው ግዞተኛ የትህነግ ቡድን በመኾኑ፤ ይህ ኃይል የብሔራዊ ደኅንነታችን የሥጋት ምንጭ ከመኾን አልፎ የሽብርና የቀውስ ማዕከል ስለኾነ፤ ለኢትዮጵያና ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም ሲባል ከመለሳለስና ከመሸከም ፖለቲካ ወጥቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሥርዓት እንዲይዝ ለማድረግ ጊዜው አሁን ስለመኾኑ እናረግጣለን፤

4) የኢትዮጵያ ዘብ የመኾን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ ያለባችሁ የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌደራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አካላት፤ የአማራ ሕዝብና ሌሎች ብሔሮች በማንነታቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ስትከፍሉት የቆያችሁትን መሥዋዕትነት መቼም አንዘነጋውም። ዛሬም ከአገራዊ ለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ፀረ-ሕዝብ የኾኑ ኃይሎች አማራውን ዘሩን መሠረት አድርገው ጥቃት እየፈጸሙበት መኾኑን አውቃችሁ፤ በየአካበቢው ለሚኖረው አማራ ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ በመስጠት፤ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኳችሁን እንድትወጡ በድጋሚ እናሳስባለን፤

5) የአማራ ሕዝብ፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ፦ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የረዥም ጊዜ የተዛባ ትርክት ውጤት መኾኑን በመገንዘብ፤ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት፣ ለሦስት አሥርት ዓመታት የገጠመንን መዋቅራዊ ማነቆ ለመቅረፍ በሚመጥን ልክ የመፍትሔ ሐሳብ በማመንጨት የበኩላችሁን እንድትወጡና በጋራ በመቆም የአማራ ሕዝብ ከተደቀነበት የሕልውና ሥጋት እንድትታደጉ 'የአማራ አንገቱ አንድ ነው' በሚል ወገናዊ ጥሪያችን እናቅርብላችኋለን።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በዘለቄታዊ መፍትሔው ላይ እንደ አማራ ለመምከር በቅርቡ ሁሉን አሳታፊ የኾነ የሕዝብ መድረክ የምናዘጋጅ መኾኑን እንገልጻለን።

የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት በመንሳት የራስን ሰላም ማግኘት አይቻልም!
አማራን ዘሩን ለይቶ በማፈናቀልና በመግደል ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም!
ክብርና ሞገስ በአማራነታቸው መሥዋዕት ለኾኑ ወገኖቻችን!
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ!
ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ