በምዕራብ ወለጋ የጸጥታ ኃይሉ በኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ እየወሰደ መኾኑ ተገለጸ
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
በዚህ አካባቢ በተፈጠረው የኦነግ ሸኔ ጥቃት ጉዳት ደርሷል
“በኦነግ ሸኔና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም” የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት
ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 2, 2020)፦ በትናንትናው ዕለት (እሁድ ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም.) በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለው ቀበሌ ኦነግ ሸኔ የሽብር ጥቃት መፈጸሙንና በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት እርምጃ እየወሰደ መኾኑን ተከትሎ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ “በኦነግ ሸኔና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም” ብለዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ኦነግ ሸኔ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የጸጥታ ኃሉ እርምጃ እየወሰደ ስለመኾኑም አሳውቀዋል።
እንደአንዳንድ መረጃዎች ከትናንት ጀምሮ ኦነግ ሸኔ ተሸሽጓል በተባሉባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ እየወሰዱ መኾኑ እየተገለጸ ነበር።
ኦነግ ሸኔ ፈጸመ በተባለው ጥቃት የዜጎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱም በዚህ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጡት መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
“በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም” የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
የአገራችን ሕዝቦች ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት በጋራ እየታገሉ መሥዋዕትነት እየከፈሉ በጋራ ተጉዘዋል። አሁም በመጓዝ ላይ ይገኛሉ። የሕዝቦች የጋራና ትግልና መስዋዕትነት ፍሬ አፍርቶ አገራችን የለውጥ ሒደት ውስጥ ገብታለች። ኾኖም በዚህ የለውጥ ሒደት በሕዝቦች ትግል ድል የተነሱት ጨቋኝ ክንዳቸው እንዲሰበሰብ፣ የብዝበዛ መረባቸው እንዲበጣጠስ የተደረገው ሴረኛው የወያኔ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ላደረሳቸው ጥፋቶች መጸጸትና መታረም ሲገባው፤ አሁንም የተካነበትን ሴይጣናዊ የተንኮል ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
ይህ ቡድን እንደለመደው ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ደም በማፋሰስ፣ በሚፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከቻለ ከተገፋበት የማዕከል ሥልጣን መመለስ ካልቻለ፤ የሚመቸውን አሻንጉሊት መንግሥት ለማቋቋም በተለመደው ዓይነ ደረቅነቱ የቀን ቅዠት ውስጥ በመግባት ሌት ተቀን ሴራ በመጎንጎን ላይ ይገኛል።
ከወያኔ እኩይ የሴራ ድርጊቶች መካከል ዋነኛው ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ሕዝብ ከሕዝብ በማጋጨት በንጹኀን ደም መነገድ ነው። በተለይም ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር መሞከር የሰርክ ተግባሩ ነው። ይህ ሙከራው አልሳካለት ሲለው የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድንን በማስታጠቅ የሎጀስቲክና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ በትሮይ ፈረስነት በመጠቀም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማስፈጸም የአገራችንን የለውጥ ተስፋ ለማጨለም እየተፍጨረጨረ ይገኛል።
አሸባሪው የኦነግ ሸኔ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሕዝብና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ትብብር እየተወሰደ ባለው እርምጃ በከፍተኛ ሁኔታ አከርካሪው ተመትቶ በመንኮታኮት ላይ ይገኛል። ይህ በሕዝብና በጸጥታ አካላት ክፉኛ እየተመታ ያለው ቡድን ተስፋ ወደ መቁረጥ በመግባቱ፤ እንዲሁም ከወያኔ የሚሰጠውን ተልዕኮ በመውሰድ ሰላማዊ ዜጎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች ላይ የሽብር ጥቃት ወደ መሰንዘር ተሸጋግሯል። በትላንትናው ዕለት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለው ቀበሌ ዜጎቻችን ላይ የሽብር ጥቃት በማድረስ በሰው ሕይወት እና አካል ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
በዚህ የሽብር ጥቃት ዉድ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማኝን ጥልቅ ኀዘን እየገለጽኩ የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቄ አወግዛለሁ። በዚህ አጋጣሚ በኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው ውጤታማ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋግጥ እወዳለሁ።
እንደዚህ ዐይነት የፈተና ወቅት የሕዝቦችን ወንድማማችነትና በጽናት አብሮ በመቆም ፈተናን የማለፍ ልምድን ያጠናክራል እንጂ፤ ጠላት እንደተመኘው ሕዝቦችን የሚያባላ ፈጽሞ አይኾንም። እንደመንግሥትም አስፈላጊውን መሥዋዕትነት በመክፈል የሕዝቦችን ወንድማማችነት እና የኢትዮጵያን አንድነት የማስቀጠል ተግባር አጠናክረን እንቀጥላለን።
በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ ሽብር እና የጥፋት ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም!
ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት



