ሕግ እስኪከበር የአየር ጥቃቱ ያለከልካይ እንደሚቀጥል የአየር ኃይል አዛዥ አስታወቁ

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
የጁንታው እስትንፋስ ከጥቅም ውጭ መኾኑ ተገለጸ
ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 11, 2020)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጠላት ሊጠቀምባቸው ያሰባቸውን ምርጥ ዒላማዎች በመደብደብ ከጥቅም ውጭ ማድረጉንና “ጁንታው ለሕግ እስኪቀርብ ድረስ ጥቃታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ አስታወቁ።
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫቸው፤ የጁንታው እስትንፋስ የነበሩ የነዳጅ ማደያዎች፣ የመሣሪያ ማከማቻዎች እና ሌሎች ምርጥ ዒላማቸውን ያለምንም ከልካይ ማውደም ተችሏል ብለዋል።
የአየር ኃይል ፓይለቶች የተመረጡ ዒላማዎችን ለመደምሰስ በሚሰጣቸው ግዳጅ ሲቪሎች እንዳይጎዱ የማድረግ ስትራቴጂ ተከትለው ግዳጃቸውን እየተወጡ ስለመኾኑ ዋና አዛዡ አመልክተዋል።
ፓይለቶቹ ዒላማዎችን ለመደምሰስ መሣሪያ ጭነው በሚሔዱበት ወቅት፤ ሲቪል የሚጎዳ ከመሰላቸው የጫኑትን ማሣሪያ ሳይተኩሱ በመመለስ፤ ነጥሎ የመምታት ስትራቴጂ እየተከተሉ መኾኑንም ሜ/ጄኔራል ይልማ ገልጸዋል።
አየር ኃይሉ ጁንታው ለሕግ እስኪቀርብ ድረስ የአየር ጥቃቱን እንደሚቀጥልም አመልክተዋል። (ኢዛ)