Ethiopian ariforceየኢትዮጵያ አየር ኃይል ለዳግመኛ ክህደት እንዳይዳረግ

ግንቦት 83/91 ላይ የኢትዮጵያ ሰማይ ክፉኛ በኀዘን ሲመታ፣ ደመናው ሲጠለሽ፤ ወንዞች መደፈራረስ ሲጀምሩ፤ የሰውን ልብ ባር ባር ሲለው ... የክፉው ቀን ጅማሮ፣ የውርደት ሃሌታ፣ የሀገር አልባነት ስሜትና የዜግነት ውርደት ደጃፍ ላይ መውደቃችን እውነት ነበር።

 

ውርስ ከአባት ወደ ልጅ ሊተላለፍ ካልቻለ፤ አባት የጀመረውን ልጅ ካልቋጨው፤ አዲስ መንግሥት ሲቀየር የድሮውን በጐ ነገር ሁሉ ብትንትኑን አውጥቶ ካጠፋ፤ የትውልድ ቅብብሎሽ ገደል ገባ ማለት አይደል? እናም በሀገሬ ምድር ላይ የእርግማን ዘመን ያኔ በ1991 "ሀ" ብሎ ጀመረ።

ሌባው ከሳሽ ... ቀማኛው ፈራጅ የሆነበት፤ አባት ተቀምጦ ልጅ የሁሉ ነገር አዛዥ ሲሆን፤ አህያ ወደ ሊጥ ... ውሻም ወደ ግጦሽ ከተሰማራ ... እነሆ ዘመነ ብልሹ ላይ መድረሱን ያልተረዳ ካለ ... እሱ ባይፈጠር ... እናቱ ሆድ ውስጥ ውሃ ሆኖ ቢቀር ይሻለው ነበር።

ሀገር ሲገነጠል ዝምታ፤ ንብረት ከመሃል ሀገር ተግዞ ሲያልቅ ዝምታ፤ ገዳማት ሲታረሱ፣ ቤተ ክርስቲያናት ሲዘረፉና ታቦታት በየገበያው ሲቸበቸቡ ዝምታ፤ ደን ሆን ተብሎ በሰደድ እሳት እንዲወድም ሲደረግ ዝምታ፤ ግዙፉ የሀገር መከላከያ ኃይል እንደተረት ዓይናችን ስር ሲበተን ዝምታ ... የምንወደው ዝነኛው የአየር ኃይላችንም አብሮ ተደርምሶ እንዳልነበረ ሲሆን ዝምታ ነገሠ። የሚቆጭ፤ የሚመክር፤ የሚቆጣና ሃይ የሚል ወንድ ጠፋ። የአድዋና የማይጨው አርበኞቻችን የክብር ሐውልቶች ሲፈርሱም ዝምታ፣ የጦር ካምፖቻችንም ታሪካዊ ስያሜ በማን አለብኝነት ለጐጠኞች ስያሜ ሲውልም ዝምታ ነገሠ።

ዛሬ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዋሺንግተን በሚመላለሱና ከዘመነኞቹ ጊዜያዊ የይሁንት ፈገግታ በተቸራቸው የኛና የኔ ቢጤዎች አማካኝነት የቬተራን አሶሴሽን እናቋቁማለን፤ የአየር ኃይሉንም ታሪክ እንፅፋለንና ለዕርዳታ እጃችሁን ዘርጉ የምትል የኢሜል መልዕክት ደርሳን በትዝብት ተደምመናል። እስኪ ከበጐ መንፈሥ የመነጨ ነው ብለን እንመን። ግን ሥጋት አለን!

የአየር ኃይላችንን ታሪክ ለትውልድ ዘግቦ ማስቀመጥ ምንኛ የተቀደሰ ዓላማ ነው! የአቭዬሽን ቬተራን ማኅበርን ማቋቋምስ እንዴት ትልቅ ራዕይ አለው? ነገር ግን የአንድ መንደር ልጆችን ዓላማ አድርጐ በጐጠኝነት ማማ ላይ እየተንጠለጠለ እኛ እና እነሱ፤ የቀድሞውና አዲሱ፤ ዲሞክራቲኩና የአንድነት አርበኛ እያለ ሊለያየንና ሊከፋፍለን ሌት ተቀን የሚተጋው ጐጠኛና ሽፍታ መንግሥት የሚገነባውን ከእውነተኛው አየር ኃይል በቅጡ መለያየት ያስፈልጋል።

ውሃና ዘይትን ለመቀላቀል በማምሻ ዕድሜ መባጀት ጉልበት ማባከን እንዳይሆን! የነፃነት አርበኛው ጀ/ል ተጫነ መስፍንና የሽፍቶቹ ጀ/ል አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) በምን ተዓምር ለአንድ ዓላማ ሊሰለፉ ይችላሉ?

በምንስ ሂሳብ የህወሓቱ አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) የቬተራን አሶሴሽን መስራች ሆኖ በቬተራን አዲስ ይደግሳል? እነዚህ ሁለት ፍጥረታት ውሃና ዘይት ናቸው። በዓላማም በራዕም አንድ አይደሉም ... አሳዳጅና ተሳዳጅ! ወንጀለኛና ወንጃይ ... አርበኛና ባንዳ ... ውሃና ዘይት ናቸው። ሊዋሃዱ አይችሉም።

የእኛው አየር ኃይል በጅምላ ጨፍጫፊና ወንጀለኛ ተብሎ እንደ ጉም በተበተነበት ዘመን ላይ ተቆሞ ... ለሀገር የደሙ ከያሉበት ታድነው በውርደት በየማጐሪያው ተወርውረው ልባቸው ተሰብሮና ጥሪት አልባ ሆነው በሰው እጅ ላይ እንዲወድቁ በተበየነበት ዘመን ላይ፤ ዛሬ ከሲሶው በላይ እውነተኛው አርበኛ ሀገር አልባ ሆኖና ተዋርዶ አልጋ ላይ እየዋለ፤ ያለ ደጋፊና አጋዥ ቀና ማለት ባቃተው ሰዓት ላይ የቬተራን አሶሴሽን እያቋቋምን ነው ሲሉንና ግንባታውን በገንዘብ እንድንደግፈው ስንጠየቅ እውን ለእውነተኛው የአየር አርበኛ አገልግሎት እንዲመስለን ይሆን?

በእርግጥ ጥቂቶች ደም የተገበረበትን አርበኝነታቸውን ሳይሆን የሽንፈት ታሪካቸውን አሜን ብለው በመቀበል በውርደት በጅምላ የተለጠፈብንን የጨፍጫፊነት ማንነት፤ በተጨማሪም ለሀገር በመሞታችንና ደማችንን በማፍሰሳችን ምክንያት እንደ ተራ ነፍሰ ገዳይ የሞትና የዕድሜ ልክ ፍርደኞች መሆናችንንና/መሆናቸውን ዘንግተው "ማምሻም ዕድሜ ነው" በሚል የመሰንበት ጉጉት በድለላ እያግባቡን ማየታችን ከላይ በበጐ መንፈሥ ተነሳስተው ነው የሚለውን አቋማችንን እየሸረሸረብን ተቸገርን።

ለመሆኑ በማን አየር ኃይል ... በነማንስ ደም ይቀለዳል?

የእነ ሚሽካ ባቢቼቭ አየር ኃይል ... የእነ ባህሩ ካባ አየር ኃይል ... የእነ ጀነራል አበራ ወ/ማሪያም ... የእነ ጀነራል አሰፋ አየነ ... የእነ ጀነራል አሰፋ ገ/እግዚ ... የነ ጀነራል ታዬ ጥላሁን ... አየር ኃይል እንዴት ሆኖ ከዚህኛው ዘመን ጋር ይዋሃዳል?

እነ ጀ/ል ለገሰ ተፈራ፣ ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስ፣ ኰ/ል ታደለ ዓለሙ፣ ኰ/ል ትርሲት፣ ኰ/ል ወርቁ፣ ሻ/ል ጥላሁን በዛብህ፣ መ/አ አባይነህ ኃይሉ፣ መ/አ ደመላሽ መኰንን የመሳሰሉት በምርኰና በእስር መስዋዕትነት የከፈሉበት፤ የነ መርዕድ ዳጨው ደም ... የነ አማኑኤል አምደሚካኤል ... የነ ጥላሁን ኃይሉ፤ የነ ለዊ ደሬሳ ... የነ መንግሥት ዓለሙ ... የእነ ሊ/ካዴት ይኩኖ ታደሰ ጨቅላና አድገው ያልጨረሱ ልጆች ደም፤ የነ ተስፋዬ ብ/ሥላሴ ... የነ ማ/ቴክ ደገፋ ሆራ ... የነ ኰ/ል ጥላሁን ቦጋለ ... የነ ሠለሞን መክብብ ... የነ አብረሃም ስንቄ ደም ላይ እንዴት ዳንኪራ ይጨፈራል?

እነ ጀ/ል ፋንታ በላይ ... ጀ/ል አመሃ ደስታ ... ጀ/ል ሠለሞን በጋሻው ... ጀ/ል ተስፉ ደስታ ... ጀ/ል ንጉሴ ዘርጋው ... ጀ/ል ገናናው መንግሥቱ ... እንዲህ ደማቸው ደመ ከልብ ይሁን? ለአፍታ ቀና ብለው ቢያዩስ ምንኛ በባልንጀራቸው ያፍሩ ይሆን!

ዘመናቸውን ሙሉ ለሀገራቸው የአየር ክልል መከበር ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ... ንብረት ማፍራት ... ሀብት ማካበት ... ሚስት ማግባትና የአብራካቸውን ፍሬ ለማየት ሳይጓጉ ዕድሜያቸውን የጨረሱ የአየር ኃይሉ ጌጦችና የሀገር አለኝታዎች እንደ ወሮበላ ማጅራት መቺ የሞትና የዕድሜ ልክ ፍርደኛ በተሆነባት ሀገር ላይ እንዴት አይነቱ የአየር ኃይል የአቪየሽን ቬተራን አሶሴሽን ይገነባል?

እነ ኰ/ል ታከለ አበበ፣ ሻ/ቃ አለማየሁ እሳቱ፣ ሻ/ቃ ከበደ ጫኬ፣ በላይነህ ተገኝ፤ ደበበ ሞላ ... ደሳለኝ ስሜነህ ... ወዘተ በጉልበት ከሀገር ተሰደው በበረሃ ላይ ያለ አልቃሽና ቀባሪ ነፍሳቸውን እንዲሰጡ ላደረገ ሽፍታ፤ እነ ሻ/ል ፍሰኀ መለስን በእስር ቤት ለገደለ ወንበዴ እንዴት ብለን ክብራችንን ዝቅ አናደርጋለን? እነ ኰ/ል ብርሃነ መስቀል፤ ኰ/ል ሠለሞን ከበደ፤ ኰ/ል ግርማ አስፋው፤ ሻ/ል ክፍሌ ውቤ ከዕድሜያቸው ከሩብ በላይ በእስር የገበሩበት ምክንያት ምን ይሆን? ዘንግተነውስ ይሆን?

እነ ማ/ቴክ ሽብሩን ... እነ ማ/ቴክ ፀጋዬ ሁሉቃን ... እነ ማ/ቴክ ግርማ ሰቦቃንና የመሳሰሉትን በአጠቃላይ አፕሬንቲሱን፣ ኤርሜኑን፣ ቴክኒሻኑን፣ የአየር ፖሊሱን፣ በራሪውን፣ መኰንኑን፣ ባለሌላ ማዕረግተኛውን እንደ አሮጌ ቁና ሜዳ ላይ በትኖ በስተእርጅና የሰው እጅ እንዲያዩ የተደረጉበትን እንደ ጨዋታ ቆጥረነው ይሆን?

እነ ኰ/ል ብርሃኑ ከበደን፤ ኰ/ል ብርሃኑ ውብነህ፤ ኰ/ል ጣሰው ወዳጄነህን ... ኰ/ል ጌታቸው መንገሻን ... ኰ/ል መንገሻ ሁንዴን ... ኰ/ል የሺጥላ መርሻን ... ኰ/ል ይልቃልን ... አለማየሁ አጐናፍርን ... አለማየሁ ኃይሌን ... ስንታየሁ አሽኔን ... መስፍን መንግሥቴን ... በኃይሌ ደግፌን ... ጂልቻ ዱራን ... ኰ/ል ነብዩን ... አሰፋ ተገኝን፤ አቦነህ ነጋሽን ... ዳዊት ወንዲፍራውን፤ መስፍን ግርማን ... በአጠቃላይ ስማቸው ያልተዘረዘሩትን የተዋጊውን፣ የትራንስፖርትና የሄሊኮፕተር ስኳሮኖች በራሪና የቴክኒክ ባለሙያ ሲቪል ሠራተኞችን ሁሉ ሀገር አልባ አድርጐ ... እንዴትስ አይነት የአቪዬሽ ቬተራን ማኅበር ሊመሰረት ይችላል?

እነዚህ እንዴት ...

Ethiopian ariforce

በአንድ ጊዜ ወድቀው እዚህ ይደርሳሉ?

Ethiopian ariforce

ጀነራል ተጫኔ መስፍን ደም ገብረው በአቀኑት አየር ኃይል ውስጥ አበበ ተ/ኃይማኖት አንዳችም የአየር ኃይል ትምህርትና ዕውቀት ሳይኖረው የቬተራኖቹ አየር ኃይል አዛዥ ሆኖ በራሪ ተማሪዎችን ሲሸልም በአፍሪካ ውስጥ በበረራ ሰዓታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው የተዋጊ አውሮፕላን በራሪና ኢትዮጵያን በተለያየ ጊዜ የተቃጣባትን ወረራና ጥቃት በጀግንነት የመከቱ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጅ ጀነራል ተጫነ መስፍን በዚህ አይነት በአሳላፊነት መታየታቸው ምን ያክል ሀገር አልባ እንደሆንን አያሳይ ይሆን? እውን ታዲያ ይሄ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ነው? እንደዚህ አይነት ሀገር የማታከብረው ቬተራንስ የት ሀገር ነው ያለው?

ጀነራል ተጫኔም በዚህ አይነቱ ሁኔታ እራሳቸውን ለማሳነስ ባይፈቅዱ እንዴት ጥሩ ነበር? እነ ጀነራል መስፍን ... ጀነራል ተሻለ ... ኰ/ል ጥላሁን ነብሮን የመሳሰሉት ባለ ወርቅዬ ታሪክ ባለቤቶች እንደ ሀገር አልባና ሁለተኛ ዜጋ ተገልለውና ተጥለው ያለ ፎቶግራፍ ይኖሩ የለ?

በእርግጥ በዚህ ዘመን ጀ/ል ተጫነ ከአቻዎቻቸው በተለየ ሁኔታ ከነ ሙሉ ክብራቸውና ጥቅማቸው በሀገራቸው በቬተራን ማዕረግ እየኖሩ ያሉ ብቸኛ ሰው ናቸው። ቀደም ሲልም እንደ ጀ/ል ተጫኔ ሁሉ ጀ/ል ሠለሞን በየነ በዚሁ በተንቆጠቆጠው ማማ ላይ ተሰቅለው እንዳሉ እናውቃለን፤ ይህ እንግዲህ የልደታ አየር ምድብ አዛዥ ተደርጐ ተሹሞ የነበረውን ሻለቃ ተስፋዬ ተገኝን ሳንዘነጋ፣ የሚሊታሪ አታቼውንና ጀ/ሉን ኃይለሥላሴ ገብሩንም ማ/ቴክ ረዳዕይና ማ/ቴክ ክንድያን እንዲሁም ካላዩ አፅበሃንም በማሰብ ነው። በእርግጥ አድሎው ዓይን ያወጣ ቢሆንም ከወደ ኰረም፣ አዲግራትና አድዋ የመወለድ ጣጣ ነው እያልን ቆይተናል።

እነሆ ምክር እንለግሳለን ...

የአየር ኃይላችንን ታሪክ መፃፉን እናበረታታለን። ይሁን እንጂ ... ዛሬ የሚፃፍ ካለ አየር ኃይሉ እንዴት እንደተመሰረተ ብቻ ሳይሆን እንዴትም እንደፈረሰ፤ ለሀገር የደሙና የሞቱ እንዴት እንደወንጀለኛ በየማጐሪያው እንደተጋዙ ... ሕብረብሔሩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንዴት ወደ አንድ ዘር የሽፍቶች ስብስብነት እንደተቀየረ የሚተርክ ካልሆነ ... ጀ/ል ተጫነ መስፍን፣ ኰ/ል አስፋው አየልኝንና የመሳሰሉትን የትውልድም የታሪክም ተወቃሽ፤ የሀገርም ክህደት እንዳይሆን ይታሰብበት።

የአቭዬሽን ቬተራን አሶሴሽንም ከመመስረቱ በፊት አርበኛውን ከጐጠኛው መለየት፤ እውነተኞቹን የአየር አርበኞችና ቬተራኖች ከብቀላ ፍርደኝነታቸው ነፃ ማድረግና ዝነኛውን አየር ኃይል በጅምላ ከተለጠፈበት የጨፍጫፊነት ስያሜ እንድናላቅቅ የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል።

ጨረስን።

ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!

ትብብር ለመልሶ ማቋቋም የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ