20210302 adwa

ሕወሓት ሊጠቀምባቸው የነበሩና በአማራ ፖሊስ መያዛቸው ከተገለጹት መሣሪያዎች በከፊል

ሕወሓት ሊጠቀምባቸው የነበሩና በአማራ ፖሊስ መያዛቸው ከተገለጹት መሣሪያዎች በከፊል (ፎቶ፣ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን)

በአዲስ አበባ አንድ ሺህ ሽጉጦች ተይዘዋል
በሑመራ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያ ተይዟል፤ በሱር ኮንሽትራክሽን ካምፕ ውስጥ ጭምር

ኢዛ (ሰኞ ኅዳር ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 16, 2020)፦ ባለፉት ጥቂት ቀናት በተደረጉ ፍተሻዎች ከአንድ ሺህ በላይ ሽጉጦችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የጦር መሣሪያዎችን መያዙን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። በቃፍታ ሑመራ በሚገኘውና በሕወሓት ባለቤትነት በሚተዳደርው የሱር ኮንስትራክሽንም በርካታ የጦር መሣሪያዎች ተይዘዋል።

ከፌዴራል ፖሊስ ዛሬ ሰኞ ኅዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. የተሰጠው መግለጫ፤ ባለፉት ቀናት በተደረጉት ፍተሻዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያ መያዙንና ከዚህ ውስጥም ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋው ሽጉጥ መኾኑን መረዳት ተችሏል።

ከሽጉጦቹ ሌላ በርካታ ቦምቦች፣ ፈንጂዎች፣ የጦር መንጽሮች፣ የቡድንና የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን የፌዴራል ፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።

በድንገት በተደረጉ ፍተሻዎች ጭምር እነዚህ መሣሪያዎች የተያዙ ሲሆን፤ የፍተሻው መጥበቅ ለሽብር የተዘጋጁት ኃይሎች የጦር መሣሪያዎችን በማዳበሪያ ጭምር በመጠቅለል እየጣሉ ስለመኾኑም ተገልጿል።

በተመሳሳይ ዜና ሕወሓት አገር ለማተራመስ ሲዘጋጅባቸው የነበሩ በርካታ የጦር መሣሪያዎች በሑመራ ግንባር መያዙ ተገልጿል።

ዛሬ በሑመራ የተያዘውን መሣሪያ በተመለከተ ከተሰጠው ዝርዝር መረጃ፤ የጦር ሚዳ መንጽሮችን ጨምሮ የተለያዩ መለያ ያላቸው ዘጠኝ ሞርተሮች፣ አንድ ስናይፐር፣ አሥር ጠብመንዣ፣ ሰባት ተከላካይ መትረየስ፣ ስምንት ተከላካይ ክላሽ፣ 102 ቦምቦች፣ 94 ካልሽ፣ 202 የክላሽ መጋዘን፣ 41 ኤስኬስ፣ 30 የመትረየስ ሰንሰለት፣ አምስት ሺህ የስናይፐር ጥይት፣ ስምንት ሺህ የክላሽ ጥይት፣ ሦስት ላውንቸር፣ 38 የላውንቸር ጥይት፣ 4,500 የመትረየስ ጥይት፣ 26 ከመካከለኛ እስከ ረዥም ርቀት የራዲዮ መገናኛ፣ 108 የሞርተር ጥይት፣ የተለያዩ አልባሳት እና የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የአማራ ፖሊስ ዛሬ እንዳስታወቀው ደግሞ ሕወሓት ሊጠቀምበት የነበረ ከ230 በላይ ክላሽ፣ ከአንድ ሺህ በላይ ቦምቦችና ሌሎች ተተኳሽ መሣሪያዎችን በቁጥጥር ሥራ ማዋሉን አስታውቋል።

ብዙዎችን እያነጋገረ ያለው የጦር መሣሪያ፤ የሕወሓት ኩባንያ በኾነው ሱር ኮንስትራክሽን ውስጥ የተገኘው ሲሆን፤ በሑመራ ቃፍታ በሚገኘው የሱር ኮንስትራክሽን ካምፕ ውስጥ ሕወሓት አከማችቶት የነበረው የጦር መሣሪያዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ በሑመራ ከተማ በአንድ የሕወሓት ደጋፊ በነበሩ ባለሀብት ድርጅት ውስጥ በርካታ የጦር መሣሪያዎች መገኘታቸውም ታውቋል። በየአካባቢው እየተደረጉ ባሉ ፍተሻዎች ተመሳሳይ የጦር መሣሪያ እየተገኘ ነው።

በትናንትናው ዕለትም ሕወሓት የኤርትራን ተቃዋሚዎች ያሠለጥንበት የነበሩ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸው አይዘነጋም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!