ለትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ የተሰጠው የ72 ሰዓት ጊዜ ገደብ አለቀ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
የጊዜ ገደብ ስላለቀ ወደ መጨረሻው የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚገባ ዶ/ር ዐቢይ አስታወቁ
ኢዛ (ማክሰኞ ኅዳር ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 17, 2020)፦ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ የስግብግቡ ጁንታ እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ ከመኾን ይልቅ እጁን እንዲሰጥ የተሰጠው የሦስት ቀን የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ፤ ወደ መጨረሻው የሕግ ማስከበር ተግባር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለጽ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መልእክት “የተሰጠው የሦስት ቀን የጊዜ ገደብ ዛሬ ተጠናቅቋል” ብለዋል።
በዚህ ጥሪ የተጠቀሙ የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላትን ለወሰዱት ኃላፊነት የተሞላው ሕዝባቸውን የማዳን ውሳኔ ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ስለተጠናቀቀ፤ በቀጣይ ቀናት የመጨረሻ ሕግ የማስከበር ወሳኝ ተግባር ይከናወናል” በማለት አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀሌ አቅራቢያ የተጠጋ ሲሆን፤ በምዕራብና በደቡብ የትግራይ ክልል የሚገኙ ወሳኝ የተባሉ ቦታዎችን በማስለቀቅ ወደፊት እየተጓዘ መኾኑ እየተገለጸ ነው። (ኢዛ)