የአማራ ክልላዊ መንግሥት በአጣየ የተፈጸመው ጥቃት አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው አለ

አጣየ ከተማ (ፎቶ፣ በረከት መብራቱ)
ጥቃቱ በከባድ መሣሪያ ጭምር የተፈጸመ መኾኑን አስታውቋል
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 21, 2021)፦ የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ብሔረሰብ አስተዳደር ሕዝቦች ለዘመናት በሰላም የኖሩና እየኖሩ እያለ፤ አገር ሰላም እንዳትኾን በንጹሐን ላይ የፈጸሙት ጥቃት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው፣ አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው ሲል የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።
በአጣየና በአካባቢው ባለፉት ሦስት ተከታታይ ቀናት የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ዛሬ (እሁድ መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም.) የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች አገር በሰላም ውላ እንዳታድር የሚፈልጉ እንዳንድ ተላላኪ ኃይሎች እንደኾኑ አመልክቷል።
የድርጊቱ መነሻ በግለሰቦች ፀብ ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን የደረሰውን ሞት ምክንያት በማድረግ በሽማግሌዎች እርቅ ካለቀ በኋላ የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የኾኑ አባላት ከዓርብ መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በከባድ መሣሪያ ጭምር በአጣየ ከተማ ጥቃት ተፈጽሟል።
“አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድ የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቅ ኃይል በአጎራባች የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኝ የኾነ ጥቃት ተፈጽሟል” ያለው የክልሉ መንግሥት መግለጫ፤ ይህ ጥቃት የተፈጸመበት አካባቢም ኾነ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የትሕነግ ርዝራዦች የፈጸሙትንና የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመከላከል ሕዝባችን ከመንግሥት ጎን ይቁም ብሏል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። የክልሉ መንግሥት የጸጥታ ተቋማቱን ሪፎርም በማድረግ፣ በአዲስ መልክ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችል ብቃት ያለው ኃይል እየገነባም ይገኛል።
ባለፉት ዓመታትም ኾነ በቅርቡ በተደረገው የሕግ ማስከበር የሕልውና ዘመቻ ላይ የክልላችን የጸጥታ መዋቅር በሕዝባችን ላይ የተቃጣውን ጥቃት በመመከት፣ በማጥቃትና በማክሸፍ አኩሪ ገድል ፈጽሟል። በዚህም ምክንያት ከምንጊዜውም በላይ ክልላችን የተቃጡበትን ጥቃቶች በአኩሪ ድል መክቶ ሕዝባችን በሰላም ተረጋግቶ የሚኖርበትና ሰላማዊ የኾኑ ዜጎች ሁሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበት ሰላማዊ ክልል እንዲኾን አድርጓል።
በክልላችን ውስጥ አልፎ አልፎ በአንዳንድ እኩያን ተንኳሽነት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በሕዝባችን ውስጥ ለዘመናት አብሮ በኖረው ሰላማዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ እንዲፈቱ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ከወጣቱና ከመንግሥት መዋቅር ጋር በጋራ በመኾን የሚፈታበት ሥርዓትም ያለ ነው። በመኾኑም በሕዝቡ፣ በአመራሩና በጸጥታ መዋቅሩ ጥምረት የትሕነግ ቅሪቶች እንዲሁም የትሕነግ ተላላኪ የኾኑ ኦነግ ሸኔና መሰሎቹ በየቦታው የሚፈጥሩትን ትንኮሳዎች ሁሉ በአስተውሎትና በሰከነ የትግል ሥልት እያሸነፍን ሕዝባችን የሰላም አየር እየተነፈሰ ከድህነት ለመውጣትና ኑሮውን ለማሻሻል መደበኛ ሕይወቱ ላይ አተኩሮ የሚሠራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
የአሁኑ ግጭት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች የተፈጠረ ሲሆን፤ ሐሙስ መጋቢት 9/2013 ዓ.ም ምሽት ጅሌ ጥሙጋ ላይ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት የአንድ ሰው ሕይወት ህልፈትን ምክንያት በማድረግ የተቀሰቀሰ ነው። በግለሰቦች መካከል የነበረውን ግጭትና የደረሰውን ሞት ምክንያት በማድረግም በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቅ ተፈጽሞ ነበር።
ይሁን እንጂ የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የኾኑ አካላት በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ፤ ከዓርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የኾነ ጥቃት ተፈጽሟል።
የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሕዝቦች ለዘመናት በሰላም የኖሩና እየኖሩ ያሉ መኾኑ እየታወቀ አገር በሰላም ውላ እንዳታድር የሚፈልጉት አንዳንድ ተላላኪዎች በንጹሐን ላይ የፈጸሙት ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው። በዚህ ጥቃት እጅግ ክቡር የኾነው የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል። ንብረትም ወድሟል። ለጠፋው ሕይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመትም የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው የክልላችን የጸጥታ መዋቅር ሕግ በማስከበር የሕልውና ዘመቻው ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ በሚገኝበት ወቅት ላይ ነው። በተለይም ክልላችን ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጦ የቀረው የትሕነግ ርዝራዥ የሚተነኩሰውን ግጭት ለመከላከል እቅስቃሴ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው። ይህን ምክንያት በማድረግ በአጣየና አካባቢው ፀረ ኢትዮጵያ እና አገር አፍራሽ የኾኑ ኃይሎች ከዚህም ከዚያም ተቀናጅተው የክልላችን ሕዝብ እረፍት ለመንሳትና አገር ለማተራመስ እያደረጉት ያለ አስነዋሪ ድርጊት መኾኑን የክልሉ መንግሥት በሚገባ ይገነዘባል።
በመኾኑም የክልሉ መንግሥት ይህ ወንጀለኛ ቡድን በንጹሐን ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ጥቃቱ ከጀመረበት ሰዓት ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመኾን ተጨማሪ የጸጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠርና ንጹሐን ዜጎችን ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ እየሠራ ይገኛል። በአጣየና በአካባቢው የተፈጸመውን ዝርዝር ጥቃት፣ የደረሰውን ሰብአዊና የንብረት ጉዳት መንግሥት በፍጥነት መረጃውን አጣርቶ ለሕዝቡ ይፋ የሚያደርግ ይኾናል።
የክልሉ መንግሥት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በንጹሐን ላይ ለደረሰው የሕይወት መሥዋእትነትና የንብረት ውድመት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን በድጋሚ እየገለጸ፤ አጥፊ የወንጀለኞችን ቡድንና በድርጊቱ የተሳተፉት ተባባሪ አካላትን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለሕግ የሚያቀርብ መኾኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን።
ይህ ጥቃት በተፈጸመበት አካባቢም ኾነ በሌሎች የክልላችን አካባቢዎች የትሕነግ ርዝራዦችም ኾኑ የትሕነግ ቅሪት ተልእኮ አስፈጻሚና ፈጻሚ የኾኑ ኃይሎች የፈጸሙትንና የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመመከት ሕዝባችን ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል። እነዚህ ኃይሎች እድሉን ካገኙ ኢትዮጵያን ለማፍረስም ኾነ ለማተራመስ በክልላችንና ከክልላችን ውጭ በሚኖረው ሕዝባችን ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንደማያመነቱ ደጋግመን ተመልክተናል። በተጨማሪም አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች የተፈጠረውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በክልላችን ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ግጭቱን ለማባባስ ጥረት ሲያደርጉ ታዝበናል። እነኝህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የክልሉ መንግሥት በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።
ስለኾነም መላው ሕዝባችን ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንድነት ለሰላማችን በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ላይ መኾናችንን ተገንዝቦ፤ በየትኛውም አካባቢ ለጸጥታው ሥጋት የሚኾኑ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥመው ለሚመለከተው የመንግሥት አመራርና የጸጥታ መዋቅር መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መጋቢት 12/2013 ዓ.ም ባሕር ዳር